ሁላችንም ልናነበው የሚገባ ከሰማያዊ ብሔራዊ ሸንጎ የተሰጠ መግለጫ
(ከሰማያዊ ብሔራዊ ሸንጎ የተሰጠ መግለጫ)
ዛሬ በሀገራችን ከላያችን በተጫነው አገዛዝ ምክንያት በዜግነታችን እና በሉዓላዊነታችን ላይ ያልተጋረጠ የችግር ዓይነት የለም፡፡ የችግሩ ስፋትና ጥልቀት ከሀገር መፍረስ አደጋ ጀምሮ እስከ ዘር ፍጅትና የማያባራ የእርስ በእርስ ጦርነት ይደርሳል፡፡ በእነዚህ ችግሮች ፍርሃትና ጭንቀት ውስጥ ሆነን ምንም ሳናደርግ በየዕለቱ በአገዛዙ አረመኒያዊ ተግባር በዜጎች ላይ የተፈፀመው ግድያ፣የጅምላ እስር እና መፈናቀል በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ጥልቅ ሀዘንና የልብ ስብራት ጥሎ አልፏል፡፡
ከላይ በጠቀስናቸው ውስብስብ ችግሮች ምክንያት እኛ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻችንን በቅደም ተከተል አስቀምጦ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ የመከራና የግፉ መብዛት የግልና የጋራ አስተሳሰባችንን ቆልፎ ምንም ነገር ወደ አለማድረግና መጭውን የመፍራት ለቁዘማ አስተሳሰብ የተዳረግን ይመስላል፡፡ ተስፋ ቢስነት፣አለመተማመን እና ስጋት የጋራ መገለጫዎቻችን እየሆኑ መጥተዋል፡፡
የጨቋኞቹ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ሀገርን እስከማፍረስ የደረሰ ከመሆኑም በተጨማሪ የአገዛዙ መፍረስ እውን መሆኑን የተረዳን የተደራጀንም ሆነ ያልተደራጀን የፖለቲካ ኃይሎችም ብንሆን "ለውጡን የመሸከምና የመምራት አቅም የለንም" በሚል የመንፈስ ድካም የለውጡን አይቀሬነት ውስጣችን እያመነ ለውጡን በፍርሃት እንድንጠብቀው ተገደናል፡፡ በመሆኑም ይህ አመለካከታችን አውቀነውም ይሁን ሳናውቀው ለአገዛዙ እድሜ መራዘም አወንታዊ አስተዋፅዖ ከማድረጉም በተጨማሪ ባይቀሬው ለውጥ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገሯን ተስፋ በማመንመን የምንፈራውን መራራ ፅዋ እንድንጎነጭ ያደርገናል፡፡
ተደጋጋሚ መስዋዕትነትና የድል ርሃብ በህዝባችን ላይ የተስፋ ቢስነትና አለመተማመን መንፈስ እንዲያቆጠቁጥ ቢያደርገን የሚያስገርም አይደለም፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው ለእኛ ኢትዮጵያውያን አዲስና እንግዳ የሆኑ ከማህበራዊ ስነ ልቦናችን ጋር ያልተዋሃዱን ስር ያልሰደዱ ተንሳፋፊ ባህሪዎች ናቸው፡፡ ይልቁንም በእኛ በኢትዮጵያውያን ጥልቅ ስነ ልቦና ውስጥ አሸናፊነት፣ሙሉ ልብነት፣ሚዛናዊነት፣ጨዋነት እና ኃይማኖተኛነት እውነተኛና የማንነት መገለጫዎቻችን ናቸው፡፡ እነዚህን መልካም እሴቶቻችንን በስንቅነት በመያዝ የማንወጣው ችግር ስለሌለ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በማለም ለችግሮች ሁሉ ምንጭ የሆነውን አገዛዝ ለማስወገድ በሙሉ አቅማችን የምንነሳበት ጊዜ አሁን ነው፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ በሕወሐት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን ከእኛ አልፈን ለዓለም ጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነፃነት ጮራ የሆንበትን የታሪካችን ክፍል የሞራልና የሙሉ ልብነት ስንቅ ማድረግ እንደወንጀል ተቆጥሯል፡፡ ይህ ክፉና ወኔ አምካኝ ተግባር በስልጣን ለመቆየት የተቀነባበረ ክፉ ደባ መሆኑን ተገንዝበን ለፈተና ሳንበገር በሙሉ ልብነትና በአርቆ አስተዋይነት ለምንወዳት ሀገራችን ህልውና መረባረብ አለብን፡፡
በአጠቃላይ አገዛዙ ማርጀቱና መበስበሱ በራሱ ተግባር ተጋልጧል፡፡ አሁን ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ ወደ መፈራረስና የእርስ በእርስ ጦርነት ወይም ወደ መረጋጋትና ዴሞክራሲ የመራመድ እጣ ፈንታዎች ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ ወድቋል፡፡ ዛሬ ሀገራችን በዘረኝነትና በፍርሃት ያልተሸመቀቁ ሙሉ ልብና ባለራዕይ የሃሳብ መሪዎች ከመቸውም ጊዜ በላይ ያስፈልጓታል፡፡ በመሆኑም ያንዣበበብንን መከራ ተሻግረን ወደ ዴሞክራሲና ብልፅግና ለመጓዝ የሚያበቁ በታሪክ የተረጋገጡ የመንፈስና የሞራል እሴቶች ስላሉን እነዚህን እሴቶቻችንን በማስተባበር ለዘላቂ ድል በቆራጥነትና በአንድነት እንድንነሳ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
መስከረም 14 ቀን 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ
No comments:
Post a Comment