(የሳምንቱ አጫጭር ዜናዎች)
የእስክንድር ነጋ ጉዳይ ለመንግሥታቱ ድርጅት ቀረበ
የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያላግባብ የታሠሩ ሰዎችን ጉዳይ ለሚያጠናው ግብረኃይል መቅረቡን ለህሊና እስረኞች የሚሟገተው ፍሪደም ናው “Freedom Now” ስራ አስፈጻሚ ዋና ዳይሬክተር ማርዳ ተርነር ለአሜሪካ ሬዲዮ አስታውቀዋል።
ዳይሬክተሯ እንዳሉት ድርጅታቸው የእስክንድር ነጋን ጉዳይ በጥልቀት ከመረመረ በኋላ የጋዜጠኛነት ስራውን ብቻ ሲያከናውን እንደነበር ሙሉ አረጋግጠዋል። የታሰረውም ያለ አግባብ እንደሆነ ታምኖበታል። በእስር ቤት ከአያያዝ ጀምሮ በርካታ ጥሰቶች እንደተፈጸሙበት አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለዓለም አቀፍ ህግጋት የገባውን ኪዳንና ግዴታ በመጣሱ የእስክንድር ጉዳይ በተባበሩት መንግስታት ያለ አግባብ የታሰሩ ሰዎችን ጉዳይ ለሚመረምረው አካል ባለፈው ሚያዚያ ቀርቧል። የእስክንድር ጉዳይን የያዘው አካል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀበለቻቸውን የሰብአዊና ፖለቲካ ጉዳዮች ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ህጎች ስለመጣሷ መርምሮ ውሳኔውን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል። ለእስክንድር ነጋ ጉዳይ አዲስ አበባ መሄዳቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሯ በውሳኔው መጨረሻ እስክንድር ነጻ ሊወጣ እንደሚችል ቀደም ሲል በፓኪስታንና በበርማ ከተሰሩት ስራዎች ጋር በማነጻጸር አስረድተዋል “እንደ መንግስታቱ ድርጅት ያሉ አካሎች የሚወሰኑት ውሳኔ ቀላል አይደለም” በማለት ተናግረዋል፡፡
እስክንድር ነጋ በአሸባሪነትና በአገር መክዳት ወንጀሎች ተከሶ 18 ዓመት እንደተፈረደበት ይታወሳል።
የባንኮች የውጭ ምንዛሬ ገቢ አሽቆለቆለ
የግል ባንኮች የውጪ ምንዛሪ ገቢ በአማካይ 34 በመቶ ማሽቆልቆሉን በሂሳብ ሪፖርታቸው ታወቀ። የባንኮቹ ከውጭ ምንዛሪ ግብይት የሚያገኙት ገቢ የቀነሰው ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ቀውስ ጋር በተያያዘ ዜጎች ወደ አገር ቤት የሚልኩት ሐዋላ በመቀነሱ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የአገሪቱ የውጪ ንግድ ገቢ ዝቅተኛ እየሆነ መምጣቱና አገሪቱ ባጋጠማት የወጪ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ የውጪ ምንዛሬ ግብይት መቀነሱ ዋናው ተጠቃሽ የችግሩ መንስዔ መሆኑን ሪፖርተር ጋዜጣ አስታውቋል።
የግል ባንኮቹ ያጋጠማቸው ችግር ካለፈው ሁለት ዓመት ጀምሮ እየተባባሰ እንደሚሄድ ባለሙያዎችን አነጋግሮ የዘገበው ሪፖርተር እንዳለው በሚቀጥለው አሁን ባለው የውጪ ምንዛሪ እጥረት አንጻር የተያዘው የበጀት ዓመት የግል ባንኮች ገቢ በጣም ዝቅ እንደሚል ተገምቷል።ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ የውጪ ምንዛሪ እጥረት እንደሌለ በቅርቡ ለፓርላማቸው ተናግረው ነበር።
የአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ሊፈርስ ነው
ሰሞኑን ከአዲስ አበባ የሚወጣው አስደንጋጭ ዜና የሰማዐቱ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት እንደሚፈርስ፣ የአጤ ሚኒልክም ሃውልት በተመሳሳይ አደጋ ውስጥ እንደሆነ የሚያመለክት ነው። አዲስ አበባን ይዞራታል ተብሎ የተነገረለት የባቡር መስመር ግንባታ ለጊዜው ሁለቱን ሃውልት ሊያፈርስ እንደሚችል በርካታ የዜና አውታሮች አስተጋብተዋል።
