ኢሳት ዜና:-ህዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ (ህወሀት) ከ 160 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በመመደብ በትግራይ ክልል በሚገኙ ወረዳዎች በሙሉ ሰሞኑን ያደረገው የድጋፍ ማሰባሰቢያ ህዝባዊ ስብሰባ የታሰበውን ውጤት ሊያስገኝ አልቻለም ተባለ።
በስፍራው የሚገኘው የ ኢሳት ወኪል እንዳደረሰን መረጃ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሞት በሁዋላ አብዛኛው ህዝብ አሁን በቀሩት ባለስልጣናት በራስ መተማመን እያጣ መምጣቱን ያመለክታል።
ከህብረተሰቡ እየተሰሙ ባሉ ጠንካራ ጥያቄዎች ግራ እየተጋቡ የመጡ አንዳንድ የህወሀት አባላት ራሳቸውን ከድርጅቱ አባልበነት እስከማግለል መድረሳቸውንና ጥቂት የማይባሉ የደህንነት ሠራተኞች መክዳታቸውንም መረጃው ይጠቁማል።
በክልሉ የህወሀት ባለስልጣናትና ጥቂት ዘመዶቻቸው በምቾት ቢኖሩም፤ አብዛኛው የትግራይ ህዝብ ግን ከ21 ዓመት የህወሀት አገዛዝ በሁዋላ የተጣራ ንፁህ የመጠጥ ውሀ እንኳ ማግኘት አልቻለም።
የክልሉ ቁንጮ ባለስልጣናት መቀሌ ውስጥ ከህብረተሰቡ መኖሪያ ራቅ ባለ ከፍታማ ቦታ በከፍተኛ ወጪ ለራሳቸው መኖሪያ የሚሆኑ ዘመናዊ ቪላዎችን እየገነቡ እንደሚገኙና አብዛኛው ህዝብ ወደዚያ እንደማይደርስ ፤ ይህ የባለስልጣናቱ መኖሪያ አካባቢም በከተማው ነዋሪ ዘንድ <አፓርታይድ መንደር> ተብሎ እንደሚጠራ በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከህወሀት የተቀነሱት ነባር ታጋዮች ብዙዎች በልመና መሰማራታቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
ከመቀሌ ለኢሳት የተላከው መረጃ እንዳመለከተው በ17 አመታቱ የትጥቅ ትግል የታገሉ እና በጉዳት ወይም በሌሎች ምክንያቶች ከድርጅቱ የተባረሩ ታጋዮች በከፍተኛ ድህነት ውስጥ በመግባታቸው ብዙዎች ወደ ልመና ተሰማርተዋል።
ህወሀት ከ120 ሺ በላይ በጦርነቱ ወቅት አካል ጉዳተኞች የሆኑትን መልሶ ለማቋቋም ከኢፈርት ገንዘብ በማውጣት እንደረዳ ይፋ ቢያደርግም፣ በትክክል ተጠቃሚ የሆኑት ግን እጅግ አነስተኛ መሆናቸውን መረጃው ያሳያል።
በአንጻሩ የህወሀት መሪዎች አብዛኞቹ ልጆቻቸውን በውጭ አገራት ልከው ከማስተማር ባሻገር ፣ በመንግስት ወጪ የውጭ ህክምና ከማግኘት ባሻገር በስማቸው ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን ሰርተው ያከራያሉ ይላል መረጃው።
እነዚሁ ነባር የህወሀት የአመራር የነበሩ ግለሰቦች በላኩት መረጃ የህወሀት ንብረት የሆነው ኢፈርት ትርፉን ሳይጨምር ቋሚ ሀብቱ ብቻ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን ጠቅሰዋል። ድርጅቱ በእየአመቱ የሚያጋብሰው ትርፍ ሲደመር የአጠቃላይ ሀብት መጠኑ በተመሳሳይ መንገድ ሊጨምር እንደሚችል ጠቅሰዋል። የህወሀት አጠቃላይ የሀብት መጠን የኢትዮጵያ መንግስት በእየአመቱ ለ90 ሚሊዮን ህዝብ ከሚመድበው አመታዊ በጀት ጋር እየተስተካከለ መምጣቱን ለማወቅ ተችሎአል።
