Translate

Saturday, November 24, 2012

ተሃድሶ ... ተሃድሶ .... ተሃድሶ ..... ተሃድሶ .......

በኢትዮጵያ ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት የድርጅት እጥረት አላጋጠመንም። ለቁጥር የሚታክቱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቋቁመዋል። ከመንደር እሳቤ ጀምሮ እስከ ብሄራዊ ደረጃ ከተዋቀሩት የተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ምን ያህል እንደተሳካላቸው በውል ባይታወቅም ህዝብ አደራጅተናል የሚሉ አሉ። መቋቋማቸው ሳይሰማ “እንደወጡ” የቀሩ ብዙ ናቸው። እንደው ለወጉ ያህል ስያሜያቸውን እያሰሙ በመግለጫና በዘለፋ “አልጠፋንም” የሚሉም አሉ። ለዓመታት ጎረቤት አገር መሽገው ከዛሬ ነገ “መጣን” የሚሉን አሉ። መኖራቸውም መሞታቸውም ልዩነት በሌለው መልኩ የሚንከላወሱ “ሙት” ነዋሪ ፓርቲዎችም አሉ። የፖለቲካ ዓላማቸው ሌሎችን በሾኬ መጣል፤ የኢኮኖሚ ፕሮግራማቸው ሌሎቹን ማክሰር፤ የማኅበራዊ ፖሊሲያቸው ማበጣበጥ፤ የሃይማኖት አመለካከታቸው “እኛ ካልባረክነው ዉጉዝ ነው” የሚል ፕሮግራም ያላቸው የሚመስሉም አሉ፡፡ ኢህአዴግ ጥብቆ አልብሶ ያደራጃቸው “ተለጣፊ” የሚባሉትም አሉ። ቤተሰብ ሰብስበው ቃለ ጉባኤ እያጸደቁ አገርና ህዝብ ነጻ እናወጣለን የሚሉም አሉ። አጋነናችሁ ካላላችሁን ከእቁብና ከእድር ባነሰ አደረጃጀት አገር ለመምራት ተነስተናል የሚሉ እፍረት ያልፈጠረባቸውም አሉ። እየተሰነጠቁና እየተሰነጣጠሩ ኤ፣ ቢ፣ ሲ፣ ዲ፣ ኢ፣ ኤፍ፣ … የሚባሉትና ሌላም ሌላም ዓይነት፡፡ ለምን እንዲህ ይደረጋል ሲባሉ “ለአንድ ኢትዮጵያችን ብለን ነው” ይሉናል!

ታግለው የሚያታግሉ አመራሮች አሉ። ስብዕናቸው የሚወደድ መሪዎች አሉ። ከሃሳብ እንጂ ከድርጅትና ከግለሰቦች ጋር ጸብ እንደሌላቸው በማስተጋባት ያመኑበትን የትግል አቅጣጫ የሚከተሉ አሉ። በርካታ ደጋፊና ተንከባካቢ ያላቸው ዘወትር ስለመቀራረብና ስለመተባበር አስፈላጊነት የሚሰብኩ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ድርጅት ባቋቋሙ ማግስት በትዕዛዝ የሚወገዙ፣የሚሰደቡና ቀጠሮ ተይዞ በደቦ የጥላቻ ዘመቻ የሚከናወንባቸው አመራሮችም አሉ። ደረጃ የሚወጣላቸውና የሚፈረጁም ጥቂት አይደሉም። ይህም የሚሆነው ለኢትዮጵያ ሲባል ነው ይባላል።
ድርጅት ባቋቋሙ ማግስት ሌሎች ድርጅቶችን በማውገዝ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁ አመራሮች አሉ። በሚያራምዱት ያረጀና የነተበ ፖለቲካ ስንዝር መራመድ ሳይችሉ ቀርተው ሌሎችን በማወገዝ የተጠመዱ አመራሮች አሉ። ፓርቲን ከፖለቲካ ስራ ይልቅ ወደ ግል ማህበር በመቀየር ሲሳደቡና ሌላውን ሲያወግዙ ኖረው ለመሞት የወሰኑ አመራሮች አሉ። ምን እየሰሩ እንደሆነ የማናውቃቸው አመራሮች አሉ። እነዚህና ሌሎች ሁሉም የሚናገሩት ግን ስለ አገርና ህዝብ ነው። “ነጻ አውጪ” ስለ መሆናቸው!!
ብዙ አይነት የተቃዋሚ ድርጅቶች ደጋፊዎች አሉ። ያለአንዳች መታከት በችግርና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ እያለፉ የሚታገሉ አሉ። ዳር ሆነው የሚያሽሟጥጡ፣ በሌሎች መስዋዕትነት የድል ክሬም ለመላስ የሚመኙ አሉ። በስድብና በዘለፋ መንግስት መቀየር እንደሚቻል አድርገው የሚናደፉ፣ ነገር ግን በተግባራዊ ድጋፍ ሲመዘኑ መስፋሪያ የማይሞሉ አሉ። አስር ዶላር በማዋጣት የሚደግፉትን ፓርቲ ሚስጥርና እንቅስቃሴ በዝርዝር በአድራሻቸው ሪፖርት እንዲቀርብላቸው የሚጠይቁ አሉ። ከሁሉም በላይ ወዴት እንደሚያዘሙ ግራ ተጋብተው ዝምታ የመረጡ አሉ። እነዚህ ዝም ያሉ ብዙሃን (silent majority) ተብለው የሚጠቀሱት ክፍሎች ትልቁን ቁጥር ስለሚይዙ ወደ ትግልና “እኔም ያገባኛል” መንፈስ ሊዛወሩ የግድ ነው። እንዴት? በእውቀት ተሃድሶ!!
ከተሃድሶዎች ሁሉ የእውቀት ተሃድሶ ካልቀደመ መሪው፣ ተመሪውና ድርጅቱ ሁሉም ተያይዘው ሲጓተቱ 21ኛው ክፍለ ዘመን ይጠናቀቃልና የሚቀድመውን ማወቅ ብልህነት ይሆናል። ለሁሉም የእውቀት ተሃድሶ በቅድሚያ! ለዲያስፖራው ሆነ ለአገር ቤቱም ወገን የእውቀት ተሃድሶ በቅድሚያ!! የእውቀት ተሃድሶ ባስቸኳይ፣ የእውቀት ተሃድሶ የዘለቀው ደጋፊና ዜጋ ሲነፍስ አብሮ በነፈሰበት አይነፍስምና!!

No comments:

Post a Comment