“ውበትን ከማየት ይልቅ ለማሳየት እንባክናለን ” Teddy Afro’s New Interview with Addis Admas
ስለ ኢትዮጵያ ማንነትና ታሪክ፤ ስለ አገራችን ባህልና አዝማሚያ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ጥያቄዎችን በማንሳት፤ ከቴዲ አፍሮ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ባለፈው ሳምንት ማቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው የመጨረሻ ክፍል፤ በአንድ ርእሰ ጉዳይ ላይ እናተኩራለን – የኪነጥበብ ፈጠራ ላይ። የመረጥነው ርእሰ ጉዳይ፤ በጣም አስፈላጊ የመሆኑን በዚያው ልክ ለውይይትና ለትንታኔ፤ ለጥያቄና ለመልስ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ እንገነዘባለን። ቢሆንም ልንደፍረው ሞክረናል።
የኪነጥበብ የፈጠራ ስራ እንዴትና ከየት ይፈልቃል? የቴዲ አፍሮ ምላሽ፤ “ኪነጥበብ የሚፈልቀው ከስሌት ነው ወይስ ከስሜት?” የሚለውን ጥያቄ የሚያስቀይር ሊሆን ይችላል። ብቃትንና ሰብእናን፤ ነፍስንና ሃሳብን፤ ከራስ ጋር መሆንንና ውበትን፤ ፍቅርንና ቅንነትን እያወሳ ከኪነጥበብ ፈጠራ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምን እንደሆነ ቴዲ አፍሮ ሲናገር፤ ጥበብ አምልኮ ነው ይላል። ውበትን ማድነቅ አምልኮ ነው፤ ድንቅ ነገሮች ሁሉ የፈጣሪ ስራዎች ናቸውና በማለትም ይገልፃል።
ለውይይት እንዲመች፤ አንጋፋ አርቲስቶችን ፈተና ውስጥ ሊያስገባ በሚችል ነጥብ ቃለምልልሱን እንጀምራለን – ቀጥለንም የታዳጊ አርቲስቶችን ፈተና እናነሳለን።
የአንጋፋ አርቲስቶች ፈተና -
ማንኛውም አርቲስት፤ ሁለተኛው የፈጠራ ስራ ከመጀመሪያው የፈጠራ ስራ የተሻለ እንዲሆንለት ይፈልጋሉ። ሶስተኛው ስራ ደግሞ ከቀድሞዎቹ የላቀ እንዲሆን አድርጎ ለመስራት ያስባል። እንዲህ አይነት አስተሳሰብ ጥሩ ነው ወይስ ጭንቀትንና ጫናን ይፈጥራል?
የተሻለ ነገር ለመስራት ከፈለግህ፤ ውድድርና ንፅፅር ላይ ማተኮር የለብህም። ውብትን ለመፈለግ፤ ነፍስህ ወደሚፈልገው አቅጣጫ እንዲሄድ መልቀቅ አለብህ። ሌላ አማራጭ የለም። የውድድር መንፈስ ከተጫነህ ግን፤ የምትፈጥረው ስራ እውነትነት እንዳይኖረው ይታገልሃል፤ ያሰናክልሃል።
የተሻለ ነገር ለመስራት መወዳደር ምን ችግር አለው?
