Translate

Thursday, September 14, 2017

ህልውናውን በህዝቦች ቅራኔ ላይ የገነባ ዘረኛ ቡድን (በያሬድ አውግቸው)

በያሬድ አውግቸው
Ethiopia, TPLF officials
“Whoever sows injustice will reap calamity.”
በአሁኑ ወቅት የህወሃት  ዋነኛ  ስራ  በህዝቦች መካከል ቅራኔዎችን መፍጠር የሚመስልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። እንደ ጥሩ ምግባር ለቅራኔዎችም እቅድ ተዘጋጅቶና በጀት ተመድቦ  የህዝቦች ደም ሲፈስ ይታያል። ለዚህም የወቅቱ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልዩ ሃይልና የአጎራባች የኦሮሚያ ወረዳዎች ነዋሪዎች መካከል ያለው ጦርነት መሰል ግጭት አንዱ ማሳያ ነው።  ግጭቱ በመንግስት ዝም ባይነት አንዳንዴም መሪነት ሲቀጣጠል የወቅቱ አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሶአል። ይህ ክስተት ለብዙዎች ግራ አጋቢ ሆኖ ቆይቶአል። 
ለምን   ህወሀት ከተለመደው የመንግስታት ባህርይ ወጣ ባለ መልኩ ለቅራኔዎች  መፈጠር እቅድ አውጥቶ ይሰራል በሚል። ለምንስ በአሰቃቂ የእርስ በእርስ እልቂት ውስጥ ካለፉ እንደ ርዋንዳ  እይነት ሀገራት  ውድቀት መማር አቃተው የሚሉ ጥያቄዎች ወደ አምህሮአችን  መምጣታቸውም አይቀርም።  መልሱ የህውሃት ተፈጥሮአዊ ባህርይ  አንድነትን ለመስበክ  እንዳይችል አግዶታል የሚል ይሆናል። የድርጅቱ ባህርይ በስሙ፣ በተቋቋመበት አላማ፣ በግቡ፣ በአሁኑ ወቅት እየቀረጹ በሚተገበሩ ፕሮግራሞቹ እና ለሀገሪቱ ባለው ራእይ ሲገለጽ  ይታያል።
ህወሀት ሌሎች ጠፍጥፎ የሰራቸው  ብሄረሰብ ተኮር ድርጅቶች  በስማቸውና ፕሮግራማቸው ላይ ተደጋጋሚ  ክለሳ እንዲያደርጉ ሲያስገድድ ቢቆይም እራሱ ግን በነጻ አውጭነት ላይ ተንጠልጥሎ መቅረቱ አስገራሚ ጉዳይ ነው።  እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሳዊ ንቅናቄ /ኢህዴን/ ወደ ብአዴን እንዲሁም የአጋር ድርጅቶች ፓርቲዎችን ሲያፈርስና ሲሰራ 26 ኣመቱን እንዳስቆጠረ ማስታወስ ይገባል። ሆኖም ህወሀት አዲስ አበባን  ከተቆጣጠረ ጀምሮ ስሙን ለምን አያስተካክልም የሚሉ ጥያቄዎች ሲቀርቡ ከፍተኛ አመራሮቹ ወደ ቁጣና ብስጭት ሲያመሩ ይታያል። ለምንስ ነጻ አውጭ የሚለው ቅጥያ በሌሎች ላይ ሀጢአት፤  ህወሀት ላይ ሲደርስ ግን ወደ በረከትነት ይቀየራል? አሁንም መልሱ ህወሀት እራሱን የሀገሪቱ ብቸኛ ገዢ አድርጎ  ስለሚመለከት ነው። እስከቻልኩ እየገዛለሁ፤ እዘርፋለሁም  ካልሆነ ግን እራሴን  ወደ ነጻ ሀገርነት እቀይራለሁ የሚል ትእቢት።
እድሜ ለግዜ በህወሃት አላማና ግብ ላይ ብዥታ የነበረባቸው ጥቂት ዜጎች ሳይቀር  ሀገር ከማፍረስ ውጭ ሌላ የተሸከመው ተልእኮ እንደሌለ የተረዱበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።    ህወሃት ህብረብሄራዊም ሆነ ዘውጋዊ ፓርቲዎችን/ ድርጅቶችን በእኩል መጠን የሚጠላ ድርጅት ነው። ይህም ከአምባገነናዊ ባህሪው የሚመነጭ ነው። ተራራን ያንቀጠቀጠ ትውልድ በሚል መጽሀፉ በወዳጅነት ያቀረባቸውን የኢአፓ ታጋዮችን እንዴት በተኙበት በካራ ህይወታቸውን እንደቀማ በኩራት የተረከ ድርጅት መሆኑን ማስታወስ ይገባል። በመአህድ፣ ቅንጅት፣አንድነት፣ መድረክ እና ሌሎች መሰል ፓርቲዎች ውስጥም ሰርጎ በመግባትና በመወንጀል የሰራው ስራ  ይታወቃል። ህወሀት እንደ ቀን ገዥ  የኢኮኖሚ መሰረቴ ነው ብሎ የሚያምንበት ʿይዞታውʾ  በተወዳዳሪ ሌላ አካል  እንዲተዳደር አይፈልግም።  ይገዛል ካልሆነ ደግሞ ሀገሪቷን የብጥብጥ የቤት ስራ ሰጥቶ ለመሄድ የሚሰራ ድርጅት ነው።
በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ልዩ ልዩ ቦታዎች የሚታዩ የብሄረሰብ ግጭቶችም መሰረታቸው  ከዚሁ  ህወሀት የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ሜዳውን ለብቻው ለመቆጣጠር ካለው ከመስመር የወጣ ፍላጎት የመነጩ ናቸው። ሰላም ካለ በህዝቦች መካከል መነጋገርና መግባባት ይፈጠራል ብሎ ከመስጋት የመጣ ማለታችን ነው። በእውነትም  ሰላም ካለ እንደ ህወሃት ላለ የህዝብ መሰረቱ አነስተኛ የሆነ ፓርቲ  የሀገሪቱን ፖለቲካ እንዳሻው እንዲዘውር   እድል አይሰጠውም። አስገራሚው  ነገር የእርሱን ኢፍትሃዊ አስተዳደር ለመቃወም ህዝቦች  ሰላማዊ ሰልፍ ሲወጡ በብርሃን ፍጥነት ወታደሮቹን የሚያዘምተው  ይህ ዘረኛ መንግስት ለብሄረሰቦች ጦርነት መሰል ግጭት ግን  ከብዙ ጥፋት በሃላ  ጦሩን መላኩ ነው። ይህ እንግዲህ ከሃያኛው ክፍለ ዘመን ቀኝ ገዥዎች የተቀዳ ስልት መሆኑ ነው። ያልነበረ ፍላጎት እንዲፈጠር ይሰራል። ፍላጎቱ እንዲጠናከር  ያግዛል። በመጨረሻም  ግጭቶችን ለሱ ርካሽ የብዝበዛ ፍላጎት ማስፈጸሚያነት  ይጠቀማል። ከፋፍለህ ግዛ።

No comments:

Post a Comment