Translate

Thursday, November 22, 2012

የህወሃት ምስለ-ወራሪነት ሚና በኢትዮጵያ /Quasi-occupiers and their War Trophy /


አዜብ መስፍን በቅርቡ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የሰጠችውን መግለጫ ተከትሎ በመገናኛ ብዙኃን ልክ እንደ አዲስ ከየአቅጣጫው ውግዘት ደርሶባታል።ምናልባትም ውግዘቱ ለ21 አመታት በህወሃት በኩል ሲሰራበት የኖረውንና ሊሰራ የታቀደውን እሷ በቃላት በመግለጿ ይሆን እንደሆነ እንጂ በተግባር የሚታየው የህወሃት ምስለ-ወራሪነት ሚና ያው በነበረው አካሄድ መጠኑን እያሰፋ ከመሄድ በዘለለ የተለየ እንግዳ የሆነ ነገር አልታየበትም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እስኪ የህወሃትን ምስለ-ወራሪነት፣የህወሃትንና የኢትዮጵያን የግንኙነት መስመር እንዲሁም ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዮች ቀጥለን እንመልከት።
ከማኒፌስቶ-68 ወደ ምስለ-ወራሪነት የተደረገ ሽግግር
ከህወሃት መስራች አንዱ የሆኑት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991) በተሰኘ መጽሐፋቸው በመለስ ዜናዊ፣ስብሀት ነጋና አባይ ፀሐዬ አማካኝነት እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1968 ዓ.ም. ´´ማኒፌስቶ-68´´ የተሰኘ ሰነድ ተዘጋጅቶ እንደነበር ይገልፃሉ።
በርግጥ የዚህ ማኒፌስቶ ማጠንጠኛው ሉአላዊት ትግራይን /Sovereign State of Tigray Republic / መመስረት የነበረ ሲሆን በሂደት አዋጭነቱ ሲሰላ የማያዛልቅ በመሆኑ ህወሃት አዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት ከሪፐብሊክ ምስረታ ይልቅ ወደ ምስለ-ወራሪነት ሽግግር አድርጓል።ይህ ማለት ግን አንዳንድ ሀሳቦች ከማኒፌስቶው ላይ ተግባራዊ አልተደረጉም ማለት አይደለም።ለምሳሌ የትግራይን የግዛት ወሰን በሚመለከት ማኒፌስቶው ላይ ከተገለፀው ጋር በሚቀራረብ መልኩ ለቅባት እህል ምርት ምቹ የሆኑ መሬቶችን ከአማራ ክልል በመውሰድ የትግራይ ክልል አካል እንዲሆን ተደርጓል።
የምስለ-ወራሪነት አስተሳሰብም ሉአላዊት የትግራይ ሪፐብሊክ ምስረታን በመተው በሉአላዊት ኢትዮጵያ ውስጥ በፖለቲካ፣በኢኮኖሚና በወታደራዊ መስኮች የህወሃትን የበላይነት ብቻ ሳይሆን አይነኬነትም የተረጋገጠበት፣እንዲሁም የትግራይን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማእከልነት ለማሳካት በግልጽም ይሁን በህቡዕ መንቀሳቀስን ያካትታል።
በመሰረቱ ከታሪክ እንደምንረዳው የሁለተኛው የአለም ጦርነት ሲገባደድ የተባበሩት ኃይሎች /The Allied Power/ ማለትም ዩ.ኤስ. አሜሪካ፣ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ በምዕራብ በኩል የሶቪየት ዩኒየን ጦር ደግሞ በምስራቅ በኩል ጀርመንን ሙሉ በሙሉ ወረው የነበረ ሲሆን እንደማንኛውም ወራሪ ሃይል ሁሉ ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል ለጦርነት ካሳ /Reparation/ እና በጦርነቱ ላገኙት ድል /War Trophy/ እንዲሆን የጀርመን ኢንደስትሪዎችን በመነቃቀል በተለይ ወደምስራቅ አውሮፓ ሀገራት እንዲጫን አድርገዋል።በርግጥ ይህ እጅግ ሰፊና ብዙ ምክንያቶች የነበሩት ጉዳይ ሲሆን የወራሪ ሀይሎች መገለጫ ባህርይ አንዱ ከተወራሪ ሀገርና ህዝብ ላይ የሚደረግ የንብረት ዘረፋና የማሸሽ ተግባር ነው።በተመሣሣይ ህወሃትም የምስለ-ወራሪነት ተግባሩን የጀመረው አዲስ አበባን በተቆጣጠረ ሰሞን ሲሆን በወቅቱም ከመላው ኢትዮጵያ በሚባል ደረጃ በርካታ የካፒታል መሣሪያዎችን /Capital Equipments/ ወደ ትግራይ ያሸሸ ሲሆን በኢትዮጵያ ላይ ያለውን የዘረፋና የምስለ-ወራሪነት ሚናም ለማስቀጠል የሚከተሉትን የማስመሰያ ታክቲኮችን /Camouflage/ በመፍጠርና ተግባራዊ በማድረግ እስከዛሬ መቀጠል ችሏል።
1. ተለጣፊ ድርጅቶችን ማዘጋጀት
ህወሃት ገና ወደ አዲስ አበባ ከመምጣቱ በፊት ኢህአዴግ የሚል የአራት ድርጅቶችን ጥምረት ሲመሰርት ´´–ዴን´´ እና ´´–ዴግ´´ የተሰኙ ድህረ-ቅጥያ /Suffix/ የተጨመረላቸው እነዚህ ድርጅቶች በራሳቸው ማሰብም ሆነ መመራት የማይችሉ ይልቁንም የህወሃት ትርጁማን በመሆን የህወሃትን ህቡዕ አጀንዳ ለመደበቅ ወያኔ እንደሽፋን የሚጠቀምባቸው እንዲሁም በነዚህ ክልሎች ውስጥ ተቀባይነት /Internal Legitimacy/ ለማግኘት ተብለው የተዘጋጁ ናቸው። ይህ ባይሆን ኖሮ ከአማራ ክልል ለግብርና ምቹ የሆኑ መሬቶች በኃይል ወደ ትግራይ ክልል ሲጠቃለል ብአዴን ዝም ባላለ ነበር።ከ800 ኪ.ሜ. ርዝመትና ከ30 ኪ.ሜ. በላይ ስፋት ያለው መሬት ከአማራ ክልል ህወሃት ለሱዳን ሲሰጥ ብአዴን ዝም ባላለ ነበር።በሌላ በኩል 42% የሚሆነውን የጋምቤላ መሬት ህወሃት ለእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች /Neo-Colonizers/ እዚህ ግባ በማይባል ዋጋ ሲሸጠውና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ሲፈናቀሉ የጋምቤላ ተለጣፊ ድርጅት ዝም ባላለ ነበር።በኦሮሚያና በደቡብም እንዲሁ በተመሳሳይ የክልሎቹ የተፈጥሮ ሀብት በህወሃትና በህወሃት የቀድሞ ወታደሮች በግፍ አሁንም ድረስ ሲዘረፍ ኦህዴድና ደህዴን ዝም ባላሉ ነበር።
2. የዘውጌ ፌደራሊዝምን ማስፈን /Implementation of Ethnic Federalism/
ህወሃት በኢትዮጵያ የዘውጌ ፌደራሊዝምን ሲያሰፍን እንደመከራከሪያ የሚያነሳው ነጥብ ይህ የዘውጌ ፌደራሊዝም በሀገሪቱ ´´ደም መፋሰስን የሚያስቆምና ሀገሪቱንም ከመበታተን የሚታደግ፤እንዲሁም ህዝቦች ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲያሳድጉ የሚረዳና ለሁሉም ብሄሮች የፖለቲካ ውክልናን የሚሰጥ ነው´´ የሚል ሲሆን በርግጥ በኢትዮጵያ ያለው የህወሃት የዘውጌ ፌደራሊዝም ባህርይ ከላይ የተዘረዘሩትን የሚያሟላ ሳይሆን ይልቁን በተቃራኒ አቅጣጫ የሚነጉድ ዝንፍ ተፈጥሮ /Asymetric nature / ያለው ሆኖ እናገኘዋለን።ለምሳሌም፦
ሀ. ምንም እንኳን የህወሃት ህገ-መንግስት ሁሉም የዘውጌ ቡድኖች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት እንዳላቸው ቢገልፅም በተግባር እየታየ ያለው ግን አምስት የዘውጌ ቡድኖች ብቻ የራሳቸው ክልል ሲኖራቸው ቀሪዎቹ በባለ ብዙ ዘውጌ ክልል /Multi-ethnic region/ እንዲጠቃለሉ አልያም በሌሎች አምስት ክልል ውስጥ አናሳ ቡድን /Minor group/ እንዲሆኑ ተደርጓል።
ለ. የሀገሪቱ የፖለቲካ ስልጣን ከጠቅላላው የሀገሪቱ ህዝብ 5% ውክልና ብቻ ካለው ከትግራይ ህዝብ በወጣው ህወሃት እጅ ይገኛል።
በእርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከ70 በላይ ብሄረሰቦች በሚኖርባት ሀገር የዘውጌ መስመርን /Ethnic line/ ብቻ ነጥሎ በማውጣት የፌደራል ሥርዓት ለመመስረት መሞከር ውጤቱን ዝንፍ ፌደራሊዝም ስለሚያደርገው በቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ መካከል በርካታ ችግሮችን የሚፈጥር ሲሆን ለአናሳው ምስለ-ወራሪ የህወሃት ቡድን ግን ለሚያደርገው ዘረፋ ሁኔታውን በሰፊው የሚያመቻች ይሆናል።
ይህም በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል ካስከተላቸው ችግሮች መካከል፦
ሀ. በባለ ብዙ ዘውጌ ክልሎች ውስጥ በየጊዜው የሚያገረሽ ግጭቶች መከሰት።በተለይ ውክልናን፣የተፈጥሮ ሀብት ክፍፍልን፣በማንነት ጥያቄ ላይ በሚነሱ ነጥቦች መሠረት ለዘመናት አብረው የኖሩ ህዝቦች እንዲቃቃሩና በጠላትነት እንዲፈራረጁ አድረጓቸዋል።
ለ. በምስለኔዎች /titular/ እና በተገፉ ቡድኖች /non-titular/ መካከል ከፍተኛ የሆነ መቃቃር እንዲፈጠር አድርጓል።ለምሣሌ በሀረሪ ክልል ምንም እንኳን የአማራ ተወላጆች ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም በሀረሪ ም/ቤት ውስጥ በቁጥር ለሚያንሱት ለሌሎች ውክልና ሲሰጥ ለነዚህ ውክልና የላቸውም፤በመሆኑም በክልሉ በአማሮችና በሀረሪዎች መካከል የሚስተዋል ውጥረት ሲኖር በሌላ በኩል የህወሃት ማዕከላዊ መንግስት ስልጤዎችን በማቅረብና ጉራጌዎችን በመግፋት ለዘመናት አብረው የኖሩትን ህዝቦች በጠላትነት እንዲተያዩ አድርጓቸዋል።
ሐ. በአጠቃላይ ይህ የፌደራል ሥርዓት ሀገራዊ ራዕይ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይፈጠሩ ይልቁንም በየአጥቢያቸው በዘውጌ ደረጃ የተመሰረቱ አቅመ-ቢስ ተቃዋሚዎች እንዲበራከቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርግ በዚህ ሁሉ ብቸኛው ተጠቃሚ ብረት የታጠቀው ምስለ-ወራሪ ኃይል /ህወሃት/ ሲሆን የብዙኃንን የመገዳደር አቅምም በዚህ መልኩ በማሽመድመድ ይህን ያህል መጓዝ ችሏል።
የህወሃትና የኢትዮጵያ የግንኙነት መስመር
ከስያሜው ጀምሮ ህወሃት ራሱን ኢትዮጵያዊ ለማድረግ የተቸገረ ቡድን ነው።በሌላ በኩል በሁለት ወገኖች መካከል የሚኖር ግንኙነት አንዱን ወገን ተጠቃሚ ሌላኛውን ተጎጂ የሚያደርግ ከሆነ ይህ ግንኙነት ጥገኛ /parasitic/ ይሆናል።በኢትዮጵያ እና በህወሃት መካከልም ያለው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ጥገኛ ሲሆን መገለጫዎቹንም ከዚህ ቀጥሎ እንመልከት።
