ABE TOKCHAW
ናፍቃው ናፍቃው አሁንም ናፍቃው ደወለችለት።
ነግሯታል። በእርሱ ውስጥ የተሾመች ባለስልጣን እርሷ ነች። ና ስትለው ይመጣል ሂድ ስትለው ይሄዳል። ግባ ስትለው ይገባል ውጣ ስትለው ይወጣል።
ለዚህም ነው የወደደችው ታዛዥነቱን ትህትናውን “ጠብ እርግፍ” ማለቱን አይታ ነው በፍቅሩ “ጠብ እርግፍ” ያለችው።
ናፍቃው ናፍቃው አሁንም ናፍቃው ደወለችለት።
“ይቅርታ የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይሉም!” በተስረቅራቂ ድምፅ ከወዲያኛው መስመር የሆነች ሴትዮ መለሰችላት። ቅናት አይሉት አንዳች ሰይጣናዊ ስሜት ሲሰማት ታወቃት። ሰውነቷ በበስጭት ጋለ። ከዛም ምን ነካኝ… ብላ በሀፍረት ሳቅ ብላ…
ደግማ ደወለች…
ቴሌዎች በየስኩ ላይ ያስቀመጧት ሴትዬ የሰዉን አባወራ ሁሉ “ይቅርታ የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም” ስትል “ከኔጋ የሚቆይበት ጉዳይ አለው” የምትል ትመስላለች፤ እንጂ ምክንያቱን አትገልፅም። አነጋገሯ ደግሞ ከሌሎቹ የተለየ ቅላፄ አለው። “ያልዎት ቀሪ ሂሳብ አነስተኛ ነው…” ከምትለው እና ቀልቀል ባለ ድምፅ “The network is busy now” ከምትለው ሴትዬ የተለየች ናት። ማሽን ላየ የተገጠመች ሳይሆን ከሰዉ ወዳጅ ጋር አጓጉል የገጠመች ነው የምትመስለው።
የገዛ ፍቅረኛዋን ያለ በቂ ምክንያት “አሁን ማግኘት አይችሉም” መባሏ እያብከነከናት ደግማ ደወለች…
ከዛኛው መስመር ቆጣ ያለ የሴት ድምፅ ሰማች፤
“ሁለተኛ በዚህ ስልክ ባትደውይ ደስ ይለኛል ነገርኩሽ አይደል እንዴ!”
ተሳስታ የደወለች መስሏት ስልኳን አየት አደረገችው። በፍፁም አልተሳሳተችም። የእርሱን ስልክ መሳሳት ስሙን የመሳሳት ያክል ከባድ ነው።
ማናት ይቺ…?
እንደቅድሙ ማሽኗ በሆነች… ስትል እየተመኘች… ቀሰስ ባለ ድምፅ “ሃ…ሎ” አለች፤ ቅስሟ ስብር ሲል ታወቃት። ቅስም የቱጋ ነበር…? እንጃ ብቻ ከወገብ ስብራት የበለጠ ያማል። ታመመች…
በተሰበረ ቅስም እና በተሰበረ ድምፅ ድጋሚ “ሃ…ሎ” አለች። የእርሱን ድምፅ ሰማቸው። ግን አልገባትም… “በቃ እንደነገረችሽ አድርጊ የኔ እመቤት”
ራሷ ሊፈነዳ ነው።
————————————————————————————-
“በቃ እንደነገረችሽ አድርጊ የኔ እመቤት” አለና፤
ተጣድፎ ስልኩን ዘጋው። አንዳንድ ደንበኞች ይገርሙታል ከሰራተኞች የተሰጣቸውን መረጃ ድጋሚ ከእርሱ ካልሰሙ ደስ አይላቸውም። እርሱም “እነርሱ እንደነገሯችሁ አድርጉ” ብሎ ይሸኛል።
ስልኩን ገና ሳይዘጋው ሌላ ጥሪ መጣ… ውዱ ናት። ገብረክርስቶስ ደስታ ከገጠመላት በላይ ሚካኤል በላይነህ ካዜመላት የበለጠ የሚወዳት ውዱ…
“የኔ ናፍቆት…” ብሎ ሲጀምር፤ “ማንነቷን ብቻ ንገረኝና እዘጋልሃለሁ።” የሚል የተሰበረ ድምፅ የእንባ ሳግ እየተናነቀው ከጆሮው ደረሰ።
አልገባውም…
“እሷ እንደነገረችኝ አደርጋለሁ… ግን ማናት…!?”
የት ነበርሽ…? ይሄ ቃል እርሷ ከመደወሏ በፊት የተናገረው ነው…! የት ሆና ሰማችው… ደግሞስ ምን ክፋት አለው… የስራ ጉዳይ ነው… “እርሷ እንደነገረችሽ አድርጊ የኔ እመቤት…” እመቤት ማለቴ ይሆን ያስከፋት…
እያሰበ እያለ ሃይሏን አሰባስባ አምባረቀችበት።
“ማናት?”
“ደንበኛችን ናት…” አለ። ከዛኛው ጫፍ ውዱ ከምትገኝበት ጫፍ ስቅስቅታ… ተሰማው… አዎ አለቀሰች ሆዷ ባባ… ስልኩንም ዘጋችበት።
———————————————————————-
ግራ ተጋብቶ በተቀመጠበት አንድ ወዳጁ ቢሮውን ላመል ያህል “ኳኳ..” አድርጎ ገባና… “ሰሞኑን ቴሌ የሰዎችን የፍቅር ተቋማት ለማፈራረስ ቆርጦ ተነስቷል” አለው።
“እንዴ….ት” አለ ሙትት ባለ ድምፅ፤
“የአንዱን ስልክ ለአንዱ እያጠላለፈ የሰዉን ፍቅር እያናጋው ነዋ” አለው።
ይሄኔ “ከትክት ብሎ ሳቀ” ወዳጁ የነገረው ነገር ይሄን ያህል የሚያስቅ መሆኑ አልገለጥልህ አለው። ጭራሽ ተነስቶ፤ “ተጠልፎ ነው ተጠልፎ ነው… ተጠልፎ ነው” እያለ እንደቀውስ ብቻውን እየጮኸ በሩጫ ወደ “ውዱ” ሄደ አንገቷን ደፍታ አይኗ ቀልቶ አገኛት…
“ተጠልፎ ነው! ተጠልፎ ነው! ተጠልፎ ነውኮ…”
No comments:
Post a Comment