Translate

Thursday, August 30, 2012

ሴተኛ አዳሪዎች በአቶ መለስ ዜናዊ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ገለፁ


Postby ቅዱስ » Thu Aug 30, 2012 12:34 am
ትናንት በስቲያ ስራ ልገባ እየተጣደፍኩ ስለነበር የላኩላችሁን መልዕክት መልሼ እንኳን ሳላነበው እንደወረደ ነው ጣል አድርጌላችሁ የበረርኩት። በወቅቱ ኢቲቪን እያየሁ ስሜቴ ክፉኛ ተጎድቶ ስለነበር የሰዓቱ ነገር ባይገድበኝ ውስጤን ያላውሰው የነበረውን ስሜት በቀላሉ ከትቤ የምጨርሰው አልነበረም። ታዲያ ዛሬ ኢትዪ ትዪብ ድረ ገጽ ላይ “የአዲስ አበባ ጎዳና ተዳዳሪዎች በአቶ መለስ ዜናዊ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ” የሚለውን የኢትዮጵያን ቴሌቭዥን ዘገባ ስመለከት እነበረከት የተቆጣጠሩት ስርዓት ምን አይነት ጨዋታ በመጫወት ላይ እንዳሉ ወለል ብሎ ታየኝና መፅናናት ያዝኩ። ሕዝባችን በግዴታ ሃዘኑን እንዲገልጽ የተላለፉት የጥሪ ደብዳቤዎችንም አንዳንድ ድረ-ገፆች ላይ ለመመልከት ችያለሁ።

ይህ ከአሳዛኝነቱ ይልቅ አስቂኝነቱ የሚጎላው የዜና ዘገባ፣ የኢቲቪ ጋዜጠኞች ብቃት ምን ያህል የወረደ መሆኑን ከማመላከቱ በተጨማሪ ለምስል ቀረፃው የመረጧቸው የጎዳና ተዳዳሪ ተብዬዎች ፊት ላይ የሚነበበው ስሜትና በእጅጉ የሚያደምም ሆኖ ነው ያገኘሁት። እኛ የምናውቀው አዲስ አበባ ላይ በርሳቸው ዘመን ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ላይ ጎዳና ላይ እንኳን ማደር እየተከለከሉ እየተከለከሉ ሲሳደዱ ነው። በተለይም አላሙዲ ፒያሳ ላይ እስካሁን አጥሮ ያስቀመጠው ቦታ አጥር ስር ከነቤተሰባቸው ለዓመታት ተጠልለው ይኖሩ የነበሩ ምስኪን ወገኖቻችን መጨረሻ ላይ የመንግስት ታጣቂዎች በምን አይነት መልኩ ከቦታው ላይ እየደበደቡ እንደነቀሏቸው ምንጊዜም የማይረሳኝ የቅርብ ጊዜ ትዝታዬ ነው።

በተረፈ “ቴዲ አፍሮ ለመለስ ዜናዊ ዘፈን አወጣ” የሚለው ዜና የፈጠራ መሆኑን በማረጋገጤ በእጅጉ ተጽናንቼአለሁ። 

ይህንን የኢቲቪ ዘገባ እንዳየሁ የሚቀጥለው የዜና ዘገባ የአዲስ አበባ ሴተኛ አዳሪዎች በአቶ መለስ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ የሚል ይሆናል ብዬ ገመትኩ። ገምቼም አልቀረሁ በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብላ ሴተኛ አዳሪዎቹን በመወከል መልዕክታቸውን የምታስተላልፈው ካድሬ ስሜት በዚህ መልኩ ከተብኩት ። ዜናው እንዲህ ነበር ኢቲቪ ያቀረበው፦

ሴተኛ አዳሪዎች በአቶ መለስ ዜናዊ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ገለፁ

(“የጎዳና ተዳዳሪዎች በአቶ መለስ ዜናዊ ሞት የተነሳ የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ” በሚለው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ዘገባ ላይ ተመስርቶ የተፃፈ ወቅታዊ ልቦለድ ዜና)

በአዲስ አበባ የሚገኙ በርካታ ሴተኛ አዳሪዎች በታላቁ ባለ ራዕይ መሪያችን በ/ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ዛሬ በብሄራዊ ቤተ መንግስት አዳራሽ በመገኘት ገለፁ።

ሴተኛ አዳሪዎቹ ለባለቤታቸው ለወ/ሮ አዜብ መስፍንና ለልጆቻቸው ካስተላለፉት የሃዘን መልዕክት በተጨማሪ፣ አቶ መለስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለሴተኛ አዳሪነት ስራ መስፋፋት ያደርጉ የነበረውን ጉልህ አስተዋጾ በመጥቀስ፣ የርሳቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ወደዚህ የስራ መስክ የሚገቡትን ሴቶች ቁጥር ይቀንሰው ይሆናል የሚል ስጋት እንዳላት የሴተኛ አዳሪዎቹ ተወካይ ለሪፖርተራችን ገልፃለች።


እስኪ ንግግርዋን አብረን እንከታተለው፦

ተወካይዋ እንባዋ እንዲመጣላት፣ የግንቦት 1997 ዓ.ም ምርጫን ተከትሎ በአጋዚ ክፍለጦር ወታደሮች የተገደለው ታናሽ ወንድሟን በልቧ እያሰበች እንደምንም ጠብ! ያለላት እምባዋን በእራፊ ጨርቅ እያባበሰች ወደ ቴሌቭዥኑ መስኮት ብቅ ትላለች፦ 

“ እንዲሚታወቀው ጠ/ሚ/ር መለስ ከርሳቸው በፊት ከነበሩ መሪዎች በበለጠ አናሳ ቁጥር ያላቸው ባለሙያዎችን በመደገፍና በማበረታታት በልማቱ መስክ ጉልህ አስተዋጾ እንዲያደርጉ የለፉ መሪ ነበሩ። እኔም የዚህ እድል ተጠቃሚ ከሆኑት ሴተኛ አዳሪዎች አንዷ ነኝ። ባለፉት 20 ዓመታት በዚሁ ስራ ያገለገልኩ ሲሆን፣ ይህ የስራ መስክ በአገሪቷ ውስጥ እየተፈጠረ ያለውን ከፍተኛ የስራ አጥ ችግር በመቅረፍ በኩል ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ሆኖ ተገኝቷል። የሴተኛ አዳሪነት ስራ ባለፉት መንግስታት እጅግ የተጠላና የተወገዘ በመሆኑ ቀደምት የሙያ አጋሮቻችን በአንዳንድ ቡና ቤቶችና አነስተኛ መሸታ ቤቶች ውስጥ ብቻ ያውም ተደብቀው ይሰሩ እንደነበር ታሪክ መዝግቦት ይገኛል። በኢሕአዴግ ዘመነ መንግስት ግን ይህ ኋላ ቀር ባሕል ሙሉ ለሙሉ ተቀርፎአል ማለት ይቻላል። በተለይም ጠ/ሚ/ር መለስ ባጎናፀፉን የዴሞክራሲያዊ መብት በመጠቀም እኔን ጨምሮ ሲያዮዋቸው የሚያማልሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ውብና ለግላጋ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በተለይም ምሽት ላይ ጎዳና ላይ በመቆም መኪና ላላቸው ደንበኞቻችን ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ሁሉ ችለናል። ታላቁ መሪያችን በቀየሱት የድሕነት ቅነሳ ስትራቴጂ ተግባራዊ በማድረግ፣ ባብዛኛው የምናገኘውን ገንዘብ የችግረኛ ቤተሰቦቻችንን የዕለት ጉርስ ለመሸፈን ነው የምናውለው።

እንዲያውም ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ከተለያዩ የአገራችን ዩንቨርሲቲዎች በዲግሪና ከዚያም በላይ በልዩ ልዩ ሙያ የተመረቁ በርካታ እሕቶቻችን፣ ጠ/ሚኒስትራችን የነደፉት በምግብ ራሳችንን የመቻል ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ ወደዚህ የስራ መስክ መግባቱ አማራጭ የሌለው የስራ ዕድል ሆኖ አግኝተውታል። ስለዚህም የሴተኛ አዳሪነቱ ስራ በቂ መስሕብነት ብቻ ሳይሆን በልዩ ልዩ ሙያ የዳበረ ዕውቀት ባላቸው ሴት እሕቶቻችን ተሳትፎ ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ ነው።

“ምንም እንኳን የኢትዮጵያውያን ደንበኞቻችን ቁጥር ከዕለት ዕለት እየቀነሰ ቢመጣም፣ ጠ/ሚ/ር መለስ በቀየሱት የዕድገትና የትራንፎርሜሽን እቅድ ተጠቃሚ ለመሆን በተለይም ከአረብና ከፈረንጅ አገር፤ እንዲሁም ከሱዳንም ሆነ ከሌላ የአፍሪካ አካባቢዎች የሚመጡት አዳዲስ ደንበኞቻችን ቁጥር እጅግ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ይገኛል። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት በአንድ ቀን ለሊት ሁለትና ሶስት ደንበኞቻችንን እስከማስተናገድ ደርሰናል። በዚህ በኩል ለአገራችን የምናስገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። እንዲያውም አዲሱ የአገራችን አስተዳደር እርሳቸው የቀየሱትን የልማት መርሃ-ግብር ለማስፈፀም ጥረት ካደረገ፣ ወደፊት አገራችን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ቡና ወደ ውጭ ኢንቨስት ለማድረግ መከራዋን ማየት አይጠበቅባትም ብዬ እገምታለሁ። 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም፣ ጠ/ሚ/ር መለስ በነደፉት የድሕነት ቅነሳ ስትራቴጂ ተጠቃሚ የሆኑ ቀላል ቁጥር የሌላቸው “ወንደኛ አዳሪዎችም” በዚሁ የስራ መስክ በመሰማራት ላይ ናቸው። አብዛኞቹም ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ እንዲሁም ከሌላው ዓለም የሚመጡ ቋሚ ደንበኞች እንዳሏቸው ይነገራል። ይህ ደግሞ የታላቁ ጠ/ሚኒስትራችን የዘመናት ድካምና ጥረት ውጤት በመሆኑ ሁላችንንም ደስ የሚያሰኝ ነው።

እንደሚታወቀው ጠ/ሚኒስትር መለስ ሕዝባችን የራሱን እርግፍ አድርጎ በመተው የሰለጠኑትን አገሮች ባህል እንዲወርስ ብርቱ ጥረት ሲያደርጉ ኖረው ያለፉ ታላቅ የአገር መሪ ናቸው። በዚህ በኩል በዓለማችን ብቸኛው የአገር መሪ ላይ እንዲህ አይነት አዳዲስ ስልጣኔዎችን ወደ አገራችን ለማስገባት እድሜያቸውን ሙሉ ጥረት ሲያደርጉ ኑረዋል። በተለይም በቅርቡ ዓለም ዓቀፍ የግብረሰዶማውያን ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ እንዲደረግ በመፍቀድ ለህዝባችን ግንዛቤ ለማስጨመጥ መሞከራቸው አይዘነጋም። ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣውና ሕዝባችንን ተብትቦ ከያዘው “ኢትዮጵያዊነት” ለማላቀቅ አገሪቷን በብሔርና በቋንቋ ከማዋቀራቸውም በተጨማሪ፣ ኢትዪጵያዊ እሴቶቻችንን ሙሉ ለሙሉ በመድፈር፣ ብዙዎች መስዋዕትነት የከፈሉበት ሰንደቅ ዓላማችን “ጨርቅ” እንደሆነ ባደባባይ የነገሩን ታላቅ የለውጥ አርበኛ መሆናቸው አይዘነጋም።

እዚህ ላይ አያይዤ ላነሳ የምወደው ነገር ቢኖር ወዳጃቸው አላሙዲ በርሳቸው ልዩ ፈቃድ ከአዶላ የሚስያወጡት ወርቅ ሞልቶ ተርፎ ሳለ፣ ጠ/ሚ/ር መለስን የመሰለ ታላቅ መሪ በሕይወት ዘመናቸው ጨርቅ እንደሆነ በነገሩን ሰንደቅ ዓላማ አስከሬናቸው መሸፈኑ በእጅጉ ክብራቸውን የሚቀንስ ሆኖ መገኘቱን ልጠቁም እወዳለሁ። ምናልባት አላሙዲም በግዜር እጅ ተይዘው ስለሚገኙ ባስቸኳይ ወርቅ ማልበስ ባይቻል እንኳን፣ የሕወሃት፣ የትግራይ ክልል፣ እንዲሁም ለኤርትራ መገንጠልም ሆነ ለነበራቸው ተቆርቋሪነት ሲባል የሻዕቢያ አርማ ባለው ጨርቅ አስከሬናቸው ቢሸፈን ነፍሳቸው ባግባቡ ልትደሰት እንደምትችል እገምታለሁ።

በተጨማሪም እንደዋልድባ አይነት ዘመናት ያስቆጠረ ገዳምን ወደ ሸንኮራ አገዳ ልማት ጣቢያ ለመቀየር በብቸኝነት ደፍረው የተንቀሳቀሱ፣ እንዲሁም በነቢዩ መሃመድ ቤተሰቦች ከዘመናት በፊት ወደ አገራችን የገባውን የእስልምና እምነት ሙሉ ለሙሉ ወደ አሕባሽ እንዲቀየር ደፍረው እንቅስቃሴ ያስጀመሩ ብቸኛው ደፋር የአገራችን መሪ መሆናቸው መዘንጋት የለበትም። ይህንንም ሆነ ሌሎች በርካታ ስራዎቻቸውን ያስተዋለ ሰው ደግሞ፣ እኚህ ታላቅ መሪያችን “አባይን የደፈረ መሪ” ተብሎ በአንድ ተራ ወንዝ ስም ብቻ መሞካሸታቸው አግባብ እንዳልሆነ ለመረዳት ጊዜ አይወስድበትም። ስለዚህም አባይም የሚገኘው ኢትዮጵያ ውስጥ ከመሆኑ በተጨማሪ እርሳቸው የደፈሯቸው ነገሮች (ሴቶችም ካሉ መጨመር ይቻላል) በሙሉ ተጠቃለው “ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያዊነትን የደፈረ ብቸኛው መሪ” ተብለው እንዲሰየሙ ማሳሰብ እወዳለሁ። “

አመሰግናለሁ!
ቅዱስ ሃብት በላቸው
ቅዱስ
 

No comments:

Post a Comment