Translate

Thursday, August 3, 2017

የማላውቀው ሲሳይ አጌና! (ኤርሚያስ ለገሰ)

ኤርሚያስ ለገሰ
Ethiopian journalist Sisay Agena
ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና
ባለፋት ወራት ” ሲሳይ አጌና!” በሚል የፌስቡክ ስም የተሳሳቱ መረጃዎች መዛመታቸው ይታወቃል። በዚህ ፌስቡክ ስም ከተስተናገዱት መረጃዎች መካከል አንጋፋው ኢትዬጲያዊ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ማረፋቸው፣ አንጋፋው ድምፃዊ አሊ ቢራ ማረፋ፣ የኢትዮጵያ ሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊዎች በሳኡዲ አረቢያ የሞት ፍርድ እንደተፈረደባቸው ይገኙበታል። ሰሞኑን ደግሞ በብዙ ኢትዬጲያውያን ዘንድ የፅናት ተምሳሌት ተደርጐ የሚወሰደው ታማኝ በየነ በመኪና አደጋ ህይወቱ እንዳለፈ የተገለጠበት ነበር።

ነገ ደግሞ ቴዲ አፍሮ በሽብርተኝነት ሊከሰስ እንደሆነ በሰበር መረጃ እንሰማለን ። ከነገ ወዲያ በረሃ የወረደውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ሻእቢያ በቁም አሰረው ልንባል እንችላለን። ከነገ ነገ ወዲያ ደግሞ አንዳርጋቸው ፅጌ የአገዛዙ የሞት ፍርድ ብይን ተፈፀመበት እንባል ይሆናል። እና ምን ይጠበስ?
በግሌ እንደ ትላንቱ ሁሉ የተሰማኝን ሐዘን መደበቅ አልችልም። የሀዘኔ ምንጭ እንዲህ አይነት የወረዱ ኩታራ ሰዎች ለኢትዮጵያ ህዝብ ያላቸው ንቀት ገደብ የሌለው በመሆኑ ነው። እርግጥ ንቀቱ ተደጋግሞ የተገለፀ እና የተፃፈ በመሆኑ አዲስ ግኝት አይደለም። እንደውም መነገሩና መፃፉ ንቀቱን ይበልጥ አሰፋው እንጂ አላጠበበውም ። ይበልጥ ስልቱን እየለዋወጠ እንዲሄድ አደረገው እንጂ አላጠፋውም። የሚነዙት የመንደር ወሬ እና አሉባልታ ስር እየሰደደ ከግለሰብ ተሻግረው ኢትዬጲያዊ ባሕልና ወጋችንን እየናዱት ሄዱ እንጂ ወደ ትቢያ አልገቡም።
ታዲያ እንደዚህ አይነት ሰዎች ምን ላይ ቆመው ነው በድፍረት እና ባለማቋረጥ ያሻቸውን ሁሉ የሚሉት? ለመሆኑ እንደዚህ አይነት ሰዎች እያደረሱ ያሉትን ጉዳት እንዴት እንመለከተዋለን?…ሰዎቹ ከኢትዮጵያ ሕዝብና ባህል የፈለቁ ናቸው ወይ? ህብረተሰባችን ከእንደዚህ አይነት የባለጌዎች ስብስብ ድርጊት ምን ትምህርት ሊቀስም ይገባል?… ለመሆኑ የኢትየጵያ ሕዝብ ነው የነውረኞቹ አይን ውስጥ ትንሽና ደካማ ሆኖ የታየው ወይንስ የቅጥፈታቸው ኃይል ነው ከህዝቡ በላይ ገዝፈው እንዳፈተታቸው እንዲዋሹ የረዳቸው?…በግላጭ እየታየ ያለው የንቀታቸው ምንጭ መሰረቱ ምንድነው? …ለመሆኑ ከሰሞኑ ክስተት ምን ያህል ተምረናል?…ከሁላችንም ምላሽ የሚፈልግ ጥያቄ ይመስለኛል። እነዚህ የእያንዳንዳችንን ህሊና ሊዳስሱና ሊኮረኩሩ የሚገባቸው አበይት ቁምነገሮች ናቸው።ልናወጣና ልናወርድ ብሎም መልስ ልንሻላቸው የሚገቡ ጥያቄዎች ናቸው። በዚህ አጭር ማስታወሻ በሁለት ምክንያት በሚመስሉኝ ጉዳዬች ላይ ብቻ አተኩራለሁ።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጉዳዩን በጣም አቅልሎ ከሚመለከቱት ሰዎች አንዱ ነበርኩ። እንደዚህ አይነት ቅጥፈቶች ከጥቂት ሰአታት ትርምስ በኃላ የትም ድረስ መሄድ አይችልም የሚል እምነት ነበረኝ። ታማኝን ጨምሮ ከስራ ባልደረቦቼ ጋር ስንነጋገር ማደናገሩም በጥቂት ሰዎች ላይ ካነጣጠረ በኃላ በራሱ ጊዜ ይከስማል የሚል መከራከሪያ አቀርብ ነበር። ለነገሩ ከመካከለኛ እና ረጅም ጊዜ አኳያ ይሄ እምነቴ እንደተጠበቀ ነው። ይሁን እንጂ ከአጭር ጊዜ አንፃር ጊዜያዊ አደጋ ሊያመጣ ስለሚችል ንቆ መተው ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል መመልከት ችያለሁ። በተለይም ከቶሮንቶ ካናዳ ለታማኝ የደወለች ኢትዬጲያዊ እንባዋን እየዘራች ” በሕይወት አለው በለኝ!” እያለች ስትማፀን መስማቴ የሁኔታውን አጣዳፊነት አሳይቶኛል። ከርቀት ያለ ቤተሰብ በተለይ ” የሕውሓት ማእከላዊ ኮሚቴ” አባል ያልሆነች ባለቆብ እናት ተይዞ ጊዜ መስጠት እንደማያስፈልግ እጅጉን ተረድቶኛል። የሀሰት ወሬውን ምንጭ እንድመረምር የመጀመሪያው ምክንያት ይሄ ነው።
የሀሰት ወሬዎቹ ከተሰራጩ በኃላ የኢሳት አስተያየት መስጫ ስልክ፣ የኢሳት ባልደረቦች የግል ሞባይል ፣ የጉዳዩ ዋና ባለቤቶች የግልና የቤተሰብ ስልክ መጨናነቅ ራሱን የቻለ ከባድ ስራ ነበር። ከአውሮፓ ፣ አውስትራሊያ ፣ ካናዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኢትዮጵያ የሚመጡት የስልክና ፅሁፍ መልእክቶች ፋታ የሚሰጡ አልነበረም። ህዝቡ የተሟረተባቸውን ወገኖቹ ድምፅ ለመስማት የሚያቀርበው ተማፅኖ መደበኛ ስራን ተረጋግቶ ለመስራት አያስችልም ነበር። ይህም እንደ ቁምጣ ያጠረንን ጊዜ ከመሻማቱም በላይ ከመሰራታዊ ጉዳያችን ለማናጠብ እና አጀንዳ ለማስቀየር በማሰብ እንደሆነ መጠርጠር የሚቻል ነው። ሁለተኛው ምክንያቴ ይሄ ነው።
በተለይ ይሄን ጥርጣሬ ያጠናከረልኝ የአንድ ተስፋ የቆረጠ የህውሓት የፌስቡክ ስኳድ እና ንፁሐንን እየጠቆመ የሚያሳስር የትግራይ ተወላጅ መመልከቴ ነው። ይሄ ሰው አማሪካ በስደት በነበረ ሰአት ኢሳት ውስጥ ለመስራት የነበረው ህልም ትልቅ ነበር። ሆኖም እባብ ልቡን አይቶ እንደሚባለው ያቀረበው ተማጽኖ በመክሸፉ ቂም እንዲቋጥር አደረገው።በዚህ ምክንያት ሲቆምም ሲነሳም፣ ቺቺኒያ ሲጠጣም ሲተኛም፣ በህልሙም ሆነ በቀን በኢሳት ዙሪያ ያሉ ሰዎች ያቃዡት ጀመር። ከማንቆርቆሪያ እስከ ብረት ድስት፣ ከቤት ኪራይ እስከ ሙታንታ ከኪሳቸው አውጥተው የገዙለትና የዘወትር የምሽት እንባውን የጠረጉለት ሰዎች ደግነት ረፍት ነሱት ።በአንድ በኩል ከልጅነቱ ጀምሮ የተነገረው ” የወርቅ ፍልቃቂ ዘሩ” በሌላ በኩል ማረፊያ ያጣች ወፍ የሆነ የመሰለው ስነ ልቦናው አልታረቅለት አለ። የገባበት ወለፈንዲ በሂደት ቅንቅን እንደበላው ግንድ ውስጡን ይቦረቡረው ጀመር። ሁለቱን ተቃርኖዎች ቁርስ ፣ምሳ እና እራት ያደረገው አእምሮው አይኑ ደም እስኪያረግዝ በጠበጠው።
እንደ እውነቱ ከሆነ በፀፀት ውስጥ መኖር በብረት ሰንሰለት የመገረፍ ያህል ከባድ ቅጣት ነው። እናም ይሄ ገደብ የለሽ በሆነ የበታችነት ስሜት የተሳከረ ሰው በቲውተር ገጹ ” የኢሳቱ ሲሳይ አጌና አሊ ቢራ መሞቱን ገለፀ” ብሎ ለመፃፍና ለመለጠፍ ሰአታት አልፈጁበትም። ለሰአታትም ቢሆን የገባበትን የሕሊና ቀውስ እና ደካማ ጐን ለመደበቅ ተጠቀመበት ። ይህም ሆኖ ከኢትዮጵያ ህዝብ ባህልና ግብረ ገባዊ እሴቶች ተኰትኩቶ አለማደጉን ሙሉ ለሙሉ መሸፈን አልቻለም። እንዲያውም የሐሰት መረጃው ከተሰራጨ በጥቂት ሰአታት ውስጥ ተቀብሎ ሲያሰራጨው አንዳንዶች የተጠረጠሩት የውሸት ፌስቡኩ ባለቤት ራሱ ሳይሆን አይቀርም የሚለውን ነበር። በተለይ አንድ ወግ የማያጣ ጓደኛችን ” ዳዊት ከበደ በእውኑ እና በህልሙ መሆን የሚፈልገውን ሰው በፌኩ አገኘው!” በማለት ለደቂቃዎች ፈገግ አስባለን። እስቲ ይታያችሁ ዳዊት ከበደ ሲሳይ አጌና ሲሆን! እኔም በፋንታዬ ” መብራህቱ ገ/እግዚአብሔር በረከት ስምኦን እንደተባለው?” በማለት ወጋችንን ዘለግ አደረኩት። መቼም ከእንዲህ አይነት የእእምሮ ባርነት እና ራስን ሆኖ ካለመገኘት ይሰውራችሁ ከማለት ውጭ ምን አይነት ትልቅ ምርቃት ሊገኝ ይችላል?

No comments:

Post a Comment