Translate

Friday, December 7, 2012

ከዚህ በሁዋላ ለወያኔ ተጨማሪ ዕድሜ ከተሰጠው፣ ከወያኔ በላይ ወንጀለኛ የሚሆነው ተቃዋሚው ነው


ከዚህ በሁዋላ ለወያኔ ተጨማሪ ዕድሜ ከተሰጠው፣ ከወያኔ በላይ ወንጀለኛ የሚሆነው ተቃዋሚው ነው


(ከመኮንን ተድላ)

የወያኔ ጥንካሬ፣ ዓላማው፣ አደረጃጀቱ፣ ያሰባሰበው የሰው ኃይል ወይም የነደፈው ፖሊሲ አይደለም። የጥንካሬው መሠረቱና ምንጩ ወየኔ ጠንካራ ተቃዋሚ የሌለው ዕድለኛ ቡድን መኆኑ ነው፡፡ የሕወሓት ጥንካሬ ሌላ ምንም ሳይሆን፣ የተቃዋሚው ሁለንተናዊ ድክመት ነው። የተቃዋሚው ድክመት መሠረትና ምንጩ ደግሞ፣ የተበታተነና እንኩዋን አብሮ ለመሥራትና ለመኖር የጋራ ጠላቱ በሆነው ወያኔ ላይ አንድ ዓይነት አመለካከት መቅረጽ ያልቻለ መኆኑ ነው። ይህም በመሆኑ፣ የተቃዋሚው ሁለንተናዊ ድክመት፣ ለወያኔ ዙሪያገብ ጥንካሬ ሰጥቶት ይገኛል።

 ይህ የተቃዋሚ ሁለንተናዊ ድክመት፣ ወያኔ ያላንዳች ሀሳብ፣ ምን ይመጣብኛል ሳይል፣ ተንጋሎ ተኝቶ 21 ዓመት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን እንዲያጠፋ ሠፊ ዕድል ሰጠው። የመለስ ዜናዊ ሕልፈተ ሞት ያስከተለው የሥልጣን ባለቤትነት ክፍተት በተቃዋሚ ወገን መካከል ያለውን ድክመት አጉልቶ አሳይቱዋል። በመሆኑም የመለስ ሕልፈትን ተከትሎ በወያኔ/ኢሕአዴግ መካከል ሠፊ ልዩነት ተፈጥሮ፣ ሥልጣን የምታርፍበት ቦታ አጥታ፣ በአውላላ ሜዳ ላይ በቆመችበት ወቅት፣ እኔ አለሁ የሚላት ተቃዋሚ ወገን ጠፍቶ፣ ይኸውና በመለስ የሙት መንፈስ አገርና ሕዝብ ይገዛል።

አገርና ሕዝብ በሙት መንፈስ የመገዛቱ መንስዔ ደግም የወያኔን ጥንካሬ ሳይሆን፣ የተቃዋሚውን ድክመት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ሕግ የሚጥስ፣ ዜጎቹን በኃይል የሚገዛ፣ በሀሳብ ሳይሆን በኃይል የሚያምንና የሚመካ አገዛዝ የደካማ መንግሥት ዋነኛ መገለጫ ባሕሪይ ነው። ይህም በመሆኑ፣ ሰሞኑን ወያኔ የራሱን ሕገ-መንግሥት ጥሶ፣ ሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ለመሾም የተገደደው፣ በኢሕአዴግ አባል ድርጅች መካከል የዓላማ አንድነት የሌላቸውና ከመካከላቸው አንዳቸውም ሌሎቹን ሊቆጣጠር ወይም ሊገዛ የሚችል ሀሳብ ወይም ኃይል የሌላቸው መሆኑን አመልካች ነው። ድርጊቱ ልዩነታቸው መሥፋቱን፣ በብላጣብልጥነት፣ በውሸት፣ በቅጥፈት እንዲያም ሲል በግሉ ባሰለፈው መቺ ፈዳይን ኃይል እየመታ ቛጥሮ ይዞ ይገዛቸው የነበረው መለስ በድንገት ሲያሸልብ የቀሩት ነገሮች ሁሉ ውል የጠፋበት ልቃቂት ሆነባቸው። በሌላም በኩል አባል ድርጅቶቹ፣ በመለስ አማካኝነት በሕወሓት ይፈጸምባቸው የነበረው ሁለንተናዊ ጫናና ንቀት፣አሳንሶና አዋርዶ ተከታይ የማድረግ ግፍ፣ ከመለስ ሞት በሁዋላ በነበረው መልኩ ለመቀጠል አለመፈለጋቸውን፣ ሕወሓትም ባለፈው መንገድ ለመቀጠል አለመቻሉን የሚያሳይ ነው። ይህም የሥላጣን አቻነት ወይም ጉቢነት የተፈጠረ መሆኑን ሲያሳይ፣ በአንፃሩ፣ የሕጋዊነትም ሆነ የዲሞክራሲያዊነት ባሕሪይ የሌለው መተካካት የሚሉት የአባትን ለልጅ የማውረስ ትልም፣ ወያኔ ከሚጠብቀውና መሆን ከሚፈልገው ውጭ ብቻ ሳይሆን፣ ባላሰቡትና ባልጠበቁት ሁኔታ የሀሳቡ አፍላቂ የፊታውራሪ መለስ ከዚህች ዓለም መሰናበት፣ የመተካካቱን ሂደት የጨለማ ጉዞ እንዳደረገባቸው በግልጥጽ ይታያል። ይህም የፖለቲካ ሥላጣኑን ሳይወዱ በሁኔታዎች አስገዳጅነት፣ ከትግሬ ወደ ወላይታ በማሸጋገሩ፣ ዕውነተኛ ሥልጣን በትግሬ እጅ ሆኖ የምስል ሥልጣኑ በወላይታው ደሳለኝ ኃይለማርያም እጅ እንዲሆን የሚያደርግ ቀመር መቀመር ግድ ብሉዋቸዋል። በዚህ ቀመር አቶ ደሳለኝ የምስል ጥጃ ነው። ምስሉ ጥጃ ወተት እንደማይጠባ ሁሉ፣ ደሳለኝም የስልጣኑ ተጠቃሚ አይደለም። ላሚቱ ወተቱዋን የምትሰጠው ላላቢዋ እንደሆነ ሁሉ፣ አሁንም ኢትዮጵያን ሚያልባት ትግሬውደብረጽዮን ነው። ሕገ-መንግሥቱን በመጣስ ሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች በድርጅቶች ስም ማስያዝ በግልጽ የሚሰጠን ሥዕል፣ የዕውነተኛ ሥልጣኑን ዛብ የጨበጠው ደብረጽዮን መኆኑንና የቀሩት እንደተለመደው እንዲያጨበጭቡ ለማድረግ መሆኑን የተሰጣቸው ኃላፊነት አፍ አውጥቶ ይናገራል። የሕገ-መንግሥቱ መጣስ፣ ወያኔ ለአሽከርነት ያደራጃቸው የጎሳ ድርጅቶች አፋዊም ቢሆን፣ ባርነቱን ያወቀ ባሪያ ግማሽ ባሪያ ነው እንዲሉ፣ እኛም ሥልጣን ያምረናል ብለው ምንቸቱን ሳይሆን፣ ወጥንጨቱን ለመላስ መሞከራቸው የወያኔን መከፋፈል የሚያመለክት ዕውነታ መሆኑ መያዝ ያለበት ጉዳይ ነው። በነዚህ ነባራዊ ሁኔታዎች ተጠቅሞ፣ ተቃዋሚው ወገን፣ ከየግል ማዕቀፉ ወጥቶ፣ ለወል በሚበጅ ገዥ ሀሳብ ዙሪያ ተሰባስቦ ማረፊያ ለምትፈልገው ሥልጣን መቅደስ መሆን ካልቻለ፣ ከወያኔ በበለጠ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ዋና ጠላትና ወንጀለኛ ሆኖ በትውልድ የሚቆጠረው ተቃዋሚው ወገን እንደሚሆን መጠራጠር አይቻልም።


    No comments:

    Post a Comment