Translate

Monday, November 19, 2012

ሰንበት ምሳ፤ መንግስት “ሲጠብሸው”


Abe Tokchaw
ዛሬም ሰንበት ምሳ ይዤ ብቅ ብያለሁ። ጨዋታዋን ትላንት ለታተመችው ፍትህ፤ አዲስ ታይምስ መፅሄት ሰድጃት ነበር። ዛሬ ደግሞ በዕለት እሁድ ኢንተርኔት መስኮታቸውን ከፍት ለሚያደርጉ ወዳጆች በሰንበት ምሳ መልክ እነሆ አስቀመጥኳት! መልካም ሰንበት…
ጠብሽ የሚለውን ቃል፤ ችግር፣ ርሃብ፣ ጉስቁልና፣ ማጣት እና  መንጣት ሲል ያልታተመው የአራዶች መዝገበ ቃላት ይፈታዋል። ታድያ “መንግስት ሲጠብሸው” የምትለው ቃል ለምን የዛሬ ጨዋታችን ርዕስ ሆነች? ብሎ የሚጠይቅ ካለ እስከ ማብቂያው ያንብብልኝማ ብዬ እጋብዛለሁ።
ሰላም ወዳጄ እንዴት ሰነበቱልኝ…? ባለፈው አስራ አምስት ቀን በአዲሲቷ አዲስ ታይምስ ላይ የወጣው ጨዋታችን አንዳች የሆነ የመሰዳደር ችግር ነበረው። በዚህም የተነሳ ለተደነቃቀፈ ንባብ ዳርጌዎታለሁ እና በይፋ ይቅርታ እጠይቃለሁ።
መቼለታ ወዳጃችን እና “አለቃዬ” ተመስገን ደሳለኝ በፌስ ቡክ ግድግዳው ላይ እስክንድ ነጋን ንብረት መወረስ አስመልክቶ አንድ መረጃ ለጥፎ ተመልክቼ ነበር።

ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድ ነጋ መንግስት በቃሉ “አንተን ማሰር ሰለቸን” ቢለውም፤ በተግባር ግን ለስንተኛ ጊዜ እንደሆን እንጃ በመንግስት እስር ተፈፅሞበታል። በዛውም ፀሐዩ መንግስታችን ማንንም ማሰር እንደማይሰለቸው አሳይቶናል።
ካቻምና በውበሸት ታዬ የተጀመረው የጋዜጠኞች እስር ርዮት አለሙን እና እስክንድር ነጋን ባለመሰልቸት አስሯል። አረ ወዳጃችን ተመስገንም ቃሊቲን በጨረፍታ እንዲቀምሳት እና እንዲያቀምሰን ተዳርጎ ነበር።
እኔም ትንሽ ብቆይ ኖሮ ቃሊቲ የሚቀርልኝ እንዳልነበር “ሲንከባከበኝ” የነበረው ደህንነት “በአጠቃቀስኩ” ነግሮኛል።
እዝች ጋ የበሀይሌ ጨዋታ ትምጣ። ያኔ በ97 ዓ.ም፣ ያኔ በቀውጢው ሰዓት ያኔ መንግስታችን ወጣት እና ጣት ማየት ደሙን በሚያፈላበት ጊዜ፤ የፌደራል ፖሊሶች በምሽት አንድ ቤተሰብ ቤት ዘብ ብለው ገቡ።
እቤት ውስጥ ያገኙት ሁለት ወጣት ወንድማማቾች ነበር። የቤተሰቡ ኃላፊዎች የእንጀራ ነገር ሆኖባቸው ውጪ ሀገር ነበሩ። ነገር ግን “ልጅህ ባለበት ልብህ አለ” እንዲሉ ቀልባቸው ግን ከልጆቻቸው ጋ ነበርና፤  ልክ ፖሊሶቹ ገብተው ወጣቶቹ ላይ አይናቸውን ሲያጉረጠርጡባቸው እና ቤተሰቦቻቸው ስልክ ሲደውሉ እኩል ሆነ።
ይሄን ጊዜ ወንድማማቾቹ፤ ስልኩን አንተ አንሳ አንተ… ሲተያዩ ፖሊሱ “አንሳ” ሲል አንደኛው ላይ አንባረቀበት። ከድንጋጤው የተነሳ “ቫይብሬት” ላይ እንዳደረጉት ስልክ እየተንቀጠቀጠ አነሳው። አባት ከዛኛው መስመር ላይ ሆነው፤ “እንዴት ናችሁ… ምንድነው የምንሰማው ጉድ… ለመሆኑ እናንተ ደህና ናችሁ!?” ብለው ይጠይቃሉ። ፖሊስ ሆዬ አንዳች መረጃ እየተቀባበሉ ቢሆንስ ብሎ ጠርጥሮ ከልጁ እኩል ጆሮውን ስልኩ ላይ ለጥፎ የሚባባሉትን ይሰማ ጀመር። በዚህ ሁኔታ ወጣቱ ምን ይናገር?
ድንገት ግን ይቺ ንግግር በአንደበቱ ላይ ተከሰተችለት… “አባዬ አታስቡ እኛ ፖሊሶች ቤታችን ድረስ መትተው እየተንከባከቡን ነው!” ብሎ በፖሊስ መከበባቸውን ለአባቱ በመላ ተናገረ።
ይቺን ጨዋታ ወዳጃችን በሀይሉ ገ/እግዚአብሔር በ “ኑሮ እና ፖለቲካ” መፅሐፉ ላይ አካቷታል። እናመስግነውና እንቀጥል።
እኔም ከሀገር ከመውጣቴ በፊት የደህንነት ሰራተኛ “ደህና አድርጎ ሲንከባከበኝ” ነበር። ታድያ ይሄ ሲንከባከበኝ የነበረ ደህንነት ለስድስት ወራት ሲመረምረኝ ቆይቶ ምን አለኝ መሰልዎ…
“ከአሁን በኋላ እኔ እና አንተ ያለን ግንኙነት ተቋርጧል። ከዚህ ቀጥሎ የአንተን ጉዳይ የሚይዙት አለቆቼ ናቸው። እነርሱ አንተን ለመክሰስ የሚያስችል በርካታ ማስረጃ አላቸው። እስከዛሬ እኔ እመለስሀለሁ ብዬ ነበር እንዳትከሰስ ያደረኩህ። አንተ ግን አልመለስም አልክ…ስለዚህ አለቆቼ ያናግሩሃል። ግን አይዞህ ላትታሰርም ትችላለህ…” አለኝ።
በቅርቡ አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ እናቴ “አልዳነችም” እና እንድትመለስ እፀልይላታለሁ። ብለው የሰጡትን ቃለ ምልልስ ሳነብ፤ ኢህአዴግ ግቢ ያሉ ሰዎች በሙሉ አንድ ሰው እንደነርሱ ካለመነ “የታመመ” ነው የሚመስላቸው ማለት ነው? ብዬ ስደነቅ ነበር።
እናልዎ ደህንነቱ ወዳጄም ለስድስት ወራት ያህል እድን ዘንድ መከረኝ። በመጨረሻ ላይ ከነገረኝ ነገር ታድያ ያስደገረመችኝ “ከዚህ በኋላ አለቆቼ ያናግሩሃል ግን አይዞህ ላትታሰርም ትችላለህ” ያላት ነገር ናት።
