Translate

Friday, November 23, 2012

ፈተናን ረቶ የተፈጠረ ሚስጢር


ከሥርጉተ ሥላሴ 21.11.2012

አንዳንድ ጊዜ በዬትኛውም ሁኔታ በራዲዮ፤ በቴሌቪዢን፤ በስብሰባ፤ ወይንም በማህበራዊ ኑሮ የሚኖሩ አገላለጾችን በትርጉም ማቃናት የተገባ ነው። አብሶ በዘበኝነት የተሰማሩ ብዕሮች ይህንን ኃላፊትነት ተግተው መወጣት ይኖርባቸዋል።
ብቁ – ንቁ – ሞራል፤ – ትእግስታዊ – ሰላማዊ – ትዕይንት። – መምህራዊ – ማህበራዊ — ዕምነታዊ ሞገድ። ምን ቀረኝ ይሆን? …  የሰለጠነ … ዓላማውን ጠንቅቆ ያወቀ – ፍላጎቱን የተረዳ – ያደገ – አህታዊነት የተከተበበት ድንቅ የነፃነት እንቅስቀሴ ነው የኢትዮጵያ የእስልምና እምነት ተከታዮች ተጋድሎ።
የእንቅስቃሴው ተመክሮ ማሳ ግን የንጋት ወጤት አይደለም። ከ40 ዓመት በላይ ዕድሜን ያስቆጠረ  የኢትዮጵውያን የወል እንቅቃሴ ልምድ ተጨባጭ ወጤት ነው። የኢትዮጵያ እስልምና እምነት ተከታዮችን የእንቅስቃሴ ድንቅነት ጉልበታም የሚያደርገው መሰረታዊ ነገር፤ በነበሩ ድክመቶች ላይ አልተመለሰባቸውም። ይልቁንም አዳዲስ የፈጣራ ቅኔዎችንም ተግባር ላይ አውሏል።
ሂደቶቹ በሙሉ ሙሉዑና የታቀዱ መሪም ያላቸው ናቸው። በሌላ በኩል ሰላማዊ ትግል ብቁ፤ ደፋር፤ መሪ ካገኘ ካሰቡት የሚያድርስ ሰጋር ስለመሆኑም ትዕይነቱ ተግባራዊ ታሪክ ሰርቷል። ትልቁ ነገር ወያኔ በግፍ የጫነውን ፍርኃትንና ስጋትን ገርስሷል። ይህ በራሱ ድርብ ድል ነው።
ሰላማዊ ትግል ሰላማዊ ነው። ሰላማዊነቱ ሙት መሬት ላይ ሆኖ ገዢ መሬት ላይ ያለውን በሁሉም ዘርፍ የተሟላ የሎጅስቲክስ ድጋፍ ያለውን መንግስታዊ ተቋም በእውነትን መዳፍነት፤ ግፍን ለመጣል በጀግንነት ፊት ለፊት መጋፈጡ ነው።
ሰላማዊ ትግል ህጋዊ መብቶች የታፈኑባቸውን የአፈጻጻም ሥርዓቶችን ጥሶ በመጓዝ በተለያዬ ሁኔታ ተቃውሞውን በመግለጽ ነፃነቱን ከጨቋኞች መንጋጋ በሰላማዊ ኃያል ማስላቀቅ ነው። እኩልነቱን በሰላማዊ አመጽ አስገድዶ ማምጣት መቻሉ ነው። መስዋዕትነቱ ግን ሰፊ ነው። ባዶ እጅ ነውና። የነፃነት አምላክን ግን በመንፈሱ ሰንቆ  የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ጥበቃው ሰማያዊ ነው።
