ሕገ መንግስቱና ምርጫ ቦርድ እያነቡ እስክስታ (ተቃዋሚ ፓርቲዎች)
በዚህ ዓመት ሊከናወን በእቅድ የተያዘው የአካባቢና የአዲስ አበባ ምርጫ በሚያዚያ ወር 2005 ዓ.ም እንደሚካሄድ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቷል፡፡ ምርጫ ቦርድ እንደተለመደው ነጻ፣ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ተአማኝነት ያለው ምርጫ እንዲሚካሄድ አረጋግጧል፡፡ ምርጫ ቦርድ ነጻ፣ ግልጽና ተአማኒነት ያለው ሲል ከየትኛው የምርጫ መመዘኛና መስፈርት ተነስቶ እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡ ያው እንደተለመደው በውዝግብ ተጀምሮ በውዝግብ የሚጠናቀቀውን ዓይነቱን ምርጫ መሆኑ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም እንደታየው ሚዛናዊ የሆነ ውድድር ማድረግ ባለመቻሉ ምክንያት ውጥረት ውስጥ የወደቀው የመድብለ ፓርቲ ምርጫ ስርዓታችን በመቀጠል ፍጹም እንዳይዳፈንና በአንጻራዊነትም ቢሆን ሚዛናዊነቱን ሳይስት ከቅርጫ ወደ ምርጫነት እንዲሸጋገር በማሰብ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ባደረግነው ድርድር መሰረት በ2001 በተረቀቀውና በጸደቀው የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ደንብ አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የገንዘብም ሆነ የቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያገኙ ቢደነገግም፣ በአሁኑ ምርጫ ይህ ሕጋዊ መሰረት ያለው ድጋፍ እንደማይኖር ምርጫ ቦርድ ገልጿል፡፡ ምርጫ ሰላማዊ ነጻና ገለልተኛ፣ በሁሉም አካለት ዘንድ የታመነና ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ከተፈለገ አንዱና ወሳኙ ነጥብ የውድድር ሜዳውን ጨምሮ የቁሳቁስና የገንዘብ አቅርቦቱ ያለአድልዎ ለሁሉም በእኩልና በሚዛናዊነት መኖሩ ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ይህ ሚዛናዊ ስሌት ተጠብቆ ተግባር ላይ መዋሉን የማረጋገጥ ኃላፊነት የተጣለው ደግሞ በምርጫ ቦርድና በሌሌች መሰል የዴሞክራሲ ተቋማት ላይ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጉዳይ በኃላፊነት እንዲመራ በሕግ ስልጣን የተሰጠው ምርጫ ቦርድ፤ የሃገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ በማጤን ፓርቲዎች ተመጣጣኝ የውድድር አቅም እስኪፈጥሩ ድረስ በገንዘብና በቁሳቁስ እንዲደገፉ፣ በቂ፣ አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው፣ ሁሉንም አካታችና ሚዛናዊ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን እንዲያገኙ መከታተልና በተግባር ላይ መዋሉን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ጉድለትም ካለ ሚዛናዊነቱን ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ምርጫ እየታዘብን ያለነው እውነታ ግን ከዚህ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡ ከላይ እንዳነሳሁት ምርጫው ከመጀመሩ በፊት ምርጫ ቦርድ እያወጣ ከሚገኘው መግለጫ ለመረዳት እንደሚቻለው፣ ፓርቲዎች ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማገዝ በተለምዶ ይደረግ የነበረው የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንደማይኖር ገልጿል፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይ ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እዚህ ግባ የማይባል አቅማቸውን ይዘው ተቀናቃኛቸው ከሆነውና እጅግ ከተደራጀው፤ ከ-እስከ በማይባል ደረጃ የሃገሪቱን ሃብት የማዘዝ መብት ከተጎናጸፈው ኢህአዴግ ጋር ለመወዳደር ወደ ምርጫ እንዲገቡ እየተገደዱ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ማንም ዜጋ ለመረዳት እንደሚችለው በዚህ ምርጫ ትርጉም ያለው ፉክክር ሊያደርጉ እንደማይችሉ በግልጽ የሚጠቁም ነው፡፡ የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 5/2001 አንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት “መንግሥት በፌደራል ወይም በክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ላይ ለሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ እንደሚሰጥ ” ይደነግጋል፡፡ ምርጫ ቦርድ በሕግ ላይ ከሰፈረው ድንጋጌ ውጭ ረጅም ርቀት በመሄድና ያለ በቂ ምክንያት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍን መከልከል ለምን እንዳስፈለገው ወይም ይህንን የአድልዎ መንገድ ለምን እንደመረጠ ለመረዳት ምርመራ የሚያሻው ጉዳይ አይደለም፡፡ ማንም ሊረዳው እንደሚችለው ምርጫ ቦርድ ነጻና ገለልተኝነቱን ሊያረጋግጥባቸው ከሚገቡ እርምጃዎቹ መካከል አንዱና ዋነኛው በሕግ የተደነገጉ ምርጫና ፖለቲካ፣ ፓርቲ ነክ ጉዳዩች እንዲከበሩ ዘብ ሲቆምና ለምን ብሎ መጠየቅ ሲጀምር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በሚወስደው ከመድሎና የጸዳን በሕግ ላይ የተመሰረተ አቋሙ ምክንያት በሌሌች መንግስታዊ ተቋማት ያልተገባ ተጽእኖ የሚደረግበት ከሆነም ከተጽዕኖዎቹ እራሱን ለማላቀቅ የሚችለው በመጀመርያ እራሱ እንደ ተቋም የሚገዛበትን ሕግን ሲያከብር ነው፡፡ ሕግ ለማስከበር ደግሞ በመጀመርያ ሕግን ማክበር ያሻል፡፡ በዚህ መልኩ ለሕግና ለስርዓት የመገዛት ዝንባሌ ወይም ተሞክሮ በምርጫ ቦርድ ታሪክ ውስጥ ከዚህ ቀደም ፍንጩ ያልታየ ቢሆንም ለፍትህና ለርትዕ ዘብ ለመቆም ከተፈለገ፣ ጊዜው ስለማይረፍድና ከታሪክ ተጠያቂነት ለመዳንም ጭምር ምርጫ ቦርድ ዛሬም ከፊቱ የተደቀነውን ይህንን እድል ተጠቅሞ ከፍትሕና ርትዕ ተርታ በመቆም ሰልፉን ማሳመር ይኖርበታል፡፡
ምርጫ ቦርድ የምርጫውን ተአማኒነት ከወዲሁ በእጅጉ የሚሸረሽሩና ተስፋ የሚያስቆርጡ (ተስፋ የሚቆርጥ ከተገኘ) አሳሳቢ እርምጃዎችን መውሰዱ ሕግን እየተፃረረ መሆኑን ለማስረዳት በገሃዱ ዓለም ከዚህ የተሻለ መረጃ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል አንዳችም ነገር የለም፡፡ በማንኛውም መስፈርት የምርጫው ውጤት ከወዲሁ የተዛባ እንደሚሆን ደግሞ ይህ እውነታ በቂ ምስክር ነው፡፡ የ2002 ዓ.ም. ምርጫ እንዳስተማረን ከሆነ የምርጫ ውድድሩ በሕዝባዊና ሃገራዊ አጀንዳዎች ዙርያ በሚቀርቡ አማራጭ ፖሊሲዎች ከመመረጥ ይልቅ ልክ በአሜሪካ እንደሚደረጉት ምርጫዎች፣ ውድድሮች ያተኮሩት የምርጫ ዘመቻን በማሳመርና በማስዋብ ማለትም ፖስተርን፣ ፍላየርስንና ቲሸርትን ለማሳመር እንደ ሰዓትና ብዕር የመሳሳሉ ቁሳቁሶችን በነጻ ለማደል ወይም ምሳ፣ ቁርስና እራት እንዲሁም ቡና ለመጋበዝ የሚያስችል በቂ መዋለ-ንዋይ ማፍሰስ መቻልን ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የ2002 ምርጫ አንዱ አሳዛኝ ገጽታ በአንድ በኩል ገደብ የሌለው የገንዝብና የቁሳቁስ አቅርቦት ይዞ በሚንቀሳቀሰው ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግና በሌላ በኩል እጅግ በተመናመነ አቅም በሚፍጨረጨሩ ተቃዋሚዎች