የተሻለ ነገር ለመስራት ትመኛለህ። ጥሩ ነው። ግን፤ ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ ደረጃ የምትሸጋገረው በምኞት ብቻ አይደለም። በአንድ ቅፅበት ወይም በአንድ ቀን ወደ ተሻለ ደረጃ አትሻገርም። ጥበብና ፈጠራ ከነፍስ የሚመነጩ ናቸው። በየጊዜው ከነፍስህ ጋር የሚዋሃዱ ሃሳቦችና ስሜቶች አሉ። እነዚያ የምታስባቸውና የምታሰላስላቸው ነገሮች፤ ከቀድሞው የተሻሉ ከሆነ፤ በየጊዜው ከነፍስህ ጋር እየተዋሃዱ፤ ልብ ሳትለው፤ ከአንድ ደረጃ ወደ ተሻለ ደረጃ ትሸጋገራለህ። ራስህን ከፍ ወዳለ ደረጃ ተሻግረህ ታገኘዋለህ። ያኔ ነፍስህ ከቀድሞው የተለየ ውበትን የማየትና የማድነቅ አቅም ይኖረዋል። ያኔ ነፍስህ፤ ከቀድሞው የተለየ ጥበብና ፈጠራ ማመንጨት ይችላል። ፈጠራና ጥበብ እንዲመነጭ ነፍስህን በነፃነት ለፈጠራ መልቀቅ፤ በነፃነት ነፍስህ በሚፈልገው አቅጣጫ እንዲበር መፍቀድ፤ በሚፈልገው ጥልቀት እንዲመሰጥ መልቀቅ… ከድሮ የተሻለ የጥበብና የፈጠራ ስራ ያመነጫል።
የተሻለ ነገር ለመስራት ስለተመኘህ ብቻ አይደለም። ብቃትህን ከአንድ ደረጃ ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግር ህይወት ያስፈልጋል። በንፅፅርና በውድድር መንፈስ፤ ዛሬ ከትናንት የተሻለ ነገር መስራት አለብኝ ብለህ ስለተጨነቅክ የተመኘኸውን ጥበብ አትፈጥርም። የብቃትህን ያህል መፍጠር የምትችለው፤ ነፍስህን በነፃነት በመልቀቅ ነው። ነፍስህን በነፃነት ለመልቀቅና ለመመሰጥ፤ ከሚረብሹ ሃሳቦችና ስሜቶች መራቅ አለብህ። የጥበብ ስራህ ላይ ብቻ የማተኮር የውበት ፍቅር ያስፈልጋል፤ ቅንነት ያስፈልጋል። በውድድር መንፈስ ከስራህና ከተመስጦህ መጣላት የለብህም።
መቼም፤ የተሻለ ነገር ለመስራት አለመመኘት መፍትሄ አይሆንም …
የተሻለ ነገር መመኘት ጥሩ እንደሆነማ ምን ጥያቄ አለው። ነገር ግን፤ የተሻለ ነገር ለመስራት፤ የተሻለ ነገር ማሰብና የተሻለ አቅም ላይ መድረስ ይኖርብሃል። የተሻለ ነገር ለማሰብና ለመሸጋገር ደግሞ፤ በንፁህ ልቦና፣ ለእውነት ታማኝ ሆነህ፣ በቅንነት ውበት ላይ ማተኮር አለብህ። ለፈጠራ ቁጭ ስትል አይደለም፤ ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ የምትሸጋገረው። በህይወትህ፤ የምታስባቸው፣ የምታደርጋቸው፣ የምታተኩርባቸው፣ የምትማረክባቸው ነገሮች ናቸው፤ ከነፍስህ ጋር ተዋህደው የሚያሸጋግሩህ። ዛሬ የት ደረስኩ፤ ነገ የት ድረስ አለፍኩ እያልክ አትለካውም። ታጣጥመዋለህ እንጂ። ለካኸው አልለካኸው፤ ለዛሬ የሚመጣ ለውጥ የለም፤ ጊዜህንና የነፍስህን ሃይል ከማባከን ውጭ ጥቅም የለውም።
በቃ፤ አሁን የሆነ ደረጃ ላይ ነህ፤ በዚያው መጠን ጥበብ ለመፍጠርና ለተመስጦ ነፍስህን በነፃነት መልቀቅ። ማየት በቻልከው አቅምና መጠን ታያለህ። ዛሬ የሆነ አቅም ላይ ነህ። ለፈጠራ ስራ የምትቀመጠው፤ የማየት አቅሜ ምን ያህል ነው ብለህ ለማስላት አይደለም። አቅምህን የምታሳድግበት ሌላ ጊዜ አለህ፤ እያንዳንዷ የህይወት ቀን ማለት ነው። አሁን ግን፤ አቅምህን ተጠቅመህ ለመስራት ተዘጋጅተሃል። በቃ ሌሎች ነገሮችን በሙሉ ወደ ጎን ትተህ፤ የማየት አቅምህን በነፃነት ከፍተህ ማየት ብቻ ነው … ውበትን ማየት። ለፈጠራ መመሰጥ በሚኖርብህ ጊዜ፤ የትኛው ደረጃ ላይ ነኝ ብለህ ለመለካት የምትጨነቅ ከሆነ፤ ትደነቃቀፋለህ። እና ከነፃነት መንፈስ ጋር መለማመድ አለብህ።
አቅምህን በላቀ ደረጃ ለፈጠራ የምታውለው በነፃነት ለመመሰጥ ከፈቀድክ ነው። ከነፍስህ ከሚመነጨው ሃሳብና ስሜት ጋር ትከንፋለህ፤ ትጓዛለህ። በነፃነት ትፅፋለህ፤ ትቀኛለህ፤ ታዜማለህ። እንዲህ ካደረግክ በኋላ ስራው አለቀ ማለት አይደለም። ከነፍስህ በነፃነት የመነጨውን ስራ፤ ገለል ብለህ ታየዋለህ። የመመጠን፤ የማመጣጠን፤ የማብሰል፣ የማጉላት ስራዎች ትጨምርበታለህ። እንዲህ ማስተካከያዎችን ከማድረግህ እና ውበትን ከማሰማመርህ በፊት ግን፤ በቅድሚያ ያንን ውበት ማየት መቻል አለብህ። ወይም ደግሞ ውበትን ለማሳየት እያሰብክ ከመባከንህ በፊት ውበትን ለማየት አይንህን መክፈት አለብህ። ውበትን ከማየት ይልቅ ለማሳየት ስንባክን እንኖራለን።
የአርቲስት ስራ ውበትን ማሳየት አይደለም እንዴ? የምሰራው ነገር ሰው ይወድልኛል ወይ ብሎ ማሰብ ፈጠራን ያደነቃቅፋል እያልከኝ ነው?
