Translate
Friday, November 2, 2012
የሃይለማርያም ቃለመጠይቅ በሻዕቢያ የተዘጋጀ?
ከተስፋዬ ገብረአብ
ሰሞኑን ሃይለማርያም ደሳለኝ አንድ አስገራሚ ቃለመጠይቅ ሰጥቶ ነበር። አገር ውስጥ ለሚታተም መፅሄት በሰጠው በዚሁ ቃለመጠይቅ ላይ፣ “ዘላለማዊ ክብር ለመለስ ዜናዊ” በማለቱ ከቤተሰቡ የደረሰበትን ተቃውሞ ገልፆአል። በርግጥም ሃይለማርያም ልጆቹንና ባለቤቱን ሰብስቦ፣ “ተሳስቼያለሁ።” ብሎ ይቅርታ ጠይቆአል። ይህን እንግዲህ ከመፅሄቱ ላይ ያነበብነው ነው። የሃይለማርያም ሴት ልጅም አባቷን በዚህ መልኩ በማረሟ ታዋቂ ሆና ሰንብታለች። በርግጥም ዘላለማዊ ክብር ለአምላክ እንጂ ለሰው የሚሰጥ አልነበረም።
በዚሁ ቃለመጠይቅ ሃይለማርያም አንዳንድ አፈንጋጭ የሚመስሉ ቃላት አምልጠውታል። ያነበበው ወረቀት ከእሱ እውቅና ውጭ ተዘጋጅቶ መቅረቡን መግለፁ አነጋጋሪ ነበር። ከጀርባ ያሉትን ዘዋሪ ሾፌሮች የሚጠቁም ነበር። መለስን የሚቃወም ከሚመስሉ የሃይሌ የምላስ ወለምታዎች መካከል፣
“እኛ የአይን ቀለም አንመረምርም” ማለቱ የሚጠቀስ ነው።
መለስ የሚታወቀው የአይናችንን ቀለም በመመርመር ነበር። ሃይለማርያም ይህን የአይን ቀለም ምርመራ ካልተከተለ፣ አንድ ትልቅ ለውጥ ነው። የምላስ ወለምታም ከሆነ እናዋለን።” ብዬ በተስፋ በመጠበቅ ላይ ነበርኩ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ Ethiopia first እና Aiga forum የተባሉት የወያኔ ድረገፆች ባስነበቡት ዘገባ ዝነኛ ሆኖ የሰነበተው የሃይለማርያም ቃለመጠይቅ፣ “በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስም ተቀነባብሮ የተዘጋጀ እንጂ ሃይለማርያም የሰጡት ቃለመጠይቅ አይደለም” ሲሉ አውጀዋል። “ትልቁ ጀበና ተሰነጠቀ” ማለት ይሄኔ ነው። ወያኔ በጉዳዩ ላይ ያወጣው ዘገባ የሚከተለውን ይመስላል።
“…ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰጥተውታል የተባለው ቃለ ምልልስ ሙሉ በሙሉ ሀሰትና የፈጠራ ቃለመጠይቅ ተሰርቶ መሆኑ መታወቅ አለበት። ይሄንንም ሆን ብለው ያዘጋጁት ወገኖች ጠንቅቀው ያውቁታል። ይህ ዜና የተፈበረከው ኢትዮጵያን ከድቶና ዘርፎ በሄደ ለሻዕቢያ ተላላኪነት ባደረ ባሕርማዶ በሚገኝ ቅጥረኛ ነው። ይሄን ከማዶ (ከአስመራ ለማለት ነው) ተቀብሎ ወገን መስሎ አገር ውስጥ ላሉ ጋዜጦችና መጽሔቶች ያሰራጨው ደግሞ ሁሌም ከሴራና ተንኰል እጃቸው ጠርቶ የማያውቀው ወቅትና ሁኔታ በተቀየረ መጠን እንደ እስስት እየተለዋወጡ፣ እንደመርዘኛ እባብ አድብተው ለመናደፍ የሚከለፈለፉ አንዳንድ የግል ትልቅ ጋዜጣ ነን ብለው ራሳቸውን የከመሩ የግል ፕሬስ እንደሆኑ እናውቃለን። እነ ሰንደቅ እና ሌሎችም ይኼንን የጠላት ፕሮፖጋንዳ አራጋቢና አናፋሽ በመሆን በመሳሪያነት ያገለገሉትና የተሰለፉትም ከሀገር ውስጥ ሆነ ከውጭ በምስጢር የገንዘብ ክፍያ ተፈፅሞላቸው ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በበሉበት ቢጮኹ ምን ይገርማል?”
ስድቡን አራግፈን ይዘቱን ብቻ መዘን ስናወጣ በጣም አሳሳቢው ጉዳይ፣ “የሃይለማርያም ተብሎ ሲነበብ የሰነበተው ቃለመጠይቅ፣ በርግጥ የራሱ ነው ወይስ በሻእቢያ ተዘጋጅቶ የተበተነ?” የሚለው ጥያቄ ነው። ሃይለማርያም የእምነት ሰው በመሆኑ ይዋሻል ብዬ አልገምትም። “ቃለመጠይቁን አልሰጠሁም በል” ብለው ማስገደድም አይቻላቸውም።
ሃይለማርያም በርግጥ ቃለመጠይቁን አልሰጠም? ማነው ታዲያ ይህን ተንኮል የፈፀመው? ይሄ በግልፅ መታወቅ አለበት። ሃይለማርያም በርግጥ ቃለመጠይቁን ካልሰጠ ዘገባውን የሰሩ ሜዲያዎች ሁሉ ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው። ይቅርታ ለመጠየቅ ግን ሃይለማርያም፣ “ቃለመጠይቁ የኔ አይደለም። እኔ አላልኩም” ብሎ በአንደበቱ እንዲገልፅ እንጠብቃለን። አነጋገሪዎቹ አባባሎች የሚከተሉት ናቸው።
ጥያቄ :- ቃለ መሐላ በሚፈጽሙበት ጊዜ <ዘላለማዊ ክብር ለጠ /ሚኒስትራችን > ያሏት ቃል ብዙ ክርስቲያኖችን ያጠያየቀ ጉዳይ ሆናለች ይህችን ቃል ሆን በርግጥም አምነውባት ነው ያሏት ወይስ የተጻፈልዎትን ነው ያነበቧት ?
