ባለፉት ጥቂት ቀናት ከስድስት ያላነሱ መነኰሳት ተሰደዋል።- “ታጋይ ገድላችኹ እናንተ አትኖሩም” (የፀለምት - ማይ ፀብሪ ወረዳ ሓላፊዎች)።
(ደጀ ሰላም፤ ነሐሴ 21/2004 ዓ.ም፤ ኦገስት 27/ 2012/ READ THIS NEWS IN PDF)፦ በዋልድባ አብረንታንት ገዳም መነኰሳት ላይ ባተኰረውና ካለፉት አራት ቀናት ጀምሮ እየተባባሰ በቀጠለው እስርና እንግልት ሳቢያ ከስድስት ያላነሱ መነኰሳት የፀለምት - ማይ ፀብሪ የፀጥታ ኀይሎች በሚያደርሱባቸው ግፍ ሳቢያ ወደ ሌሎች ገዳማት መሰደዳቸውን፣ በተቀሩትም አባቶች ላይ ድብደባ እየተፈጸመባቸው መኾኑን የሥፍራው ምንጮች እየገለጹ ናቸው፡፡
የዜናው ምንጮች እንደሚያስረዱት÷ የወረዳው ፖሊሶችና ታጣቂዎች በገዳሙ መነኰሳት ላይ የሚፈጽሙት እንግልትና ድብደባ የተባባሰው የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኅልፈተ ሕይወት መሰማቱን ተከትሎ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽኑ ሕመም እና ኅልፈት ገዳማውያኑን ተጠያቂ በማድረግ ነው፡፡ ቀደም ሲል በየጊዜው እየታሰሩ በተለቀቁት አበው መነኰሳት ላይ ያነጣጠረው ይኸው ርምጃ በአሁኑ ወቅት ደግሞ መነኰሳቱ ጨርሶ ገዳሙን ለቀው እንዲወጡ ከማዘዝና ከማስገደድ ጋራ የተያያዘ መኾኑም ተመልክቷል፡፡