በቅርቡ አቶ በረከት ስምዖን ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከዛም ቀጥሎ ውጪ ሀገር ለሚገኝ ራዲዮ ጣቢያ ቃለ ምልልስ ሰጥተውም አልነበር! በዛን ወቅቅት የኮሚኒኬሽን ሚኒስቴራችን ደረታቸውን ነፍተው ደምፃቸውን አወፍረው “የአቶ መለስ ጤና ባለፈው ጊዜ ከገለፅኩት በጣም እየተሻሻለ መምጣቱን እና በቅርቡም ወደ ስራቸው እንደሚመለሱ ልነግራችሁ እወዳለሁ!” ብለው ነገረውናል።
ታድያ ውጪ የሚገኘው ጋዜጠኛ አቶ በረከትን አንድ ፈታኝ ጥያቄ ጠይቋቸው ነበር። “አቶ መለስ በህይወት ካሉ ወይ ድምፃቸውን ወይ ደግሞ ምስላቸውን አለማቅረብዎ እንደ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊነትዎ የብልህ እርምጃ ነው ይላሉ?” ብሏቸው ነበር።
እርሳቸውም እንደ ማህረቤን ያያችሁ ጨዋታ ዙሪያውን ተሽከርክረው ተሽከርክረው “እኛ ምስል ባናሳይም ድምፅ ባናሰማም ህዝባችን ያምነናል ውጪ ሀገር ያለው ህዝብ ነው የማያምነው እርሱ ደግሞ የራሱ ጉዳይ” ብለዋል።
እውነታቸውን ነው። አቶ በረከትን እና እምዬ ኢህአዴግን ካላመንን ማንን እናምናለን!? ስለዚህ አዎ ልክ ናቸው በሀገሩ ህዝብ ኢህአዴግ ይታመናል። ችግሩ ግን እኛ ስናምነው እርሱ ደግሞ ያመናል እንጂ… ማመኑንስ እናምነው ነበር።
ለምሳሌ በ97 ቱ ምርጫ የምርጫውን ውጤት ተቀብሎ “ላጥ” ይላል ብለን አምነን ነበር። ግን አልታመነም በጥይት አሳመመን እንጂ… አሁንም ለምሳሌ በ2002 ቱ ምርጫ ፍትሀዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያደርጋል ብለን አምነነው ነበር ነገር ግን በተቃራኒው ሆነ ታመምንም። አሁንም ለምሳሌ የዛሬ ሃያ አመት ከአስር አመት በኋላ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በቀን ሶስቴ ይበላል ተብለን አምነነን ነበር። ነገር ግን ከሃያ አመት በኋላ እንኳን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በርሃብ እንደተጠቁ ከራሱ የመንግስት ሚዲያ ሰምተን ታመናል።
የሆነ ሆኖ አሁንም የአቶ መለስን ነገር ከራሱ የመንግስት አፍ ካልሰማን በስተቀር “በህይወት አሉ በቅርቡ ወደ ስራቸው ይመለሳሉ” በሚለው የአቶ በረከት ንግግር እናምናለን አምነን ግን እንጠይቃለን!
ታድያ በህይወት ካሉ፤ ታድያ ካለፈው ጊዜ የተሻለ ጤንነት ላይ ከተገኙ፤ ባለፈው ጊዜ አትሌቶቹ ያንን ሁሉ ድል ሲያስመዘግቡ በርካታ የበታች ሹማምንቶቻቸው” ደስ ብሎናል እንኳን ደስ አላችሁ” ሲሉን እርሳቸው ምነው ዝም አሉን? የህዝቡ ደስታ የእርሳቸው ደስታ አይደለምን!? ብለን ጠየቅን መልስ ግን የለም። ይሁን እንግዲህ የኢትዮጵያን ህዝብ በሆነ ነገር ተቀይመውት ቢሆን ነው። ብለን እኛም ዝም አልን።
አሁን ደግሞ የብፁህ አባታችን ዜና እረፍት ተከትሎ በርካታ የመንግስት ባለስልጣናት “እግዜር ነብሳቸውን ይማር” ብለው ሀዘናቸውን ሲገልፁ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ግን “ከእጃቸው እንዳልተሳለመ ሰው” ዝም ብለዋል። እኛ እስከምናውቀው ድረስ አቶ መለስ እና አቡኑ በጣም ወዳጅ ነበሩ…! ታድያ አቶ መለስ ሞታቸውን ሲሰሙ ዝም ማለት እንደምን ሆነላቸው። ፀብ ነበራቸው ማለት ነው? ወይስ አቶ መለስ ሌላው ሌላው “ባለፈው ጊዜ ከተገለፀው ሲሻላቸው” መስማት እና ማየት ገና አልጀመሩም…!? ታድያ ምኑን ተሻላቸው?
እባክዎን አቶ በረከት እስቲ ደግሞ ብቅ ብለው ይንገሩን!
በመጨረሻም
‘ሕገ ቤተ ክርስቲያን’
የቤተክርስቲያን መተዳደሪያ ህግ አንቀፅ 17 እንዲህ ይላል
“ፓትርያርኩ በሞት ሲለይ ቅዱስ ሲኖዶስ በሹመት ቀደምትነት ካላቸው ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በዕለቱ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ መርጦ ይሾማል፡፡ የተተኪው ፓትርያርክ ምርጫም ይካሔዳል፡፡” ብራቮ ቤተክርስቲያናችን!
ሕገ መንግስቱ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሞቱ የሚል ቃል የለውም… ሳስበው ያኔ ህገ መንግስቱ ሲረቅ አቶ መለስ “ተዉ አታሟርቱብኝ… እኔ አልሞትም!” ብለው እንዳይጠቀስ አደረጉ ይመስለኛል።
No comments:
Post a Comment