- ህወሓት በትግራይ ላይ የራሱን አቋም እንዲወስድ ተመክሯል
በኢትዮጵያ ያለማቋረጥ ሲካሄድ ከቆየው ሕዝባዊ ተቃውሞ አኳያ በህወሓት የደህንነት ክፍል የተሰበሰበው መረጃ፤ አሁን ካለው የተቃውሞ ንቅናቄ የተነሳ የኢህአዴግ የገጠር መዋቀር በኦሮሚያና በከፊል የአማራ ክልሎች ሊፈርስ እንደሚችል አስታወቀ። ከሁኔታው አሳሳቢነት የተነሳ ሊወሰዱ የሚችሉ አማራጮች ቢኖሩም ህወሓት ትግራይን አስመልክቶ የራሱን አቋም እንዲወስድ ሃሳብ ተሰጥቶታል።
ኢትዮጵያን በነጻ አውጪ ስም እየገዛ ያለው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሓት) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየደረሰበት ያለውን የሕዝብ ተቃውሞ ለመቆጣጠር ተስኖት ይገኛል። በተለይ “ባለራዕዩ መሪውን” ሞት እንደ ቡሽ ክዳን ካስፈነጠረው ወዲህ ግምባሩ በአንድ መጓዝ፣ በአንድ መስማማት፣ በአንድ ማሰብ አቅቶት በተቃዋሚው መዳከምና በአንጋሾቹ አለሁ ባይነት ብቻ በሥልጣን መንበር ላይ ሲንገታገት ቆቷል። ሕዝብ ፊቱን ካዞረበት ቢቆይም በተለይ ትውልድ ካመጸበት ወዲህ ግን የአገዛዙ ኃይል እንደ ሹራብ ክር መጎልጎል ጀምሯል የሚሉ ጥቂቶች አይደሉም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራና በኦሮሞ ቦታዎች የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ ህወሓት በኢህአዴግ ሥም እንደ ጭቃ ጠፍጥፎ የሠራቸው ብአዴንና ኦህዴድ “ሕዝባቸውን” መምራት የተሳናቸው መሆኑን ያስመሰከረ ሆኗል። የእነዚህ ሁለት ድርጅቶች የበታች አመራሮች መክዳት በስለላና በጥርነፋ ሁሉንም “ልክ አስገባለሁ” እያለ የሚፎክረውን ህወሓት ከራሱ የውስጥ ችግር ጋር ተዳምሮ የማይለቅ ራስ ምታት ሆኖበታል። እንደ አንዳንዶች አገላለጽ ሁለቱን ድርጅቶች አራቱም ጎማው ወልቆ መንገድ ዳር ከቆመ መኪና ጋር ያመሳስሏቸዋል።
የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ የተጀመረውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲነሳ ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ሁኔታውን በዘገበበት ወቅት ስለ ኦህዴድ መክዳት ይህንን ብሎ ነበር፤ “ሳምንታት ያስቆጠረውና የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን ምክንያት በማድረግ የተነሳው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ በመጠኑም ሆነ በዓይነቱ ልዩ እየሆነ መሄዱ ኦህዴድ ኢህአዴግን የመክዳቱ ማስረጃ ነው ሲሉ በኦሮሚያ ጉዳዮች ላይ ለጎልጉል መረጃ የሚያቀብሉ አመራር አስታውቀዋል።
“በኢህአዴግ የአንድ ለአምስት ጥርነፋ፤ ስለላ፤ ሕዝባዊ አደረጃጀት፤ ቁጥጥር፤ … መዋቅሮችን ሁሉ አልፎ ይህንን ያህል ሕዝብ ያለአንዳች ከልካይ መውጣቱ አገዛዙ ሕዝቡን ለመጠርነፍ የተጠቀመበት አሠራር መልሶ ራሱን እየጠረነፈው እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ታማኝ ተብሎ የተቀመጠው ካድሬም ሆነ የጥርነፋው መዋቅር ሕዝቡን ሊያስቆም አለመቻሉ የኦህዴድ እምቢተኛነትና ለአገዛዙ ድጋፍና እገዛ ከማድረግ ይልቅ ከሕዝቡ ጋር ለመቆሙ እንደ ዓይነተኛ ማስረጃ ይጠቀሳል”።
