ኢሳት ዜና:-<<ኢትዮጵያ የኑክሌር ቴክኖሎጂን ሰላማዊ የልማት አጀንዳዋን ለማሳካት ብቻ ጥቅም ላይ ለማዋል ቁርጠኛ ናት>>ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።መንግስታዊው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃለማሪያም ይህን ያሉት፤የአለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዩኪያ አማኖን ሰሞኑን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው ባነጋገሩበት ወቅት ነው።
<<ኑክሌርን ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ በመጠቀም ረገድ ኢትዮጵያ ከኤጀንሲው ጋር ምንጊዜም ተባብራ ለመስራት ዝግጁ ስለመሆኗ ለዋና ዳይሬክተሩ ለዩክያ አማኖን አረጋግጠውላቸዋል>>ብሏል አዜአ።
እየጨመረ የመጣውን የካንሰር በሽታ በመከላከል ረገድ አገሪቱ እያደረገች ያለውን ጥረት ለማሳካት ከዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ በአቅም ግንባታና በቁሳቁስ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲጠናከርም አቶ ሀይለማርያም ጠይቀዋል።
አቶ ሀይለማርያም በዚሁ ውይይት ላይ ኢትዮጵያ የኑክሌር ቴክኖሎጂን ለመቀጠም ብቃት ያለው ሥርዓት ለመዘርጋት በኤጀንሲው በኩል የተዘጋጀውን የስምምነት ፕሮቶኮል ለመፈረም የስምምንት ይዘት ፈትሻ በቅርቡ ፈጣን ምላሽ እንደምትሰጥ መናገራቸውን፤ ውይይቱን የተከታተሉት የሳይንሰና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አቶ ደሴ ዳልኬ ለዜና አገልግሎቱ አስረድተዋል።
ይህንኑ ተከትሎ የኢራን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ አክባር ሳሊህ ትናንት አርብ አዲስ አበባ ገብተዋል።
እንዲሁም የቱርክ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር አህመድ ዳቩቶግሉ ዛሬ ማምሻውን ለተመሳሳይ ጉብኝት አዲስ አበባ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢራን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ጋር መነጋገራቸው ተዘግቧል።
ኢራን በኑክሌር አጠቃቀም ሳቢያ በሀያላን አገሮች እየተወገዘች ያለች አገር መሆኗ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ የኒውክሊየር ሀይል ለመገንባት ብቃቱም አቅሙም ይኖራታል ተብሎ አይታስብም፣ እንደ ታዛቢዎች ገለጻ።
No comments:
Post a Comment