አትክልት አሰፋ – ከቫንኩቨር
የመለስን ሞት ኢሳት በነገረን ሰሞን ብዙ ውዥንብሮች ነበሩ… ብዙ ብዙ ውጥንቅጥ የበዛበት ወቅት ነበር። አገዛዙ ይይዝ ይጨብጠው አጥቶ በየ መገናኛ ብዙሃኑ የሚወጡ ባለ ስልጣናት መርበትበትና መራወጥ ከትላንት ትዝታነት አልመከነም። ያኔ… የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ…
የመለስ አስከሬን አዲስ አበባ ሲገባ የተከሰተ ነገር አሁን በሙት አመቱ መታሰቢያ ወቅት ታወሰኝ፡፡
መለስ የሞተ ሰሞን አንድ ወዳጄ ኢትዮጵያ ሄዶ ነበር። ለቀብር ሽር ጉድ በሚባልበት ጊዜ መሆኑ ነው። ያኔ ስለዚያ ሰሞን ሁኔታ ስናወራ አንድ የቆዳ ሃኪም የሆነ ዘመዱ የመለስ አስከሬን አዲስ አበባ ገባ በተባለበት ወቅት ቤተ መንግስት ተጠርቶ ሙያዊ እገዛ ተጠይቆ ነበር።
በመሪው ሞት እጅግ ተደናግሮና በተለያዩ ፍርሃት ተተብትቦ የነበረው የህወሃት አመራር ህዝብ ውስጥ የሰረጸውን ውጥረት ለማርገብ የመሪውን የመለስ ዜናዊን ተክለሰውነት በመገንባት ነበር አስፈሪውን ጊዜ ለማሳለፍ የወሰነው።
የሰውየውን /የመለስን/ ‘በጎ’ ተግባራት በረንዳ አዳሪው፡ ሴተኛ አዳሪዋ፡ አልቃሽና አስለቃሽ፤ ሊቅ ከደቂቅ ሳይቀር ሲመሰክር በአይናችን አሳይቶናል፡፡ ትላልቅ ፎቶዎችም በአዲስ አበባ አውራ ጎዳኖች ተሰቅለው ብዙ መፈክሮች ተጽፎባቸው ታይተዋል፤ አባይን የደፈረ… የህዳሴው ምናምን… የመፈክር መአት አዲሳቤ አእምሮ ላይ ለመጫን ብዙ ተሞክሮ ነበር፡፡
ህወሃታዊያን ‘የሰውያቸውን’ ተክለ ሰውነት አጉልቶ በማሳየት የተበጣጠሰ የጨቋኝ ስርአቱን ፍጻሜ ለማትረፍ ይፍጨረጨሩ የነበረበት ወቅት ነበር… ።
ይህ የወዳጄ ዘመድ የሆነው የህክምና ባለሙያ /ዶክተር/የተፈለገው ታዲያ ለዚህ ከንቱ የሙገሳ ውዳሴ አላማ መሳካት አንዱ ግብአት ይሆናል ተብሎ ለታሰበው ተግባር ነበር፡፡ የመለስን አስከሬን በመስተዋት የታጀበ የሬሳ ሳጥን ውስጥ አስቀምጦ ለህዝብ በይፋ ለማሳየትና ክብሩን በብዙሃኑ ዘንድ አስርጾ ለማቆየት፡፡ /እንደፈረንጆቹ መሆኑ ነው/
በዚህ ሙያ የተሻለ ነው ተብሎ የተመረጠው ሃኪም ታዲያ ይህ የኔ ወዳጅ የሆነ ሰው የቅርብ ዘመድ ነበር…፡፡ ይህ ሰው በካንሰር የተጎዳውን የመለስን ከአንገት በላይ ክፍል አስተካክሎ እንዲሰራና እንዲያስውብ ነበር ቤተ መንግስት የተወሰደው፡፡ ዶክተሩ…
