(ፕ/ር መስፍን ወልደ-ማርያም)
ሶርያ አሮጌ አገር ነው፤ ታሪኩ ረጅም ነው፤ ከሶርያ ጋር ሲወዳደር አሜሪካ ሕጻን ነው፤ ነገር ግን ለብዙ ወራት በሶርያ ውስጥ የሚካሄደውን ጦርነትና በቅርቡ በአሜሪካ የተደረገውን ምርጫ ስንመለከትና ስናነጻጽራቸው፣ የሶርያ ሕዝብ እርስበርሱ ሲጨራረስ አሜሪካኖች በጥቂት ቀናት ውስጥ ሐዝቡ ድምጹን ሰጥቶ ምርጫው ተጠናቅቆ በሰላም የሥልጣን ርክክብ ተደረገ፤ ዕድሜ የመብሰል ምልክት ላይሆን እንደሚችልና ፍሬ-አልባ እንደሚሆን መረዳት እንችላለን፤ ከርሞ ጥጃ እየሆኑ ዕድሜ መቁጠር፤ በሶርያ የሚካሄደው ጦርነት ግን አንድ ሰው፣ በሺር አላሳድ፣ እስቲሞት ድረስ መጋደሉና አገር መፈራረሱ ይቀጥላል፤ ዓለምም፣ የተባበሩት መንግሥታትም፣ የአረብ ማኅበርም ሁሉም ከንፈሩን እየመጠጠ የሶርያን ሕዝብ ስቃይ ያያል፤ የፍልስጥኤማውያንንም ስቃይ እንዲሁ፡፡
ለምን አንዲህ ይሆናል? ምክንያቱ ሉዓላዊነት የሚባል ነገር ነው፤ ሉዓላዊነት ምን ማለት ነው? በመሠረቱ ሉዓላዊነት ሦስት ሀሳቦችን ያዘለ ይመስለኛል፤ አንዱ ሥልጣን ነው፤ ሁለተኛው ከበላዩ ሌላ ሥልጣንን የማይቀበል ነው፤ሦስተኛው አጥር ነው፤ በኋላ አንደምናየው ሥልጣንም፣ የበላይነትም አጥር አለው፤ ለወጉ ሉዓላዊነት ማለት ራስን ችሎ ከውጭ ድጋፍ ሳይፈልጉ መቆም ነው፤ ከውጭ ምንም ዓይነት የበላይ ሥልጣንን አለመቀበል ነው፤ በአገሮች መሀከል ተደጋግሞ የሚሰማው በራሳችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አትግቡብን እየተባለ መከላከያ የሚሰጠው ከሉዓላዊነት መሠረት በመነሣት ነው፤ በዚህ ዓይነት መልኩ ብዙ ጊዜ ሥራ ላይ ቢውልም በሉዓላዊነት ሀሳብ አጠቃቀም ላይ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ፡፡
ሉዓላዊነት የሚለው ሀሳብ ከሁለት በጣም ከተለያዩ መሠረቶች የሚነሣ ነው፤ በአንድ በኩል የሕዝብ ሉዓላዊነት አለ፤ በሌላ በኩል የአገዛዝ ሉዓላዊነት አለ፤ ሕዝብ የአገሩ ባለቤት በሆነበት፣ ሕዝብ በነጻነትና በሕጋዊ ሥርዓት በተካሄደ ምርጫ ተወካዮቹን ሰይሞ ራሱ የሚቆጣጠረውን መንግሥት ባቋቋመበት አገር ሉዓላዊነት ማለት የሕዝብ የሥልጣን የበላይነት ነው፤ ሉዓላዊ፣ የአገሩ ባለቤት፣ የአገሩ የበላይ ባለሥልጣን የሆነ ሕዝብ ማለት ነው፤ በአገሩ የበላይ ባለሥልጣን የሆነ ሕዝብ መንግሥት የሚባል ድርጅት ያቋቁምና ውክልና ይሰጠዋል፡፡
በአንጻሩ በአገዛዝ ስር ያለ ሕዝብ የአገሩ ባለቤት አይደለም፤ ሥልጣንም የለውም፤ የአገሩ ባለቤት ሆኖ ሙሉ ሥልጣንን የጨበጠው አገዛዙ ነው፤ ስለዚህም ሉዓላዊነት የሕዝቡ ሳይሆን የአገዛዙ ነው፤ ነገር ግን ከሕዝቡ የተለየ አገዛዝ የአገር ባለቤት ነው ማለት ለሰሚው ግራ ስለሚሆን የይስሙላ ምርጫ እየተደረገ አገዛዞች ሁሉ ሕዝቦቻቸውን እየረገጡ ለመግዛት (አንዳንዴም በ99.7 ከመቶ እያሸነፉ!) የሚረገጡትን ሕዝቦች ፈቃድ ያገኙ እያስመሰሉ ጡሩምባቸውን ይነፋሉ፤ የሚራብና የሚጠማ፣ የታረዘና የተጎሳቆለ፣ ከዓመት ዓመት በውጭ ምጽዋት የሚኖር፣ በየዕለቱ ግፍን የሚቀበል ሕዝብ ይህ ሁኔታ እንዲቀጥል ፈቃዱን ለአገዛዝ ሰጥቷል ብሎ የሚያምን አገዛዝ ብቻ ነው፡፡
ወደሶርያ ስንመለስ ሕዝቡ የአገሩ ባለቤት አይደለም፤ ስለዚህም ሕዝቡ ሉዓላዊነት የለውም፤ ሉዓላዊነቱን በጉልበት የጨበጠው አገዛዙ ነው፡፡
ዓለም በሙሉ፣ የተባበሩት መንግሥታትም ጭምር የሶርያን አገዛዝ ሉዓላዊ አድርገው ይመለከቱታል፤ እውነተኛው የሉዓላዊነት ባለቤት የሆነው የሶርያ ሕዝብ ሲደቆስ የሐዘን ስሜት ያድርባቸው እንደሆነ እንጂ ሕጋዊ አቅዋም ሊይዙና ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ይቸገራሉ፤ አይችሉም፤ ምክንያቱም የሶርያን ሕዝብ ሀብትና ጉልበት ለጊዜው የሚያዝዝበት አገዛዙ ነው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ለትክክለኛው የሉዓላዊነት ባለቤት፣ ለሕዝቡ እውቅና ለምን አይሰጥም? የቂል ጥያቄ ይመስላል፤ በተባበሩት መንግሥታት ውስጥ አብዛኛዎቹን ወንበሮች የያዙት አገዛዞች ናቸው፤ ስለዚህ አገዛዞቹ ለነሱ የተመቸውን ሁኔታ በመለወጥ ራሳቸውን የሚያሰናክሉበት ምክንያት ምን አለ? ይህ አንድ ምክንያት ነው፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የአሜሪካና የአውሮፓ ዴሞክራሲያዊ አገሮችም ቢሆኑ በሦስተኛ ዓለም አገሮች ውስጥ የእነሱን ጥቅም ለማራመድ የሚሻላቸው አገዛዝ ነው፤ በዴሞክራሲ አገር ውስጥ ብዙ ውጣ-ውረድና ልፋት ያጋጥማቸዋል፤ ነጻ ጋዜጦች የተለያዩ ሀሳቦችንንና አስተያየቶችን ያናፍሳሉ፤ ምሁራን የተለያዩ ጥናቶችን ለሕዝብ እያቀረቡ ያስተምራሉ፤ የፖሊቲካ ቡድኖች የተለያዩ አስተያየቶችን ለሕዝብ ያስጨብጣሉ፤ እንዲህ ያለው ሁኔታ ለአሜሪካና ለአውሮፓ አገሮች አይመቻቸውም፤ ለእነሱ ቀላል የሚሆንላቸውና የሚመቻቸው ከአንድ አምባ-ገነን ጋር ለብቻ ተነጋግረው የሚያጎርሱትን አጉርሰውት እነሱ በፈለጉት አቅጣጫ የሚዘውሩትን ነው፤ ስለዚህም ለሕዝብ ሉዓላዊነት ግድም የላቸው፤ በአውሮፓና በአሜሪካ የሚገኙት የሰብአዊና የዴሞክራሲ ድርጅቶች ከመንፈሳዊና ከሰብአዊ መሠረት ተነሥተው ጠንካራ ቢሆኑም የፖሊቲካውን ኃይል ሙሉ ለሙሉ መቋቋም አይችሉም፤ ይህ የሚሆነው አምባ-ገነኑ ጠግቦ ወይም በአጋጣሚ ከኃያል መንግሥት ጋር አስኪላተም ድረስ ነው፤ ያን ጊዜ ጉዳቱ ከጥቅሙ ስለሚያመዝን ፊቱን ያዞርበታል፤ በሙባረክ ላይ የደረሰው ይህ ነው፤ ሕዝቡ የጠላው አምባ-ገነን ለአሜሪካና ለአውሮፓም አይበጅም፤ የአምባ-ገነኑን ተፈላጊነት ለማስመስከር ሲሞት ሕዝቡ እንዲያለቅስ ይደረጋል፡፡
ሦስተኛም ምክንያት አለ፤ እንደሩስያና ቻይና ያሉ ኃያላን የሆኑት አገዛዞች ትንሽ ትንሽ እያጎረሱ በንግድ በኩል የሚያገኙትን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚመሳሰሏቸውን አገዛዞች ይደግፋሉ፤ ለዚህ ነው ሩስያና ቻይና የአል በሺርን ግፍ ዓይናቸውን ጨፍነው የሚደግፉት፤ እነሱም ቢሆኑ ምጥጥ ከአደረጉት በኋላ የሚጋጥ ነገር ሲጠፋ ወዳጅነታቸውም አብሮ ይጠፋል፡፡
ዓለም-አቀፍ ሕግ እውነተኛውንና በሕዝብ ሥልጣን ላይ የቆመውን ሉዓላዊነት ከመደገፍ ይልቅ ባለጉልበቱን አገዛዝ መደገፍ ይቀናዋል፤ ለዚህ ነው የሰብአዊ መብቶችን በመርገጥ ስማቸው የገነነ አገዛዞች እንኳን በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ውስጥ አባል ሆነው የሚመረጡት፤ አንዱ ምክንያት እንደተገለጸው የተባበሩት መንግሥታት በአብዛኛው የአገዛዞች ስብስብ ስለሆነ ወር-ተራ እየገቡ በመረዳዳታቸው ነው፤ ሌላው ምክንያት ምናልባት ከስብሰባዎቹ ይማሩ ይሆናል የሚል አጉል ተስፋ ነው፡፡
ሉዓላዊነትን የምናይበት ሌላ መንገድም አለ፤ ሕዝብ ሉዓላዊ ነው ስንል ምን ማለታችን ነው? ሕዝብ ማለት እያንዳንዱ ዜጋ በእኩልነት ቆሞ የሚታይበት ስብስብ ነው፤ሰው በዜግነቱ ሰውነቱን አያጣም፤ ሰውነቱ የተፈጥሮ ሲሆን ዜግነቱ በሕግ የተከለለ ነው፤ ዜጋ ማለት በሕግ የታጠረ ሰው ነው፤ ግለሰብ የምንለው ነጠላው ሰው ሰውም ነው ዜጋም ነው፤ ስለዚህም ለአንድ አገርም ሆነ ለአንድ ሕዝብ የሉዓላዊነቱ መሠረት እያንዳንዱ ዜጋ ነው፤ ከሉዓላዊነት ተነሥተን ወደሰውነት ደረጃ ስንገባ (ሰዎችን ሁሉ እኩል አድርገን) እያንዳንዱ ሰው ሰብአዊ መብቶች አሉት፤ እነዚህ መብቶች የሰው ልጆችን ሁሉ በአንድ ላይ ይዘው በሰውነት የታጠሩ ናቸው፤ ቀጥለን ወደአገር ደረጃ ስንወርድ ደግሞ ሰብአዊ መብቶች ዜጎችን ሁሉ በእኩልነት ይዘው በዜግነት የታጠሩ ይሆናሉ፤ በሰውነት ደረጃ በሰዎች መሀከል ልዩነት የለም፤ በዜግነት ደረጃም በዜጎች መሀከል ልዩነት የለም፡፡
ወደሶርያ ጉዳይ ስንመለስ ተጽእኖ ለማድረግ የሚችለው የዓለም-አቀፍ ማኅበረሰብ ሶርያን የሚመለከተው በሰውነት ደረጃም ሆነ በዜግነት ደረጃ አይደለም፤በጥቅም መለኪያ ነው፤ ለዚህ ነው የሶርያ ሕዝብም ሆነ የፍልስጥኤማውያን ሕይወት ዋጋ-ቢስ የሆነው፤ ለዚህ ነው በአገሩ ውስጥ የባለቤትነት መብት የሌለው ግለሰብ በሕዝብነት ወይም በዜግነት ደረጃ ውስጥ ሲገባ ገለባ የሚሆነው፤ ለገለባ ማንም ግድ የለው፡፡
ሰብአዊ መብቶች ተጣሱ ወይም ተረገጡ የሚባለው በግለሰብ ደረጃ ያለውን አጥር፣ በዜግነት ደረጃ ያለውን አጥር፣ በሰውነት ደረጃ ያለውን አጥር የሚያፈርስ ለሕግ ግድ የሌለው ጉልበተኛ ሲነሣ ነው፤ ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ!
No comments:
Post a Comment