ነሀሴ ፳፫ (ሀያ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የኢትዮጵያ ህዝብ በኢህአዴግ አገዛዝ እየተፈፀመበት ካለው አፈናና ረገጣ ተላቆ በሰላማዊ መንገድ የስልጣን ባለቤት የሚሆንበት ሁሉን አቀፍ ኮንፈረንስ እንዲጠራ ሲል የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጥያቄ አቀረበ።
ፓርቲው ሰሞኑን ባቀረበው ጥሪ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ የሚገኙ በሰላማዊም ሆነ በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የተቋቋሙ ፓርቲዎች በሙሉ እንዲሁም ሲቪክ ማኅበራት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራን፣ አርሶ አደሮች፣ነጋዴዎች፣ ሠራተኞችና የገዢው ፓርቲ ተወካዮች እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትም በሀገራዊ ኮንፈረንሱ ላይ ተገኝተው በመመካከር ሀገሪቱ ወደ ሁከትና የእርስ በርስ ብጥብጥ ሳትገባ የስልጣን ባለቤት የሚሆንበትን መፍትሄ ሊያበጁ ይገባል ብሏል።
በኮንፈረንሱ ላይም ህዝብን ከእልቂት ኢትዮጵያንም ከውድቀት ለማዳን የሚችሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ይደረጋል።
በሚዘጋጀው ብሔራዊ ኮንፈረስ ላይ ተሳታፊዎች ያለፉትን ጊዜያት ፖለቲካዊ ሁኔታዎች በመገምገም አዲስ የፖለቲካ አቅጣጫዎችን የመቀየስ፣ አሁን ያሉትን የኢህአዴግ ኃላፊዎች ለመተካት ጊዜያዊ የሽግግር ካውንስል መምረጥ እና መተካት፣ለሙስሊሞች እና ለመምህራን ጥያቄ ምላሽ መስጠት፣ የዋልድባ ገዳም ይዞታ በነበረበት እንዲመለስ የማድረግ የመፍትሄ ሀሳብ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪም ከቴሌ ኮሙኒኬሽንና ከሌሎችም መስሪያ ቤቶች የተባረሩ ሰራተኞች ወደ ስራቸው እንዲመለሱ እንዲሁም ገለልተኛ የሆኑ የፍትህ ተቋማት፣ የሚዲያና የማስታወቂያ ተቋማት፣ የብሔራዊ ምርጫ አስተባባሪ እና የደህንነት ተቋም ይቋቋማል ተብሎ እንደሚጠበቅ ፓርቲው ገልጿል።
No comments:
Post a Comment