ባህር ከማል
የኢትዮጵያ ህዝብ የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ ካንገሸገሸው ሰንብቷል። ለዚህም የ1997 ብሄራዊ ምርጫ ውጤት በቂ ምስክር ነው።ድምጹን ተነጥቆ ከያኔ ጀምሮ አፉ ተለጉሞና ነጻነቱን አጥቶ ሲኖር ከርሞ ዛሬ ግን ከምንጊዜውም ይበልጥ ከሰሜን አስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስክ ምዕራብ፤መሃልን ጨምሮ ራሱ የህወሃት/ኢህአዴግ የጻፈውን “ህገ-መንግስት” መሰረት በማድርግ የመብት ጥያቄዎችን እያነሳ በሰላማዊ መንገድ የአሻፈረኝነትንና የበቃኝን ጩሀቱን እያሰማ ነው። ለዚህ ሰላማዊ ለሆነው የህብረተሰቡ የመብት ጥያቄ ግን ትክክለኛና አግባብ ያለው መልስ እንደመስጠት ፈንታ አንባገነናዊው የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት የሃይል እርምጃ በመውሰድ የንጹሃን ዜጎችን ደም እያፈሰሰ ነው።
የሃይማኖት ነጻነት ቤት-ክርስትያን ወይም መስጂድ መስራትን መፍቀድ ብቻ እንዳልሆነ፤የብሄር እኩልነት በራስ ቋንቋ መናገርና መዝፈን ብቻ እንዳልሆነ፤እድገት ለእርዳታ መሰብ ሰቢያ “ደረሰኝነት” እንዲያገለግል ጥራታቸውን ያልጠበቁ ህንጻዎችንና መንገዶችን መስራት ብቻ እንዳልሆነ ህዝቡ ከተረዳ ሰንብቶአል።
አንድ ማስሮ ልይዝ ከሚችለው በላይ ውሃ ሊይዝ እንደማይችል ሁሉ፤ህብረተሰቡ ግፉ በዝቶ ከሚችለው በላይ ሲሆንበት አምርሮ ማመጹ አይቅሬ ነው። እንኳንስ የአገዛዙ ቁንጮዎች ቀርቶ ሆድ አደሮቹንና ሎሌዎችን አያድርገኝ የሚያስብል ቀን መምጣቱ የማይቀር ቢሆንም እኛስ ለዚያን ቀን ምንያህል ተዘጋጅተናል?
ስልጣን ላይ ስላለው የህወሃት/ኢህአዴግ ጥፋትና አንባገነናዊነት የዕድሜውን ያህል ስንናገርና ስንወቅሰው ከርመናል። ለቀባሪ አረዱ እንዲሉ ህብረተሰቡ የሚያውቀው ከመሆኑም በላይ እየኖረውም ስለሆነ መደጋገሙ ጆሮ ከማዶንቆር አልፎ የትም አላደረሰንም።ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ያልሆኑ ግለሰቦች፤ድርጅቶችና መንግስታት ባዛሬው በ 21ኛው የኢንፎርሜሽን ዘመን ስለኛ አያውቁም ለማለት ባንደፍርም ማስታወሱ የአምባገነኑን ሞራል ለመስበር እጅግ ይጠቅማል።