BY TAMIRU TSIGE
የፌደራል ዓቃቤ ሕግ በመሠረተበት ሦስት ክሶች ምክንያት ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. ዋስትና ተከልክሎ በማረሚያ ቤት እንዲቆይ የተደረገው የፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ በዛሬው ዕለት ክሱ እንዲቋረጥ ተደረገ፡፡
ክሱ እንዲቋረጥ ያዘዘው ከሳሹ የፌደራል ዓቃቤ ሕግ ሲሆን፣ ለክሱ መቋረጥ በምክንያትነት ያቀረበው ተጨማሪ ምርመራ አደርጋለሁ በማለቱ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በዛሬው ዕለት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 16ኛ የወንጀል ችሎት በጻፈው ደብዳቤ በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ ያቀረባቸውን ክሶች ማቋረጡን አስታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት ተመስገን በዛሬው ዕለት ከእስር እንደሚለቀቅ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ክስ የተመሠረተበት በ2003 እና በ2004 ዓ.ም. ራሱ በዘገባቸውና በጋዜጣው ዓምደኞች በተዘገቡ አመፅ ቀስቃሽ ናቸው በተባሉ ሦስት ጽሑፎች ሳቢያ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ፍትሕ ጋዜጣ ሐምሌ 13 ቀን 2004 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስር መለስ ዜናዊ ሕመም ጋር በተገናኘ ዘገባው ምክንያት ከታተመ በኋላ እንዳይሠራጭ በፍትሕ ሚኒስቴር መታገዱም ይታወሳል፡፡ ጋዜጣው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አላትምም በማለቱ ምክንያት ሕትመቱ ተቋርጧል፡፡
No comments:
Post a Comment