Translate

Sunday, November 18, 2012

እኛም ሁላችንም “አበበ በቀለ” ነን!


አበበ በቀለ

ኅዳር 7 ቀን፣ 2005 (November 16, 2012)
ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ሦስት ነገሮችን በጥልቀት ብዙ ሳሰላስል ነበር። በመጀመሪያ የከነከነኝ ነገር አንዲት አቢጌል የምትባል የአራት ዓመት ሕፃን ስለ “ብሮንኮ ባማ እና ሚት ራምኒ” በሬዲዮ መስማት እንደሰለቻት ለእናቷ ስቅስቅ ብላ እያለቀሰች ስትናገር ማየቴ ነው።የዚህች ሕፃን ቪድዮ በዩቱብ ከ 15 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያየው ሲሆን፣ ከሬዲዮ ጣቢያውም ይቅርታ ተጠይቃለች፣ አንጋፋው የታይም ሜጋዚን (Time Magazine) ደግሞ “እኛም ሁላችንም አቢጌል ነን! We are all Abigael” በሚል “መፈክር” የአሜሪካ ፕሬዜዳንት ምርጫ ውድድር ሕዝቡን እንዳሰለቸው አትቷል። ባራክ ኦባማ እንዳለፈው የአራት ዓመት ምርጫ ሕዝብን ባለመሳባቸው፣ ራምኒ ደግሞ ለመመረጥ ሲሉ ያንንም ይሄንንም በመቀባጀር በመዋሸታቸው፣ የምርጫ ውድድሩ አሉታዊ ነበር። ቀልብ የሚስብም ሀሳብ ስላልመነጨ እውነትም ጭቅጭቅ ይመስል ነበር። ግን ኢትዮ አሜርካዊ ስለሆንኩና ኦባማን ስለመረጥኩ እንደገና በመመረጣቸው ተገላገልን፣ እፎይ ብያለሁ።

