Translate

Monday, November 19, 2012

የዛሬው የዚያራ መርሐ ግብር ሪፖርታዥ


ትግሉ ዛሬም በሌላ ምዕራፍ ላይ ነው፡፡

ድምፃችን ይሰማ
የዛሬው የዚያራ መርሐ ግብር ሪፖርታዥዛሬ በስኬት የተጠናቀቀው የጉዞ ቃሊቲ የዚያራ መርሐ ግብራችን ይፋ ከተደረገበት ሐሙስ ምሽት ጀምሮ ነበር በርካታ ሕዝብ ሂደቱን በስኬት ጀምሮ በስኬት ለማጠናቀቅ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ የጀመረው፡፡ በሁሉም አካባቢዎች በተደረገው የተቀናጀ አንቅስቃሴ ሁሉንም መዳረሻ መንገዶች ያካተተ ሰፊ የቅስቀሳ ስራ ተሰርቷል፡፡ በመርሐ ግብሩ እቅድ ላይ መንግስት ያሰማራቸው አካላት ትእይንተ ዚያራውን ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊለውጡት ይችሉ ይሆናል የሚል ስጋት የነበረ ቢሆንም ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ባካበተው እና ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ ባሳያቸው ሰላምን እሰከመጨረሻው የመጠበቅ
ስልት በመተማመን መርሐ ግብሩ በታቀደለት መልኩ ሊሄድ ችሏል፡፡