ቋሚ ካፒታላቸው ከሚታወቁት ድርጅቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል። መሰቦ ስሚንቶ ቁጥር 1፣ 3 ቢሊዮን 500 ሺ ፣ መሶቦ ሲሚንቶ ቁጥር 2 ፣ 4 ቢሊየን 400 ሚሊዮን፣ ሱር ኮንስትራክሽን 4 ቢሊዮን 200 ሚሊዮን፣ ትራንስ ኢትዮጵያ 3 ቢሊዮን፣ መስፍን ኢንጂነሪንግ መቀሌ 2 ቢሊዮን 500 ሚሊዮን፣ መስፍን ኢንጂነሪንግ ቃሊቲና ዱከም 2 ቢሊ ን 600 ሚሊዮን፣ ጉና ኮርፖሬሽን 5 ቢሊዮን 400 ሚሊዮን ፣ ሜጋ አሳታሚ 1 ቢሊየን 200 ሚሊየን፣ ውቅሮ ሳባ ቆዳ ፋብሪካ 600 ሚሊዮን፣ አዲግራት መድሀኒት 700 ሚሊ ን፣ ኢዛና ወርቅ 910 ሚሊዮን፣ ብሩህ ተስፋ ላስቲክ 480 ሚሊዮን፣ ማይጨው ጂፑድ ፋብሪካ 746 ሚሊዮን፣ ሂወት እርሻ መካናይዜሽን 820 ሚሊዮን፣ ተከዞ ጥልቅ ጉድጓድ ፋብሪካ 467 ሚሊዮን፣ አድዋ እምነበረድ፣ 790 ሚሊዮን ፣ አድዋ ጋርሜንት ጨርቅ ስፌት 315 ሚሊዮን ፣ አድዋ ጨርቃጨርቅ ቁጥር 1 ፣ 1ቢሊዮን 700 ሚሊዮን፣ አድዋ ጨርቃጨርቅ ቁጥር 2 1 ቢሊዮን 700 ሚሊዮን፣ መስፍን ኢንጂነሪንግ የትናንሽ መኪና መገጣጠሚያ 350 ሚሊዮን ፣ ስታር መድሀኒት አስመጪና አከፋፋኢ፣ 150 ሚሊዮን፣ ደደቢት በድርና ቁጠባ፣ 6 ቢሊየን 250 ሚሊየን፣ ፔርሊ የተሽከርካሬ ጎማ አከፋፋይ ፣ 560 ሚሊየን ፣ ጥጥ ማዳመጫ ሁመራ ዳንሻ፣ 200 ሚሊዮን ብር ናቸው። ካፒታላቸው በውል ከማይታወቁት መካከል ደግሞ ኤክስፐረስ ትራንዚት፣ ድምጸ ወያኔ ትግራይ ፣ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል፣ ሬዲዮ ፋና፣ ወጋገን ባንክ፣ አፍሪካ ኢንሹራንስ፣ በለንደን ዱባይ ፣ አሜሪካና ሳውዲ አረብያ ያሉ ቤቶች ፣ በተክሊ ወይኒ አሰፋ የሚመራው የትግራይ ልማት ማህበር፣ የትግራይ አካል ጉዳተኞች ማህበር፣ በተክለወይን አሰፋ የሚመራው ህወሀት የነበሩ ታጋዮች መረደጃ ማህበር፣ አበርገሌ የፍየል ና በግ ማድለቢያ፣ የቻይና እና ኢፈርት ወርቅ ቁፋሮ በሸሬ መደባይ ታብር፣ የኢፈርት ወርቅ ቁፋሮ በሽሬ ጽንብላ መይሊ የሚሉት ይገኙበታል።
በሌላ ዜና ደግሞ በሀውዜን ወረዳ በደጋምባ ቀበሌ ፣ የቀበሌው አባዎራዎች መታሰራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።
በቀበሌዋ ውስጥ የሚኖሩ ከ100 በላይ አባዎራዎች የታሰሩት ማዳበሪያ አንገዛም በማለታቸው ነው። አርሶ አደሮቹ ማዳበሪያ አንገዛም ያሉበት ዋና ምክንያት ወቅቱ የአዝመራ ጊዜ አይደለም የሚል ነው። አንድ አርሶ አደር ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የቀበሌዋ አባዎራዎች በእስር ላይ በመሆናቸው አዝመራቸውን ለመሰብሰብ አልቻሉም።
No comments:
Post a Comment