´´ዕዳ የኢትዮጵያ፥ትርፍ የህወሃት´´ /Opportunity Maker, Opportunity Taker Approach/:- የዮም ኪፑር /Yom Kippur/ጦርነት በእስራኤልና በአረቦች መካከል ሲካሄድ የሪቻርድ ኒክሰን አስተዳደር ለእስራኤል ወገንተኝነቱን ከማሣየቱም በላይ የ2 ቢሊየን ዶላር እርዳታ ማድረጉን ተከትሎ ነዳጅ አምራች የአረብ ሃገራት በነዳጅ ዋጋና አቅርቦት ላይ ማዕቀብ በማድረጋቸው የአሜሪካ ኢኮኖሚ ለወራት የዘለቀ መናጋት ገጥሞት ነበር።እናም በወቅቱ የነበሩ ፖሊሲ አውጪዎች ከእንደዚህ አይነት ቀውስ በዘላቂነት ራሳቸውን ለመካላከል ያዘጋጁት መንገድ ሀገራትን የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ጥገኛ ማድረግ ሲሆን ይህንንም ተፈፃሚ የሚያደርጉ ´´ኢኮኖሚክ ሂት ማን´´ በመባል የሚታወቁ ሃይሎችን አሰማርተው በርካታ ሃገራትን ከማይወጡት ዕዳ ውስጥ እንዲዘፈቁ በማድረግ ያለምንም መገዳደር ለአበዳሪ ሃገራት ተንበርካኪ እና የሃብት ምንጭ እንዲሆኑ ማድረግ ችለዋል።
በተመሳሳይ የኢኮኖሚ አቅሟ እየፈረጠመ የመጣው ቻይና ኤክሲም ባንክ /Export-Import Bank of China/ በሚባለው የፋይናንስ ተቋሟ በኩል የብዙ አፍሪካ ሃገራትን ጓዳ ባዶ ያስቀረች ሲሆን ወደ እኛ ሃገር ስናመጣው የህወሃትና የቻይና ግንኙነት የጋራ ጥቅምን መሠረት ያደረገ /Mutualism/ ግንኙነት ሲሆን በዚህ መካከል ተጎጂው ቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ይሆናል።ለምሳሌ የደ/ማርቆስ-መርዓዊ መንገድ ስራ ፕሮጀክትን እንውሰድ።የ300 ኪ.ሜ. መንገድ ለመስራት የኤክሲም ባንክ ለኢትዮጵያ ያበድራል /ብድሩ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ይመዘገባል/።ኮንትራቱን የቻይና ካምፓኒ ሲይዘው የተወሰነውን ሥራ ለሱር ኮንስትራክሽን በንዑስ ኮንትራት እንዲሰጠው ተደረገ /የስምምነቱ አንድ አካል በመሆኑ/ የአስፋልት ስራውም እንደነገሩ ተጠናቀቀ። የሂደቱም ዑደት ይህን ይመስል ነበር፦የቻይናው ኤክሲም ባንክ ለኢትዮጵያ አበደረ፣የቻይናው ዋምቦ ኮንስትራክሽን የአንበሳውን ድርሻ ወሰደ፣የህወሃቱ ሱር ኮንስትራክሽን የድርሻውን ወሰደ፣የኢትዮጵያ ህዝብም እንደነገሩ የተሰራ አስፋልትና ወለዱ የትየለሌ የሆነ ዕዳ ታቀፈ።
በሌላ በኩል የአባይ ግድብን እንመልከት።ለግንባታው ከሚያስፈልገው የግንባታ ብረት /Structural Steel/ ውስጥ 90%ቱን ያለጨረታ እንዲያቀርብ የተሰጠው ለህወሃቱ መከላከያ ኢንጂነሪንግ ሲሆን የሲሚንቶ አቅርቦቱን በዋናነት መሰቦ ሲሚንቶ ይሸፍናል።
ለማሳያ ያህል እንዲሁ ጠቀስኩት እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ´´ተገነቡ´´ በተባሉትና በሚባሉት ነገሮች ውስጥ ሃገሪቱ ለትውልድ በሚተላለፍ ዕዳ ውስጥ ስትዘፈቅ የህወሃት ካምፓኒዎች አቅም ግን በተቃራኒው መጠናከርና ማየል ችለዋል።ይህም በግልፅ የሚያሳየን በኢትዮጵያ ህዝብ ኪሳራ ምን ያህል ህወሃት እየበለፀገ እንደሆነ ሲሆን ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነትም ጥገኛ ለመሆኑ አይነተኛ ማሳያ ነው።