መካከል የሚደረግ ሚዛናዊነት የጎደለው ምርጫ ነበር የምንለው፡፡ ይህ ብቻ አልነበረም፤ እንዲህ ናላ በሚያዞር ደረጃ የተካሄደው የቅስቀሳ ፕሮፓጋንዳ አናቱ ላይ ምርጫ ማጭበርበር፣ እጩ ማሳደድ፣ ማዋከብና አፈና ጨምሩበትና አስሉት፡፡ በ97 አርባ ስልሳ የነበረው የምርጫ ውጤት አቻምና በ2002 ወደ 99.6 ፐርሰንት ተለውጧል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ የቀረችውን 0.4 ፐርሰንት ጠቅልሎ ውጤቱ በመቶ ፐርሰንት እንደሚጠናቀቅ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ውጤት እንግዲህ ለታሪክም ቢሆን ትንግርት ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ ሳዳም ሁሴን፣ መንግስቱም ሃይለማርያምና፣ ሆስኒ ሙባረክ በበላኤ ሰብነት በእጅጉ የተዘመረላቸው አምባገነኖችም በታሪካቸው ዘጠና ዘጠኝም ሆነ መቶ ፐርሰንት አሸንፈው አያውቁም፡፡ ከዚህ አኳያ በሕገ መንግስቱ አማካኝነት የተረጋገጠው የመድብለ ፓርቲ ስርዓታችን አደጋ አልተጋረጠበትም በሚል የሚነዛው የገዢው ፓርቲ ክርክር ጉንጭ አልፋ ከመሆን አይዘልም!! ከመርሃ ግብሩ ለመረዳት እለደሚቻለው ምርጫ ቦርድ በሂደት እየቀጨጨ መጥቶ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ስራው ምርጫ ማመቻቸት፣ ሂደቱንና ውጤቱን መታዘብ ብቻ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በምርጫዎች መሐል ፓርቲዎች የት እንደደረሱና ምን እያከናወኑ እንደሆነ መረጃ የለውም፡፡ ለጠቅላላ ጉባኤ ካልተጠራ በስተቀረ የራሱንም ሆነ የሕልውናው መሰረት የሆኑ ፓርቲዎችን ከፖለቲካ ፍልስፍናቸውና ርዕዮተ ዓለማቸው ውጭ ባሉ በርካታ ጉዳዮች ላይ አቅም የመገንባትም ሆነ የማጠናከር ስራ ሲሰራ አይታይም፡፡ ያለፉትን ምርጫዎች ሂደትና ውጤት በመመርመር ተግዳሮቶቹን በመቅረፍና የተሻለ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የማጎልበት ጥረት አይታይም፡፡ አልፎ ተርፎም የመድብለ ፓርቲ ስርአትን አጠቃላይ ሂደት የማረጋገጥ ፋይዳ በተለይ በዴሞክራሲያዊ መድብለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ ዓይነተኛ ተጠቃሽ ከሆነው ከምርጫ ቦርድ ውጭ ለማን እንደተተወ ማወቅ አይቻልም፡፡ ኃላፊነትን ከመወጣት ጀምሮ በራስ ተነሳሽነት ላይ ተመስርቶ፣ የሕዝባዊነትን መርህ በማስቀደም ከጥላቻ ፖለቲካ መጽዳትን፣ እውቅ መስጠትን፣ የመቻቻል ፖለቲካ ማስረጽን የመሳሰሉ ሊሰሩ የሚገባቸው ሌሎች ተመሳሳይ ነገር ግን ትልልቅ ፋይዳ ያላቸው ሃገራዊ ቁም ነገሮች እንዳሉ ለምርጫ ቦርድ መንገር ለቀባሪው የማርዳት ያህል ነው፡፡ ለዚህም በምሳሌነት የሚነሳው በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በየወቅቱ የሚነሱት ውዝግቦችና ንትርኮች ሕዝቡን ዘወትር ግር ሲያጋቡት ይታያል፡፡ አልፎ ተርፎም ለጥላቻ ፖለቲካ ሰለባ ሲያደርጉት ቆይተዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ ይህንን መሰረታዊ ችግር ቆሞ ከመታዘብ ባለፈ በገለልተኝነትና በያገባኛል መንፈስ ውዝግቦቹ እንዲፈቱና ፓርቲዎቹ ለማህበረሰቡ መልካም ምሳሌ እንዲሆኑ፣ አልፎ ተርፎም ዴሞክራሲያዊ መድብለ ፓርቲ ስርዓቱን ከማጠናከር አኳያም በባላንጣነት ከመተያየት ይልቅ ተቀራርበው ለመስራት እንዲችሉ፤ በመነጋገርና በመቻቻል መፍትሔ እንዲያመነጩ የሚያስችል የማግባባት ሚና ሲጫወት ታይቶ አይታወቅም፡፡ ገዢው ፓርቲ ከሁሉም ምድራዊ ችግሮችና ስህተቶች የጸዳ፣ ተቃዋሚዎች የሃገሪቱ ችግሮች ሁሉ ማከፋፈያ ምንጭ አድርጎ ከማየት ያለፈ ዝንባሌ አንጸባርቆ አያውቅም፡፡ በአጠቃላይ የምርጫ ቦርድ የወቅቱ ሚና ምርጫው ሲቃረብ ብቻ ተፍ ተፍ በማለት ምርጫው ጐልቶ እንዲታይ ለማድረግ ሲባል ምርጫን ጠብቆ ተቃዋሚዎች የገባችሁ በነፍስ ድረሱልኝ የሚል ጥሪ ከማሰማቱ ውጭ ከተቋቋመበት ዓላማና እንዲያስፈጽም ከታቀደለት ግብ አኳያ የሚመጣጠን ድርጊት እየፈጸመ አይደለም፡፡