ሰላማዊ ትግል ትዕቢተኞችን በሞራል ድቅቅ አድርጎ የሚያስተንፈስ ጉልበቱም ነው።  ኃይሉ ወደር የለውም። ታዳሚዎች ወደውና ፈቅደው ስለሚሰማሩበት ምንም የመንፈስ ሃብት – ንብረት ሳይባክን ለታሰበው ዓላማ ስኬታምነት በተዋህደ ቅንብር መንፈሳዊ ሃብቱን በአግባቡ መዋል ይችላል። አብሶ መሰረቱ የበሰበሰ ሥርዓት ከሆነ ተጨባጭ ሁኔታዎች እራሳቸው ገዢ መሬቱን ደልድለው ይጠብቁታልና።
ሰላማዊ ትግል ላይ ሁሉንም በእኩልነት መሬት ላይ በስፋት ስለሚያሳትፍ የዕድሜ፤ የጾታ፤ የብሄረሰብ፤ የእውቀት፤ የዕምነት ተዋፆውም ሙሉዑ ሰለሚሆን ተመክሮው ሆነ ልምዱ፤ መንፈሳዊ ሃብቱን ጨምሮ ጥሪተ – ዲታ ያደርገዋል።  ለሰላማዊ ትግል አርበኛ መቋጠሪያም አለው። መሰብሰቢያም አለው እሱም ድንግሉ ቅንነት ነው።
ቅንነት እንደ ቃሉ የአራት ፊደላት ቅመረት አይደለም። ቅንነት ለማናቸውም ዘርፍ ነፍሱ እስትንፋሱ ቅምጥ ሃብት ነው። ቅንነት ካለ ድል አለ። ቅንነት ካለ ፍቅር አለ። ቅንንት ካለ መደማመጥ አለ። ቅንነት ካለ ከበዱ ሸክም ቀላል ነው። ጨለማማው ጉዞ  - ብርሃናማ፤ ኮረኮንቹ – ደልዳላ፤ ወጣገቡ  - ሰጥና ለጥ ያለ ይሆናል።  የማናቸውንም ትግል ቀመስ  ፈተና ትብትብ የመፍታት አቅሙ ያለው ከቅንነት ዘንድ ብቻ ነው። ለእኔ ከፍቅር ይልቅ ቅንነት ይበልጥብኛል። ቅንነት ሲኖር ነው ፍቅርን እንደ ተፈጥሮ መተርጎም – ተጠቃሚ መሆንም የሚቻለው።
በዘመናችን ያየናቸው ህዝባዊ እንቅስቀሴዎች በቅነነት ሲመሩ ጉዟቸው ወደፊት፤ ውጤታቸው ሰብላማ ይሆናሉ። ቅንነት ሲያነክስ ደግሞ  ጉዞው ወደ ኋላ ይጎተታል። ልፋቱም ብላሽ። ስለሆነም ለህዝባዊ የነፃነት እንቅስቃሴ ሁለገብ መፍቻ ያለው ከቅንነት ነው። እኔ የእስልምና እምነት ተከታዮች እንቅስቃሴ አብዝቼ ታዳሚ የሆንኩበት መሰረታዊ ምክንያት ቅንነትን ሰንቀው ለዓላማቸው በመነሳታቸው። ከአንዱ ደረጃ ወደ ሌላው ደረጃ የሚያደርጉት ሽግግር ሁሉ ማራኪ፤ ልብ አንጠጠልጣይ ኪኖ ሆኖ ነው ያገኘሁት  - እኔ በግሌ። ለነፃነት እንቅስቃሴም አዲስ ፊኖሚናም ነው … ሥነ ጥበባዊም ውበት አለው። እንቅስቃሴው አሁን ደግሞ በአደገ ደረጃ ላይ በመገኘቱ እስረኞችን በታሰሩበት ቦታ ጸጥ ብሎ ተሞ የልቡን አድርሶ በጸጥታ ተምልሷል። ወሸኔ!
