Translate

Wednesday, November 7, 2012

በቃሊቲ ግንቦት 7 እየተባሉ በሚጠሩ እስረኞች ላይ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑ ታወቀ


ኢሳት ዜና:-የኢሳት የቃሊቲ ምንጮቻችን  እንደገለጡት በተለምዶ የአማራ ተወላጅ የሆኑትንና ከፖለቲካ ጋር  በተያያዘ የታሰሩትን  በሙሉ  የማረሚያ ቤቱ ሀላፊዎች ግንቦት7 እያሉ እንደሚጠሩዋቸው ገልጸው፣ በእረኞች ላይ ኢሰብአዊ ድርጊቶች እየተፈጸመ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም  በእነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ መዝገብ በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተከሰው በእስር ላይ በሚገኙት ወታደራዊ መኮንኖች ላይ እጅግ ኢሰብዓዊ የሆነ አሰቃቂ ድብደባ ( ቶርች) የተፈጸመባቸው መሆኑን ኢሳት የቃሊቲ ምንጮችን በመጥቀስ ለህዝብ ይፋ አድርጎ ነበር።
ዘገባው አለማቀፍ ትኩረትን በመሳቡ፣ በቃሊቲ የነበረው ሁኔታ በአንጻራዊ መልኩ ተሻሻሎ እንደነበር የጠቀሱት ምንጮች፣  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በእነ አቶ አንዱአለም አራጌ መዝገብ በተከሰሱትና በሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች ላይ የሚደርሰው እንግልት እየጨመረ መምጣቱ ታውቋል።

በቃሊቲና ቂሊንጦ ማረማያ ቤቶች በሚገኙ እስረኞች ላይ ከሚተገበሩት የማሰቃያ መንገዶች መካከል ድብደባ አንዱ መሆኑ ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሽብር ወንጀል ተከሶ ፍረደኛ የሆኑት አቶ አንዱአለም አባተ ትናንት እኩለ ቀን ላይ ይግባኝ ሰሚ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
አቶ አንዱአለም በግላቸው ጠበቃ ለመቅጠር እንደማይችሉ በመግለጻቸው መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱም መንግስት ለእስረኛው ጠበቃ እንዲያቆምላቸው ትእዛዝ ሰጥቷል።  ይግባኙን ለማየትም ለህዳር 24 ፣ 2005 ዓም የጊዜ ቀጠሮ በመስጠት ችሎቱን አጠናቋል።

No comments:

Post a Comment