ምርጫ ቦርድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውጣ ውረዱን ተቋቁመው ለዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ታማኝ በመሆን ለውድድር መብቃታቸውን አድንቆ፣ ችግሮቻቸውን በቅን መንፈስ በማዳመጥ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ ጥያቄዎቻቸውን ማጣጣልና ፓርቲዎቹን በደካማነትና በሕገ ወጥነት መክሰስና መውቀስ የተለመደ ተግባሩ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ ገዢው ፓርቲ የዚህ ስርዓት መገለጫ ናቸው፡፡ በዚህች አገር ፖለቲካ ውስጥ ተምረውና አድገው እራሳቸውን ለፖለቲካ ትግል ያጩ ሰዎች ስብስብ የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ደካማ ከሆኑም ደካማነታቸው ከተቀናቃኛቸው ከኢህአዴግ አባላት በአስተሳስብ፣ በተሞክሮ አሊያም በትግል መንፈስ የሚያንሱ ስለሆኑ ወይም እንዲያው በአንዳች የማይታወቅ ምክንያት ደካማ ስለሆኑ አይደለም፡፡ ፓርቲዎቹ እንደማንኛውም ተቋም አንዳንድ ውስጣዊ ችግሮቻቸው እንደተጠበቁ ሆነው ደካማ የሚያደርጋቸው ነገር ምክንያቱ ሌላ ሳይሆን የተሰናከለና (dysfunctional) ለችግሮቻቸው መፍትሄ መስጠት ያልቻለ ሚዛናዊነት የጎደለውና አድሎአዊ የዴሞክራሲ ስርዓት በመዘርጋቱ መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዴሞክራሲያዊ የሆነ የመደብለ ፓርቲ ስርዓትን ለመገንባት ገና አንገቱን ቀና በማድረግ ላይ በሚገኝ ማህበረሰብ ውስጥ በመፈጠራቸው መጠነ ሰፊ ውጣ ውረድ፣ ወከባና እንግልትን ተቋቁመው ማለፍ የግድ ይላቸዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአፈና ውስጥ ተወልደው በአፈና ውስጥ በማደግ መብትና ግዴታውን ለማስከበር ይቅርና በህይወቱ ላይ ለመወሰን ህልውናውን በተካደ ማህበረሰብ ውስጥ ለዘመናት ኖረው፣ ዛሬ አንገታቸውን ቀና በማድረግ የሚታሙትን ያህል ቁጥር ለመሙላት እንኳን በተደራጀ መልክ የመቆየታቸው ዜና ለትንግርት ሊነገር የሚገባው እውነታ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ከማንም በፊትና በላይ በተጠሪነት የሚያስተዳድራቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች መዳከም በሂደት የዴሞክራሲ ንቅናቄውን መዳከምና መጥፍታን በማስከተል፣ በመጨረሻም የራሱ የምርጫ ቦርድን ህልውና አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ያውቅ ዘንድ ምርጫ ቦርድ ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልገውም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሌሉበት ስለመድብለ ፓርቲ ስርዓትና ስለምርጫ ለመነጋገር ማሰብ አይሮፕላን በሌለበት ስለኤርፖርትና ስለአየር መንገድ እንደማውራት የሚቆጠር ነው፡፡ ስለ ዴሞክራሲያዊ መድብለ ፓርቲና ስለምርጫ ዴሞክራሲ ለመነጋገር ከተፈለገ፣ የተጀመረው ስርዓትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቁርጠኝነት ከታመነበት፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ምርጫ ቦርድና ሌሎች መስል ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሕገ መንግስቱና ምርጫ ቦርድ እያነቡ እስክስታ ከመሆን አያልፉም፡፡
No comments:
Post a Comment