አያ ጅቦ ሆዬ ጦጢትን ዛፍ ላይ ሆና ቢመለከታት ለካስ ራብ ብሎት ነበርና፤ “ጦጢትዬ አይዞሽ ውረጂ አልበላሽም!” ቢላት ጦጣስ ታድያ ማናት…? ጦጣ እኮ ናት። ምን አለችው? “አያ ጅቦ አልበላሽምን ምን አመጣው!?” ብላ ላጥ አለች።
እኔም “አያ ደህነነት አትታሰርምን ምን አመጣው!?” ብዬ በኩሩው ኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮራም ፈራም እያልኩ ነካሁት፤
በነገራችን ላይ ይህ ከሆነ ዛሬ ልክ አንድ አመት ሆነው። ጊዜው እንዴት ይሮጣል!? እግረ መንገዴንም ለስደቴ አንድ አመት መታሰቢያ ብዬ ስሎ ደህነነቱ ወዳጄ ነካ ነካ አደረኩ እንጂ… የነበረውን ሁሉ ልዘርዝረው ካልኩ ብዙ ነው…! ቆይማ ወዳጄ ሌላ ቀን ቁጭ ብለን እናወጋታለን!፡
እንደኛ በቦሌ ጎዳና ሽው ሊሉ እየቻሉ “እምቢኝ ለሀገሬ” ብለው የታሰሩት ጋዜጠኞች እነ ውብሸት ታዬ፣ ርዮት እና እስክንድር ነጋ መንግስት አሸባሪ ቢላቸውም እኛ ደግሞ የመጣው ይምጣ ብለን “ሀገር አኩሪ” እንላቸዋለን!
ወደ መነሻችን ስንመለስ፤ መንግስታችንን አንዳንዶች በሰፈር ጎረምሳ ሲመስሉት ተመልክቻለሁ። ዝም ብሎ ጎረምሳ ሳይሆን ማናባቱ ይናገረኛል የሚል፤ እግዜርን ጨምሮ ማንንም የማይፈራ ባለ ጡንቻ እና ባለ ጡቻ ወጠብሻ ጎረምሳ።
እንዲህ አይነት ጎረምሶች በተለይ “ጠብሿቸው” አያግኙን… ካገኙን ግን ጉዳችን ፈላ!
“ና…”
“አረ ተልኬ እየሄድኩ ነው እቸኩለለሁ…!”
“ዝም በል … ጥጋበኛ ደግሞ ተልኬ ነው ትላለህ እንዴ…!? አረ ድፍረት አረ ጥጋብ…!”  አቤት ኩርኩማቸው! አንዳንዴ ደግሞ አምበርክከው አይቀጡ ቅጣት ይቀጣሉ ባስ ሲልም የተላክንበትን ፍራንክ ይወርሳሉ። ምክንያቱም እነርሱ ባለ ጡንቻ ናቸው። እነርሱ ማንንም አይፈሩም። እነርሱን “አረ ተልኬ እየሄድኩ ነው…” ብሎ መናገር ድፍረት ነው። ህግ እና ደንብም መተላለፍ ነው። በዛ ላይ ደግሞ ጠብሿቸዋልና ገንዘባችንንም ይወርሱታል።
ባለ ጡንቻው መንግስታችን፣ ማንንም የማይፈራው መንግስታችን “ጥብሽ…” ብሎታል ብዬ እንዳስብ ያደረገኝ ታድያ የእስክንድር ነጋን ንብረቶች ለመወረስ ማቆብቆቡ ነው።
እስክንድር ታክስ አላጭበረበረ… ቤቱንም በሙስና አልገነባውም። በምን ምክንያት ንብረቱ እንደሚወረስ አይገባም። የእርሱ ብቻ ሳይሆን በቅርቡ በሞት የተለዩት የእናቱ ንብረትም ነው የሚወረሰው አሉ። ምንድነው ጉዱ ቢሉ “መንግስት ጠብሾታል” ከሚለው ውጪ የተብራራ መልስ የሚሰጠን አካል ያለ አይመስለኝም።
እሺ ሌላው ይቅር የባልና ሚስት ንብረት የሁለቱም መሆኑ ይታወቃል። እሺ እስክንድር ንብረቱን መወረስ ይገባዋል ብለን እንመን ግን የባለቤቱ እና የልጁ ድርሻ በምን እዳ ነው የሚወረስባቸው? “ጎረምሳውና ባለ ጡንቻው መንግስት፤ እስክንድርን “ና…” ቢለው እስክንድርም “አረ ተልኬ ነው እቸኩላለሁ” ስላለ “አረ ጥጋብ” አረ ድፍት ብሎ የማናለብኝ ቅጣት እድሜ ልክ እስር ተበየነበት እሺ ይሁን… ከዛ አልፎ ተርፎ “ያለህን በሙሉ ቁጭ አድርጋት!” ብሎ ማለት ከዋልጌ ጎረምሳ እንጂ ከመንግስት አይጠበቅም! ብንልስ!?
ወዳጄ ለማንኛውም ለዛሬ ይቺን ያክል አስቴአየት ከሰጠሁ ይበቃኛል።
አማን ያሰንብተን!

No comments:

Post a Comment