ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው ህወሓት የሚመካበትን የታጠቀ ሰራዊት የሚመሩ ከፍተኛ መኮንኖችና ጄኔራሎች በጡረታ ለመሰናበት ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰማ። የአስቸኳይ አዋጁ ሲነሳ መልስ እንደሚያገኙ ቃል የተገባላቸው እንዳሉም ታውቋል።
የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ለደህንነት ሲባል መረጃውን ያገኘበትን ሳይገለጽ እንደጠቆመው “መከላከያ ሰራዊት” የሚባለውን የህወሓት ሥልጣን አስጠባቂ የታጠቀ ኃይል ከሚመሩት ጄኔራሎች መካከል “በቃኝ” ያሉት ጄኔራሎች ከሰባት በላይ ሲሆኑ፣ በከፍተኛ መኮንን ደረጃ ያሉት ግን ቁጥራቸው በርከት ያለ ነው።
ጄኔራሎቹ ሰራዊቱን ለመሰናበት ያቀረቡትን ዋና ምክንያት የመረጃ ሰዎቹ ቃል በቃል ይፋ ባያደርጉም፣ ከሰራዊቱ ጋር ላለመቀጠል ዕድሜ፣ ጤና፣ ጋብቻና ተያያዥነት ያላቸው ጥያቄዎችን እንደ ምክንያት አቅርበዋል። መልቀቂያ ያስገቡት ብቻ ሳይሆኑ በርካቶች ተመሳሳይ ፍላጎት እንዳላቸውም ጠቁመዋል። የዚህም ምክንያቱ ሥርዓቱ አያያዙና አሁን የደረሰበት ደረጃ ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ሰላም አስጊ በመሆኑ ነው።
በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ውስጥ ባለው የኃይል አሰላለፍ ስጋት ውስጥ የገቡና ችግሩ ሊወሳሰብ እንደሚችል በማሰብ አድፍጠው በመጠባበቅ ላይ ያሉ ከፍተኛ የሰራዊቱ አመራሮች ሲሰናበቱ አገር ውስጥ የመኖር ዕቅድ እንደሌላቸውና ለዚሁም አስቀድመው የጉዞ ዝግጅት ያደረጉ እንዳሉም ተጠቁሟል።
ጥያቄውን የተቀበለው ውሳኔ ሰጪ አካል ለጊዜው የሰጠው ቁርጥ ያለ መልስ የለም። በአስቸኳይ አዋጁ ምክንያት ሰራዊቱን የመልቀቅ ጥያቄ በመመሪያ በመታገዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መነሳት ተከትሎ ውሳኔ ሰጪዎች ምን እንደሚመለሱ ሊታወቅ እንደሚችል የመረጃው ሰዎች ለጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ነገረዋል።
በሰራዊቱ ውስጥ በሚታየው መረን የወጣ አድልዎ የተማረሩና የተሰላቹ ከፍተኛና መካከለኛ የመስመር መኮንኖችን ጨምሮ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሰራዊቱ አባላት ስንብት እንደሚፈልጉ በመረጋገጡ በወታደራዊ ውሳኔ ሰጪዎችና ፖሊሲ አውጪዎች ዘንድ ስጋት ፈጥሯል።
በዚህም የተነሳ የአገልግሎት ጊዜያቸውን ጠቅሰው ስንብት የጠየቁ በከፍተኛ ደረጃ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑ ታውቋል። “አገሪቱ አሁን ባለችበት ችግር ውስጥ፣ አስቸኳይ ጊዜ ላይ እያለን እንዴት ስንብት ለመጠየቅ አሰብህ” በሚል እንደሚገመገሙም ከመረጃው ሰዎች ለመረዳት ተችሏል።
በሰራዊቱ ውስጥ ያለውን የ“በቃኝ” ህገ መንግስታዊ ጥያቄ በአስቸኳይ አዋጁ ስም አንቀው የያዙት ወሳኔ ሰጪዎች፣ ሰራዊቱን ፍልሰት እንዳያርደው ፍርሃቻ ስለገባቸው ከወዲሁ የአዳዲስ ሃይል ምልመላ ሲያካሂዱ እንደነበር ለመረዳት ተችሏል። ከዚህም በላይ በየክልሉ ያለውን የልዩ ሃይል ከአስችኳይ ጊዜ መነሳት በኋላም በአንድ ዕዝ ውስጥ የማስገባት ስራ እንደሚሰራ ታውቋል።
እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የሰራዊቱ አባላት የመሰናበት ፍላጎታቸውን አፍኖ መዝለቅ ስለማይቻል “ከጥልቅ ተሃድሶ በኋላ” በየክልሉ አዳዲስ ታጣቂ የማስፈለፈሉ ስራ እየተሰራ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል። አሁን ባለው አሰራር ከመከላከያ መሰናበት የሚችለው በጋብቻ ወደ ውጪ አገር የሚሄድ ወይም ቀደም ሲል በማመልከት የትምህርት ዕድል ያገኘ ብቻ እንደሆነና ይህ መመሪያ መቼ እንደሚነሳ በግልጽ የተቀመጠ ነገር እንደሌለ የመረጃው ምንጮች ተናገረዋል።
የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን አገዛዝ ወደ ፍጻሜው ለማምጣት እንዲረዳ “በመፈንቅለ መንግሥት” ሙከራ ሳቢያ በርካታ ጄኔራሎች ከሠራዊቱ ተወግደው ነበር። ይህ የተቀነባበረ ድርጊት ለህወሓት ወደ አዲስ አበባ መግባት ዕንቅፋት ይሆናሉ ተብለው የታሰቡን በቀላሉ “ከመንገድ የጠረገ” እንደነበር የሚታወስ ነው። አገር ውስጥ ባሉ የውስጥ አርበኞችና በውጭ አገራት የለውጥ ፈላጊ ሆነው በቀረቡ “ከሃዲዎች” ቅንብር ሳይካሄድ የከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት የሚጠርገውን ጠራርጎ ካለፈ በኋላ ኮ/ሎ መንግሥቱ ከሥልጣን የመወገዳቸው ጉዳይ “የቀናት” ብቻ እንደሆነ “ያበሰረ” እንደነበር ብዙዎች የሚያስታውሱት ነው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ሰበብ አድርጎ የታፈነው የህወሓት ጄኔራሎች “የበቃኝ” ጥያቄ አስቀድሞ ከሥልጣናቸው የተለዩትን፣ በተለያዩ የሃብት መሰብሰብ ተግባራት የተሰማሩትንና ወደፊታቸውን የሰበሰቡትን ሃብት እየበሉ ለመኖር ባሰቡት ዘንድ እንዲሁም በሥልጣን ለመቆየት በሚያስቡት ጭምር የተደበላለቀ ስሜትን ፈጥሯል። ሆኖም የጄኔራሎቹ “የበቃኝ” ጥያቄ መነሻ ምክንያት ከላይ የተጠቀሱት ብቻ ይሁኑ ወይም ሌሎች ያልተጠቀሱ መነሾዎች ይኑራቸው ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም። (ፎቶው “የበቃኝ” ጥያቄ ካቀረቡት ጋር ግንኙንት የለውም)
ከጎልጉል ድህረ ገጽ የተወሰደ
No comments:
Post a Comment