የዛሬ ዓመት በጎንደር ከተማ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ ሰላማዊ ትዕይንተ ሕዝብ በማካሄድ “በኦሮሚያ የሚደረገው የወንድሞቻችን ግድያ ይቁም፤ በጎዳና ላይ የሚፈሰው የኦሮሞ ወንድምና እህቶቻችን ደም የእኛም ደም ነው” ባሉበት ወቅት “ስልታዊ ጥርነፋውን አልፎ ሕዝቡ ሰላማዊ ሰልፉን ለማድረግ መቻሉ ብአዴን ህወሃት የሚዘውረውን ኢህአዴግ ለመክዳቱ ፍንጭ ሰጥቷል” በማለት ጎልጉል ዘግቦ ነበር።
ይህንን መሰሉ ግልጽ መከዳት ያሳሰበው ህወሓት በቅርቡ በደኅንነት ክፍሉ በኩል የቀረበለትን የመረጃ ትንተና አዳምጧል። እንደ መረጃው ከሆነ በአገሪቷ ላይ ሲካሄድ የቆየው ሕዝባዊ ንቅናቄ ኢህአዴግን ክፉኛ ጎድቶታል። የድርጅቶቹ በሕዝቡ ላይ ያላቸው የበላይነት ካከተመ ሰነባብቷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ ሁኔታው በዚህ መልኩ መቀጠሉ በህወሓት አዛዥነት የሚተገበረው የኦህዴድና የብአዴን የጥርነፋም ሆነ የስለላ መረብ መርገቡ የሚያሳይ ሆኗል። በመሆኑም በቅርብ ጊዜ ውስጥ በመላ ኦሮሚያና በከፊል አማራ ክልል የህወሓት/ኢህአዴግ የገጠር መዋቅር ሊፈርስ እንደሚችል የደኅንነት ክፍሉ ዘገባ ትንበያ ሰጥቷል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ዘገባው አማራጭ የሚላቸውን “የመፍትሔ” ሃሳቦችን ጠቁሟል። አንዱ፤ ያለውን ኃይል ሁሉ ተጠቅሞ ሕዝባዊ ንቅናቄውን መቀልበስ፤ ሕዝቡን የሚያነሳሱ የፕሮፓጋንዳ መስመሮችን ሁሉ መዝጋት፤ ሌላው በምዕራባውያን አገራት ገለልተኛ ዕገዛ ኢህአዴግን ከተቃዋሚው ጋር ጠረጴዛ ላይ በማቅረብ ወደ ድርድር መምጣት፤ ይህ ካልሆነ ግን የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር የሆነው ህወሓት የትግራይን መጻዒ ዕድል በተመለከተ የራሱን አቋም እንዲወስድ ምክር ተለግሶታል።
ምዕራባውያን ፊታቸውን በሕወሓት ላይ ከማዞራቸው አንጻር ሁለቱ አማራጮች ምን ያህል ውጤታማ እንደሚሆኑ ለመገመት የሚከብድ ቢሆንም ሦስተኛን በተመለከተ ግን አሁን አገሪቱ ውስጥ እየተከሰተ ያለው እምቢተኝነት ትግራይን አገር ለማድረግ እየተሠራ ካለው ሥራ በመፍጠኑ ሁኔታዎችን ያወሳሰበ ይመስላል። ሆኖም ከመለስ ዜናዊ “እንኳን ከናንተ ተወለድኩኝ! እንኳንም የሌላ አልሆንኩኝ..” ንግግር ጀምሮ መለስ ትግራይን ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ አውጥቶ እንደ ነበር አዜብ መስፍን
“ምሥጢሩን” እስከተናገረችው ድረስ ትግራይን አገር ስለማድረግ በአስረጂነት የሚጠቀሱ ናቸው። ከዚህም አልፎ ሕዝባዊ ንቅናቄው በተነሳበት ወቅት የትግራይ ወጣቶችን ለ“ትግራይን አድን”የውትድርና ስልጠና ከመጥራት ጀምሮ የዛሬ አምስት ዓመት በትግራይ በክልተአውላዕሎ ወረዳ ውስጥ የምትገኘው አብርሃ ወ-አጽብሃ የገጠር ቀበሌ “የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን በማቀጣጠል”በዓለምአቀፍ ደረጃ መሸለም፤ ከአግዓዚያን የትግራይ ድንበር እስከ አስመራ ነው ርዕዮት እስከ ‘‘(ትግራይ) በተፈጥሮ ሃብት አጠባበቅ ባካናወነችው ድንቅ ስራ በዓለም አቀፍ ደረጃ በእጩነት ከቀረቡ ስድስት (እጩዎች) መካከል በአንደኝነት በመመረጥ የወርቅ ተሻለሚ” መሆን የትግራይን በሉዓላዊ አገርነት የመመሥረት ምልክቶች ሆነው በአስተያየት ሰጪዎች ይቀርባሉ።
No comments:
Post a Comment