በደል የረሳል ወይስ ይለመዳል ወገን?
አንዳንዶች ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል እድሜ ዘመናቸውን እንደጣሩ፣ እንደፈለጉ፣ እንደናፈቁ ሳይሳካላቸው ያልፋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ሌሎች ይህ ወረቃማ እድል ያለጊዜው እጃቸው ላይ ወድቆላቸው ያላግባብ ያለምንም ጥቅም ሲያሳልፉትና የወገንና የታሪክ ተጠያቂ ሲሆኑ እንመለከታለን። ከዚህም እጅግ በከፋ መልኩ ያገኙትን ሀገርንና ወገንን የመርዳት ወርቃማ እድል በተቃራኒው የሀገርን ሉአላዊነት ማስደፈሪያ፣ ወገንን ማስገረፊያ፣ ማሰቃያና ማሳደጂያ እንዲሁም ለራስ ምስል ግንባታ ብቻ በማዋል የሀገርም፣ የወገንም እንዲሁም የታሪክም ፍጹም ማፈሪያ ሆነው ሲያልፉ በተደጋጋሚ አስተውለናል።
በታላቁ መፅሐፍ መጽሐፈ አስቴር በምእራፍ 4 ቁጥር 13-14 አስቴር ስለምትባል አይሁዳዊት ሴት እንዲህ ተፅፏል መርዶክዮስም አክራቲዮስንሂድና ለአስቴር እንዲህ በላት አለው ”አንች በንጉስ ቤት ስለሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ ይልቅ እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ። በዚህ ጊዜ ቸል ብትይ እረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፣ አንቺና ያባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ ወደ መንግስት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደሆነ ማን ያውቃል?” ይህን ጥቅስ ስመለከት ላለፉት 21 ዓመታት የሀገራችን ቀዳማዊት እመቤት የነበረቺው አዜብ ጎላ ትዝ ትለኛለች ትውልዷ የዛሬ ቅኝቴ ከሆነው ከወልቃይት ጸገዴ ህዝብ ነውና። አሳዛኝ ግጥምጥሞሽ።
የዘሩት ሜዳ ሙሉ የሚያምር ፍሬ ያንዠረገገ ሰብል ከነማሳው በጠራራ ጸሐይ የተዘረፉ፣ እልፍኝ ካዳራሽ ቤታቸው ከነ ሙሉ ንብረቱ በህዝብ ፊት የተነጠቁ፣ የቤት እንሰሶቻቸው ከነ አይነቱ እነዲሁም ልጆች ወልጄ ኩየ ድሬ እኖርበታለሁ ሃብት ንብረት አፍርቼ አክብሬና ተከብሬ ለልጅ ልጆቼ አወርሰዋለሁ ካሉት ቀዬና ሸንተረር በግፍ በጉልበት በሃይል ተዋርደውና ተጎሳቁለው እንዲሰደዱ የተደረጉ ምስኪን ህዝቦች፤ የወልቃይትና ፀገዴ ወገኖቻችን። ሴቶቻቸው በወያኔ ኢህ አዴግ በተደራጀና በተቀነባበረ መልኩ የራሳቸውን መሰል ወንዶች ሳይሆን አገዛዙ የመረጠላቸውን ወንዶች እንዲያገቡ ሆን ተብሎ የግፍ ግፍ የተሰራባቸው፤ ከስር ከመሰረቱ ነቅለው እንዲወጡና የአካባቢ፣ የመሬት ባለቤትነት እንዳያነሱ ተስፋ መሬታቸውን፣ ትዝታ ቀያቸውን የተወረሱ አሳዛኝ ህዝቦች፤ የወልቃይታ ፀገዴ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን። ታዲያ ይህ ይረሳል ወይስ ይለመዳል?
ከላይ እንዳየነው በታላቁ መፅሃፍ የተጠቀሰችው አስቴር አይገቡ ገብታ እና ንጉስ ባለቤቷን አሳምና የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውን አይሁዳዊያን ወገኖቿን የቁርጥ ቀን ወገን ሁና ከሞት ስትታደጋቸው እናነባለን። ምስኪን የወልቃይትና የፀገዴ ህዝብ ግን ዘሩ ሲመክን፣ ሃብቱ ሲራቆት፣ ከቅየው በባዶ እጁ ሲባረርና ተመልሶ የይገባኛል ጥያቄ እንዳይጠይቅ ባገሩ ስደተኛና ለማኝ ሲሆን ወልዶ ያሳደጋትና የኔ የሚላት ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን እንደ አይሁዳዊቷ አስቴር በቤተ መንግስት ብትሆንም ወገኖቿን ለመርዳት ግን ጊዜ አላገኘችም። ውሃ የተራጨችባቸው የወልቃይት ወንዞች፣ ጭቃ አቡክታ የተሯሯጠችባቸው የፀገዴ ባድማዎች፣ አኩኩሉና ድብብዎሽ የተጫወተችባቸው የወልቃይት ፀገዴ ጫካዎች በግፍ ያለፍርድ ከታሪክ ምስክርነት ውጭ ወደ ታላቋ ትግራይ ሲካለልና ኗሪው ህዝብም አይሆኑ ሆኖ ሲባክን አዜብ ጎላ ግን ያለ ወገን የሚበላ፣ ያለ ዘመድ የሚደሰቱበት ያለ እህት ያለ ወንድም፣ ያለ አክስት ያለ አጎት የሚዝናኑበትን የቢዝነስ ኢምፓር እየገነባች ነበር። ታዲያ ይሄ እንዴት ይረሳል ወገን? እንዴትስ ይለመዳል?
ለወልቃይት ፀገዴ ህዝብ ተቆርቃሪና ደም መላሽ ወገን ከኛ ከኢትዮጵያዊያን ከወገኖቻቸው አለ። ጊዜው መቼም ይሁን መች ይህ በግፍ የተሰደደ ህዝብ ሃብቱን መሬቱን ሀገሩን ቅየውን ያገኛል። የተዋረደው ክብሩ የተንቋሸሸው ማንነቱ የተደፈረው እሱነቱ በወገኖቹ የማያቋርጥ ተጋድሎ ይመለሳል። ይህ ደግሞ አይቀርም። ወገኖቿ ሲሳደዱ ስትሳለቅ የነበረችው አዜብ ጎላ ግን የመከራ የስጋትና የጭንቀት ዘመኗ ጀምራል። ቤተመንግስቱን ለተመራጩ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ለማስረከብ ስታንገራግር የነበረውም ከዚሁ ፍርሃትና ጭንቀት የተነሳ እንደሆነ ይተወቃል። ምስኪን የወልቃይትና የጸገዴ ወገኖቻችን ባካል እንደተሳደዱ ሁሉ አዜብ ጎላ ዛሬ ኮሽታ የሚያስበረግጋት የራሷ ጥላ የሚያስደነብራት ድንጉጥና በመንፍስ ስደተኛ ሆናለች። በሰፈሩት ቁና መሰፈር ማለት ይህ ነው። ታዲያ ይህን ሁሉ የወገኖቻችንን ስቃይና መከራ ማን ይረሳል? እንዴትስ ተላምደን ልንኖር እንችላለን? ሁላችንም አንድ ሆነን የወያኔን ግብአተ መሬት ማፋጠን ይገባናል እንጂ።
No comments:
Post a Comment