አዎ አርቲስት ውበትን ያሳያል። ግን ውበትን ማሳየት የምትችለው፤ አንተ ራስህ ባየኸው መጠን ነው። ለፈጠራ ስትዘጋጅ፤ ውበትን እንዴት አሳያለሁ ብለህ የምታስብ ከሆነ፤ ውበትን የማየት ተመስጦህ ይበታተናል። አንተ ራስህ ሳታይ፤ ለሰው ማሳየት አትችልም። ውበትን ለማየት ስትነሳ ግን፤ ሌሎችም እንዲያዩ ትጋብዛለህ። ባየኸው መጠን።
ለፈጠራ ስትቀመጥ፤ ምን ያህል የፈጠራ አቅም አለኝ ብለህ ማሰብ የለብህም። ባለህ አቅም ትሰራለህ። እሺ፤ ግን በሌላ ጊዜስ የፈጠራ አቅምህን እንዴት ታሻሽላለህ?
ውበት አለ። ውበትን የምናየው ግን፤ ባለን አቅም ነው። አቅማችንን ለማሳደግ፤ አንዱና ትልቁ ነገር ፍቅር ይመስለኛል። ፍቅር አይንህን ይከፍታል። እንድታይ ሃይል ይሆንሃል። በየቀኑ በፍቅር የምትንቀሳቀስ ከሆነ፤ ወደ ተሻለ ደረጃ ይመራሃል። ራስህን ከፍ ያለ ቦታ ላይ ታገኘዋለህ። ወደ ተራራው አናት ያደርስሃል።
ውበት ሁሉ ክፍት ሆኖ ይጠብቅሃል። የማየት ደረጃችን ነው ልዩነቱ። ፍቅር ደግሞ እንደ ብርሃን ነው። በብርሃን ውበትን እንድታይ ያደርጋል። በሃዘን፣ በንዴት፣ በችግር ውስጥ ስትሆን፤ ጥሩ ነገር አይታይህም። ውበት ጠፍቶ ሳይሆን፤ በመጥፎ ስሜት ውስጥ ስትሆን አይታይህም። የምትወዳቸው ነገሮች እንኳ ይደበዝዙብሃል። ስትታመም፤ የምትወደው ምግብ ያስጠላሃል፤ ጣእሙ ይጠፋብህ የለ? ምግቡኮ የምትወደው ምግብ ነው። አልተቀየረም። ግን፤ ማጣሪያውና ማጣጣሚያው ተበላሽቷል። መጥፎ ስሜት ውስጥ ስትሆን፤ ድሮ የማይረብሽህ ድምፅ ይረብሽሃል፤ እንደ ተራ ነገር የምታያቸው ነገሮች ያናድዱሃል፤ ማንኛውም ሰበብ ያነጫንጭሃል። ሁሉም ነገር ይጨልምብሃል፤ የሚማርክ ውበት ማየት ይሳንሃል።
በፍቅር ውስጥ ስትሆን ደግሞ፤ ብርሃን ታገኛለህ። ውበትን ደምቆ ታያለህ። በቅንነት ውስጥ ስትሆን፤ ውበትን ጥርት ብሎ ታያለህ። ከቅንነትና ከፍቅር ጋር ስትለማመድ፤ ራስህን ከፍ ያለ ብርሃናማ ቦታ ላይ ታገኘዋለህ። ፍቅርን የራስህ ካላደረግከው ግን፤ ያንን ውበት ሳታየው ትኖራለህ። ወይም ጫፍ ጫፉን ብቻ እያየህ፤ ጭምጭምታውን ብቻ እየሰማህ ትኖራለህ። ፍቅር ግን አጥርቶ ያሰማሃል፡ በብርሃን ያሳያሃል። ፍቅር፤ ላምባዲና ነው።
የአዲስ ድምፃዊያን፤ የታዳጊ አርቲስቶች ፈተና።
አዲስ ዘፈን መስራት፤ አዲስ አልበም ማውጣት በተለይ ለታዳጊ አርቲስቶች ዛሬ ዛሬ ከባድ ሆኗል። ቢሆንም፤ ወደ ሙያው እስከገቡ ድረስ፤ ክብደቱን ተቋቁመው ለመስራት እየወደቁና እየተነሱ የሚሞክሩ መኖራቸው አይቀርም። እስቲ፤ ብዙ መላላጥ እንዳይደርስባቸው የሚያግዙ ሃሳቦችን ከእስካሁኑ ልምድህ አካፍላቸው …