ምርጫ እንደአቢጌል ሰልችቶኝ ነበር፣ አሁን ግን ይናፍቀኝ ጀምሯል። የምርጫ ናፍቆቴ አሜሪካ ሳይሆን ኢትዮጵያ ነው። የናፈቀኝ ከሀርማን ኬይን 999 የቀልድ ፕላን እስከ የራምኒThe Obama-Romney rematchሽንፈቴን ተቀብያለሁ ብለው ሲናገሩ ማየት ነው። ያገሬ ሰዎች ቀልዳቸው ብዙ፣ በሀርማን ኬይን፣ “ሪፐብሊካንነትና ኢሕአዴግነት በጥቁርና በአማራ አያምር” ሲሉና፣ ራምኒ ደግሞ ሽንፈታቸውን ለመቀበል ጊዜ ስለወሰደባቸው “ራምኒ የአዜብ መስፍን በሽታ ተጋባበት እንዴ?” እያሉ ያፌዙ ነበር። ቀልዱ ይቅርና መብታችሁን ተጠቀሙ ተብሎ መጨቅጨቅ ለሀገራችን ኢትዮጵያ አትመኙላትም? የእኔ ዋና ምኞት ይህ ስለሆነ ሕፃን አቢጌል ትዝ እያለችኝ የደላት ብዬ ዘወትር እቀናባታለሁ። ወገኖቼ ቅናት ለማንም አይበጅ፣ መፍትሔ እንፈልግ።
ሁለተኛው ሳብላላ የከረምኩት ነገር ስለሬዲዮ ነው። ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ አካባቢ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን “የአዲስ ድምፅ” ሬዲዮ ድምፅን ለማጥፋትና የዳያስፖራውን ሕብረተሰብ ለማስፈራራት፣ ኢሕአዴግና የጥቅም አደር ሎሌዎቹ ትልቅ ጥረት አድርገው ነበር። በእዚህ ጉዳይ ላይ ታዋቂው ተንታኝና ፀሐፊ ክፍሉ ታደሰ ከበቂ በላይ ስላስረዱት አልደግመውም። አበበ በለውም ቤት ቢኖረኝ፣ በአሜሪካዊ ባለቤቴና ልጆቼ ኢሕአዴግን አልከስምን? ሲል አስረድቶናል። ሕግ ያለበት አገር መኖር ጥሩ፣ በአሜሪካ ህግ መሠረት የአሜሪካዊ ንብረት በሌላ አገር ከተወረሰ፣ ለእዚያ አገር ከሚሰጠውው እርዳታ ተቆርጦ ለዜጋው ክፍያ ይሰጣል። ያም ሆነ ይህ፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ህዝቡ ለአዲስ ድምፅ ሬዲዮ የድጋፍ ምሽት አድርጓል። የኢሕአዴግ ጥረትም እንዳልተሳካ ገብቶኛል።
ብንያም የሚባል ካናዳ ነዋሪ የነበረ ሰው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ “የምርመራ ሪፖርት” በድረገፁ ላይ አውጥቶ ነበር። “የምርመራ ሪፖርት” ከሁለት ወገን መረጃ ማቅረብ ይጠይቃል። ምዕራብ አገር ተማርኩ የሚል ሰው፣ ሸፈፍ ሸፈፍ እያለ፣ የፍትህ እልባውን ሚኒስቴር ስለ ወንጀል ሲጠይቅ፣ ሰው ቤት ገብቶ ሲፎልል፣ የውል ሰነድ በድረገፁ ሲለጥፍ ሳይ፣ አንድ ሰው እንዴት ህሊናውን እንደዚህ ይሸጣል ብዬ ተገረምኩ። ሌኒን እንዳለውና (ለማለቱ መረጃ የለም) እነ በረከት ስሞዖን እንደሚያውቁት እነዚህ ዓይነት ሰዎች የኢሕአዴግ “ጠቃሚ ደደቦች – Useful Idiots” ናቸው። ሙከራው ዳያስፖራውን ለማስፈራራት ነው፣ ተቃዋሚዎችም አጉል ተመፃዳቂዎች (Hypocrite) አድርጎ ለማቅረብ ነው። ያሳየን ግን ግልፅ የፍትህ አልባነትን ነው።
እኔ እንዳየሁት ፍርሐት ዳያስፖራውን ራሱን በራሱ እንዲያስር አድርጎታል። ተመፃዳቂ እንዳልሆን እያለም ራሱን ይገድባል። ለምሳሌ ሁለት የራሴን ቤተሰብ ጉዳዮዎች ላቅርብ። ስለራሴ ለመናገር እኔ በተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ውስጥ ያንዱ አባል ነኝ። ከኢትዮጵያ መጥቶ የሚሸጥ እንጀራ አልገዛም ከሚሉት ሰዎች መኃልም አንዱ ነኝ። ባለቤቴ ግን ለጤና ጥሩ ነው፣ማዕቀብ ምንም ለውጥም አያመጣም ብላ ከእኔ ጋር አትስማማም። ታዲያ እንጀራ መግዛት የኔ ተራ ሲሆን ለቤተሰብ ሰላም ስል ከኢትዮጵያ የመጣ እንጀራ እገዛለሁ። ስለዚህ ከሀበሻ ሱቅ ስወጣ ለሚያየኝ ሰው አጉል ተመፃዳቂ ሊያስመስለኝ ይችላል። ነገር ግን ከቤተስቦቼና ጓደኞቼ ጋር የኢትዮጵያ እንጀራ አለመግዛት ማዕቀብን ሁለት ዓይነት እንጀራ ማዕድ ላይ በማቅረብ በጉዳዩ እንከራከርበታለን። ይህን ክርክር እናቴ አዎ ለኢትዮጵያ ድሀ ኑሮ እያስወደዳችሁ ነው ብላ ትደግፈኛለች። አንድ ቀን ሁሉም ዳያስፖራ እንደሷ በማዕቀቡ እንደሚስማማ እገምታለሁ። እስከዚያው ድረስ አላማዬን ለማስረዳት፣ ሀሳብ ለማስቀየር መድረክ ይከፍትልኛል።
ሌላው አጉል ተመፃዳቂ ሊያስብለኝ የሚችለው አበበ በለው ተወረሰበት እንደተባለው ኢትዮጵያ ከእህቶቼና ወንድሞቼ ጋር ያሰራንው ትንሽ ህንፃ ነው። የእናቴ የንግድ ቦታ አዲስ አበባ አማካይ የንግድ ቦታ ላይ ስለሆነ ለሌላ ሳይሰጥብን እንስራበት ተብሎ፣ በርካታ መሆን ጥሩ፣ ተረባርበን፣ በእናቴ ሥም ሰርተንበት እያከራየች ትንሽ ገንዘብ አግኝታበታለች። አብዛኛውን ጊዜ አሜሪካ ስላምታጠፋ ያገኘችውንም ለዘመዶቿ ታከፋፍላለች። ስለዚህ ሀቅ እንናገር ከተባለ የኔ ቤተሰብ በኢሕአዴግ የኢኮኖሚ ማዕቅብ ማድረግ ላይ ሳይሆን ያለው፣ መደገፍ ነው የያዘው። እኔ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ገንዘብ እንዳናጠፋ የተቻለኝን ሞክሬያለሁ። አንድ ወንድሜ ደቡብ ሱዳን ንግድ ጀምሮ ስለነበር ከእሱ ጋር እንስራ የሚል ሃሳብ አምጥቼ ቤተሰቡን አበጣብጬ ነበር። በድምፅ ብልጫ ተሸንፌ፣ እናቴ ከሁሉም ልጆችዋ እኔን የመጀመሪያ ወንድ ልጅዋን ስለምትወድ በእሷ የድምፅ ማሻር መብቷ አሸንፌ ነገር ግን አሁንም ለቤተሰብ ሰላም ስል ተስማማሁ። ታዲያ ይህ አጉል ተመፃዳቂ ያስብለኛል፣ ግን እህቶቼና ወንድሞቼ አቋሜ፣ በሀሳብ ደረጃ ትክክል እንደሆነ ነግረውኛል። ኢሕአዴግ ልክ በአበበ በለው ላይ አደረኩት እንዳለው ቤታችንን በፈለገው ጊዜ በሚያወጣው ሕግ እንደሚደፍር ስለምናውቅና ያንን አጥብቀን ስለምንጠላ ሁሉም ቤተሰቦቼ የተቃዋሚ ኃይሎችን ይደግፋሉ። አሁን ፍርሀትና ንብረት ትንሽ አስሮናል። ግን የኔ ቤተሰብ ከሌሎች ቤተሰቦች ጋር ሲተባብር፣ ኢሕአዴግን ሊፈታትትን እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ።
ሶስተኛው አዕምሮዬን የነካው ነገር ባለፈው ሁለት ሳምንት ከአንድ ሃበሻ ጋር ቨርጂንያ ነዳጅ ስንቀዳ ተገናኝተን ያወራንው ነገር ነው። ኦባማ ባይደን የሚል ስቲከር መኪናዬ ላይ መለጥፌን አይቶ፣ ተጠንቅቅ መኪናህን እንዳይሰብሩብህ አለኝ። አይ ምንም አልሆንም አልኩት። በውስጤ የተሰማኝ ግን፤ ፍርሀትን ከአገራችን ተሸክመን አምጥተን፣ አሜሪካ ከ50 ዓመት በፊት የታገደው ጥላቻና፣ እስር ቤት የሚያስገባ ወንጀል በአሁኑ ጊዜ ለምን የሚጎዳን እንደሚመስለንና እንደምንፈራው ነው።
መፅሐፍ ቅዱስ ላይ መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 26 ቁጥር 1 እስከ 3 ላይ “እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኃኒቴ ነው፤ የሚስፈራኝ ማን ነው?” ይላል። በኢንጊልዘኛው “Fear No Evil” የሚለው ምዕራፍ 23 ላይ አለ። እኛም አምላክን የምናምን ኢትዮጵያውያን የኢሕአዴግ ፍርሃታችንን አውልቀን ስንጥል ግፍን እንደንምናሸንፍ እተማመናለሁ። በቅርቡ አንድ የግብፅ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ የሰጠውን ቃለምልልስ ሳዳምጥ በግብፅ የፀደይ አብዮት (Arab Spring) ዋናው ለውጥ “እያንዳንዱ ግለሰብ መንግስትን አለመፍራቱ ነው” ማለቱ በግሌ ፍርሐቴን አሸንፌ ድፍረትን መታጠቅ እንዳለብኝ ግልፅ አድርጎልኛል። ኢትዮጵያውያን ፍርሃታችንን አውልቀን ለመጣል ግን ግብፅ መሔድ የለብንም።