ጠ /ሚ ኃ /ማሪያም ደሳለኝ :- (ትንሽ ካሰቡ በኋላ ) ያንን ንግግር ያዘጋጁት ንግግር አዘጋጆች ናቸው :: ግን የንግግሩን ጽንሰ ሀሳብ መጀመሪያ እኔ ነኝ የሰጠኋቸው እነሱ ቋንቋውን አሳምረው ቀናንሰውና ጨማምረውበት አሰካክተው ኤዲት አርገው ከጨረሱ በኋላ እኔ ጋ ይደርሳል እኔ ሀሳቤን በትክክል ይገልጻል የሚለውን አንኳሩን ክፍል ብቻ አይቼ ያቺን ቃል ሳላስተውል አመለጠችኝና እናም ምንም አማራጭ የለኝም አልኳት :: ማታ ቤት ስመለስ ባለቤቴና ልጆቼ ሁሉ ገና ከበሩ ጀምሮ አተካራ ገጠሙኝ :: ልጆቼ በተለይ የ 16 ዐመቷ ልጄ ያለችው አባ በምድር አላፊ የሆነ ሥጋ ለባሽ ከኢየሱስ እኩል በላይ ክብር መውሰድ አይገባውም ብለህ ራስህ አስተምረሄን የለም ብላ ስትለኝ በእውነት መልስ አጣሁ :: ትንሽ ፈተና ገጥሞኝ ነበር እልሀለሁ ::
ጥያቄ :- እና ተጸጽተዋል ?
ጠ /ሚኒስትር ኃ /ማሪያም :- አዎን … በኋላማ አስቀምጫቸው የሆነውን ነገር ሁሉ አስረጅያቸው በጠረጴዛ ዙሪያ ሰላም ፈጠርን :: ግን አንድ ነገር ቤተሰቤም ሆነ መላ ክርስቲያን ወገኖቼ ይረዳሉ ብዬ ተስፋ የማደርገው ነገር እኔ የትናንቱ የትንሹ ኃ /ማሪያም ቤተሰብ አስተዳዳሪና አንድ ተራ የሐሪያዊት ቤተክርስቲያን አባልና አማኝ ብሆንም ያንን ማንነቴን ምንም የሚቀይር ነገር የለም :: ጌታ እስከፈቀደ አሁንም ወደ ፊትም ያን የትናንቱን አምላክ ማምለኬ እንደ ግለሰብነቴ ተጠብቆልኝ በአንጻሩ ደግሞ የ 80 ሚሊዮን ሕዝብ አደራና ኃላፊነት ስላለ የሁሉንም እምነትና ኃይማኖት የማክበር ግዴታ አለብኝ :: ሌሎቹም እንዲሁ የእኔን ኃይማኖት ለግሌ ነጻነቴን ትተውልኝ በመቻቻል ተያይዘን በወንድማማችነት በጋራ እንደምንኖር መገንዘብ አለባቸው :: ግን ማንም ኃይማኖቱን ሽፋን አርጎ ፖለቲካዊም ሆነ ኃይማኖታዊ አድቫንቴጅ ለመውሰድ የማንንም ሂሊና መጋፋት እንደለለበት አምናለሁ ::
ጥያቄ :- ባሁኑ ጊዜ በኢህአደግ አመራር ውስጥ የውጭ አገር ተወላጆች አሉ ስለሚባለውስ ?
ጠ /ሚኒስትር ኃ /ማሪያም :- አሁን አንተ ባለበቴን ይላሉ እንዳልከው ዐይነት አሉባልታ ነው ምንም መሰረት የለለው ተራ አሉባልታ ነው:: በኢሕአዴግ አመራር ውስጥ ያሉ ታጋዮች አገሬ ናት ለማይሉትና ለማያምኑበት ዓላማ መተኪያ የላላትን ሕይወታቸውን አሳልፈው አይሰጡም። ኢሕአዴግ ከትጥቅ ትግል ዘመን ጀምሮ አንድ ይዞ የመጣ ባህሉ ኮራፕት የሆነ አባሉን ካለምንም ምሕረት እያንጠባጠበ ያጭበረበረ ከተገኘ እያሽቀንጠረ እያጣራ ነው የመጣው :: ባንጻሩ ነባር አመራር ሆነ ዝቅ ያለ ደረጃ ያለ በመልካም ሥነ ምግባሩ ከመለካት ባሻገር ማንነቱ ከታወቀ ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ ሕይወቱን አሳልፎ እስከመስጠት በግንባር የተሰለፈውን ታጋይ በዜግነት ጥርጣሬ ውስጥ ገብቶ የማንንም የዐይን ቀለም የሚመረምርበት ምክንያት የለውም ::
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment