(ኢሳት ዜና–መስከረም 10/2010) በኢትዮጵያ ውስጥ በሚካሄደው ሌብነት በግንባር ቀደምትነት ሲጠቀሱ የነበሩትና ከሀገር እንዳይወጡ እገዳ ተጥሎባቸው የቆየው አቶ አባይ ጸሀዬ ለሕክምና ከሀገር መውጣታቸውን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ራሳቸውን በኮሚቴ ያደራጁ የትግራይ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች በሌብነት ላይ የተጀመረው ዘመቻ እንዲቆምና የታሰሩትም እንዲፈቱ መጠየቃቸው ተሰምቷል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በሚካሄደው ሌብነት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት አቶ አባይ ጸሃዬ ናቸው።
ይህን ተከትሎም ከሀገር እንዳይወጡ እገዳ ተጥሎባቸው መቆየቱም የሚታወስ ነው።
ሌቦችን የማደኑ ስራ እየተካሄደ ነው በሚባልበት በአሁኑ ሰአት ደግሞ ራሳቸውን በኮሚቴ ያደራጁ የትግራይ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች በሌብነት ላይ የተጀመረው ዘመቻ እንዲቆምና የታሰሩትም እንዲፈቱ በመጠየቅ ላይ መሆናቸውም ተሰምቷል።
እነዚህ በኮሚቴ ተደራጁ የተባሉት የትግራይ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች ባሳደሩት ተጽእኖም አቶ አባይ ጸሀዬ ለሕክምና ከሀገር እንዲወጡ ተደርጓል ሲሉ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
ባለትዳርና የልጆች እናት ከሆኑት ወይዘሮ ሳሌም ከበደ ጋር በአንድ ጣራ ስር መኖራቸው የተገለጸው አቶ አባይ ጸሀዬ ወይዘሮ ሳሌም ከበደ ከታሰሩ በኋላ በምርመራ እየወጡ ያሉ የወንጀል ድርጊቶቻቸው እንዲሁም ባለቤታቸውን መታደግ አለመቻላቸው በፈጠረባቸው ውጥረት መታመማቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ራሳቸውን በኮሚቴ ያዋቀሩት የትግራይ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች አቶ አባይ ጸሃዬ በሕወሃት ትግል ውስጥ በመሪነት ጭምር የተጫወቱትን ሚና በመዘርዘር እንዳይታሰሩ ሲማጸኑ መቆየታቸውም ተመልክቷል።
ይህ ርምጃ በሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ውስጥ ያለውን ችግር ያባብሳል፣ለጠላትም በር ይከፍታል በሚል የጸረ ሌብነት ዘመቻው እንዲቆም ሲወተውቱ መቆየታቸውም ተሰምቷል።
የታሰሩትም ይቅርታ ጠይቀው በማስጠንቀቂያ እንዲፈቱም ተማጽኖ ማቅረባቸው ታውቋል።–የታሰሩትን ለመፍታት ስለመወሰኑ የታወቀ ነገር ባይኖርም እንኳን።
ሆኖም ክትትል ሲደረግባቸው የነበሩትና ይታሰራሉ ተብለው የሚጠበቁት ባለስልጣናትና ነጋዴዎች የሚደረግባቸው ክትትል መቆሙን እነዚሁ ምንጮች ገልጸዋል።
በሀገሪቱ በሚፈጸመው ሌብነት ፊታውራሪ ተብለው የሚጠቀሱት አቶ አባይ ጸሃዬ ለሕክምና እንዲሄዱ የተፈቀደው በሌብነት ላይ የተጀመረው ዘመቻ በመቆሙና ከትግራይ ሽማግሌዎች ተጽእኖ ጋር በተያያዘ እንደሆነም መረዳት ተችሏል።
አቶ አባይ ጸሃዬ ለህክምና የወጡት ወደ ጀርመን እንደሆነ ቢገለጽም በትክክል ወደየትኛው ሀገርና የህክምና ማዕከል እንደሄዱ ግን ማወቅ አልተቻለም።
No comments:
Post a Comment