Translate
Sunday, August 5, 2012
ማጭበርበር – የመለስ ዜናዊ የአገዛዝ ብሄል መሠረት
የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በማጭበርበር ተወልዶ፤ በማጭበርበር አድጎ፤ እያጭበረበረ ወደ መቃብር በመንጎድ ላይ ይገኛል። የመለስ ዜናዊ አገዛዝ እና ማጭበርበር በጥብቅ የተሳሰሩ ናቸው። መለስ ዜናዊ በእርዳታ ስም አጭበርብሯል፤ በእድገት ስም አጭበርብሯል፤ በፍትህ ስም አጭበርብሯል፤ በዲሞክራሲ ስም አጭበርብሯል። ሌላው ቀርቶ በበሽታና በሞትም እያጭበረበረ ነው።
ማጭበርበር በበረሃ
ትግራይን ነፃ የማውጣት ዓላማ አንግቦ የተነሳው እና በመለስ ዜናዊ ሲመራ የነበረው ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ (ሕወሃት) በበረሃ በነበረት ወቅት ከፍተኛ ማጭበርበሮችን ፈጽሟል። ሕወሃት በረሃ እያለ ጀምሮ አሸዋ የሞሉ ከረጢቶችን እህል ነው እያለ ለእርዳታ ድርጅቶች በመሸጥ የማጭበርበር ልምድ ያካበተ ድርጅት ነው። በድርቅ ለተጎዳ ሕዝብ የመጣውን እርዳታ በአግባቡ አከፋፍላለሁ እያለ ለእርዳታ ሰጪዎች እየተናገር በተግባር ግን 55 በመቶው ለማሌሊት ማጠናከሪያ፤ 40 በመቶው ለቀይ ሠራዊት፤ እና 5 በመቶው ደግሞ ለተረጂዎቹ ማከፋፈሉ የቀድሞ አባላቱ፤ የብርታኒያ የዜና ወኪል (ቢቢሲ) እና በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ በርካታ ተቋማት ያረጋገጡት ሃቅ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ሕወሃት በረሃ ውስጥ እያለ በርካታ የፓለቲካ ማጭበርበሮችን ሲፈጽም የኖረ ድርጅት ነው።
ማጭበርበር በአራት ኪሎ
ወያኔ ምኒሊክ ቤተመንግሥት በጉልበት ከገባም ወዲህ ሥልጣኑን የዘረጋው በማጭበርበር ነው። ስለእኩልነት እየተናገረ ዘረኛ የሆነ ሥርዓት ገንብቷል። “የመሬት ጉዳይ በመቃብሬ ላይ” እያለ በሄክታር ከአስር ዶላር ባነሰ የሊዝ ዋጋ ለራሱ ወገኖች፣ ለቱጃር አረቦችና ህንዶች ለም መሬት ሲቸበችብ ኖሯል። ለመለስ ዜናዊ አገዛዝ ግድብ፣ መንገድ፣ ድልድይ፣ ኮንዶሚኒየም፣ ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክ ወይም ሌሎች ግንባታዎች ሁሉ ሕዝብንና እርዳታ ሰጪዎችን የማጭበርበሪያ መሣሪያዎች ናቸው።
ማጭበርበር በፓርላማ
ወያኔ በምርጫ ማጭበርበር “ጥበብ” ከፍተኛ “የብቃት” ደረጃ ላይ የደረሰ ድርጅት ነው። ይህንን የላቀ የሌብነት ችሎታውን በምርጫ 97 ማግሥት በተግባር ላይ አውሎታል። ሕዝብ “ወያኔ ድምፅ ዘረፈን” በማለት አቤቱታ ሲያቀርብ፤ ወያኔ ደግሞ “ተቃሚዎች ድምፅ ዘረፉኝ” በማለት የሚያማርር ዓይን ዓውጣ አጭበርባሪ ድርጅት ነው። ነፃ፣ ግልጽና ፍትሃዊ ምርጫ አካሂጃለሁ እያለ በማጭበርበር 99.6 በመቶ የፓርላማ ወንበሮችን ይዞ ስለዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር ይደሰኩራል። የአዋጅ ረቂቆችን በማንበብም “በውይይት ዳበሩ” እያሉ ያጭበረብራል።
ማጭበርበር በሆስፒታል አልጋ
መለስ ዜናዊ የአልጋ ቁራኛ በሆነባቸው ጥቂት ወራት ውስጥም የቆየው በማጭበርበር ነው። ታሞ አልታመመም፤ አልታመመም ተብሎ ታመመ ይባላል። መለስ ዜናዊ ሰውነቱ ቢዝልና አንደበቱ ቢታሰር እንኳን መዋሸት አይቸግረውም። መለስ ዜናዊ ያቆመው ሥርዓት እራሱ መለስ ዜናዊ ሞቶም ቢሆን ማጭበርበሩን የሚተው አይደለም።
የማጭበርበርን ባህል ከመለስ ዜናዊ ሥርዓት ጋር ካልቀበርነው በስተቀር ለትውልድና ለሃገር እድገት እጅግ ከፍተኛ እንቅፋት መሆኑ የማይቀር ነው።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በማጭበርበር ባህል ላይ የተገነባው የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ በአጭር ጊዜ ለማስወገድ ተግቶ ይሠራል።
መለስ ዜናዊ እያጭበረበረ ኖራል፤ ሞቶም እንዲያጭበረብር ግን ፈጽሞ አንፈቅድለትም።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment