Translate

Sunday, December 30, 2012

“[ሻዕቢያ] በየቀኑ እየሞተ ነው”


ፕሬዚዳንቱ ግን "በልማት" ተግባራት ተጠምጃለሁ ይላሉ

isayas afewerqi
ኤርትራ ከውጪና ከውስጥ ተዥጎርጉራለች። ከውጪ ደግሞ “በየቀኑ ትንሽ ትንሽ እየሞተች ነው፤ በቅርቡም የሚፈነዳ ነገር አለ” በሚል ግምት ከየአካባቢው እየተሰጠ ነው። ከውስጥ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የኢንቨስትመንት ጥያቄና ግብዣ ላይ ናቸው። የተበላሸባቸውን ዲፕሎማሲ ለማቃናት ላይ ታች እያሉ ነው።
“ኤርትራን በተመለከተ የሚወጡት መረጃዎች የችግሮቿን መወሳሰብና የፕሬዚዳንት ኢሳያስ እጣ ፈንታ መገባደጃው ላይ ለመድረሱ አመላካች ነው” የሚሉ ያሉትን ያህል “ኢሳያስ በውጪ ግንኙነታቸው ላይ የሰሩትን ስህተት በማረም ከበፊት ይልቅ አሁን ወደ ተሻለ መረጋጋትና የኢኮኖሚ ተሃድሶ ተሸጋግራለች” በሚል የሚከራከሩም አሉ። እንደውም ከህወሃት/ኢህአዴግ ይልቅ ሻዕቢያ ከስጋት የራቀ እንደሆነ አድርገው የሚከራከሩ አሉ።
በኤርትራ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ፣ መንግስት ከያዘው ሞኖፖሊ አስተሳሰብ እንደሚወጣና ቃል በመግባት ተወላጆቹንና ውጪ ባለሃብቶችን የሚወተውተው ሻዕቢያ “እየተንፈራገጠ ነው” በሚል ከመሸ የሚያደርገውን ጥረት ኑዛዜ አድርገው የሚመለከቱ አገሪቱ በለውጥ መብላላት ውስጥ እንደምትገኝ ነው የሚናገሩት። ይህንኑ የሚያጠናክር ዘገባ ቪኦኤ አሰምቶ ነበር።
ፈረንሳዊው የመገናኛ ብዙሃን ተመራማሪና ጋዜጠኛ ሊዮናል ቫንሶ ከምስራቅ አፍሪቃ የቪኦኤ ዘጋቢ ፒተር ሃይን ላየን ጋር ባካሄደው ጥያቄና መልስ ሊበጠስ የደረሰ የሚመስል ጉዳይ መድረሱን የሚያመላክት መረጃ አስተላልፏል። ስለ ኤርትራ መንግስት የተደራጀ መረጃ እንዳለው የሚያስታውቀው ጋዜጠኛ ቃለ መጠይቅ ያካሄደው “ተሰወሩ” የተባሉትን የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ አሊ አብዶን አስመልክቶ ነው።
አቶ አሊ ለህክምና ጀርመን እንደነበሩና በታህሳስ ወር አገራቸው መመለስ ሲገባቸው እስካሁን ኤርትራ እንዳልገቡ ከቅርብ የመረጃ ምንጩ ማረጋገጡን የገለጸው ጋዜጠኛ፤ አጋጣሚውን በ2006 ከተሰወሩት የኤርትራ የወጣቶች ንቅናቄ መሪና የቀድሞ የአቶ አሊ አለቃ ጋር አገናኝቶታል። ለጉብኝት ኢሲያ ከሄዱ በኋላ ሲመለሱ ኢሳያስ እንደሚያስሯቸው መረጃ ስለደረሳቸው አገራቸው አልገቡም። እስካሁን ያሉበት አይታወቅም።
አቶ አሊም አውሮፓ ስዊድንና ጀርመን ከመታየታቸው ውጪ የት እንዳሉ መረጃ ማግኘት እንዳልቻለ የጠቆመው ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ፣ የአቶ አሊን መሰወር “በየቀኑ ትንሽ ትንሽ እየሞተ ካለው መንግስት ራሳቸውን ማግለላቸው ይሆናል” ሲል ግምቱን ሰጥቷል። ፒተር ሃይን አቶ አሊ አገራቸውን የሚከዱ ሰው እንዳልሆኑና አሁን የት እንዳሉ ስለማወቁ ላቀረበው ጥያቄ “የት እንደሆኑ አናውቅም። የምናውቀው በተቀነባበረ ደረጃ መሰወራቸውን ነው” በሚል ፈረንሳዊው ተጠያቂ ጋዜጠኛ መልስ ሰጥቷል።
ጋዜጠኛ ሊዮናል የአቶ አሊን በተቀነባበረ ደረጃ መሰወር ተከትሎ ያሉትን መረጃዎች ሲያብራራ ሴት ልጃቸው የሳቸውን ዱካ ተከትላ ወደ ሱዳን ማምራቷን፣ ባለቤታቸው ከሁለት ወንድሞቻቸው ጋር ካናዳ የሚኖሩ መሆኑና አስመራ መኖሪያ ቤታቸው በደህንነት ሰዎች መከበቡን አቶ አሊ አገር ውስጥ እንደሌሉ ማረጋገጫ አድርጎ ያቀርባል። በማያያዝም ቤተሰቦቻቸውን ተለይተው ብቻቸውን አስመራ በመኖራቸው ደስተኛ እንዳልነበሩ ተናግሯል።
በኤርትራ ውስጥ የሚታየው ሁኔታ የተካረረ መሆኑንን ያመለከተው ጋዜጠኛ አቶ አሊ በፖለቲካና በግል ጉዳይ በተጠና መንገድ እንደ ተሰወሩ ግምቱን አስቀምጦ፣ “ነገሮች አንድ ቀን ይፈነዳሉ። መንግስትም በአንድ ሰው የመተዳደሩና የመመራቱ እድል ያከትማል” ብሏል።በኤርትራ በጀኔራሎችና በሲቪል ባለስልጣናት መካከል አለመተማመን መንገሱንም አመልክቷል። የቅርብ መረጃ እንዳለው የተናገረው ጋዜጠኛ አቶ አሊ “አገራቸውን ከዱ” እንደማይባል፣ “ከዱ” የሚባለው ካሉበት ሆነው መንግስታቸው የሚያካሂደውን በሙሉ እንደማያምኑበትና እንደማይቀበሉት በገሃድ ሲያስታውቁ ብቻ መሆኑንን እንደሆነ ተናግሯል።አቶ አሊን አስመልክቶ “የኢሳያስ ልጅ አይከዳም! አናምንም” በሚል በስደት የሚኖሩ የኤርትራ  ተወላጆችን በማነጋገር ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ መዘገቡ ይታወሳል።
አቶ አሊ ኢሳያስን ወደ ማምለክ የደረሱ፣ በሽፍትነት ዘመናቸው የሬዲዮ መገናኛቸውን የሚያንቀሳቅሱ ታማቸውና የአቶ ኢሳያስን በርካታ ምስጢር የሚያውቁ የስርዓቱ ተጠቃሚ ስለሆኑ አገር ከድተው እንደማይጠፉ አሁን ድረስ የሚከራከሩ አሉ። እነዚህ ክፍሎች ኢሳያስ ታመዋል የተባሉበትን ወቅትና የርሳቸውም ምላሽ ያስታውሳሉ።
በኤርትራ ያለውን የፕሬስ ነፃነት ለማመጣጠን ጁላይ 15/2009 ከኤርትራ በተሰደዱ ጋዜጠኞች የተቋቋመና በድንበር የለሽ ዘጋቢዎች (Reporters Without Borders) የሚታገዘው ኤሬና /ERENA/ ሬዲዮ በሚያዚያ (April) ወር 2012 በኤርትራ ጄኔራሎች አስቸኳይ ስብሰባ “ኤርትራ እንዴት ትቀጥል?” በሚል መምከራቸውን ከፈረንሳይ መዘገቡን ተከትሎ ኢሳያስ አበቃላቸው ተብሎ እንደነበር ይታወሳል።