የማይከፈል ብድር /Default Debt/:-የኢትዮጵያ ልማት ባንክ መንግስታትን እየተሻገረ ዛሬ ላይ የደረሰ የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት ሲሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ ይህ ባንክ ችግር ውስጥ የገባበት ጊዜ ቢኖር በህወሃት የአገዛዝ ዘመን ነው።ለዚህም ምክንያቱ የህወሃት ድርጅቶች ያለምንም ማስያዣ /Collateral/ ከ5.1 ቢሊየን ብር በላይ በብድር መውሰዳቸው ሲሆን ያለባቸውንም ዕዳ ለመክፈል ምንም አይነት እንቅስቃሴ አያደርጉም።ዳሩ ´´አንበሳ ምን ይበላል ተበድሮ፥ምን ይከፍላል ማን ተናግሮ´´ አይደል የሚባለው።በመሣሪያ ኃይል ከሚገዛ ምስለ-ወራሪ ኃይል ይህ አይነት ዘረፋ የሚጠበቅ ነው።ለምልከታ ያህል በ2009 ዓ.ም. የተፈፀመውን እንመልከት።
እ.ኤ.አ. በ2009 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በበጀት አመቱ ለብድር ያዘጋጀው የገንዘብ መጠን 2.4 ቢሊየን ብር ነበር።ነገር ግን ለመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ማስፋፊያ በሚል 1.7 ቢሊየን ብሩን የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ሲወስደው ይህም ከጠቅላላው ገንዘብ ውስጥ 70% ያህሉን አንዱ የህወሃት ድርጅት እንዲወስደው ተደርጓል።ከቀሪው 700 ሚሊየን ብር ላይም ሌሎች የህወሃት ድርጅቶች በየፊናቸው የወሰዱ ሲሆን ከዚህ ሁሉ የተረፈችውን ቅንጥብጣቢ ነው እንግዲህ ለቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ የተተወለት።´´ለመሆኑ ይሄ ሃገር የማነው?´´ ነበር ያለው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ።
የግዳጅ ግዢ /Forced Market/:-ማንኛውም በንግድ አለም ያለ ድርጅት ቀዳሚ አጀንዳው ላመረተው ምርት አልያም ለሚሰጠው አገልግሎት ገበያ ማግኘትን ነው።የህወሃት ድርጅቶችም በዚህ በኩል ችግር እንዳይገጥማቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ንብረት የሆኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶች እጃቸው ተጠምዝዞ ለህወሃት ካምፓኒዎች የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ተደርጓል።
ለምሳሌ በሀገሪቱ በየዓመቱ የሚታተሙ የመማሪያ መፃህፍት በትምህርት ሚንስቴር ስር በሚገኝ ´´የመፃህፍት ማተሚያና ማከፋፈያ ድርጅት´´ አማካኝነት በርካሽ እየታተመ በየክልሎች ይከፋፈል የነበረ ሲሆን አሁን ግን ሙሉ በሙሉ ያለምንም ጨረታ ይህ ሥራ ለሜጋ ማተሚያ ድርጅት በችሮታ ሲሰጠው ሜጋም በየአመቱ ከትምህርት ሚንስቴር ቋሚ ገቢ እንዲያገኝ አስችሎታል።ከዚህም ባሻገር በቂ ጥናት ሳይደረግ የሚዘጋጁ የመማሪያ መፃህፍት እንዲታተሙ ከተደረገ በኋላ ያለ አገልግሎት እንዲቃጠሉ የተደረጉበት አጋጣሚ በተደጋጋሚ ሲስተዋል በዚህ ሁሉ ብቸኛው ተጠቃሚ የህወሃቱ ሜጋ ማተሚያ ነበር።ለምሳሌ በአባይ ፀሐዬ መሪ ተዋናይነት በደቡብ ክልል ለሚገኙ አራት ብሄሮች ከሁሉም የተውጣጣ የመማሪያ ቋንቋ እንፈጥራለን ብለው ለህትመት ብቻ ከ15ሚሊየን ብር በላይ ለሜጋ ተከፍሎ ከታተመ በኋላ ወደ ተግባር ለመቀየር ባለመቻሉ ፕሮግራሙ ሲሰረዝ ሜጋንም ይበልጥ ሀብታም አድርጎት አልፏል።
በሌላ በኩል ´´የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት´´ በመባል የሚታወቀው የህወሃት የጦር ክንፍ፣የፌደራል ፖሊስ እንዲሁም የአዲስ አበባም ሆነ የክልል ፖሊሶች ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ህዝብ ንብረትና በጀት የሚንቀሳቀሱ ቢሆንም በየዓመቱ የሚለብሱት የሚሊተሪ ፋቲግ ያለምንም ጨረታ ከህወሃቱ አልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በቀጥታ የሚገዛ ሲሆን ለወትሮው የምናውቀውና ንብረትነቱ የመንግስት የሆነው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ዛሬ ህልውናው ራሱ አጠራጣሪ እንዲሆን ተደርጎ የክልልም ሆኑ የማዕከላዊው መንግስት የሬድዮና የቴሌቪዥን ተቋማት ከቁርጥራጭ ዜናዎች እስከ ዘጋቢ ፊልሞች ከህወሃቱ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዲገዙ ይገደዳሉ።
ለምሳሌ ያህል እንዲሁ ነካካናቸው እንጂ በአጠቃላይ የህወሃት ድርጅቶች የገበያ እጦት እንዳይፈጠርባቸው ወይ እንዲሁ በችሮታ የሚሰጣቸው አልያም ግልፅነት በጎደለው ´´ጨረታ´´ አሸነፋችሁ እየተባሉ የሚቸራቸው ናቸው።
ማጠቃለያ
እንግዲህ ህወሃት ራሱን ዴሞክራሲያዊ ኃይል አድርጎ በቃል ከነገረን ይልቅ በተግባር የፈፀመውንና እየፈፀመ ያለውን ስንፈትሽ በርግጥም የኢትዮጵያ ህዝብን ንብረትና ገንዘብ በመዝረፍና የራሱን ድርጅቶች በማቋቋም ምርትና አገልግሎቱን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እየተገደድን እንድንገዛ ተደርገናል።አሁን ያለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም የሚመጡ ትውልዶች እንኳን በቀላሉ ሊወጡት ከማይችሉት ዕዳ ውስጥ ሀገሪቱን በመክተት ብሎም በሀገሪቱና ዜጎቿ ኪሳራ ዛሬ ህወሃት ከ50 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያላቸው ተቋማት ባለቤት ሆኗል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ለህወሃት የሃብት ምንጭ የሆነበትን የብዝበዛ ሥርዓት እንዲሁም በብረት ኃይል በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የተጫነውን የህወሃት የምስለ-ወራሪነት ሚናን ማጋለጥ፣መቃወም እንዲሁም ይህን ሥርዓት ለማስወገድ በሚደረግ ትግል ውስጥ በንቃት መሳተፍ የዜግነትና የሞራል ግዴታ ይመስለኛል።
Dawit Fanta (ዳዊት ፋንታ)

No comments:

Post a Comment