በበርካታ አካባቢዎች የሚኖሩ ሙስሊሞች የቃሊቲ ጉዞአቸውን የጀመሩት ገና ከሌሊቱ 11፡30 ጀምሮ ነበር፡፡ እለቱ እሁድ በመሆኑ ችግሩን አቃለለው እንጂ በሕዝቡ ብዛት የተነሳ ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር ገና ከማለዳው ጀምሮ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ሆኖም የተገኘውን የግልም ሆነ የሕዝብ ትራንስፖርት እንዲሁም በእግርም ጭምር በመጓዝ ቃሊቲ የደረሰው ሕዝበ ሙስሊም በደቂቃዎች ጊዜ ነበር የአካባቢውን ነፋስ የለወጠው፡፡ ቃሊቲ በውስጡ እንደያዛቸው ንጹሐን መሪዎቻችን እና ‹‹እንደ ሕዝብ ታስረናል›› የሚል መልዕክት በሚያስተላልፉ ሙስሊሞች ተሞላ፡፡ ቃሊቲና አካባቢው እየጠበበ፣ የሰው ቁጥር ግን እያየለ መጣ፡፡ የህዝቡ ወረፋ ሶስት ረድፍ ሰርቶ መንደሮችን እያቆራራጠ ነጎደ፡፡ ሳይታሰብ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የቃሊቲ አውራ ጎዳና አፋፍ ላይ ደረሰ፡፡ ‹‹ሰልፉ ወደ ጎዳና መውጣቱ ብዛቱን ያሳብቃል›› የሚል ስጋት የገባቸው የጸጥታ አካላት ሰልፉ ወደ ሌሎች አጎራባች መንደሮች እንዲቀጥል ቢያደርጉም መንደሮቹ እየሞሉ በርካታ ሕዝብ ዋናው ጎዳና ላይ ፈስሶ ታይቷል፡፡
ዘግይቶ ቢሆንም የማረሚያ ቤቱ በር ለጎብኚዎች ክፍት ሲደረግ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በተሠጠው መመሪያ መሰረት በእርጋታ ያለ ምንም ግፊያ ወደ ውስጥ መግባት ጀመረ፡፡ በማረሚያ ቤቱ የነበረው ፍተሻ ከወትሮው የተለየና ጫማን እስከማስወለቅ የደረሰ ነበር፡፡ ሕዝቡ በሌሊት ከቤቱ በመውጣትና ይሄንን አስቸጋሪ የቃሊቲ ረጀም መንገድ በመጓዝ (በአማካይ ለትራንስፖርት እስከ 12 ብር ድረስ በመክፈል) ለሰዓታትም በቃሊቲ በር ላይ ለመጠበቅ የተገደደው ሕዝብ ፍተሻውን አልፎ የናፈቃቸውን መሪዎች ሲያገኝ እንባውን መዝራት ይጀምራል፡፡ ሕጻን፣ አዋቂ፣ ሴት፣ ወንድ፣ ጎልማሳ፣ አረጋዊ ሳይል መሪዎቹን የሚቀበለው አንዳንዱ በለቅሶ፣ ሌላው ሀዘን ባጠላበት ፊት! የኅሊና እስረኞቹ መሪዎቻችን ዘወትር እንደሚደርጉት የሚያለቅሰውን ሕዝብ ከሽቦው አጥር ጀርባ ሆነው ያባብላሉ፡፡ ይህን ትእይንት የተመለከተ ታሳሪዎቹ ሕዝቡ እንጂ መሪዎቹ አይመስለውም፡፡ ለነገሩ ሕዝቡም በፍትህ እጦት ‹‹ኢትዮጵያ በምትባል ትልቅ እስር ቤት ታስሬያለሁ›› የሚል መልዕክት ለማስተላለፍም ጭምር ነበር የዚያራ ፕሮግራሙን ያካሄደው፡፡ ሕዝቡ ከኋላ ለተሰለፉት መቶ ሺዎች እድል ለመስጠት ሲል በመከራ ያገኘውን ቃሊቲ የመግባት እድል ለቅጽበት ያህል በመጠቀም ለተረኛው ሙስሊም ይሰጥ ነበር፡፡
የእድል ነገር ሆኖ ከኡስታዝ አህመድ ሙስጠፋና ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸው በስተቀር ሁሉም የኅሊና እስረኞቻችን አንድ ላይ ነበሩ፡፡ ዞን ሶስት ላይ ተደርድረው የቆሙት ቀሪዎቹ 27 የኅሊና እስረኞች ከማለዳው ጀምሮ አስከ ቀትር ድረስ ያለምንም እረፍት ሊጎበኛቸው የመጣውን ሕዝብ ሲቀበሉ፣ ሲያበረታቱ፣ ሲመክሩ እና ዱአ ሲጠይቁ ውለዋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሊዘይራቸው ከመጣው ሕዝብ እድሉን አግኝቶ በአይን የተያያቸው ሩብ ያህሉ እንኳ አይሞላም፡፡ የማለዳውን ብርድ እና የረፋዱን ጸሐይ ተቋቁሞ በትእግስት ሲጠብቅ የነበረው በቁጥር የሚበዛው ሙስሊም የመግባት እድሉን እንደማያገኝ እያወቀም ቢሆን የዚያራ ፕሮግራሙን ለማሳካት ሲል በሰልፍ ተሰድሮ ነበር፡፡ የሰልፉን ጫፍ ለማግኘት የዚህ ሪፖርታዥ አዘጋጆች ሰልፉን ተከትለው ቢጓዙም በሰልፉ ርዝማኔ የተነሳ ጫፉን ለማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ይሄ ሁሉ ሕዝብ ግን መሪዎቹንም ሆነ የመንግስትን ያልተገደበ ጣልቃ ገብነት አስመልክቶ ያለውን አቋም በማያሻሙ ቃላት ዛሬም በድጋሚ ለመንግስት በማረጋገጥ ወደ ቤቱ በሰላም መመለስ ጀምሯል፡፡
በሰላም ተጠናቅቋል ሲባል የነበረውን ሰላም ለማደፍረስ ጥረቶች አልተደረጉም ማለት አይደለም፡፡ ሰላማዊውን ሕዝብ ከማመናጨቅ አንስቶ የበርካታ ሙስሊሞችን የመኪና ታርጋ እስከ መፍታት የደረሰ ትንኮሳ በጸጥታ አካላትና በትራፊክ ፖሊሶች ተፈጽሟል፡፡ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ የፌዴራል ፖሊስ ኃይሎች በልዩ መለዮዋቸው ነገር ፍለጋ በሚመስል መልኩ ተደጋጋሚ ከበባ በተሸከርካሪዎች በመታገዝ በሙስሊሙ ላይ ቢያደርጉም ሕዝቡ ያለ ምንም መሳቀቅ ሙከራውን አክሽፎታል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ ‹‹በሞባይል ሲቀርጹ ነበር›› የተባሉ 5 የሚደርሱ ወጣቶች በፖሊሶች ታፍነው ተወስደዋል፡፡ ይሄም የትንኮሳው አካል ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዚያራውን ጨርሰው ወደ ቤታቸው ይሄዱ የነበሩ ሙስሊሞች ሳሪስ ቀለበት መንገድ አካባቢ በፖሊስ ትንኮሳ ሲደረግባቸው የነበረ ቢሆንም ሁኔታውን ሕዝቡ በሰላም ለማሳለፍ ያደረገው ጥረት ተሳክቶ ያለምንም ችግር በሰላም ተጠናቅቋል፡፡የዛሬው የዚያራ መርሐ ግብር ሪፖርታዥ
ለመርሐ ግብራችን ስኬት የሙስሊሙ መኅበረሰብ ሰላም ወዳድነት አብዩን ሚና የተጫወተ ቢሆንም የሌላ እምነት ተከታዮች በተለይም ክርስቲያን ወገኖቻችን ዚያራው በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል፡፡ በተለይም በቃሊቲና አካባቢው የሚኖሩ የክርስትና እምነት ተከታዮች ሚናቸው የጎላ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ሙስሊሞች ወደየቤታቸው የተመለሱትም ከክርስቲያን ወገኖቻቸው ባገኙት ነጻ ትራንስፖርት (ሊፍት) ነው፡፡ ይህ አጋርነትና ትብብር ወሳኝ በሆኑ አገራዊና ብሄራዊ አጀንዳዎች ላይ ተጠናቅሮ እንደሚቀጥል ተስፋ እናደርጋለን፡፡
የዛሬው ትዕይንተ ዚያራችን ወህኒ ቤት የሚገኙ መሪዎቻችንንና ውድ ወንድሞቻችንን ልእልና አጉልቶ እና ጎዳናዎችን አጥለቅልቆ በሰላማዊ ትግላችን ጉዞ ላይ ሌላ አዲስ ታሪክ አክሎበታል፡፡ ትግላችንም ቀሪውን ትውልድ አስተማሪ ሆኖ እየዘለቀ ነው፡፡ ለሁከትና ግርግር በተመቹ ቦታዎችና በተጋበዝንባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ሰላምን መምረጣችን አስተውሎት ላልተሳናቸው ሁሉ በውስጡ ጥልቅ ትምህርት አለው፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሙስሊም!
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment