የእስራኤል ወገኖች ኦባንግን “ድረሱልን” እያሉ ነው
አገር ቤት ያሉትን ወገኖች ለጊዜው መታደግ ካልተቻለ ቢያንስ ከማንም ተጽዕኖ ወጪ በስደት የሚኖሩትን ኢትዮጵያዊያኖች ለመርዳት ለሚቀርብ ጥያቄ የሚሰጠው ምላሽ የሚያሳዝን እንደሆነ አቶ ሳሙኤል አለባቸው በእስራኤል የኢትዮጵያን እናድን አንድነት ማህበር ሊቀመንበር ገለጹ። አቶ ኦባንግ ሜቶን ማህበሩ በተለይ መጋበዙን አስታወቁ።
ከሚያሳዝን መከራ ተርፈው እስራኤል ከደረሱ በኋላ እስር ቤት እንዲቆዩ የተደረጉት ታዳጊዎች መፈታታቸውን አስመልክቶ መግለጫ ያሰራጩት አቶ ሳሙኤል በተለይ ለጎልጉል እንደተናገሩት “በተለያዩ አገራት መከራ እየተቀበሉ ያሉትን ወገኖች መታደግ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ጠቅሰው፣ በተግባር ግን ይህንን ማየት” እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
በእስራኤል እየደረሰ ያለውን የወገኖች ስቃይ አስመልክቶ ለቀረበ ጥሪ ምላሽ ለመስጠት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ግንባር ቀደም እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሳሙኤል “በየአገሩ የተበተኑ ወገኖች እንደሚሉት በእስራኤል ያሉ ኢትዮጵያዊያን በአቶ ኦባንግና በድርጅታቸው አኢጋን ላይ ታላቅ እምነት አላቸው” ብለዋል።
“አቶ ኦባንግን ብቻ ሳይሆን አብረዋቸው ለሚሰሩት ሁሉ ልዩ ክብርና ፍቅር እንዳለን የምንገልጸው ዝም ብለን አይደለም” ያሉት አቶ ሳሙኤል “በጠላት ላይ ትኩረት አድርጎ በህብረት ከመስራት ይልቅ እርስ በርስ በመጠላለፍና ባለመተማመን በሚፈጥሩት ውዝግብ ጊዜያቸውን ከሚያባክኑት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ይልቅ ኦባንግ የሚመሩት ድርጅት ውጤታማ ስራ ሲሰራ ይስተዋላል። ይህ እውነት በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ በገሃድ የሚታወቅ ነው…” ሲሉ ተናግረዋል። ከህዝብ በቀረበ ጥያቄ አቶ ኦባንግ እስራኤል እንዲገኙ ጥሪ ማቅረባቸውንም አስታውቀዋል። ያስመዘገቡት ስኬት፣ የህይወት ተሞክሯቸውና ትምህርት ሰጪው ልምዳቸው፣ እንዲሁም የሚመሩት ድርጅት የገነባው ስም ለግብዣው ዋና ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል።
ለአንድ አገር ወዳድ የዜጎቹን ህይወት ከመታደግ በላይ ታላቅ ክብር የሚያሰጠው ጉዳይ እንደሌለ ያመለከቱት አቶ ሳሙኤል አድማሱ፣ “በህዝብ መወደድ እንዲሁ የሚገኝ ቀላልና ተራ ጉዳይ አይደለም። ቀናነትና መልካምነት እያደር በሁሉም ዜጎች ልብ ውስጥ የሚነደው በቀስታ ነው። ቀስ ብሎ የሚገነባ ክብር በቀላሉ አይናድም። ይህን የመሰለው ፍቅርና ክብር አቶ ኦባንግ ለሚመሩት ድርጅት አለን። ከተደረገው ነገር አንጻር ብዙ መናገር ቢገባኝም ለጊዜው ከዚህ በላይ የምለው የለም” ብለዋል፡፡
በተቃራኒው “አምላክ ይማርህ/ሽ የማይባልለት በሽታ ይዞናል። ብዙ ስራ አለብን። ብዙ ጉዳዮች ከፊታችን ተቀምጠዋል። አላማችን ኢትዮጵያ ናት ግን አንስማማም። ከመከራ፣ከግድያ፣ ከእስር፣ ልንማር አልቻልንም። ኢትዮጵያን ፊትለፊት በማሳየት ውስጥ ውስጡን ለግል ጥቅም የምንሰራ አለን። እንዲህ ያለው ድርጊት ሊያበቃ ይገባዋል” ብለዋል።
በእስር ላይ የነበሩት ታዳጊዎች ዛሬ ተፈተው ወደ ተለመደው የህይወት እንቅስቃሴ እንዲዛወሩ ኢትዮጵያን እናድን አንድነት ማህበር በእስራኤል የተሳካ ስራ ለመስራቱ ታዳጊዎቹን በመጎብኘትና በማነጋገር ያሰራጨው በምስል የተደገፈ ምስክርነት ያረጋግጣል። (ክፍል አንድ እና ክፍል ሁለትእዚህ ላይ ይገኛል) አሁን ትልቁ ጥያቄ እስር ላይ ያሉትን ተጨማሪ ከ300 በላይ ሰዎች ከእስር የማስለቀቁ ተግባር ነው። እነዚህ ወገኖች ያሉበትን ሁኔታ ለመመልከትና ከአገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር አቶ ኦባንግ ሜቶ ወደ ስፍራው የማምራት እቅድ አላቸው። ማረጋገጫ እንዲሰጡ ለተጠየቁት “ስንቋቋም ለወገን ነው።የምንሰራውም ለወገኖቻችን ነው። በተደረገው ተደስተናል። ለወደፊቱም የምንችለውን እናደርጋለን። አሁንም ውጤቱን መግለጽ ባልችልም ስራዎች እየተሰሩ ነው። እስራኤል ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ቦታዎች” የሚል መልስ ሰጥተዋል። በእስራኤል ከ2500 እስከ 3000 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ባልተሟላ የስደት ህይወት እንደሚገፉ ለማወቅ ተችሏል።
አቶ ሳሙኤል የሚመሩት ማህበር ይፋ ያደረገው በምስል የተደገፈ ቃለ ምልልስ በታዳጊዎቹ ውጫዊ አካል ላይ የደረሰ ጉዳት የሚታይበት ባይሆንም፤ ስራ እናስገባችኋለን በሚል አፍነው እንዴት እንደወሰዷቸውና ሲና በረሃ አስኪገቡ የደረሰባቸውን መከራ፣ ከዚያም በሲና በረሃ ቆይታቸው፣ እኒህ ህጻናት ይፋ ያላደረጉት ምን ደርሶባቸው ይሆን የሚል ጥያቄ ያስነሳል።
ቀደም ሲል ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ስለ ሲና በረሃ ባወጣው ዘገባ የአካል ክፍልን መሰረቅ፣ መደፈር፣ መሰቃትና ጉሮሮ ለማርጠብ እንኳን አረብኛ አለመናገራቸው ወገኖቻችንን እንዴት እንደሚጎዳቸው ጠቅሰን ነበር። በተመሳሳይ አሁን በተለቀቀው የቪዲዮ መረጃ “የታሰራችሁት ከኢትዮጵያ ስለመጣችሁ ነው” በማለት የእስራኤል ፖሊስ እንደገለጸላቸው የምትናገረዋ ታዳጊና ሌላዋ ጓደኛዋ የሚናገሩትን በጉልጉል ቲዩብይመልከቱ። ያቺ ስሟን የሰማናትና አካላዊ ግፍ የተፈጸመባት ታዳጊና ሌሎች ተበዳዮች ወደፊት ሰፊ ዘገባ ለማቅረብ እንሞክራለን።
የኢትዮጵያን እናድን በእስራኤል ማህበር ሊቀ መንበር አቶ ሳሙኤል አድማሱ በማህበሩ ስም ያሰራጩትና ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ በአድራሻ የላኩት ደብዳቤ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል።
ቀን 14/12/2012
የማያባራው የኢትዮጵያውያን ፈተና
ፍትህ ሰላም ዴሞክራሲ ስርአት የራቃት አገራችን ለብሔራዊ ዳር ድንበሯ መከበርና ለዜጎቿ የመኖር ዋስትና የሚሰጥ ወይም የሚታደግ መንግስት በማጣታችን የተነሳ በየጊዜው የሚገጥመን ሰቆቃ ማባሪያ አጥቶ ከዛሬው እለት ላይ ደርሰናል።
ይህ ዘገባ የሚያጠነጥነው ከጎንደር ክፍለ አገር በደላሎች አሳሳችነት ከደባርቅ፣ ከማክሰኝት፣ 50 ፍጭ እና አጅሬ ከተባሉ አካባቢዎች ወደ መተማ በመወሰድ ከመተማም ስራ እንሰጣችኋለን በሚሉ ግለሰቦች አማካኝነት እድሜያቸው ከ14 እስከ 16 የሆኑ ታዳጊዎችን በበረሃ ውስጥ ባዘጋጁት የመጠለያ ስፍራ ቀደም ሲል በተለያየ ጊዜ ያሰባሰቧቸውን 14 ወንዶችንና 46 ሴቶች ከሚገኙበት ቦታ በመውሰድ በጠቅላላው 60 ታጋቾችን ወደ ሲናይ በርሃ በማስተላለፍ “እስራኤል እንልካችኋለን ሰርታችሁ ገንዘብ ታገኛላችሁ” በማለትና ከዚያ በፊት ኢትዮጵያ ያሉ ቤተሰቦቻችሁን ስልክ ቁጥር አምጡ በማለት ወደ ኢትዮጵያ ስልክ በመደወል በእያንዳንዳቸው 60,000 /ስልሳ ሺህ የኢትዮጵያ ብር/ እስካልተከፈለ ድረስ እንደሚገሉን የሚያመለክት የማስገደጃ ትእዛዝ ለቤተሰቦቻችንን በመናገር የተጠየቀውን ገንዘብ ሊቀበሉ ችለዋል። ከዚያም የሲናን በረሃ በተሽከርካሪና በእግር በማቋረጥ ላይ እንዳለን ከመሐከላችን ከወሎ ክፍለ አገር ራያና ቆቦ ከሚባል ስፍራ የተሰደደች ሰሚራ ሲሳይ ወይም ቤተልሄም ሲሳይ እድሜዏ በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ የምትገኝ ወጣት መንገድ በሚመሩ ግለሰቦች በመደፈሯና በመደብደቧ የደረሰባት በደል ፅኑ ስለነበር ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል። እኛም በእድሜያችን ልጆች በመሆናችንና አካባቢው ላይ ስርአተ ቀብሯን ለመፈፀም አቅም በማጣታችን ከሜዳ ላይ ጥለናት ልንሄድ ሲሉ ቃላቸውን ከመስጠታቸውም ባሻገር እነሱ ራሳቸውን በረሃ ላይ ታግተው ከቆዩባቸው ቀናትና በጉዞው ላይ ባሳለፉት 14 ቀናት ውስጥ ከመደብደባቸውም ባሻገር በቂ ምግብ የተነፈጉና ለመጠጥ ውሃ በሚጠይቁበት ጊዜ ከቤንዚን ወይም ከናፍጣ ጋር የተቀላቀለበት ስለነበር በጤናቸው ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግር ገጥሟቸው ስለነበር ልንጠይቃቸው በሄድንበት ሰአት ገልፀውልናል።
እነዚህ በእድሜአቸው እጅግ በጣም አነስተኛ የሆኑ ታዳጊዎች ከአገራቸው የኑሮ ዋስትና በማጣታቸው በእግዚአብሔር ቸርነትና ከቤተሰቦቻቸው በተከፈለ 60000 ብር በሲናይ በረሀ ከሚፈፀም የተለያየ ወንጀሎች ተርፈው ወደ እስራኤል ብሔራዊ ድንበር በተሻገሩበት ወቅት በእስራኤል የጠረፍ ጠባቂ ፖሊሶች ተይዘው ለ1 ወር ከታሰሩ በኋላ በአገሪቱ መሀል አገር በሚገኝ ራምሌ በሚባል እስር ቤት በተጨማሪ 7 ወራት በጠቅላላው 8 ወራት ከቆዩ በኋላ ከእስር ተለቀው የእስራኤል መንግስት ባዘጋጀላቸው አዳሪ ት/ቤት መደበኛ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።
ከአዳሪ ት/ቤት ተዘዋውረን እንደተመለከትነው ሞግዚታቸው ወ/ሮ ምካኤል አነጋግረን የልጆቹ ጤንነት በመልካም ሁኔታ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ከመሀከላቸው ያለምወርቅ ሲሳይ የኔነህ የምትባል ታዳጊ ያለባትን የጥርስ ህመም በተመለከተ ተገቢው ተከታታይ ህክምና እየተደረገላት እንደሚገኝ ከመግለፃቸውም ባሻገር ተማሪዎቹ ከእስር እንደተፈቱ ለእያንዳንዳቸው 500 የእስራኤል ሼቅል ተሰጥቷቸው እለታዊ አስፈላጊ ነገር የተሟሉላቸው ሲሆን በቋሚነት በየወሩ ለእያንዳንዳቸው 150 ሼቅል የኪስ ገንዘብ እንደሚሰጣቸው ገልውልን መደበኛ ትምህርታቸውን በተመለከተ በሳምንት 5 ቀናት ከጠዋቱ 8 ሰአት እስከ ቀኑ 1፡30 እንደሚከታተሉና በትምህርት ቤት ቆይታቸው እድሜአቸው 18 አመት እስከሚሞላ መሆኑን ገልፀውልናል። ከ18 አመት በኋላ የታዳጊዎቹ እጣ ፋንታ ምን እደሚሆን አላወቅንም።
የእስራኤል መንግስት የእነዚህን ታዳጊዎች ህይወት በመታደግ ረገድ ላደረገው መልካም ትብብር በታዳጊዎቹ ስም ምስጋናችንን እያቀረብን እስራኤል አገር ታስረው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እስረኞችን በተመለከተ በመላው አለም ለሚገኙ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ለችግራች የሚዲያ ሽፋን እንዲሰጡን ጥሪ አቅርበንላቸው ምላሽ ለሰጡን የድህረ ገፅ ባለቤቶች ምሥጋናችንን እያቀረብን በተለይ ለእስራኤል መንግስትና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የተለያዩ ክፍሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የመብት ጥሰት በመግለፅ ኢትዮጵያውያን ታሳሪዎችን ከእስር ነፃ እንዲያደርጋቸው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሽግግርና ም/ቤትና ከአዲሲቱ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ለተፃፉ ደብዳቤዎችና ሁለገብ ድጋፎች በኢትዮጵያ አንድነት ማህበር ስም ምጋናችን ለማቅረብ እንወዳለን።
እነዚህን ታዳጊዎችና አሁን በእስር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በተመለከተ በመላው አለም የምትገኙ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ግለሰቦች የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት መሪዎች የሲቪክ ማህበራት የሀይማኖት መሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ኢሰብአዊ ድርጊት ለእስራኤል መንግስት በማሳዋቅ ረገድ የበኩላችሁን እገዛ ታደርጉልን ዘንድ በታሳሪዎቹ ከእስር ከተፈቱትና ቧልተሟላ የስደተኛ መብት በሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ስም የበኩላችሁን ድጋፍ እንድታደርጉ የኢትዮጵያ አንድነት ማህበር በእስራኤል ወገናዊ ጥሪውን ያስተላልፋል።
ከእስር ከተፈቱት መሐከል
ተቁ | ስም | እድሜ | የመጣችበት ክ/ሀገርና ልዩ ቦታ | መግለጫ |
1 | ዘርፌ ጌዴ እንደሻው | 14 | ጎንደር /ደባርቅ/ | |
2 | ለቄ ደጀን መለሰ | 15 | ጎንደር /ደባርቅ/ | |
3 | ባንቺ ባዜ በላይ | 15 | ጎንደር /ማክሰኝት ወረዳ/ | ልዩ ለፍሬው ባህር ግንብ |
4 | ወደር ገብሬ ጫኔ | 16 | ጎንደር /ባሪ ግንድ/ | |
5 | ገበያነሽ ተስፋ አማረ | 14 | ጎንደር /ማክሰኝት ወረዳ/ | ልዩ ቦታ 50 ፍጭ |
6 | አለምወርቅ ሲሳይ የኔነህ | 14 | ጎንደር /አጅሬ/ |
ከዱሪም ከሚባል ስፍራ የእርሻና የወጣቶች መንደር ታዳጊዎቹን በአንድ አዳሪ ት/ቤት አግኝተን ተገቢውን መሰረታዊ ቁሳቁስ እርዳታ ልናደርግላቸው ችለናል። ቀሪዎቹ 4 ታዳጊዎች ማለትም
ተቁ | ስም | እድሜ | የመጣችበት ክ/ሀገርና ልዩ ቦታ | መግለጫ |
1 | ሸዋዬ ሹመት | |||
2 | ድንቄ መብራት | |||
3 | ወርቅዬ ማሞ | |||
4 | ስለእናት ጥላዬ |
የተባሉት ከእስር የተለቀቁ ሲሆን የተመደቡበትን አዳሪ ት/ቤት አድራሻ በትክክል እንዳወቅን በተመሳሳይ መልኩ ተገቢውን የአልባሳት ስጦታና ሌሎች መሰረታዊ የሆኑ መጠቀሚያዎችን ለማዳረስ ቅድመ ዝግጅት ያደረግን ሲሆን በዚህ የእርዳታ ማሰባሰብ ስራ ላይ ከማህበሩ አባላት በተጨማሪ የእስራኤል የአካባቢ ም/ቤት አባላትና ሌሎች ግለሰቦችም የበኩላቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
በአጠቃላይ በረሀ ከነበሩት 60 ታጋቾች እስካሁን በህይወት ያገኘናቸው አስር ያህሉን ሲሆን የተቀሩት 50 ኢትዮጵያውያን እጣ ፋንታ ምን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።
ከእስር የተፈቱት ታዳጊዎች የመደበኛ ትምህርት በተመለከተ ከ3ኛ ክፍል እስከ 6ኛ ክፍል በአገር ቤት የተማሩ ሲሆን አንዷ ግን ምንም አይነት የትምህርት እድል እንዳላገኘች ለማወቅ ችለናል፡፡
የሁሉም አስተያየት ተመሳሳይ ሲሆን ስራ ፍለጋ እንደተሰደዱና የቤተሰቦቻቸው አቅም በሐብት ያልደረጁ በመሆናቸው ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ከነበራቸው ፍላጎት የተነሳ መሰደዳቸውን ገልፀዋል።
በአንፃሩም በበረሀና በእስር ቤት ያሳለፉትን ስቃይ በማሰብ ሌሎች ወገኖቻችን ስደትን የመፍትሔ አማራጭ አድርገው እንዳይወስዱ የበኩላቸውን አስተያየት በመስጠት የቆይታ ጊዜያችንን በዚህ መልክ ያጠናቀቅን ቢሆንም አሁንም የነዚህን ታዳጊዎች የወደፊት እድል በተመለከተ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊተባበራቸውና አቅሙ በፈቀደ ሁሉ ይረዳቸው ዘንድ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ከሰላምታ ጋር
ሳሙኤል አለባቸው አድማሱ
የኢትዮጵያ እናድን አንድነት ማህበር በእስራኤል ሊቀመንበር
No comments:
Post a Comment