Translate

Friday, December 14, 2012

ሱዛን ራይስ የቤንጋዚው መዘዝ ሰለባ ሆኑ!

ራሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚ/ር እጩነት አገለሉ

susan rice
በቅርቡ በተጠናቀቀው የአሜሪካ ምርጫ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለሁለተኛ ጊዜ መመረጣቸውን ካረጋገጡ በኋላ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሱዛን ራይስ ሂላሪ ክሊንተንን እንደሚተኩ በሰፊው መነገር ተጀመረ፡፡ የፕሬዚዳንቱ ቀዳሚ እጩ መሆናቸው ብዙ ቢነገርላቸውም ከተቃዋሚዎቹ የሪፓብሊካንና ሌሎች ጉዳየኞች የተቃውሞ ድምጽ ለመስማት ግን ብዙም ጊዜ አልወሰደም፡፡
ክሪስቶፈር ስቲቨንስ
መስከረም 1፤ 2005ዓም በሊቢያ ቤንጋዚ ከተማ የአሜሪካ ቆንስላ እና አምባሳደር ላይ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ ሪፓብሊካኑ የመቃወሚያ ክሳቸውን ማሰማት ጀመሩ፡፡ በወቅቱ በደረሰው ጥቃት በሊቢያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ክሪስቶፈር ስቲቨንስ እና ሌሎች ሦስት አሜሪካውያን የቆንስላው ሠራተኞች ተገድለው ነበር፡፡
ግድያው ከተፈጸመ ጥቂት ቀናት በኋላ በአሜሪካ በሚገኙት አምስት ዋና ዋና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመቅረብ ድርጊቱ የአሸባሪዎች ጥቃት ሳይሆን በካሊፎርኒያ የተሠራ ጸረ-እስላማዊ ቪዲዮ ምክንያት የተጫረ ነው በማለት አምባሳደር ራይስ ለኦባማ አስተዳደር መከላከያ አቀረቡ፡፡ ምርጫ ሊካሄድ ሁለት ወር ሲቀር የተከሰተው ይህ ድርጊት የምርጫ ፉክክር ውስጥ ለነበረው የኦባማ አስተዳደር ከፍተኛ የፖለቲካ ኪሣራ እንደሚያመጣ የተገመተው አስቀድሞ ቢሆንም የአምባሳደሯ መከራከሪያ ሁኔታውን ሊያለዝብ ችሎ ነበር፡፡
ዴቪድ ፔትሬያስ ከውሽማቸው ጋር
ምርጫው በተጠናቀቀ ማግስት መረጃዎች እያፈተለኩ መውጣት ከመጀመራቸው አልፎ የቤንጋዚውን ጥቃት አስመልክቶ ለህግ መወሰኛው ም/ቤት ቃላቸውን ለመስጠት በዝግጅት ላይ የነበሩት የአሜሪካ የስለላ ድርጅት (ሲአይኤ) ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ፔትሬያስ ሥልጣናቸውን ለቀቁ፡፡ ለዚህም እንደምክንያት ያቀረቡት ከትዳራቸው ውጪ መማገጣቸው ሲሆን ሊሰጡ የነበረውም የምስክርነት ቃል ለጊዜው ተሰረዘ፡፡ በትዳር ላይ መማገጥ ከሃይማኖት ድርጅት አመራርነት እንጂ ከከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ሊያስለቅቅ አይችልም በማለት ውሳኔውን በአጽዕኖት የሚቃወሙ ወገኖች የዳይሬክተሩን መልቀቅ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡ በሌላ በኩል አምባሳደር ራይስ በአምስቱ ቴሌቪዥኖች ላይ ቀርበው የተናገሩትን ሁሉ ያገኙት ከአሜሪካን የስለላ መ/ቤት በተሰጣቸው መረጃ መሠረት መሆኑን በመጥቀስ የዳይሬክተሩን መልቀቅ ከአምባሳደሯ ንግግር ጋር ያገናኙታል፡፡
የዳይሬክተሩ ከትዳር ውጪ መማገጥ ከወራት አስቀድሞ በፌዴራሉ የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ዘንድ በግልጽ እየታወቀ ፕሬዚዳንታዊው ምርጫ በተጠናቀቀ ማግስት ይህንን ምክንያት በማድረግና በም/ቤቱ ዘንድ ቀርበው ቃላቸውን ከመስጠታቸው በፊት የቤንጋዚው ጥቃት ምስጢር እንዳይጋለጥ የኦባማ አስተዳደር የፖለቲካ ሚና ተጫውቷል በማለት ሪፓብሊካውያኑ ይከስሳሉ፡፡
የፖለቲካው ትኩሳት እየጋለ ሄዶ የዳይሬክተሩ መልቀቅ እንደተሰማም ሪፓብሊካን የም/ቤት ተወካዮች አምባሳደር ራይስን የቤንጋዚው ጥቃት ብቸኛ ተጠያቂ አደረጓቸው፡፡ ወዲያውም ፕሬዚዳንቱ አምባሳደሯን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አድርገው በቀዳሚ ዕጩ ተወዳዳሪነት ለማቅረብ አስበዋል የሚለው ዜና ለተቀናቃኞቹ የሪፓብሊካን አመራሮች ጣፋጭ ዜማ ሆነላቸው፡፡
በተጠናቀቀው ምርጫ ከፍተኛ ሽንፈት የተጎነጩት ሪፓብሊካኖች የፖለቲካ ጡንቻቸውን ማንቀሳቀስ በመጀመር የአምባሳደሯን ታሳቢ እጩነት በገሃድ መቃወም ያዙ፡፡ በግምባር ቀዳሚነትም ከአራት ዓመታት በፊት ለፕሬዚዳንትነት ተወዳድረው በኦባማ የተሸነፉት የአሪዞናው ጠቅላይ ግዛት ሴናተር ጆን ማኬይን እና የደቡብ ካሮላይናው ሊንድሲ ግራሃም የፖለቲካውን እንዝርት ማሾር ያዙ፡፡ የቤንጋዚውን ጥቃት አስመልክቶ አምባሳደሯ የኦባማ ምርጫ እንዳይደናቀፍ የፖለቲካ ሥራ ሰርተዋል፤ ምስጢር ደብቀዋል በማለት ወቀሳቸውን ተያያዙት፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን ዘመን ሱዛን ራይስ የአፍሪካ ጉዳይ ረዳት ጸሐፊ ሆነው በሰሩበት ወቅት የአፍሪካ አምባገነኖች ጋር ወዳጅ ናቸው በማለት በሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ እንዲሁም በኮንጎው እልቂት ተጠያቂ የሚያደርጓቸው የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች የአምባሳደሯን ታሳቢ እጩነት ተቃወሙ፡፡ ከቀድሞው ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ጋር የቀረበ የግል ግንኙነት እንደነበራቸው መንግሥታቸውን ወክለው በቀብራቸው ላይ የተናገሩት አምባሳደር ራይስ በአሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንም እጅግ ከፍተኛ ወቀሳና እንዳይመረጡ የተቃውሞ ቅስቀሳ እንዲሁም ህዝባዊ አቤቱታ (ፔቲሽን) ተካሂዶባቸዋል፡፡
የሪፓብሊካኑ ተቃውሞ እያየለ ሲሄድ አምባሳደር ራይስ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ዋንኛ የሕግ መወሰኛ ም/ቤት ከፍተኛ አመራሮችን ጋር በግል ውይይት አደረጉ፤ ጥቃቱ አስመልክቶ ስለተናገሩት አወዛጋቢ ንግግርም ይቅርታ ጠየቁ ፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማም የአምባሳደሯን ችሎታና ብቃት እያነሱ ድጋፋቸውን ሰጡ፡፡ የቤንጋዚውን ጉዳይ በተመለከተ ጥያቄ ያላቸው እኔን መገዳደር ይችላሉ በማለት ሱዛን ራይስን በይፋ ከተጠያቂነት ነጻ አወጡዋቸው፡፡ ሪፓብሊካውያኑ ግን በፍጹም አልተበገሩም፡፡ ከአምባሳደሯ ጋር የተናጠል ውይይት ካደረጉ በኋላም ወቀሳና ተቃውሟቸውን ያለዝባሉ ተብለው ሲጠበቁ በውይይቱ ስለቤንጋዚው ጥቃት “መልስ ከማግኘት ይልቅ የበለጠ ጥያቄ ተፈጥሮብናል” በማለት ሁኔታውን አወሳሰቡት፡፡ ሴናተር ማኬይንም አምባሳደር ራይስ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ከታጩ ሹመቱን የማጽደቅ ሂደት እንደሚያደናቅፉ ይፋ አደረጉ፡፡ በመቀጠልም አሁን በምክርቤቱ ካላቸው የጦር ኃይሎች ኮሚቴ አባልነት በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ አባል በመሆን የአምባሳደሯን የመመረጥ ሂደት እንደሚያደናቅፉ አስታወቁ፡፡
ሪፓብሊካኑ ተቃዋሚዎች ከአምባሳደር ራይስ ይልቅ በአሁኑ ጊዜ የምክርቤቱ የውጭ ጉዳይ ሰብሳቢ የሆኑትን የማሳቹሴትሱን ጠቅላይግዛት ሴናተር ጆን ኬሪ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት እንደሚደግፉ ቢገልጹም ዴሞክራቶች ግን ጉዳዩ ግልጽ የፓርቲ ፖለቲካ የታየበት ነው በማለት ባላንጣዎቻቸውን ይከስሳሉ፡፡ እንደምክንያትም አድርገው የሚያቀርቡት መከራከሪያ በማሳቹሴትስ የተካሄደውን የህግ መወሰኛ ም/ቤት ምርጫን ነው፡፡ ከጠቅላይ ግዛቱ ያሸነፉት የዴሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይ ኤልሳቤጥ ዋረን ሲሆኑ ጆን ኬሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሆኑ ከሕግ መወሰኛ አባልነት ስለሚለቅቁ በምትካቸው በኤልሣቤጥ የተሸነፉት የሪፓብሊካን ተወካይ ስካት ብራውን ወደ ሕግ መወሰኛ ም/ቤት በመምጣት በም/ቤቱ የሪፓብሊካኑን ቁጥር እንዲጨምር ለማድረግ የተጠቀሙበት ስልት ነው በማለት ዴሞክራቶች ምሬታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ከግራ ወደ ቀኝ ጆን ኬሪ፤ ሱዛን ራይስ እና ሒላሪ ክሊንተን
ለአንድ ወር በፈጀው በዚህ የፖለቲካ ንትርክ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተጫወቱት ሚናም ቀላል አይደለም፡፡ በተከታታይ የሚወጡ ጽሁፎችና የተቃውሞ ንግግሮች እንዲሁም አቤቱታዎች የፖለቲካውን አየር ሲያጨናንቁ ቆይተዋል፡፡ አምባሳደሯ ለፕሬዚዳንት ኦባማ በጻፉት ደብዳቤ ላይ በግልጽ እንደምክንያት ባይጠቅሱትም ራሳቸውን ከእጩነት ማግለላቸው እንደ ታላቅ ድል እንደሚታይ በብዙዎች ዘንድ አስተያየት ያሰጠ ነው፡፡
ሪፓብሊካውያኑ ከሚያነሱት የቤንጋዚው ወቀሳ በተጨማሪ አምባሳደር ራይስ ከካናዳ እስከ አሜሪካ ደቡብ ጠቅላይ ግዛት ቴክሳስ ድረስ እየተዘረጋ ባለው የኪይስቶን የነዳጅ ቧንቧ ድርጅት ውስጥ የላቀ ባለአክሲዮን ድርሻ ያላቸው መሆኑ ሌላ አጠያያቂ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡ እጅግ በርካታ ንትርክ እና ተቃውሞ እያስነሳ ያለው ይኸው ፕሮጀክት ከተፈጥሮ ጥበቃ፣ ከአካባቢ ጉዳይ፣ ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ፣ ከጂኦፖለቲካ፣ … ጉዳዮች አኳያ በብዙዎች ዘንድ ታላቅ ቁጣ ያስነሳ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲሁም ከኢራን ጋር ከፍተኛ ወዳጅነት ያለው የሼል ነዳጅ ኩባንያ ውስጥ አምባሳደሯ ያላቸው የአክሲዮኖች እና የኢንቨስትመንት ድርሻ ከላይ ከተጠቀሰው ፕሮጀክት ጋር ተዳምሮ አምባሳደሯ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ቢሆኑ ኢራንን አስመልክቶ አሜሪካ ልታስፈጽመው በምትፈልገው ፖሊሲ ላይ እንቅፋት የመፍጠሩ ጉዳይ ከቤንጋዚው ጥቃት በተጨማሪ ተጠቃሽ ምክንያት ነበር፡፡
አምባሳደሯ ሐሙስ ለፕሬዚዳንት ኦባማ በላኩት መልዕክት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ታሳቢ ዕጩ በመደረጋቸው ኦባማን አመስግነዋል፡፡ ሆኖም በርካታ ጉዳዮች በእንጥልጥል ባሉበት ባሁኑ ወቅት ከእርሳቸው ሹመት ጋር በተያያዘ የሚከሰተው የፖለቲካ አታካሮ ለማንም የሚጠቅም አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡ “ለሚኒስትርነት ብመረጥ” አሉ አምባሳደር ራይስ “ሹመቴን ለማጽደቅ የሚፈጀው ሂደት ረጅም፣ ብጥብጥ የሚያስነሳና እርስዎ ቅድሚያ ከሰጡዋቸው አገርዓቀፋዊና ዓለምአቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ በመግባት ብዙ ችግር የሚፈጥር እንደሚሆን አምኛለሁ” ብለዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሹመት በፍጹም የፖለቲካ መጠቀሚያ መሆን እንደሌለበት የጠቆሙት አምባሳደሯ ፕሬዚዳንት ኦባማ ለቦታው እርሳቸውን በእጩነት ታሳቢ በማድረጋቸው ታላቅ ክብር እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡ (የደብዳቤው ሙሉ ቃል እዚህ ላይ ይገኛል)
በሪፓብሊካውያኑ ከፍተኛ ጥቃት ሲደርስባቸው ቤተመንግሥቱ ለአምባሳደሯ ተገቢውን መከላከያ አላደረገም በማለት የሚከራከሩ በአምባሳደሯ ራሳቸውን ከታሳቢ እጩነት ማግለላቸውን ሲሰሙ ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ግን ውሳኔው የአምባሳደሯ የግል ነው በማለት የቤተመንግሥቱ ቃልአቀባዮች ቢናገሩም በቤንጋዚው ጉዳይ “አምባሳደሯ የመስዋዕት በግ” ተደርገዋል የሚለውን መከራከሪያ ግን በጭራሽ አይቀበሉም፡፡
በሌላ በኩል አሜሪካ በሰሜን አፍሪካ የአረብ ጸደይ በሚል የሙስሊም ወንድማማች የፖለቲካ እንቅስቃሴ እየደገፈች ትገኛለች በማለት የሚከሱ ወገኖች የቤንጋዚው ጥቃት መንግሥት የሚያውቀው ያደባባይ ምስጢር ነው በማለት ይከራከራሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ሟቹ አምባሳደር ዲፕሎማት የነበሩ ብቻ ሳይሆን የሲአይኤ ባልደረባም ናቸው፤ በቤንጋዚም የአሜሪካ ቆንስላ የሚባል መ/ቤት ሳይሆን የነበረው የሲአይኤ የድብቅ ኦፕሬሽን ማዕከል የሚካሄድበትና የጦር መሣሪያ ማስተላለፊያ ቦታ ነው ይላሉ፡፡ በመሆኑም የሊቢያን አማጺያን በመደገፍ እና በጦር መሣሪያ በማገዝ ጋዳፊን ከሥልጣን ለማውረድ አሜሪካ ከፍተኛ ሚና ከተጫወተች በኋላ ወደ ሊቢያ በገፍ የገባውን ጦር መሣሪያ አስቀድሞ ለታለመበት ዓላማ ለማዋል ወደ ሶሪያ በመላክ እና እዚያ የአማጺያንን ቡድን በመደገፍ የአሳድን አገዛዝ በመጣል በሙስሊም ወንድማማች አገዛዝ ለመተካት ከፍተኛ ኦፐሬሽን እየተካሄደ እንደነበር እነዚሁ ወገኖች ይጠቁማሉ፡፡ ሆኖም በወቅቱ ከሊቢያ ወደ ሶሪያ የሚደረገውን የጦር መሣሪያ ሽግግር የሚቃወሙትና የሶሪያ ወዳጅ የሆኑት ሩሲያና ኢራን በተለይ ለአሜሪካ ማስጠንቀቂያ ልከው ነበር፡፡ በተመሳሳይ ወቅት ሁኔታውን በስውር ይከታተሉና በስውር የስለላ ሥራ በቤንጋዚ ያከናውኑ የነበሩ የኢራን የቀይ ጨረቃ አባላት ሲአይኤ ደርሶባቸው በተያዙበት ወቅት ግለሰቦቹ ቆንስላ ጽ/ቤት ተብሎ በሚጠራው ቦታ ናቸው በሚል እነርሱን ለማስለቀቅ የተከፈተ ጥቃትና ለኦባማ አስተዳደርም ግልጽ መልዕክት ለማስተላለፍ የተከናወነ ድርጊት ነው በማለት እነዚሁ ወገኖች ያስረዳሉ፡፡ ለማስረጃም ሟቹ አምባሳደር በድብቅ የጦር መሣሪያ ማስተላለፉን ተግባር እያከናወኑ በነበረበት ወቅት ማዕከሉ በቆንስላነት ሳይሆን በመሣሪያ ማስተላለፊያነት እንደታወቀ ባይገልጹም ግድያው ከመፈጸሙ በፊት እርሳቸው ለጥቃት የተጋለጡ መሆናቸውን በመግለጽ አደጋ እንዳዣበበባቸው የኬብል መልዕክት ወደ ዋሽንግተን ማስተላለፋቸውን የእንግሊዙ Daily Mail መዘገቡን በዋቢነት ይጠቅሳሉ፡፡
የቤንጋዚው መዘዝ በሱዛን ራይስ ሰለባነት የሚጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን እየቆየ በርካታ ምስጢሮች የሚጋለጡበት እንደሚሆን ተንታኞች ይተነብያሉ፡፡ የአምባሳደሯ ውሳኔም የሽፍንፍኑ አንዱ ገጽታ እንደሆንም ይናገራሉ፡፡ ሱዛን ራይስም ሆነ ሌላ ግለሰብ በሚ/ር ቦታው ላይ ቢሾም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ እምብዛም እንዳልሆነ ባለፉት አስተዳደሮች የታየ ጉዳይ ነው፡፡ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በዚህ ረገድ ከፍተኛውን የመወሰንና ፖሊሲ የማውጣት ኃላፊነት የወደቀው በሕዝብ አንድ እምብዛም በማይታወቁት የሦስትዮሹ ኮሚሽን (trilateral commission) እና የውጭ ግንኙነት ምክርቤት (council on foreign relations) መሆኑን ከዚህ በፊት መዘገቡ ይታወሳል፡፡
አምባሳደር ራይስ መልቀቂያቸውን ካቀረቡ በኋላ በአሁኑ ጊዜ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቀዳሚ እጩ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሴናተር ጆን ኬሪ የሪፓብሊካኑ ግልጽ ድጋፍ የተሰጣቸው በመሆኑ በቀላሉ የሕግመወሰኛ ም/ቤቱን ድምጽ እንደሚያገኙ ተነግሯል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ግን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ማንን በእጩነት እንደሚያቀርቡ እስካሁን ይፋ አላደረጉም፡፡
 

No comments:

Post a Comment