በኢትዮጵያ የስደት መንግስት ያቋቋሙትን የኤርትራ መንግስት ተቃዋሚዎች ስብስብ “የኤርትራን ነፃ አገርነት አሳልፈው የሸጡ ከዳተኞች” በማለት የሚጠራው ይህ ሬዲዮ፣ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በጠና መታመማቸውን ተከትሎ “… ጄኔራሎቹ ቀጣዩን የኤርትራ ጉዳይ ‘አገራዊ መግባባት’ በሚሰፍንበት መልኩ ለማስቀጠል ይቻል ዘንድ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ መፈንቅለመንግሥት ለማካሄድ ሲያሴሩ ተደርሶባቸዋል በሚል በእስር ላይ ያሉት ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲፈቱ ወስኗል። የሞቱም ካሉ ለቤተሰቦቻቸው እንዲነገር ከስምምነት ላይ ተደርሷል” የሚል ዘገባ አቅርቦ ነበር።
በዛው ወር ቀለል ባለ አለባበስ ነጠላ ጫማ ተጫምተው በብቸኛዋ ኤሪ-ቲቪ (ERITV) ብቅ በማለት ነገሩን ሁሉ አፈር ያስገቡት አቶ ኢሳያስ ለተወራው ሁሉ መልስ መስጠት እንደሚያስቸግር በማስታወስ፣ በልማት ስራ ተጠምደው ከመክረማቸው ውጪ በጤናቸውም ሆነ በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ አንዳችም ነገር እንዳልተፈጠረ ተናግረው ነበር።
የልማት ስራዎችን ሲጎበኙ አስራ አራት ሰዓት ያህል ያለማቋረጥ ስለተጓዙ ረዥም እንቅልፍ መተኛታቸውን፣ እንቅልፉ ሳይለቃቸው ወደ ቢሮ ሲገቡ የፕሬስ ፀሃፊያቸው ከሰጠቻቸው ወረቀቶች ላይ ስለእርሳቸው ሲወራ የነበረውን  መመልከታቸውን ተናግረዋል። “ሞባይል የለኝም፤ ኢንተርኔትም አልጠቀምም” የሚሉት አቶ ኢሳያስ የተወራውን ሁሉ እንደንፋስ እንደሚቆጥሩት አስምረውበታል። ውሸት በተወራ ቁጥር ቴሌቪዥን ላይ በመውጣት ማስተባበያ መስጠት እንደማይቻል በመጠቆም የተወራባቸውን ክፉ ወሬ በማምከን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ “እኛ ተመስገን ብለን አስራ ሁለት ሰዓት ስንተኛ፣ ውሸታሞቹ ሃያ ሶስት ሰዓት ከሃምሳ ዘጠኝ ደቂቃ እንቅልፍ የላቸውም” ሲሉ ድምጻቸውና አድራሻቸው ሳይታወቅ ለከረሙበት ጊዜያት መልስ ሰጥተዋል። አሜሪካንና ሲ.አይ.ኤንም ወቅሰዋል።
የእርሳቸው መግለጫ እንዳበቃ፣ ኢሳያስ ከጠፉበት ብቅ ብለው ኢንተርቪው መስጠታቸውን ያላጤነው በህወሃት/ኢህአዴግ የሚደገፈውና ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ሰዓት ተጋርቶ ዝግጅት የሚያቀርበው ዳሃይ ኤርትራ በፕሮግራም የፕሬዚዳንት ኢሳያስን የጤና መጓደል በተመለከተ “አጋጣሚውን በመጠቀም አዲሲቷን ኤርትራ ለመመስረት እንነሳ” ሲል ለወታደሮችና ለህዝቡ ጥሪ አሰምቶ ነበር። እስካሁን ግን ምንም የለም።
ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ “አጉራ ዘለል፣ ተናካሽ ውሻ፣ አተራማሽ …” እያሉ የሚሰድቡትን የበረሃ ባለውለታቸውን ሻዕቢያን አስፈንጥረው እንደሚወረውሩት ለዓመታት መዛታቸው አይዘነጋም።

No comments:

Post a Comment