Translate

Monday, December 10, 2012

ስለ “አንቀጽ 39” ማንን እናመስግን?


(ርዕሰ አንቀጽ)

article 39
የሶማሌ ብሄር አባል ናቸው። አቶ አብዱላሂ አብዱራሂም ይባላሉ። ዘጠነኛውን “የብሄር ብሄረሰቦች” ቀን አስመልክቶ አስተያየት እንዲሰጡ ተጋብዘው በቴሌቪዥን ብቅ አሉ “… አቅማችሁ ካደገ በኋላ፣ ልጆቻችሁን አስተምራችሁ አቅም ስታዳብሩ ለአንቀጽ 39 ትደርሱበታላችሁ…” እንዳሉዋቸው አቶ መለስን ጠቅሰው ተናገሩ። ትዝታቸው መሆኑ ነው።
ወዲያው አቶ መለስ በወቅቱ እንገነጠላለን ያሉትን የሶማሌ ህዝቦች ሰብስበው ሲናገሩ ታዩ።እንዲህ አሉ “አስራ ዘጠኝ ዓመት የታገልኩበት አላማ እንዳይቀለበስ እፈልጋለሁ። አይቀለበስም ብዬ ቃል ስገባ እናንተን ለመደለል አይደለም። ምክንያቱም ስለመብቱ ምን አልባትም ከናንተ በላይ አስባለሁ። ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም። ከልቤ ስለማምንበት ነው” ሌላ አስተያየት ሰጪ ተከተለ። ተከተለች። “አንቀጽ 39 ለዘላለም ይኑር” ተባለ።
“የኢትዮጵያዊነት ፋይዳው በጣም ጥልቅና መሰረታዊ ነው። 80 ሚሊዮን ህዝቦች አንድ ላይ ስናጨበጭብ እንደመጣለን።ተመጋጋቢ ኢኮኖሚ አለን። ለአገራችን ደህንነትም ሃይል ነው” ይህን ምርጥ አባባልም በተመሳሳይ ፕሮግራም የተደመጠው ከቀድሞው ጠ/ሚ አቶ መለስ አንደበት ነው። በዚህ አያበቃም።
“ተበጣጥሰን የምናገኘው ቴክኖሎጂ ተሰባስበን የተሻለ አይደለም። መሰባሰቡ ጠንካራ ነገር አለው። መሰባሰባችን /አንድነታችን/ የመንደር ንፋስ የሚጠራርገውና የሚበጣጥሰው አይደለም።ስሜት አይደለም። ኢትዮጵያዊነት ጠንካራ የሚሆነው ምክንያት ስላለው ነው” አንጀት የሚያርስ አባባል። ወርቅ ንግግር። ከዚያስ?
“ነጻ ኦሮሚያ” የሚሉ ሰልፈኞች ታዩ። መለስ መጡ። አዲስ አበባ እንደገቡ ሰሞን ነው። እንዲህ አሉ “እኛ ጦርነትን በቴሌቪዥን አናውቅም። እኛ ጦርነትን በወሬ አናውቅም። እኛ ጦርነትን በተቃጠሉ ቤቶች፣ በተጨፈጨፈ ህዝብ ነው የምናውቀው። ከእንግዲህ አንዋጋም። በቅቶናል። ሰልችቶናል። ከእንግዲህ አንዋጋም” በማለት የተናገሩትን አሞጋሾችን እየቀላቀለ ኢቲቪ ትውስታ አቃመሰን።
አቶ መለስ አማራ ናቸው፣ አቶ መለስ ሃረሪ ናቸው፤ አቶ መለስ ወላይታ ናቸው። አቶ መለስ ሶማሌ ናቸው። ወዘተ የሚሉ ሰዎች መለስን ባረኩ። የሶማሌ ክልል አስተያየት ሰጪ የአቶ መለስን ፎቶ ጸሃይ ሲመታው አይተው “ፎቶም ቢሆን መለስ እኮ ነው ጥላ አድርጉለት አልኩ” ሲሉ አሁንም ኢቲቪ አስደመጠ። የሃረሪው አስተያየት ሰጪ ከጭቆናው ብዛት ከምድረ ገጽ ሳይጠፉ አቶ መለስ እንደደረሱላቸው መሰከሩ። አቶ ኩማም ኦነግን እየረገሙ አንቀጽ 39 ዋጁ። ታላቅ ገጸ በረከት እንደሆነ ደጋግመው መሰከሩ። ይብቃን!!
