ግዛቸው አበጋዝ ፤ ሳሰካችዋን ካናዳ፣መስከረም 2010
በኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ እንደወያኔ በህዝብ የሚጠላ ገዢ አላየሁም፤ አልሰማሁም እንዲሁም አላነበብኩም፡፡ በዚህ ወቅት ኢህአዴግን ሀገሪቱን የሚያስተዳድር መንግስት ብሎ እና ሹማምንቱን ደግሞ ህዝቡን የሚመሩ መሪዎቹን ብሎ መጥራት አይደለም መስማት ህሊናን የኮሰኩሳል፡፡ ምክንያቱም በሀገሪቷ እና በህዘቧቿ ላይ ያደረጉት እና የሚያደርጉትን ስትመለከት፡፡ ከተራ ወንበዴነት እስከ ሀገርን እና ህዝብን ለዘርፍ የመጣ የውጪ ጠላት የሚፈፅመውን ፈፅመዋል፡፡
እነሱንም እንመራዋለን የሚሉት ህዘብም በተግባራቸው ይጠየፋቸዋል፡፡ ከቀንን ወደ ቀንም የፓርቲው እና የሹሞቹ ስም ሲነሳ እንደ ዛር የሚያንዘ ዜጋ ከትላንቱ ይለቅ ዛሬ ላይ ቁጥሩ የትዬለሌ አሻቅቧል፡፡ ይህ በርሃብ፣ በስራ አጥነት፣ በነፃነት እጦት፣ በሙስና እና በመልካም አስተዳደር እጦት የሚሰቃይው ዜጋ ይህ ከፉ ስርአት ባመጣበት ሌላ የዘር በሽታ ዛሬ ላይ በእርስ በርስ ግጭት መታመስ ከጀመረ ውሎ አድሮአል፡፡
የኢትዮጲያ ህዝብ የሚጠየፈው አምባገነን ስርአት የዘራው ክፉ የዘር ስርአት (በሽታ) ዛሬ ላይ ፍሬ አፍርቶ የሀገሪቱ ግንባር ቀደም ስጋት እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህም ክፉ ስርአት በህዝብ ጫንቃ ላይ የሚቆይ ከሆነ የሀገሪቱን ህልውና እና ዘላቂ ሰላም ላይ ምን ሊያሰከትል እንደሚችል ለመገመት ጠቢብ መሆን አያስፈልግም፡፡ ወያኔ የሚከተለውን የዘር ፖለቲካ ክፉ በሽታ እያለኩ በፅሁፉ ውሰጥ የምጠቀመው ለሀገራችን አንድነት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እንደሚያመዝን በአለፉት 26 አመታት አይተነዋል፡፡ በተጨማሪም አንድ ዜጋ በዘሩ ከሚያገኘው ነፃነት ይልቅ በዜግነቱ የሚያገኘው ነፃነት ሚዛን ስለሚደፋ እና የሚያኮራ በመሆኑ ነው፤ የዘር ፖለቲካቸውን ክፉ በሽታ ያልኩት፡፡
ወያኔ ስልጣል ላይ በቆየበት ሩብ ምተአመት ውስጥ ሀገራችን ላይ ከዚህ ቀደም ተከስተው የማያውቁ ነገሮች ዛሬ ላይ በስፋት ተከስተዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ዘር ያማከሉ ጦርነቶች እና ስደቶች ወይንም ከቦታ መፈናቀሎች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህን ቀንን ወደ ቀን እየተባባሱ የመጡ የክፉው በሽታ ውጤቶች ሀገራችን ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ በአጭሩ እንቃኘው፡፡
በቅርቡ በኦሮሚያና ሶማሌ አዋሳኝ አካባቢዎች በተቀሰቀሰው ግጭት ከ50 ሺ በላይ ኦሮሞዎችን ሲያፈናቅል በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት ቀጥፏል። በዚህ ግጭት ታጣቂ የወያኔ ሀይሎች (የሶማሌ ክልል ልዩ ሀይል) ተሳትፈውበታል፡፡ ደብረ ዘይት ላይ የእሬቻ በአል ሊያከብር በወጣው ሰላማዊ ህዝብ ላይ ጥይት ያርከፈከፈው የኦሮሚያ ልዩ ሀይል ወይንም የፈደራል ወታደር ከሞት ተርፎ ወደ ጅጅጋ እና አጎራባች ከተሞች የሚሰደደው ዜጋን መኪና እያስቆመ ሲገደል፣ ሲገረፍ እና አካሉ ሲጎድል የት ነበር ያስብላል፡፡ እየፈሰሰ ያለው የወገኖቻችን ደም እና የስቃይ ጩኸት የሚሰማ መጥፋቱ እጅግ የሚያሰቆጭ ቢሆንም ግጭቱን እሰከ ዛሬ ድረስ እንዳይበርድ ለምን እንደተገለገ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
ሌላኛው የክፉ በሽታው ምሳል የሚሆኑት በቤንሻንጉል ክልል ጉራፍ ወረዳ ይኖሩ የነበሩ የአማራ ገበሬዎች ላይ የዛሬ አምስት አመት አካባቢ የተከሰው ሞትና መፈናቀል፣ በጋንቤላ ክልል በንዌሮች እና በአኝዋክ ጎሳች መካከል የተካሄደው አሰቃቂ ጭፍጨፋ ናቸው፡፡
የነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸውን ሶስት አሳዛኝ ክስተቶች ለማስረጃነት አነሳሁ እንጂ እነዚህ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ መሽቶ እስኪነጋ መዘርዘር ይቻላል፡፡
መታወቅ ያለበት ዋናው ጉዳይ የግጭቶች መንስኤ በህዝብ ጫናቃ ላይ የሰፈረው ክፉ ስርአት መሆኑ ነው፡፡ ስርአቱ ለመሆኑ ደግሞ እኛ ተጎጂዎቹ / የምንኖረው/ አይደለንም አልፎ ሂያጅ የተቀረው የአለም ሰው ያገነዘበዋል፡፡ እኛን የስርአቱ ገፈት ቀማሾች የሆነውን ዜጎች እያሳሰበ የመጣው ይህ ዘርንና ክልልን ያማከለ ግጭት አለም ላይ ያሉ ጥልልቅ ሚዲያዎችን ትኩረት አግኝቷል፡፡ አልጄዚራም ምን እንደሸተተው ባይታወቅም በአለም ለጋዜጠኞች በአደገኝነት ሶስተኛ ደረጃ ላይ ወደ ሰፈረችው ኢትዮጲያ ተጉዞ ቢሮውን ከትሟል፡፡ ቢቢሲ ኬንያ ሆኖ ጆሮውን ከቀሰረ ሰነባብቷል ለዛውም በአራት የሀገራችን ቋንቋ ስርጭችን አካቶ፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህን ሚዲያዎች እና የዘገባዎች መንፈስ በሌላ ፅሁፍ የምመለስበት በመሆኑ ለዛሬ በዚሁ ማለፍ እወዳለሁ፡፡ ነገር ግን እየተከሰተ ያለው ዘርንና ክልልን ያማከለ ግጭት ያሳሰባቸው ሁለት ኢትዮጲያዊ ምሁራን ያሉትን መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡
የቀድሞው የህውሀት መስራችና አመራር የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ሰሞኑን ‹‹ትውልድ ፈታኝ ቀውጥ!›› በሚል ርዕስ ባስነበቡን ፅሁፋቸው በዚህ ክፉ በሽታ የተሰማቸውን ስጋት እንዲህ አስፍረውታል፡፡ ‹‹ይህ እየተሰራጨ ያለው ክፉ ክስተት ማቆምያ ካልተበጀለት ሃገር-አልባ ሊያደርገን ይችላል። ቀውሱን የፈጠረው የህወሓት/ኢህኣዴግ ገዢ መደብ ለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ይህ ሀላፊነት የማይሰማው አምባገነን ቡድን ገና ከጅምሩ የወጠናቸው ደንባራና ስግብግብ ፖሊሲዎች እንዲሁም አረመንያዊ የአገዛዝ ዘይቤዎች አሁን ከምንገኝበት አረንቋ ውስጥ ከቶናል።››
እኝህ ወያኔን ከጥንስሱ ጀምሮ የሚያቁት ሰው ስጋታቸው ‹‹አገር-አልባ›› እስከመሆን ያደረሰው የቀድሞ ወዳጆቻቸውን አላማ ሳያውቁት እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን እንዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደዚህ በፍጥነት ስጋ ለብሶ ማየታቸው ሳያስደነግጣቸው አልቀረም፡፡ ይህ ማለት ግን ስጋቱ እና ድንጋጤው የሳቸው ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ 26 አመት ሙሉ ሁሉንም ዜጋ በየደረጃው እና በሚያየው አስጨንቆታል፡፡
ሌላኛው ታዋቂ የኢኮኖሚው ዘርፍ ምሁሩ ዶ/ር አክሎክ ቢራራ በዚህ ሳምንት ‹‹በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን የውጭ ኃይሎች ጫናና ሴራ እንዴት ለመቋቋም ይቻላል? በአዲሱ ዓመት ለጠባብ ብሄርተኞች እጃችን ላለመስጠት እንወስን›› በሚል ገራሚ የመጀመሪያ ክፍል ጥናታዊ ፅሁፍ አስነብበዋል፡፡ ዶ/ሩ በፅሁፋቸው ውስጥ ‹‹የተፈጥሮ አደጋዎችና ሰው ሰራሽ ቀውሶች ለኢትዮጵያ ቀጣይነት አደጋዎች ናቸው።›› በሚል በሰጡት ንዑስ ርእስ ‹‹ዛሬ በኢትዮጵያ በመሬት ላይ የሚታየው የፖለቲካ ሁኔታ ከተፈጥሮ አደጋዎች ጋር–ለምሳሌ፤ ከድርቅ ረሃብ፤ ከድህነት፤ ከአገር ውስጥ የሕዝብ ፍልሰት፤ ከተስቦ በሺታዎች ወዘተ… ጋር ሲደማመር ኢትዮጵያን ወደማይመለስ ውድቀት እንድታመራ ያደርጋታል። ይህ፤ ከመጥፎ አገዛዝ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ሲሄድ የሚታየው ክስተት ምንን ያንጸባርቃል? ብየ ራሴን ስጠይቅ መልሱ ሆነ ተብሎ የተጸነሰውና ሊቆም የማይችል የሚመስለው የብሄር የማንነት ጥያቄ እየተስፋፋና እየከረረ መሄዱን ያሳያል የሚል ይሆናል።›› ሲሉ አስፍረዋል፡፡
የኢኮኖሚ ምሁሩ ወያኔ በሀገራችን ህዘቦች ውስጥ የዘራውን ክፉ የዘር ስርአት ከተፈጥሮ በሽታዎች ጋር ተዳምሮ የሚያስከትለው ጉዳት በቀላሉ የማይታከም መሆኑ ቢያሰጋቸውም የዘር ፖለቲካው ብቻ በራሱም ለሀገራችን ነቀርሳ መሆኑን ነግረውናል፡፡
በአጠቃላይ በሀገራች ላይ የተከሰቱ ደም አፋሳሽ ግጭቶችን ፣ የንብረት ውድመቶችን ተመልክቶ እና የሙሁራኑን የስጋቶች ጥልቀን አሰተውሎ ዝም ብሎ መቀመጥ የሚችል ዜጋ ያለ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህም ሀገራችን ኢትዮጲያ እንደ ሀገር እንደትቀጥልና በህዝቦች መካከል ያለው አንድነት እንዲጠነክር መስራት ያስፈልጋል፡፡ ወያኔ የዘራው ክፉ በሽታ እንዲከስም በጋራ መቆም ፍቱን መዳኒቱ፤ ስርአቱን ከስሩ ነቅሎ መጣል ደግሞ የሀገሪቱ ፈውስ ነው፡፡ ሰለዚህ ……
ስለዚህ ‹‹ተነሳ ተራመድ ክንድህን አበርታ ….›› እያልን እየዘመርን (የቀድሞው ስርአት ናፋቂዎች ብንባልም) ለሀገችን መስራት ነው፡፡ ጥያቄህ ለሀገሬ ምን ልስራ ከሆነ ራስህን ምን መስራት እችላለሁ ብለህ ጠይቅ ያኔ መልሱን ታገኘዋለህ፡፡ እውነቱ ግን ሀገራችን የኛ የህዝቦችዋን የአንድነት ስራ ትሻለች፡፡ (አራት ነጥብ !!!)
No comments:
Post a Comment