በዕለቱ ህዝባዊው ሞገድ በወያኔ መራሹ የፀጥታ አስከባሪዎች ቆስቋሽነት የደረሰበትን ጥቃት በትእግስት ተቋቁሞ ተልዕኮውን በጀግንነት ፈጽሟል። ሀገር ቤት ለሚገኙት ለሰላማዊ የተቃዋሚ ኃይሎች ታጋዮች ሰላማዊ ነው መንገዳችን፤ ስትራቴጃችን፤ ስልታችን ነው ለሚሉትም …. በእውነት መምህር ነው። የጀግንነት ውሎው በራሱ አንድ የተግባር የትምህርት ተቋም ነው።
አዎን በቃሊትው የኢትዮጵያ እስልምና አምነት ተካታዮች ትዕይነት ላይ ኢትዮጵውያን ወገኖቻችን ሁለገብ ተሳትፎና እገዛም እንዳደረጉ በሪፖርቱ ተደመጧል። ወሸኔ ነው። ይህ የኢትዮጵዊነትን ግብረ ገበ ነብዬ መሀመድም ገልጸውታል። ኢትዮጵያ የክፉ ቀን ዋሳቸው እንደነበረች መስከረዋል። ይህ ማለት ኢትዮጵዊነት በሁሉም መሰክ የነጠረ ሁለገብ የተግባር መስክ መሆኑን ቀደምቱን በቅኝት መፈተሽ ያስችልናል።
ኢትዮጵያዊነት በማናቸውም ፈተና ውስጥ ነጥሮ የሚወጣ የስምረት ማተብ ነው። ኢትዮጵያዊነት ለፈተና ሽንፈት ድርድር የሚያድርግ አይደለም። እደግመዋለሁ ኢትዮጵዊነት ለፈተና ሽንፈት  ድርድር የሚያደርግ አይደለም። ስለምን? ኢትዮጵዊነት ሲፈጠር ፈተናን ድል አድርጎ የተፈጠረ ነውና። አንድ ጽንስ በሁኔታዎች አለመስማማት ሊያሰወርደው ይችላል። እድገቱ ተጨንገፎ ከቀናቱ ቀድሞ ሊወለድም ነፍሱ ሳትቀጥልም ሊሞትም ይችላል …
ኢትዮጰያዊነት ግን ፍጥረተ – ነገሩ ይህ አይደለም። በሙሉ ቀን በአማላካችን በመዳህኒታችን ፈቃድ የተፈጠረ። አማኑኤል ለመንፈሱ ማረፊያነት – ጥግነት የፈጠረው ሚስጢር ነው። አሁን መጸሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንድ ቦታ ላይ ስለ ኃያሏ አሜሪካ፤ ስለ ኃያሉ ጀርመን ተጠቅሷልን? ስንት ጊዜ ነው የዓለምን የክርስትና ዕምነት በማዕከልነት ከሚመራው አንደበተ እግዚአብሄር፤ አካል ከሌለው ትጉኽ አገልጋይ ቃለ ወንጌል ላይ ኢትዮጵያ የተጠቀሰቸው? የኢትዮጵውያነት እናት ደግሞ ኢትዮጵያ ሀገራችን ናት።
… በምንም መስፈርት ኢትዮጵያዊነት ፈተናውና ያለፈው ሲፈጠር ነው! ኢትዮጵያዊነት ፈተናን ቀድሞ የተፈጠረ ድንግል መንፈስ ነው!  ኢትዮጵያዊነት ዛሬ ወይንም ትናንት የተፈጠረ አይደለም። ዓለምን ከነመሰረቱ የፈጠረ ረቂቅ መንፈሳዊ መክሊት ነው። ስለሆነም ፈተና ስለበዛ የሚያዳልጠው ወይንም የሚላጥ፤ ወይንም የሚፋቅ ወይንም የሚተረተር፤ ወይንም የሚሰነጠቅ አይደለም። ወጀብ አውሎ  በመጣ ቁጥር ወገቤን ያዙኝም የሚል አይደለም። ሊሆንም አይችልም።
አይደለም እኛን ዓለምን የፈጠረ ዕንቁ  - ቅዱስ – ድንግል  -ንጹህ መንፈስ ነውና …ገና ብዙ ተፈልፍለው የሚያበሩ ነገረ አልማዛት አሉት።
ከዚህ ጋር ልናያውና ልናስተውለው የሚገባው ትልቁ ቁም ነገር … ኢትዮጵያዊነት አብክሮ ///  በተደሞ፤ በአጽህኖት፤ ጨዋ፤ አድማጭ ፤ትዕግስተኛና የእውነት አርበኛ መሆኑን ማስተዋል አለብን። ኢትዮጵያዊነት ማለት ሐዋርያነትም ነው። ሐዋርያነቱ መሰረቱ ይሁን ጉልላቱ ማስተዋል ስለሆነ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች በተደሞ፤ በቀስታና በእርጋታ ይመረምራል፤ የሚጠፋው ምንም ነገርም የለም። እንዲያውም ቀድሞ የሚታሰቡትን ሁሉ አስቀድሞ የመተንበይ ብቃቱ ሙሉዑ ነው።
ይህ የኢትዮጵያ እስልምና ተከታዮች እንቅስቃሴ — እኛ የነጻነት፤ የእኩልነት፤ የመብት ጥያቄ ነው እንላላን። ከዚህም ሌላ
  1. 1.    ዓለም የሚታመስበት እጅግ የሚሰጋበት፤ የሚፈራበትና የሚረበሽበትም ጉዳይ አለ።  ጽንፈኛው የእስልምና ዕምነት እንቅስቃሴ።
  2. 2.   እንዲሁም የኢትዮ ጂኦ ፖለቲካዊ አቀማማጥና ለአካባቢው ያላት ሁለገብ መስህብነት።
  3. 3.   ከአካባቢው አጎራባች ሀገሮች ተለይታ ኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ተከታይ መሆኗ …።
  4. 4.   እስካሁን በነበሩት የሌሎች ሃይማኖቶች ጭቆናዎች፤ ግፎች  የዕንባ ዘመኖች ሁሉና ሂደቶችም  የእስልምና እምነት ተከታዮችን ነበር አጋርነት፤ ታዳሚነት በተጨባጭ መፈተሽ የሚፈልጉ ወገኖችም መኖር …
  5. 5.   በአመዛኙም የኢትዮጵያ የእስልምና እምነት በወያኔ ተከብሮና ተደምጦ የቆዬ ነው የሚሉም ቀላል ያልሆኑ ወገኖች ሀሳባቸውን ሲሰነዝሩ መደመጡ
ባጠቃላይ እነዚህ ነገሮች በአግባቡ ጊዜ ተስጥቷቸው ወጥ የሆነ አስተሰሰብና እገዛ ለማድረግ ጊዜ ይጠይቃል። ይህ የማስተዋል ጊዜ ደግሞ የኢትዮጵያዊነት ሥነ -ምግባር የተቀመመበት መንፈስ ነው። በጥሞናም የተቀመቀመበትም ጥልፍ ነው። ታዲያ ይህ የማስተዋል ጊዜ፤ ይህ የዳኝነት ጊዜ  ኢትዮጵያዊነትን ተጠያቂም ሊያደርገው ፈተና ላይም ሊያስቀምጠው በፍጹም አይገባም። ይህም ብቻ አይደለም ፈተናውን ማለፉንም ለመመስከር እኛ አቅም ያለን አይመስለኝም። ኢትዮጵያዊነትን ለመገምግም። ኢትዮጵያዊነት እኮ ጥልቅና ዝልቅ ነው ሚስጢራቱ።
ኢትዮጵያን አንድ ጀርመናዊ ጸሐፊ ሲጽፈው “ እኛ ከመፈጠራችን የቀደመችው ሀገር“ ሲል ነው የቀደሳት።  እኔ እንደማስበው በተለምዶ እንጂ የሶስት ሺህ ዘመነት ብቻ አይደለም ታሪካችን ከዚህም ያልፋል ዬኢትዮጵያ የግዛት ወሰን እስከ ማዳጋስካር … ነበር ይህም ብቻም አይደለም በ21 ምዕተ ዓመት የዓለም ህዝብ መፈጠሪያ መሆኗስ … ? ወደ ኋላ ስንት ዘመን በምልሰት እንደንፈትሽ ይጋብዝናል?
እንደ ማሳረጊያ …. ከሀገራችን ማንነት ጋር ያሉ ጉዳዮችን ስናነሳ ተያያዥ፤ ተወራራሽ የሆኑትን ተጨባጭ እውነታዎችን ትራስ ማደረግ ይኖርብናል። ኢትዮጵያዊነት በቀላል የሂሳብ ስሌት የሚደመርና የሚቀነስ፤ ወይንም የሚተረጎም አይደልም። ቅዱስ መንፈስ ነው። ለቅድስናው ለንጽህናው እጅግ ጥልቅ መረጃዎችን፤ ማመሳካሪያዎችን ማቅረብ ይችላል። ስለ ምንድ ነው 24 ሰዓት ሙሉ ግርማ ሌሊት ሳይፈሩ በዱር በገደል ቅጠል እዬበሉ ደናግል የሚጸልዩት … ሚስጢሩ ያለው ከዚያ ላይ ነው … የፈለቀ ጸበል የሚፈውሰውስ? በመጠነ ሰፊ ፈተናና ወጀብ የእናት ሀገር ህልውና መቀጠሉስ? የሰለጠነ  የአውሮፓን ጦር መክታ የነፃነትን ፋና ወጊ መሆኗስ? ፊደላችንስ … የውስጥ ውበታችን ጠረንና ከሩቅ ጠሪነትስ? ተፈሪነትስ? ፈተናን ሁሉ ረቶ የተፈጠረ ሚስጢር – ኢትዮጵያዊነት።
እግዚአብሄር አምላክ ትርጉም ያለውን ነፃነትን በሁሉም ዘርፍ በሀገራችን እናይ ዘንድ ይርዳን። አሜን!
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

No comments:

Post a Comment