ክፍል ሁለት (አሥራደው ከፈረንሳይ)
ከሁለት ወር በፊት “የለገደንቢ ወርቅ ሽያጭ ድራማ!! ወርቃችን እንዴት አላሙዲ እጅ ገባ?” በሚል ርዕስ ላቀረብነው ጽሁፍ የድረገጻችን የዘወትር ተሳታፊ አሥራደው ከፈረንሣይ “የአላሙዲ ኪስ በወርቅ ሲታጨቅ፤ አዶላ ኑሮ በጭንቅ!” በሚል ርዕስ የመጀመሪያውን ክፍል ጽሁፋቸውን አስነብበውን ነበር፡፡ በዚህ የክፍል ሁለት ጽሁፋቸው ደግሞ ባለፈው ያነሱትን ጉዳይ በመዳሰስ እንደሚከተለው አቅርበውታል፡፡
ወርቁ ካዶላ የሚያጌጥበት ሌላ!
በመጀመሪያው ክፍል መጣጥፌ፤ ቡችላው ማነው? ለምንስ ቡችላ ተባለ? በሚል ጥያቄ ነበር የተለየኋችሁ :: የወርቁ ቡችላ በምስሉ የሚያዩትን ይመስላል፤ ቡችላ የተባለበት ምክንያት ተለቅ ያለ የወርቅ ፍንካች በመሆኑ ነው::
እናም:
አዶላ ወርቅ ነው፤ አዶላ ማርና ወተት ነው፤ አዶላ የዱር አራዊትና አዕዋፍ በአንድላይ ሆነው የሚዘምሩበት፤ ዛፎች እጅ ለእጅ ተያይዘው በንፋስ አጃቢነት ጎንበስ ቀና እያሉ የሚሰግዱበት፤ ሰማይና ምድር መሳሳማቸውን ሳያበቁ በማለዳ፤ ጉሬዛዎች በዛፎች ላይ ሆነው ከወዲያ ወዲህ እየተንጠላጠሉ፤ በወፎች ዝማሬ ታጅበው፤ ከደኑ መሃል በሚፈልቀው ውብ የዕጣን ሽታ እየታጠኑ፤ ለፈጣሪያቸው ምስጋናውን በሽብሸባ የሚያቀርቡበት፤ ምድራዊ ገነት ነው::
አዶላ እንደሚወራው ምድራዊ ገሃነም አይደለም፤ ይልቁንም የገብስ ቆሎውን እያዘገነ፤ የገተሜ ጠጁን በብርሌ እያንቆረቆረ፤ በቆራሰማ የታጠነ ወተቱን እያስጎነጨ፤ እጅ የሚያስቆረጥም ክትፎውን በቆጮ ጠቅሎ እያጎረሰ፤ በአትክልትና ፍራፍሬው ሆድን እያንሸራሸረ፤ ለዛ ያላቸው ገጠመኞቹን በጆሮ እያንቆረቆረ የሚያስተናግድ ደግ ሕዝብና ምድር እንጂ!
አዶላ ፍቅር ነው፤ አንዱ ቢያጣ ከሌላው ተካፍሎ የሚበላበት፤ ሰው ለሰው የሚኖርበት፤ ሰው ሰው የሚሸት የሰው ልጆች ጠረን !
ደሞም አዶላ ተስፋ ነው፤ ዛሬ ቢያጡ ነገ ለማግኘት ተስፋ ሳይቆርጡ፤ የሕይወት ዑደቱ እንዳይቋረጥ፤ ዛሬን በነገ ተክቶ የወደፊቱን ሕይወት ለመኖር፤ የሚያልሙበት የተስፋ ምድር ::
አዶላ መሬቱ ዳቦ ነው ይገመጣል፤ ውሃው ጠበል ነው ይፈውሳል፤ አየሩ መንፈስ ነው፤ ሁሉንም በፍቅር ሰንሰለት የማስተሳሰር ሃይል ያለው!
አዶላ መሬቱ ዳቦ ነው ይገመጣል፤ ውሃው ጠበል ነው ይፈውሳል፤ አየሩ መንፈስ ነው፤ ሁሉንም በፍቅር ሰንሰለት የማስተሳሰር ሃይል ያለው!
አቦ የትም ተወለድ፤ ወርቅ ከእናት አገርህ ኢትዮጵያ ማሕጸን በምጥ የሚወለድበትን፤ የአዶላን ምድር ሳታይ ግን አትሙት!!
ሼክ አላሙዲ የአዶላን የተፈጥሮ ውበት ለማድነቅና ለመጠበቅ አልመጣም፤ በተቃራኒው ይህን ውብ የሆነ የተፈጥሮ ሃብት ለማውደም፤ ነዋሪዎቹን ከይዞታቸው በማፈናቀል ወርቅ ለማግበስበስና በመርዛማ ኬሚካሎች የአካባቢውን ውሃ ለመበከል እንጂ::
- ለመሆኑ ከአላሙዲ በስተጀርባ ያለውና የኢትዮጵያን ሕዝብ ሃብት እየዘረፈ የሚያዘርፈው ረጅሙ እጅ የማነው?
- የኢትዮጵያ ተማሪዎች «መሬት ለአራሹ» የሚል መፈክራቸውን አንግበው የፊውዳሉን ሥርዓት ሲታገሉ አላሙዲ የት ነበር ?
- በ17 አመታት የወታደር አስተዳደር ዘመን፤ ተማሪው፤ ገበሬውና ሠራተኛው በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ በጥይት ሲቆላ አላሙዲ የት ነበር ?
- በዘመነ ወያኔ አላሙዲ እንዴት ? በማን ? ለምን ? ተጎትቶ ወይም ሰተት ብሎ ሊገባ ቻለ ?
- የአዶላን የወርቅ ማዕድን ሁለት እግሮቹን አንፈራጦ እንዲይዝ በሩን ወለል አድርገው የከፈቱለት እነማን ናቸው ? ለምን ?
- አላሙዲ የጉጂ፤ የደራሳና ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል መተው ኑሯቸውን በአዶላ የወርቅ ፍለጋና በእርሻ ሥራ የተሰማሩ ወገኖቻችንን የማፈናቀል መብት ማን ሰጠው ?
ሕዝብ ለነዚህ ጥያቄዎች በአስቸኳይ መልስ ይፈልጋል፤ መልስ ሊሰጠውም የግድ ይላል !
«ጥቂት ቆሎ ይዘህ ከአሻሮ ተጠጋ » እንዲሉ፤
- አላሙዲ ዘፋኝ ሳይሆን ዘፋኞችን አጅቦ መድረክ ላይ ወጥቶ ሲኩነሰነስ፤ ምሥጢሩ ያልገባው ሕዝባችን አጨበጨበ፤ እሱ ግን ከመጋረጃው በስተጀርባ ሆኖ ሥራውን መሥራት ጀመረ ::
- አላሙዲ እስፖርተኛ ሳይሆን እስፖርተኞችን አጅቦ አብዶ (ፊንታ) በመሥራት ብዙ የከተማ መሬቶችና የሕዝብ ንብረት የነበሩ የማምረቻ መሥሪያ ቤቶችን ወደ ግል ንብረትነት ማዘዋወር ፕራቫታይዜሽን (privatization) በሚል ሸፍጥ: ዘርፎ በማዘረፊያ ስውር ጫረታ፤ ከንግድ ባንክ በወሰደው ብድር በሾኬ ጠልፎ በእጁ አስገባ፤ ብድሩም እስካሁን አልተከፈለም ::
- በቅርቡ ገበሬዎችን እያፈናቀለ መሬት አልባ በማድረግ ለም መሬት በርካሽ ሸመተ፤
- ከበፊቱ የሸፍጥ ስውር ጨረታ ተርፈው የነበሩ የሕዝብ የማምረቻ ድርጅቶችና፤ የእርሻ ማህበራት ድርጅቶችን፤ ሳንቲም ከኪሱ ሳያወጣ አሁንም ከንግድ ባንክ በተሰጠ ብድር አግበሰበሰ…ወዘተ
ላለው ይጨመርለታል ለሌለው ያቺው የሌለችው ትወሰድበታለች የምትለው አዲሷ የወያኔ ፈሊጥ ይሏችኋል ይቺ ናት !
የአላሙዲ እጅ ከአገርቤትም አልፎ እስከ አሜሪካን ድረስ በመሻገር፤ በአሜሪካን አገር በየዓመቱ የሚደረገውን የኢትዮጵያውያን የእስፖርት ውድድር ሳይቀር፤ ከአዶላ በሚዝቀው ወርቅ ዶላር መንዝሮ ጥቂት ሆድ አደሮችን በመግዛት ያደረገውን ጣልቃ ገብነት ያስታውሷል ::
አላሙዲ ከአዶላ በሚዘርፈው የወርቅ ሽያጭ፤ ለሆድ አደሮች ዶላር በመበተን፤ የአገር ወዳድ ዜጎችን የማሰብ ነፃነት ለማፈንና፤ የብዕሮቻችንን ልሳን ለመዝጋት፤ እንደማይተኛ ብናውቅም፤ የቆምንበት የማዕዘን ድንጋይ ሃቅ በመሆኑ ከዕምነታችን ንቅንቅ አያደርገንም::
ሕሊናችንን እያስራብን፤ ሆዳችንን ለመሙላት ስንል ብቻ፤ አገር የምንሸጥና በወገኖቻችን ዕንባ ገላችንን የምንታጠብ ከርሳሞች አይደለንም ::
አላሙዲ በብዙ ቶን ከሚዝቀው የአዶላ ወርቅ መሃል፤ በማንኪያ ቆንጥሮ፤ ጥቂት ዘፋኞችን፤ እስፖርተኞችንና ጋዜጠኞችን (ያውም ሊሞቱ ከተቃረቡ በኋላ) ፤ስሙን በዜና ማሰራጫዎች ለማስጠራት ሲል፤ አሳከምኩ ቢለን: ባይገርመን አይደንቀንም :: ፈረንጆች «L’arbre qui cache la foret» (አንዱ ዛፍ ደኑን ሙሉ ሸፈነው) እንዲሉ፤ ስውር ዘረፋውን ለመሸፈን የተጠቀመበት የተቀደደ የሱቲ ጨርቅ ነው ::
ለመሆኑ ሼክ አላሙዲ፤
- የኢትዮጵያ ሕዝብ ጤንነት አስጨንቆት፤ የትኛውን ሆስፒታልና ጤና ጣቢያ አሠራ?
- የኢትዮጵያ ሕዝብ ልጆች አለመማር አስቆጭቶት የትኛውን ት/ ቤት፤ የትኛውን ኮሌጅ፤ የትኛውን ዩኒቨርስቲ አሠርቶ የድሃ ልጆች እንዲማሩ አደረገ?
- እራሱና ሌሎች ድንበር ዘለል ከበርቴዎች ላፈናቀሏቸው ብዙ ወገኖቻችን የትኛውን የመጠለያ ጣሚያ አሠርቶ እንዲጠለሉ አደረገ?
- የአንድ አገር ትልቁ ሃብቷ ሕዝቧ መሆኑ እየታወቀ ወያኔ ሕፃናትን በጉዲፈቻ እያሳበበ ሲሸጥ፤ በመቆጨት አይሆንም ብሎ የትኛውን የሕፃናት መጠጊያ አሠራ?
- ወያኔ አደገኛ ቦዘኔ፤ እያለ ለሚሰድባቸው ወጣት የጎዳና ተዳዳሪ ወገኖቻችን የቱን መጠለያ ሠርቶ እንዲጠለሉ አደረገ ?
- ወያኔ ቤታቸውን እያፈረሰ ቀን ለሃሩር፤ ማታ ለብርድ፤ የዳረጋቸውን አዛውንት እናቶች፤ አባቶችና ሕፃናት መች ዞር ብሎ አያቸው ?
ይልቁንም ሕዝባችን ከአላሙዲ የተረፈው፤
- ለም የእርሻ መሬቶችን እየነጠቀ ገበሬዎችን ማፈናቀል
- የደን ምንጠራ፤ የአራዊትና የአእዋፍ ውድመት
- በመርዛማ ኬሚካል የአካባቢውን ውሃ መበከል
- የተዛባ የአየር ጠባይ ማስከተልና
- የወርቅ ዘረፋ ሲሆኑ:
ከዛሬ 5 እና 3 ዓመት በፊት የ1 ኪ.ግ. ወርቅ ዋጋ 14,000 እሮ ሲሆን ዛሬ የወርቅ ዋጋ በአስር እጥፍ ጨምሮ 1 ኪ.ግ. ወርቅ በ 140,000 እሮ ይሸጣል:: እንግዲህ አላሙዲ ከአዶላ የወርቅ ማዕድን በብዙ ቶን የሚቆጠር ወርቅ ስለሚዝቅ የዘረፋውን መጠን አስቡት!
ይህን ያህል መጠነ ሰፊ ዘረፋ ሲያካሂድ ለአካባቢው ሕዝብ:
- የትኛውን ሆስፒታልና ጤና ጣቢያ አሠራ?
- የትኛውን ት/ ቤት፤ ኮሊጅ፤ ዩኒቨርስቲ አሠርቶ የአካባቢው ልጆች እንዲማሩ አደረገ?
- እራሱ ላፈናቀላቸው ብዙ ወገኖቻችን የትኛውን የመጠለያ ጣሚያ ሠርቶ እንዲጠጉ አደረገ ?
- የትኛውን የንጹህ ውሃ መጠጥ መስመር ዘረጋ ?
- የትኞቹን ለአካባቢው መጣኝ የሆኑ መንገዶችን ሠራ ? …ወዘተ.
ተጠያቂነት የሌለበት የአዶላ ወርቅ የሚዘረፈውስ እስከመቼ ነው ?
አላሙዲ በወርቅ ሲያጌጥ፤ ለገዛ ወርቁ ባዳ የሆነው ጉጂ በመዳብ ያጌጣል! የማይደረገው ሁሉ የሚደረግበት ዘመነ ግርቢጥ !
ማስታወሻነቷ
ለክብረመንግሥት፤ ለኦዶ ሻኪሶ፤ ለቴፒ፤ ለመጋዶ፤ ለቦሬ፤ ለሃዲማ፤ ለኡላኡሎ፤ ለለገደንቢና በአካባቢው በኢትዮጵያዊነታቸው ኮርተው ለሚኖሩ ሕብረ ብሄር ወገኖቼ በሙሉ::
ለክብረመንግሥት፤ ለኦዶ ሻኪሶ፤ ለቴፒ፤ ለመጋዶ፤ ለቦሬ፤ ለሃዲማ፤ ለኡላኡሎ፤ ለለገደንቢና በአካባቢው በኢትዮጵያዊነታቸው ኮርተው ለሚኖሩ ሕብረ ብሄር ወገኖቼ በሙሉ::
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ! ኢትዮጵያ በተባበሩ ልጆቿ ክንድ ክብሯ ይመለሳል!!
No comments:
Post a Comment