እንዳይሆን ሆነና… በካንሰር ህመም የተጎዳውን የአቶ መለስ አካል በወቅቱ በምንም ተአምር ተስተካክሎ ለእይታ መቅረብ እንደማይችል በሃኪሙ ስለተረጋገጠ የታሰበው የሙገሳ አላማ ግቡን ሳይመታ ይቀራል፡፡ ሃኪሙ እንዳለው የመለስ አስከሬን በተለይ ከአንገቱ በላይ ያለው ክፍል በካንሰሩ ክፉኛ ተጎድቶ ነበር፡፡
ይህ የሃገራችንን ታሪክ በአደባባይ ሲያንጓጥጥ… የአክሱም ሃውልት ለወላይታው… ከወርቅ ህዝብ የወጣሁ… ጨምላቃ… ወራዳ… እያለ ሃገርን፡ ህዝብንና ታሪክን ሲያፋልስ የኖረ ፍጥረት ተሽሞንሙኖና ተቀባብቶ በአደባባይ ለእይታ ሊበቃ አልቻለም፡፡ ኢትዮጵያን የነካ… ሆነና ነገሩ…፡፡
ዶክተሩ እንዳለው የሰውዩው ፊት በነቀርሳው/በካንሰሩ/ ምክንያት ክፉኛ ፈራርሶ ነበርና፡፡
ለወትሮው ኢትዮጵያዊ በሙት ቀልድ የማያውቅ ምስኪን ፍጡር መሆኑን ክፉ የተባለ ሰው ሲሞት እንኳን እንዴት አሽሞንሙኖና መልካምነቱን፡ ትሁትነቱንና ጥሩ ሰውነቱን ብቻ ገልጾ እንደሚቀብር ይታወቃል፡፡ የጠናበት… የባሰበት… ግፍን መሸከም ሲያቅተው፡ የግፈኞች ዱላ ሲጠናበት ግን ያገኘውን ቀዳዳ ሁሉ ተጠቅሞ የልቡን እንደሚናገር እሙን ነው፡፡
ለዚህም ነው መለስ የሞተ ሰሞን ቤተመንግስቱን በለቅሶ ሰበብ ያየች እናት በዚያው ሰሞን የሸክ ሙሃመድ አላሙዲንን መታመምና ለህክምና ውጭ ሃገር መሄድ ስትሰማ ‘እሰይ… አሁን ደግሞ ሸራተንን ልናይ ነው’ ያለችው፡፡
ይሄ ግጥም መለስ ሞቷል አልሞተም’ በሚባልበት ሰሞን የተገጠመ ነው፡ እንካችሁ፦
ይኑሩ አይሙቱብን!
ትንሽ ይቆዩ እንጂ፤ ጥቂት ይኑሩልን፣
ባሉበት ላይ ሆነው ስቃይ ተካፈሉን።
ባሉበት ላይ ሆነው ስቃይ ተካፈሉን።
ጭንቀትን ይወቁት በሞቴ ይኑሩ፣
መከራን ይቅመሱት ህመምን ይጋሩ፤
መከራን ይቅመሱት ህመምን ይጋሩ፤
ወደ ላይ አይሂዱ… ወደሰላሙ አለም፣
እዚያ ከሄዱማ ምንም ነገር የለም፤
እዚያ ከሄዱማ ምንም ነገር የለም፤
ወደዚያም አይሂዱ… ወዲህም አይምጡ፣
ባሉበት ቦታ ላይ እዚያው ይቀመጡ
ከፍትህ ፊት ቆመው በፍርድ እስኪቀጡ።
ባሉበት ቦታ ላይ እዚያው ይቀመጡ
ከፍትህ ፊት ቆመው በፍርድ እስኪቀጡ።
(አቶ መለስ በጠና ታመዋል በተባለ ጊዜ)
ቸር ለናንተ ተመኘሁ
No comments:
Post a Comment