ለተከታታይ ሳምንታት ህትመቷ ተቋርጦ
የነበረችው ፍትህ ጋዜጣ ከመጪው አርብ ጀምሮ ለአንባብያን እንደምትቀርብ የጋዜጣዋ አዘጋጆች ለፍኖተ ነፃነት ዝግጅት ክፍል ገለፁ፡፡
ጋዜጣዋ በፍትህ ሚኒስቴር፤ የፌደራል ዓቃቢ ህግ መታገዷ የሚታወስ ሲሆን ከዛ በኋላ ያሉት የሁለት ሳምንት እትሞች ግን በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ባልታወቀ ምክንያት አላትምም በማለቱ ለአንባቢያን ሳትደርስ ቀርታለች፡፡
የፍትህ ጋዜጣ ቅፅ 5 ቁጥር 167 ሐምሌ 13 ቀን 2004 ዓ.ም እትም የታገደው ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል›› የሚል ዜና የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ም/ቤትን ጠቅሶ በመዘገቡ እንደሆነ የዓቃቤ ህግ ክስ ያመለክታል፡፡ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በወቅቱ የነበረው እትም እንዳይሰራጭና እንዲወረስ መወሰኑ ተጠቁሟል፡፡ የፍ/ቤቱ ውሳኔ ትዕዛዝም ሐምሌ 23 ቀን 2004 ዓ.ም ለብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፣ ለፌደራል ፖሊስ፣ ለዓቃቢ ህግና ለተከሳሹ ለፍትህ ጋዜጣ መድረሱ ታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ ከእግዱ በኋላ የፍትህ ጋዜጣ አዘጋጆች ለተከታታይ ሁለት ሳምንታት ለአንባቢያን እንድትደርስ ዝግጅታቸውን ቢያጠናቁቁም ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ‹‹አላትምም›› ብሏል፡፡ ሆኖም ከፍ/ቤት በተሰጠ ትዕዛዝ መሰረት የታገደው የሐምሌ 13 ቀን 2004 ዓ.ም እትም ብቻ መሆኑ በመገለፁ የፊታችን አርብ ለአንባቢያን እንደምትደርስ የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ በተለይ ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ፍ/ቤቱ የሐምሌ 13 እትም ሙሉ ዘገባዎች እንዲወረሱ መደረጉ አግባብ እንዳልሆነና ይወረሱ ቢባሉ እንኳ ለደህንነት ስጋት ናቸው የተባሉት ዘገባዎች ብቻ መሆን ሲኖርበት፣ የኪነ ጥበብ ዘገባዎች፣ በእውቀቱ ስዩም የለንደን ኦሎምፒክ ምልከታዎችና ሌሎም የገፅ ፅሁፎችና ዘገባዎች መልሰን እንዳንጠቀም መደረጉም ቅር አሰኝቶኛል ሲሉ ዋና አዘጋጁ ተናግረዋል፡፡
No comments:
Post a Comment