ኢሣትን ጨምሮ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የባቡሩ መስመር የአቡነ ጴጥሮስን ሃውልት እንደሚያፈርሰው የሚያመላክት ቁፋሮ እየተካሄደ ነው። መንግስት ከመስመሩ ግንባታ በኋላ ሃውልቱ ተመልሶ በነበረበት ይተከላል ቢልም ሃውልቱ ለእይታ ከተሸፈነ ምን ዋጋ አለው የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው። የሰማዕታት፣ የታጋዮች፣ የኦህዴድ ጀግኖች፣ የብአዴን ታጋዮች፣ የህወሃት የተሰዉ … እያለ በከፍተኛ ወጪ ሃውልት የሚገነባውና ለማያውቃቸው አምባገነን የአፍሪካ መሪዎች ጎዳና በስማቸው የሚሰይመው ኢህአዴግ ፕሮጀክቱ ሲጠና ጀምሮ ሃውልቶቹን በማይነካ መልኩ ማድረግ ይገባው እንደነበር አስተያየት እየተሰጠ ነው። አስተያየት ሰጪዎቹ “ህወሃት ቀደም ሲል ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትንና የኢትዮጵያን ማንነት የሚያጎሉ ታሪካዊ ቅርሶችን በማጥፋት ለሚወቀስበት እኩይ ተግባሩ መገለጫ ነው” በማለት ድርጊቱን ኮንነዋል።በግልጽ ባይወጣም አራዳ ጊዮርጊስ የቆመው የአጤ ሚኒሊክ ሃውልትም አደጋው እያንዣበበው ነው።
ይህ ዜና በተላለፈ ጥቂት ቀናት ውስጥ ከምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አቶ አበበ ምህረቱ የአቡነ ጴጥሮስ ሃውልት እንደሚነሳ ገልጸው ይህም የሚሆነው ከስዊድን በሚመጣ ከፍተኛ አማካሪ ተቆጣጣሪነት እንደሚሆንና የባቡር ዋሻው ሥራው “እንደተጠናቀቀ አንዲትም ሣ/ሜትር ሳይዛነፍ እንደነበረ በቦታው ላይ በክብር” እንደሚቀመጥ አስታውቀዋል፡፡ የአጤ ምኒልክ ሃውልት ግን አሁን ባለበት ሁኔታ እንደሚቀጥል አስታቀዋል፡፡
በዚህ በሃውልቶቹ መነሳት ጉዳይ እስካሁን ድምጹን ያሰማ የተቃዋሚ ድርጅት ካገር ቤት አልተሰማም።
ኢህአዴግ ሰሞኑን እነዚህ ታሪካዊ ሃውልቶችን አስመልክቶ ይህንን የመሰለ ውሳኔ ሲያስተላልፍ የአዲስ አበባን 125ዓመት እንዲከበር ማድረጉ ሰንደቅዓላማን እየናቀ “የባንዲራን ቀን” ከማክበሩ ስላቅ ጋር በርካታዎች አያይዘውታል።
አቶ ሳምሶን በመመሪያ መፈታታቸውን አመኑ
የኢትዮ ቻናል ጋዜጣ ባለቤት አቶ ሳምሶን ማሞ ወዳጆቹ ከእስር እንዳስፈቱት አስታወቀ። ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ቃለምልልስ ያደረጉት አቶ ሳምሶን “ወዳጆቻችን አስፈቱን አላልኩም፤ ወዳጆቻችን ለሚመለከተው የመንግስት ባለስልጣን አሳውቀው አስፈቱን ነው ያልኩት” በማለት ተናግረዋል። “ለሁሉም አለቃ አለው፤ ህገወጥ ውሳኔ ነበር። ያንን እንዲያስተካክሉ እዛ የነበሩ ጓደኞቻችን ለሚመለከታቸው ሃላፊዎች አሳውቀው ነው የተፈታነው” ያሉት አቶ ሳምሶን ኢህአዴግን እንደሚወዱ በይፋ አስታውቀዋል። ኢትዮ ቻናል ጋዜጣ በራሱ በጀት የሚተዳደር እንጂ በኢህአዴግም ሆነ በሼኽ መሃመድ አላሙዲ እንደማይደጎም ሸምጥጠው ክደዋል።
አቶ ሳምሶን ከህግ ውጪ መታሰራቸውን ደጋግመው በገለጹበት ቃለ ምልልስ እንደ እሳቸው የሰብአዊ መብት ጥሰት ለሚካሄድባቸው ጠበቃ በመሆን እስከ ህይወታቸው ህልፈት ድረስ እንደሚሟገቱ ተናግረዋል። እግረ መንገዳቸውንም የማስታወቂያ ድርጅታቸው 1.7 ሚሊዮን ብር የግብር ዕዳና የገንዘብ መቀበያ (ካሽ ረጂስተር) ሳይኖራቸው እንደሚሰሩ አምነዋል። አቶ ሳምሶን ለኢትዮ ቻናል ጋዜጣ በጀትና ስራ ማስኬጃ በአቶ አብነት ገ/መስቀል አማካይነት እንደሚረዱ፣ ስራቸውም ኢህአዴግን የሚደግፉ መረጃዎችን በመጻፍ የሼክ መሐመድን ሁሴን አለሙዲን ስምና ድርጅቶች መጠበቅ ቢሆንም በእውቀት ማነስ ኢህዴግን በማስወቀስና ሼኩን ትዝብት ውስጥ የሚጥል ሪፖርት በማስተላለፋቸው ፊት እንደተነሱ የጎልጉል ምንጮች ገልጸዋል። አቶ ሳምሶን ኢህአዴግንና ሼኩን ያስደሰቱ እየመሰላቸው የሚጽፉት ጽሁፍ በአስነዋሪነቱ ምሳሌ እየሆነ ለተሳዳቢ ስላጋለጣቸው ወዳጆቹ “የደንቆሮ ብዕር” እያሉ እንደሚሳለቁበትም ታውቋል። አቶ ሳምሶን በህወሃት ነባር ታጋዮች ዘንድ በጣም የሚጠሉና ከአቶ አማረ የግድያ ሙከራ ጋር በተያያዘ ስማቸው በተደጋጋሚ የሚነሳ መሆኑ የሚታወስ ነው።
No comments:
Post a Comment