ከሁሉም በላይ የራስህን ፍላጎት ማወቅ ነው፤ ራስህን ማወቅ። አንዳንዴ የሆነ ሙያ ውስጥ ለመግባት የምትነሳው፤ በጊዜያዊ ስሜት ሊሆን ይችላል። በሰዎች የተሳሳተ ግምት ተገፋፍተህም ወደ ሙያው አዘንብለህ ይሆናል። በሙያው ሳይሆን ከሙያው ጋር አብረው በሚታዩ አጃቢ ነገሮች ተማርከህም ሊሆን ይችላል። በዚህ በዚህ መንገድ ወደ ሙያው ከገባህ፤ ሙያው ሸክም ይሆንብሃል። በየቀኑ በግድ ልስራው ብትል፤ ሰአት ጠብቀህ ለመገላገል የምትቸኩልበት ስራ ይሆናል። ሃይል ታጣለህ።
ራስህን ማወቅ ነው ቀዳሚው ነገር። ከሁሉም በላይ የምወደውና የሚያስደስተኝ ይሄ ሞያ ነው? ለዚህ ሙያ የተፈጠርኩ ያህል ይሰማኛል? ነፍስህ ከሙያው ጋር የተሳሰረች ከሆነች፤ ወደ ሙያው ትገባለህ። ከሙያው ጋር መሆን ማለት ከራስህ ጋር እንደመሆን፤ ከራስህ ጋር እንደመገናኘት ነው። ወደ ሙያው ከገባህ በኋላም፤ ከራስህ ጋር መሆንና መገናኘት አለብህ። ያኔ የሚያስፈልጉህ ነገሮች ወዳንተ ይመጣሉ። ድምፃዊ ሆነህ፤ ግጥም ወይም ዜማ የመድረስ ተሰጥኦ ከሌለህ፤ ራስህን መሆን አለብህ። ግጥምና ዜማ ደራሲዎች ወዳንተ ይመጣሉ። ልብህን ክፍት አድርገሃላ።
ከራስህ ጋር ተለያይተህ፤ እንደ እገሌ ግጥምና ዜማ ራሴ ልፃፍ ብትል ግን አይሳካልህም፤ ግጥምና ዜማ ደራሲዎች ወዳንተ እንዳይመጡም እየከለከልክ ነው። ከራስህ ጋር ስትሆን ግን፤ ግጥምና ዜማ ደራሲዎች ትስባለህ። ሁሉም፤ ራሱን አውቆ ከራሱ ጋር ሲሆን፤ እንደየሙያው ተቀራርቦና ህብር ፈጥሮ መስራት ይችላል፤ ሁሉም ይሳካላቸዋል። ስለምን ጉዳይ ልዝፈን? ስለምን ጉዳይ ልፃፍ? በየትኛው መንገድ ልዝፈን? የትኛውን አይነት ዜማ ልፍጠር? ሁሉም ነገር ላይ፤ ራስን ማወቅ ያስፈልጋል።
ነፍሳቸው የወደደውን መስራት ነው ዋናው ነገር። ጥበብ፤ ከነፍስህ ከስብእናህ የሚመነጭ ነው። ከሌላ ሰው ነፍስና ስብእና የሚመነጭ አይነት ጥበብ ለመስራት መሞከር አያስፈልግም። በከንቱ መድከም ነው። ራስህን ስትሆን፤ ከነፍስህ ጥበብ እንዲፈልቅ እድል ትከፍታለህ።
ጥበብና ውበት፤ በተፈጥሮው ቅንነትን ይጠይቃል። የማድነቅ ቅንነት። ትህትናን ይጠይቃል – ገና ብዙ የሚታይ ውበት እንደሚቀርህ የሚገነዘብ ትህትና። ቅንነትና ትህትና ሲጓደል፤ ውስጥ ያለውን አቅም አውጥተህ እንዳትጠቀም ያደርጋል – ትንፋሽን እንደሚዘጋ፤ አይንን እንደሚጋርድ ስብ ይሆናል።
