ኢሳት ዜና:-በአባይ ግድብ ላይ የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች በውጭ አገር አሰሪዎችና ተባባሪ በሆኑት ኢትዮጵያውያን ተቆጣጣሪዎች በሚፈጸም በደል ስራቸውን እየለቀቁ መሆኑን በድርጅቱ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ገልጸዋል።
በመጀመሪያዎቹ የግንባታ ወራት አገራዊ ስሜቱ ፈንቅሎት ወደ አካባቢው በመሄድ ከአንድ አመት ከስድስት ወራት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ወጣት ፣ ሰራተኛው በየጊዜው በሚደርስበት በደል በቀን ውስጥ ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ ሰራተኞች ይለቃሉ ብሎአል። እርሱም ስራውን ለመልቀቅ መገደዱን ገልጿል።
ሰራተኛው ከሚዘረዝራቸው በደሎች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቅሰው በሰራተኛውና በማኔጂመንቱ መካከል ያለውን የተበላሸ ግንኙነት ነው። ከውጭ ተቀጥረው የሚመጡት የጣሊያን ሰራተኞች ሳይቀር የኢትዮጵያ ሰራተኞች የሚሰሩትን ስራና አያያያዛቸውን እየተመለከቱ ነቀፌታዊ አስተያየቶችን ይሰጣሉ ብሎአል
ለሰራተኛው የተዘጋጀው ቤት የአካባቢውን ሙቀት ለመከላከል እንደማያስችል፣ የሚቀርበውም ምግብ በአካባቢው የሚታየውን በሽታ ለመከላከል የማያስችል መሆኑን ፣ የመብት ጥያቄዎችን መጠየቅ የሚያሳስር ጉዳይ መሆኑንም ሰራተኛው ገልጿል
በቅርብ ጊዜ ውስጥ መኖሪያ ቤቶች መሰራታቸውን የገለጸው ሰራተኛው፣ ይሁን እንጅ ሙቀቱን ለመቋቋም የሚያስችል ኤሲ ያልተገጠመላቸው በመሆኑ ችግሩ አሁንም እንዳለ ነው ብሎአል።
ሰራተኛው ልምድ ያላቸው ሰራተኞች በብዛት እየለቀቁ፣ አዳዲሶቹ ሰራተኞችም ሶስት ወር ሳይቆዩ ሁኔታውን ተረድተው እንደሚመለሱ ትዝብቱን አስፍሯል።
ሰራተኞች ከሁለት ሳምንት በፊት ያደረጉትን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ የመንግስት ባለስልጣናት ወደ አካባቢው ቢሄዱም ከማስፈራራት በስተቀር በቂ ምላሽ ሳይሰጡ ተመልሰዋል።
እስካሁን ድረስ ሰራተኛው በአገራዊ ፍቅር ሲሰራ እንደነበር ያስታወሰው ሰራተኛው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሰራተኛው በበሽታ ሲጠቃ፣ መሰላቸት ሲመጣ ስራውም በዚያው መጠን እየተጓተተ መምጣቱን አልሸሸገም።
መንግስት ሰሞኑን ለሪዩተርስ በሰጠው መግለጫ ስራው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃል ብሎአል። ምንም እንኳ እስካሁን ድረስ የተባለው የጊዜ ገድብ በግልጽ ባይቀመጠም ከ4 እስከ 7 አመታት ሊፈጅ እንደሚችል ነው የመንግስት ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ከሚሰጡት መግለጫ ለመረዳት ይቻላል።
No comments:
Post a Comment