“የብሄር ብሄረሰቦች” ቀን ሲከበር የመጻፍ፣ የመናገር፣ የመደራጀት፣ የመቃወም፣ ህዝብ በፈቀደው መንገድ እንዲደራጅ፣ ይህ ካልሆነ እስከመገንጠል መብት አለው የሚል የተጨመቀ ዓላማ እንዳለው በተደጋጋሚ ሰምተናል። ይህንን እየሰማን አማራው መፈናቀሉ ይነገረናል። ለዓመታት ከኖሩበት እየተሰደዱ ልመና ላይ መሆናቸውን ከበዓሉ ጋር የቀጥታ ስርጭት ሆኗል። ህጻናት ለችግር ተጋልጠዋል። አባት ከጎጆው ወጥቶ የቀን ሰራተኛ ለመሆን ተገዷል። ቤተሰብ ተበትኗል። የታሰሩ አሉ። ይህ ሁሉ የሚሆነው “እገሌን ደገፍክ” በሚል የፖለቲካ ቂም እንደሆነ ሰለባዎቹ ሲናገሩ እየሰማን ነው። ለዚህ ታላቅ ብስራት ኢቲቪ ጆሮ የለውም። “ብሄር ብሄረሰቦች” እኩልነትን የተጎናጸፉበትን ክብረ በአል በቀጥታ በማሰራጨት ስራ ተጠምዷል።
ብዙ ሺህ አስረኞች “ኦነግ ናችሁ” ተብለው በአመለካከታቸው ሳቢያ እየተሰቃዩ ነው። ቅንጅን በገንዘብ ደግፋችኋል የተባሉ ከስራና ከንግድ እንዲወጡ እየተደረገ ነው። በቀረጥና በእዳ ስም የተዘረሩና የቁም ሞት የሞቱ አሉ። ጠኔ የሚቆላቸው የበይ ተመልካቾች ችግር ከጓዳ አልፎ አደባባይ ውሏል። ሃሳብን በነጻ መግለጽ የሚቻል መስሏቸውና መብቱ የተፈጥሮም በመሆኑ የተናገሩ፣ የጻፉ፣ የተቹ፣ “አሸባሪ” ተብለው ተከርችመዋል። ስለ መብት መከበርና ስለ እምነት ነጻነት የሚጠይቁ በጋሪ የሚገፋ የክስ ፋይል ተከፍቶባቸው እስር ቤት እየተሰቃዩ ነው። እነዚህ ሁሉ ሰዎች በኢህአዴግ በራሱ ቋንቋ ብሔር የላቸውም? የህዝብ አካል አይደሉም? ይህ መሰረታዊ ችግር እያለ ከበሮ ይደለቃል። ለስርዓቱ የቀለም ማስዋቢያ እንዲሆን ከየብሄረሰብ የተውጣጡ አጊጠው ሲጨፍሩ ይስተዋላል። በብሄርም ደረጃ ወርደን እንነጋገር ከተባለ በተለይ አማራ ክልል ለወገኖቹ መሟገት ሲገባው ባህር ዳር ላይ አስረሽ ምቺው መጨፈሩ ያሳፍራል። ወገኑንና የሚምልለትን ህዝብ የማይሰበስብ ድርጅት!
መራገምና ማውገዝ ሰልችቶናል። የውግዘት መንገድ ለማንም እንደማይበጅ እናውቃለን። ውግዘት ለቀጣዩ ትውልድ መርዝ የመጋት ያህል መራር ውርስ ነው። ግን ምን እናድርግ? የምናመሰግነው አጣን። ማንን እናመስግን? እንዲሁ በቅዠትና በሚያደነቁር ፕሮፓጋንዳ ኖረን እንለፍ?
ዝናውም፣ ክብሩም፣ ሃብቱም፣ ሁሉም ያልፋል። ጊዜም ከጥላችን ይልቅ ይበራል። ደጎች ላገራቸው፣ ለቤተሰቦቻቸውና ለተተኪውትውልድ መልካም ነገር አስቀምጠው ሲያልፉ በበጎ ሲታወሱ ይኖራሉ። የክፉ ታሪክና ልምድ ማጣቀሻ ከመሆን ለአገርና ለወገንመልካም ስራ ሰርቶ ማለፍ ያኮራል” ከአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ድረገጽ ላይ የተወሰደ

No comments:

Post a Comment