አርቲስት ታማኝ በየነ የተፈጥሮ ለዛ ባለፀጋ ነው። ሟቹን የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ “አበበ” የሚለው ሥም እንደማይስማማቸው በተለመደው ቀልዱ አቅርቧል። አበበ ገላው፣ አምባገነንታቸውን በአደባባይ አጋለጠ። የኢሕአዴግ አሽከሮች እንገልሀለን ብለው ሊያስፈራርሩት ሞከሩ። አበበ በለው፣ የኢሕአድግን ግፍ በየጊዜው በሬድዮ ያጋልጣል። የኢሕአዴግ አሽከሮች ቤት እንወርስብለን፣ ሌላም ችግር ውስጥ እንከትሀለን ብለው ሊያስፈራርሩት ሞከሩ። አገር ቤትማ ኢሕአዴግ በእስርና በግድያ ያስፈራራል። ያኔ በብርቱካን ሚደቅሳ፣ አሁን በእነ እስክንደር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ፣ በቀለ ደርባ፣ የደረሰባቸው ግፋዊ እስራት የኢሕአድግን አምባገነንት በአደባባይ ያጋልጣል። የእነ ሽብሬ ደሳለኝ፣ የኔሰው ገብሬና፣ የሌሎች ብዙኃንን መስዋዕትነት መርሳት የለብንም። ከበደላቸውና ያንን ለመታገል ካላቸው ድፍረት ብዙ እንማራለን።
በቅርቡ እስር ቤት የተወረወሩት በቀለ ደርባን ተመርኩዘው ሐሰን ሁሴን የተባሉ ፀሐፊ እኛም ሁላችንም “በቀለ ደርባ” ነን “We are all Bekele” ብለው ፅፈዋል። ግብፆች እንዳሉት እኛም ሁላችንም “ኻሊድ ሰይድ” ነን “We are all Khalid Said”። የደላቸው አሜሪካኖች እንዳሉት እኛም ሁላችንም “አቢጌል” ነን “We are all Abigael”። ወገኖቼ እኔም እናንተም አበበ እና በቀለ ነን! ነግበኔን እንርሳ። እኛም ሁላችንም አበበ፣ በቀለ ነን “We are all Abebe Bekele”።
ስለዚህ ለመብታችን ለክብራችን እንነሳ!!!  ታዲያ ለመብታችን ለክብራችን እንነሳ ሲባል እንዴት ተግባር ላይ ሊውል ይችላል የሚል ጥያቄ ይነሳል። ሶስት የሕዝባዊ ትግል እንቅስቃሴ መንገዶች ላሳይ፡
  1. በግላችንም ሆነ በጋራ ትግል የምንታገልበትን መንገድ እናስብበት። የሚመስለንን ተቃዋሚ ድርጀት ወይም የሲቪክ ተቋም እንቀላቀል። ለውጥ እንዲያመጡ እንደግፋቸው፣ እንሳተፍ፣ ምን ውጤት እንዳመጡ እንጠይቃቸው።
  2. በውጭ አገር ሊያስፈራሩን የሚሞክሩትን የኢሕአዴግ አሽከሮች እናጋልጥ። አንድ አሜሪካዊ ላይ ለውጭ መንግስት (ለኢሕአዴግ) መረጃ መስጠት ወንጀል መሆኑን አንርሳ። ንብረታችን ቢወረስብን፣ ከሰን ካሳ መቀበል እንደምንችል እንወቅ። አገር አትገቡም እንዳንባል ከሰጋን በኅቡዕ እንታገል። ፍርሃታችንን እናሸንፍ። መብታችን የሚጠበቅበትና በሰብዕናችን ብቻ የምንከበርበት ሥርዓት ለመመሥረት በፅናት በአንድነት እንታገል።
  3. የትብብር መድረኮችን እንፍጠር። የራሳችን “እኛም ሁላችንም ኻሊድ ሰይድ ነን” የሚል ፌስ ቡክ (Facebook) ገፅ ይኑረን። “እኛም ሁላችንም አበበ በቀለ ነን” የሚል ገፅ እናዘጋጅና እዚያ እንገናኝ። የሕዝባዊ ትግላችንን እናቀነባብርበት። የሕዝባዊ ትግላችንን እስኪ በእዚህም ግንባር እናካሂደው።
እኛም ሁላችንም አበበ በቀለ ነን ለመብታችን፣ ለክብራችን ተባበረን እንነሳ!!!

No comments:

Post a Comment