የፈጠራ አቅምህን አንቆ፤ ውበትን የማድነቅ እይታህን ደፍኖ ይይዛል። የቅንነት ስብእናን፤ የማድነቅ ባህርይን ማዳበር ያስፈልጋል። የማድነቅ ባህርይ ማለት፤ ድንቅ ነገሮችን የማየት አቅምህን የሚያሳድግ ነው። ጥሩና መልካም ነገሮችን ማድነቅ ቅንነት ነው። ጥበብ ይህንን ይጠይቃል። ጥበብ አምልኮ ነው። ፍቅርን ስታደንቅ አምልኮ ነው። አበባን ስታደንቅ አምልኮ ነው – ሁሉም ድንቅ ነገሮች የፈጣሪ ስራዎች ናቸው። የወንዝና የተራራ ውበት፤ የሰው ውበትና መልካም ፀባይ እያደነቅክ ስትፅፍ፤ ስታዜም አምልኮ ነው።
እንጃ
ማን ነሽ አንቺ
ማን ነን እኛ
ውበትስ ምንድን ነው
ምንድነውስ ማድነቅ
ብዬ እስከምጠይቅ
ብዙ እንድመራመር መልክሽ አስገደደኝ
ከተራ ሰውነት ወደ ሊቅ ወሰደኝ
ወሰደኝ ወሰደኝ ወሰደኝ ከማላውቀው ቸአገር
አንቺን ብቻ ሳስብ ትቼ ሌላ ነገር
እያደር ተጋለጥኩ ለፍቅርሽ ታየሁት ተደብቄው ከኔ
አንቺስ ልቤ ላይ ነሽ የቱ ጋ ነኝ እኔ
እንጃ!
ሕዳር 21/2001 ዓ.ም.
ቃሊቲ
ዝናባማው ምሽት
ጊዜው ማታ ነበር፣ ዝናባማ ምሽት
ደጁ ረጥቦ በ’ንባ፣ ሰማይ ባለቀሰው
በጐዳናው ማዘን፣ አይሄድም
አንድ ሰው
ውዴ፤ እኔና አንቺ፣ በከተማው መሃል፣ ብዙ መንገድ አልፈን
ከመንገድ መብራቶች፣ አንዱን ተደግፈን
ተቃቅፈን በካፊያ፣ ፍቅርን የሞቅንበት፣
ያ ጣፋጭ ውብ ማታትዝ ይለኛል ሁሌም፣ ምሽቱን አስታኮ፣
የዘነበ ለታ
ዝናባማው ለሊት፣ አንቺ የሌለሽበት
አስተክዞኝ ባሳብ፣ ይዞኝ ሄዶ ድንገት ደጅ የጣለው ዝናብ፣
ቤቴ ሆኜ አራሰኝ ያለፈው ትዝታ፣ አንቺን ሲያስታውሰኝ
የምጠለልበት፣ ናፈቅኩት ገላሽን
ቀላቅሎ ጣለና፣ ዝናብ ትዝታሽን
አስታውሳለሁ፣ መሬቱ እርጥብ
ነበር
ጐርፍ ይምቦጫረቃል
አልፎ አልፎ ይሰማል፣ የሚያስፈራ መብረቅ
በመስመር ብልጭታ፣ ሰማይ ሲሰነጠቅ
በውሀ ነጠብጣብ፣ መሬት ስትደለቅ
ዝናቡን ሊጠለል፣ ሰው ገብቶ ከቤቱ
ከሰው ልንጠለል፣ ከደጅ ወጥተን እኛ ፍቅርን የሞቅንበት፣
ያ ጣፋጭ ውብ ማታ
ትዝ ይለኛል ሁሌም፣ ሌሊቱን አስታኮ፣ የዘነበ ለታ
አስታውሳለሁ፣ ካፊያው እየጣለ፣ ብርድ ሲበረታ
ልሞቀው ስጠጋ፣ ፍሙ ከንፈርሽን
በውሃ ነጠብጣብ፣ ድንገት ብቅ ብሎ፣ ያየሁት መልክሽን
መቼም አልረሳውም፣ በየወቅት ይመጣል፣ ሌላ ክረምት ሆኖ
ትኩስ ጉም ትንፋሽሽ፣
በትዝታ ዳምኖ
ድቅን ይላል ፊቴ
ድንግጥ ይላል ልቤ፣
ሁሌም በትዝታ
ምሽቱን አስታኮ፣ የዘነበ ለታ
2000 ዓ.ም.
ቃሊቲ
ቴዎደሮሰ ካሣሁን
No comments:
Post a Comment