መሳይ መኮንን
ዛሬ የሰሜን ጎንደር ሰማይ ያረገዘው ዳመና ምን ሊያዘንብ እንደሚችል አይታወቅም። ህዝብ አማራ፡ቅማንት የሚል ልዩነት ሳይገድበው ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ድምጹን እየሰጠ ነው። አንድን ሰው ለሁለት እንደመክፈል የተቆጠረው፡ ስጋና አጥንትን የመለያየት ያህል የተወሰደው ህዝበ ውሳኔ ህወሀት ስለፈለገው ብቻ እየተካሄደ ነው። የህዝቡ አንድነት የሚያስደስት ቢሆንም ውጤቱ የሚወሰነው በህወሀት በሚመራው ምርጫ ቦርድ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ የሚባል ነገር ከተጀመረ አንስቶ አሸናፊ የሚሆነው ድምጽ የሚሰጠው ሕዝብ ሳይሆን ድምጹን የሚቆጥረው አካል ነው። ያ ደግሞ ህወሀት ነው።
የዛሬው ህዝበ ውሳኔ ለኤርትራ ህዝብ ከቀረበው ”ባርነት” ወይስ ”ነጻነት” ከሚለው በተንኮልና ሴራ ከተጎነጎነ ምርጫዎች የበለጠ ክፋት ያዘለ ነው። ህወሀት የቅማንትን ጉዳይ ተዘጋጅቶበት የገባበት ዕቅዱ ነው። በቀላሉ የሚያየው አይደለም። ብቅ ጥልቅ እያደረገ በ”ስህተት” ነው እና በ’ይቅርታ’ ሂሳብ እያወራረደ በየጊዜው የሚያሳየን፡ የትግራይ ርዕሰ መስተዳድር ቢሮ ግድግዳ ላይ በክብር የተሰቀለው የታላቋ ትግራይ ካርታ ዕውን የሚሆነው በዋናነት ‘ቅማንት’ ብሎ በመዘዘው ካርድ ነው። ይህ ካርድ ለሁለት ጥቅሞች ይውላል። አንደኛው የአማራውን ህዝብ እርስ በእርሱ በማጋጨትና በመጥመድ የታላቋን ትግራይ ምስረታ የሚያደናቅፍ ተብሎ በህወሀት ታርጌት የተደረገን ህዝብ አቅም ማሳጣት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እስከ ጋምቤላ ለተዘረጋው የተስፋፊነት ዕቅድ ከምንም በላይ በቅማንት ስም የሚተከለውን አስተዳደር በቀላሉ በእጅ ለማስገባት የሚያስችለው በመሆኑ ነው።
ህወሀት ያቀደውን ከማሳካት ወደ ኋላ አይልም። ይሉኝታ የማያውቅ፡ ዓይን ያወጣ፡ለከት የለሽ ስግብግብ፡ ጨካኝ በመሆኑ በህዝቦች ዕልቂት ላይ የሚያልመውን ከዳር ለማድረስ እንቅልፍ አጥቶ የሚያድር ቡድን ነው። ባለፉት 26 ዓመታት ይህን በሚገባ አስመስክሯል። ዛሬ የተለወጠ ነገር የለም። ምርጫው ድራማ ነው። በልቡ የተመኘውን በህጋዊነት ሽፋን የሚያሳካበት ፈረሱ ነው። በዚህ ስውርና በመርዝ የተለወሰ ሴራ ውስጥ በየዋህነትም ይሁን በፍርሃት አልያም በጥቅም ተገዝተው አብረው የተሰለፉ ሰዎች ከማንም በላይ ተጠያቂ ናቸው።
ህወሀት ለአማራ ህዝብ ለአፍታም በጎ ተመኝቶ አያውቅም። የተፈጠረው የአማራውን ጥላቻ አርግዞ ነው። አራት ኪሎ ቤተመንግስት ያደረሰውም ይሄው ነው። ብአዴን በሚባል ፈረስ እየጋለበ አማራውን ሀገር አልባ በማድረግ ሲገድል ሲያሰድድ የከረመ፡ ለመጪውም ግዙፍ ዕልቂት እየደገሰ ያለ፡ በአማራ ጥላቻ አይንና ልባቸው የታወሩ ሰዎች የተሰባሰቡበት ቡድን ነው። ከታች በተቀመጠው ቪዲዮ ላይ በግልጽ እንደሚሰማው ህወሀት ለአማራ ህዝብ ያዘጋጃቸው ሌሎች የጥፋት ድግሶች ገና አልተነኩም። በስለት ልጁ የሶማሌው ጎረምሳ አማካኝነት ህወሀት የሚነግረን ለአማራ ህዝብ የተደገሰለትን ነው። ሰሞኑን በኦሮሞ ህዝብ ላይ በህወሀት የእጅ አዙር ትዕዛዝ የታወጀው ጦርነት ያለምክንያት እንዳልሆነ ጎረመሳው አብዲ ኢሌ ከ3ዓመታት በፊት የሀገር ሽማግሌዎችን ሰብስቦ ከሚናገረው መረዳት ይቻላል።
ህዝብ ግልብጥ ብሎ ስለወጣ የሚፈልገውን ያገኛል ማለት አይደለም። እንደተባለውም በህወሀት የምርጫ መዝገብ አሸናፊ የሚሆነው ድምጽ የሚሰጠው ሳይሆን የሚቆጥረው ነው። ከ10ዓመታት በፊት የግጨው ነዋሪ ከ90በመቶ በላይ በአማራ ክልል ስር መሆንን የወሰነበት ምርጫ ውጤት በፌዴሬሽን ምክር ቤት መዝገብ ቤት ውስጥ ተቆልፎበታል። ባለፈው ሳምንት ገዱ አንዳርጋቸው ግጨውን አጨብጭቦ ለአባይ ወልዱ የአዲስ ዓመት ስጦታ አበርክቶለታል።
የግጨው ታሪክ እንዳይደገም ምን መደረግ አለበት? የህወሀትን ሉጋም ያጣ የስግብግብነት ግልቢያ ለማስቆም የዛሬውን ውጤት እንዴት ማስጠበቅ ይቻላል? ውጤቱ ህዝብ በፈቀደው መልኩ ቢጠናቀቅ እንኳን ምን ዋስትና አለው? ግጨውን ”ያለምንም ደም” የተረከበው የህወሀት ቡድን፡ ለታላቁ ህልሙ የተመኛትን የአማራ መሬት በቅማንት ካርድ ለማግኘት አሰፍስፏል። ለዚህም ከገንዘብ ወጪ አንስቶ በፊትለፊትና በጀርባ በርካታ ነገሮችን አድርጓል። ይሄ ምርጫ ለህወሀት ታልቋ ህልም፡ ወሳኝ ነው።
ብአዴን የአህያ ባል ነው። ከጅብ አያስጥልም። በውስጡ የተሰገሰጉ ጸጉረ ልውጦች ‘ታልቁን’ ህልም ለማስፈጸም የሚያግዳቸው ሃይል የለም። ህዝብ እንደሚወስን ምንም ጥርጥር የለውም። የሚወስነውን ለማስጠበቅ ምን መደረግ አለበት የሚለው ግን ትልቁ ጥያቄ ነው።
ህወሀት ልቡ ቆሟል። በቅማንት አሻግሮ ለሚመልከከታት የታላቋ ትግራይ ምስረታ ጥድፊያ ላይ ነው። በመንገዱ ላይ የሚያሰናክሉትን ለማጥፋት መሳሪያውን ወልውሎ ተዘጋጅቷል። የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ እንዳይነሳበትም የመጨረሻውን ካርድ መዟል። በየአከባቢው የጎሳ ግጭቶችን ለኩሷል። ሁሉም በየጎጥና መንደሩ ፍጥጫ ላይ ነው። እንደሀገር እንዳይነሳ በያለበት በግጭት ተጠምዷል። ህወሀት አደገኛ የሆነ የአጥፍቶ መጥፋት መስመር ላይ ወጥቶ እየተውረገረገ ነው።
የቅምናትም ጉዳይ መታየት ያለበት ከዚህ አንጻር ነው። ኢትዮጵያዊ መፍትሄ ያስፈልገናል። ሀገራዊ የሆነ መድሃኒት እንጂ አከባቢያዊ ትግል ፈውስ አይሆንም። እንደ ኢትዮጵያዊ አንድ ላይ ካልተነሳን መቼም ቢሆን ህወሀት ከደገሰልን ጥፋት ልንድን አንችልም። አራት ነጥብ።
No comments:
Post a Comment