ከ ተስፋዬ ዘነበ (ኖረዌይ በርገን) 07.12.2012
Ethiocenter.bolgspot.no
ምንም የፖለቲካ ፐሮግራም ሳያስፈልገው በየትኛውም ሁኔታ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በ ኢትዮጲያችን ቢደረግ የወያኔ ስርዓት እንደሚያበቃለት ህዝብም ሆነ እራሳቸው የስርዓቱ ሰዎች ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ስለሆነም ነው ላለፉት ሃያ አንድ አመታት ይህ አምባገነን ስርዓት እራሱ ያፀደቀውን ህገ-መንግስት ለአገዛዝ በሚመቸው መልኩ እየቀያየረ ላፀደቀው ህግ ሳይገዛ የህዝብን በነፃነት የመኖር መብት ቀምቶ ያሻውን የሚያደርገው፡፡
በእርግጥ የስርዓቱ ተፈጥሮአዊ ባህሪ፣ እንዲሁም ከጫካ የወጣ አውሬያዊ ስብህናቸው ለህግና ለስርዓት ቁብ እንዲኖራቸው ባያደርግም፣ በተጨማሪ ደግሞ በስልጣን ዘመናቸው ከህዝብ ነጥቀው ያካበቱትን ገደብ የለሽ ሃብትና ንብረት ለማስጠበቅ በስልጣን መቆየት የውዴታ ግዴታቸው አርገውታል፡፡
የሚገርመው ሟቹ አምባገነን መለስ ዜናዊ ህግን ሲጥስ በህግ እየሻረ፣ ነገ ሊያደረግ ላሰበው ነገር ዛሬ ጀሌዎቹን የፓርላማ ሰዎች በአስቸኳይ ስብሰባ አዲስ ህግ እያፀደቀ ሲያሻው ሲያስር፣ ሲያሻው ሲገድልና አገር ሲሸጥ በተመቸው መንገድ ህግን እየለዋወጠ ነበር፡፡
ይህንን እንድል ያነሳሳኝ መሰረታዊ ጉዳይ መሪውን ያጣው ስርዓት ከህግ ከለላ (ከህገ-መንግስቱ) ውጪ የአዲሱ የይስሙላ ጠ/ሚንስትር የሃይለማርያም ደሳለኝ ሹመት ከመፅደቁ በፊት ህውሃት አንድም ሃይሉን፣ ጉልበቱን ለህዝብ ለማሳየትና በፍርሃት ለመሸበብ አልያም እራሱ ህልውናዬ አደጋ ላይ ነው ብሎ በመስጋት ቀደም ሲል ሟች ያደርግ እንደ ነበረው ህግን በህግ ሳይሽር ወይም ሳያሻሸል 37 ለሚሆኑ የስርዓቱ ወታደሮች በአብዛኛው ከትግራይ ለሆኑ የማህረግ እደገት ሰጥቶ ጉድ አሰባለን፡፡
ለነገሩ ሰውዬው ማለት አዲሱ ጠቅላያችን መኖር አለመኖራቸው ህውሃት የፈለገውን ከማድረግ እንደማያግደው ቀድመው የተረዱ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ምክንያቱም የሰውየው የመወሰን አቅም ማጣትና ከአቅም በታች መሆን ለህውሃት ሰዎች የልብ ልብ ስለሰጣቸው በየትኛውም አጋጣሚ የሳቸውን ፈቃድ ሳይጠይቁ የይስሙላ ስልጣን ዋጋ ቢስነት የሚያሳዩ ተገባራት በቅርብ ሹማምንት እየተከናወኑ ነው ፡፡
የሚገርመው በህውሃት የተፈጠረውን መከፋፈል በሚያሳይ መልኩ ከዚህ በፊት ከሆነው በተለየ እነ አቶ ስብሃት ነጋ እንኳን ከታጋይነታቸው ባለፈ በአሁኑ ወቅት ይህ ነው የሚባል የፖለቲካ ስልጣን ባይኖራቸውም በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ በአመለካከትም ሆነ በእውቀት ከነሱ እረጅም እርቆ ለሄደው ህዝብ ውሃ የማይቋጥር ተራ ዲሰኩር ያሰሙ የነበረው አለቃቸው ከሞተ በሗላ ነው፡፡ እንዲሁም አለቃው ከሞተ በሗላ አለ! ይመጣል! እያለ ከአንዴም ሁለቴ አስከሬን ታቅፎ ስለመለስ ህያውነት ሲሰብክ የነበረው በረከት ስምኦን አዲሱን ጠቅላይ ሚንስትር ከቁብ ሳይቆጥር ባልተለመደ ሁኔታ እጁን አርዝሞ በተለያዩ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ከፊት በመሆን ለመታየት የሚያደርገው ጥረት ከዚህ በፊት ከነበረው በእጅጉ የገዘፈ ነው፡፡ ሁሉም በየፊናቸው አቅማቸውን ለማሳየት በህዝብ ላይ የሚያደርሱት በደል ኢትዮጲያንና ኢትዮጲያዊነትን ከጫማቸው በታች አድርገው የሚፈነጩብን በእውቀት ሳይሆን በግምትና በጉልበት ሃገራችንን በማን አለብኝነት እየመሩ የሉ ሽፍቶች እንደሆኑ ያሳያል፡፡
እንዲሁም ከባለቤቷ ሞት በሗላ በህውሃት ውስጥ የተፈጠረው ክፍፍልና አለመግባባት ከጫወታ ውጪ ያረገኛል ብላ የፈራችው አሮጌዋ ቀዳማዊ እመቤት አዜብ መስፍን እንደሌሎቹ የቀድሞ ሎሌዎቿ እሷም ተቀባይነት ለማግኘት ኢትዮጲያን የምታክል ሃገር ሲያስተዳድር የነበረው ባለቤቷ ከሌላው ህዝብ በተለየ ለትግራይ ህዝብ በመጨነቅ እሱ በሚስጥር ለአምስት አመታት ያህል ትግራይን የእንደስትሪ ማህከል ለማድረግ የቀረፀውን እቅድ ይፋ ያረገችው፣ አንድም በተቀረው ህዝብ ላይ ካላት የመረረ ጥላቻና ንቀት ምን ያመጣሉ በሚል ሲሆን፣ ሌላው ግን በዚህ ወንጀለኛ ብድን ውስጥ ያላትን ተሰሚነትና ሃላፊነት ለማሳወቅ ብሎም ከትግራይ ህዝብ ይሁንታን ለማግኘት የተጠቀመችበት አንዱ መንገድ ነው፡፡
በመሰረቱ አቶ ሃ/ማሪያም ደሳለኝ በይፋ ሰልጣን ከያዙ በሗላ በተለያዩ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ ከፍተኛ ክፍፍል መፈጠሩን ከተለያዩ የዜና ምንጮች ስንሰማ ከርመናል፡፡ ወያኔ ለአለፉት ሃያ አንድ አመታት የሄደበትን የዘር ፖለቲካ ያዋጣናል ብለው ሲያጎበድዱና መለስና ስርዓቱን ተሸክመው እዚህ ያደረሱት አባል ድርጅቶች በአዲሱ የመንግስት ሹመት ተገቢውን ኮታ አለገኘንም በማለት እርስ በእርሳቸው ሲታመሱ ከረመዋል፡፡ ይህችን ታላቅ ሃገርና ህዝብ በአንድነት እንደ አንድ ሊመራት የሚችለውን የቀደመ ታሪካችንን አኮስምኖ ለዛሬው ውጥንቅጡ ለጠፋው ማንነታችን የዳረገን ይህ እኩይ ስርዓት በዘረጋው የዘር መረብ ተጠልፎ ከርሰ መቃብር ሳይገባ ይህው በታሪካችን ያላየነው ኮታ ለማሟላት ሲባል፣ በዛውም ተዳክሞ የነበረውን ህውሃት እንዲያገግም ለማድረግ ከሃገሪቱ ህገ/መንግስት ውጪ ሁለት ተጨማሪ ምክትል ጠ/ሚንስትሮችን እኝሁ የህውሃት ሎሌ በሆኑት ጠ/ሚንስትር ተመርጠዋል፡፡
እዚህ ላይ በሶስት ም/ጠ/ሚንስትርሮች ሃገሪቱ መመራቷ ብቻ ሳይሆን አስብቶና አስልቶ ከወደቀበት በአፍታ የተነሳው ህውሃት በአንድ ሃገር ውስጥ በጣም አስፈላጊና መሰረታዊ ናቸው የሚባሉ የሚንስትር ቦታዎችን ሁሉ ለራሳቸው አድርግው ተቀራምተውታል፡፡
በሆነ ወቅት አቶ ስዩም መሰፍን ከውጪ ጉዳይ ሚንስትርነት ቢለቁ ከአማራና ከኦሮሞ ለዚህ ቦታ የሚመጥን ሰው የለም ብሎ ነበር ይባላል ሟቹ መለስ፡፡ በዚህ መንደርደሪያ መሰረት የህውሃትንም አቅም ለመገነባት ወደፊት በስልጣን ላይ የመቆየት ፍላጎትንም ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም በአስተማማኝ ሁኔታ በዚች ሃገርና ህዝብ ላይ ለመንገስ አሁኑኑ የመሰረት ድንጋይ ጥለዋል፡፡
በአጠቃላይ ይህ ከህገ-መንግስት ውጪ የተደረው የሚንስትሮች ምርጫ ለሞተው ህውሃት ነብስ ለመዝራት የታሰበ ህገ-ወጥ ሹመት ከመሆኑም በተጨማሪ አይን ያወጣና ፍፁም ተቀበይነት የሌለው የስልጣን ክፍፍል እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
ስለሆነም እነሱ ከህግ ውጪ አቅማቸውን ለማጎልበትና ለማንሰራራት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በመቃወምና በአቋም መግለጫ ብቻ ልንገታቸው እንደማንቸል አውቀን በአንድነት በባርነት አረንቋ ለሚመቅቀው ወገናችን እንድረስለት፡፡
ድል ለኢትዮጲያ ህዝብ ሞት ለወያኔ
http://www.ecadforum.com/Amharic/archives/4984
No comments:
Post a Comment