ለዚህም ጋዜጠኛ አበበ ገላው በሬገን ህንጻ ውስጥ የ8ቶቹ ቡድን ባካሄዱት የምግብ ዋስትና ስብሰባ ላይ የአለም ጋዜጠኞች፡ የአለም አቀፍ ድርጅትና መንግስታት መሪዎች ፊት በህወሃት/ኢህአዴግ አንባገነናዊ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ላይ ያሰማው ተቃውሞ በሥርኣቱ ላይ የፈጠረው የሞራል ወድቀት በቂ ማስረጃ ነው። የወደቀውን የስራቱን መሪ ሞራል ለማንሰራራት ከቁንጮዎችጀምሮ እስከ ሆድ-አደር ሎሌዎች እስክዛሬ ድረስ እንቅልፍ አጥተዋል። አንዳንዶቹም ራሳቸውን ለማግለልና ለተተኪው ሥርአት/መንግስት እንደልማዳቸው ሆዳቸውን ካሁኑ ለማዘጋጀት ይሁን ወይም ለማዘናጊያ በየፓልቶኩና ራዲዮ ፕሮግርማቸው ስርአቱን ሲወርፉ ተደምጠዋል።
ስለዝህ የዚህ የጎጠኛው አምባገነናዊ ሥረኣት ችግር ቀማሾች እኛው ስለሆን መፍትሄውንም የምናገኘው እኛው ነን።ከሌሎች መጠበቅ የዋህነት ነው።ከድል በኋላ ግን የወዳጅ እጥረት አያጋጥመንም።ለዝህም በጊዜ ብዙ ሳንጓዝ ከግብጹ ሁስኒ ሙባረክ፡ከየመኑ አሊ አብደላህ፡ከሊቢያው ጋዳፊ ተመክሮ አግኝተናልና።
ትግሉን ወደ ምንፈልገው ትክክለኛ አቅጣጫ ለመምራት ዝግጁ የሆነ ድርጅት ካልተገኘ ከዚህ ቀደም በዘውዱ ስርዓት ማክተሚያና በደርግ መውደቂያ ወቅት የተፈጠሩ ሁኔታዎች እንዳይገጥሙን ያሰጋል። በእርግጥ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት በሃገር ውጥትም ሆነ በውጭ በብዛት ባሉበት በአሁኑ ወቅት ከዚያን ጊዜ ጋር ማወዳደር ባይቻልም ከብዛታቸው አንጻር በጋራ የመስራትም ሆነ ወይም ለብቻ አውራ መሪ ድርጅት ሆኖ የመውጣት ሁኔታም እምብዛም ጠንክሮ ስለማይታይ ታሪክ በመጥፎ መልኩ ራሱን እንዳይደግም ያለው ስጋት ሙሉ በሙሉ ተወግዷል ማለት ያስቸግራል።
ከአንባገነኖች የሥልጣን ማቆያ መሠረታዊ ባህሪያት መካከል በውሸት ፕሮፓጋንዳ የራሳቸውን ከልት (cult) በመገንባት ፡ ሃይልንና የስለላ ተቋምን በመጠቀም ህዝቡን ፈሪ ማድረግ ናቸው። ስለሆነም ሀዝባችን በዚህ ፍርሃት ውስጥ ነው ያለው ፍርሃቱን የሚሰብርለት ይፈልጋል።በአንፃሩ ግን በተለይም ብዙ አማራጮች ባሉበት ነፃ በሆነው ዓለም/ሃገር እየኖርን ለዚያ ድምፁ ለታፈነው ህዝብ ድምፁ መሆን ሲገባን ሌላው ቀርቶ ሃሳብ ስንሰጥ እንኳን ስማችን እንዲጠቀስ የማንሻ ፤በብዕር ስም ብቻ የምንጠቀም ስንቶቻችን ነን።እዚህ ላይ የአጉል መስዋዕትነት አለአስፈላጊነትን ከግምት ውስጥ ሳላስገባ ቀሪቼ አይደለም፡ ለጋራ ጥቅምና ለሚፈለገው ለውጥ ስኬታማነት ከሆነ የራስን ማንነት ይፋ አለማድረጉ ከጉዳቱ ጥቅሙ ያመዝናል። የግል ጥቅም ከማጣት ፍራቻ ከሆነ ግን፡ ለኔ ለናንተ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነት ቀደም ሲል የሚፈለገውን መስዋዕትነት የከፈሉና አሁንም ለመክፈል ዝግጁ ሆነው አምባገናናዊውን ሥርአት ፊት ለፊት በመጋፈጥ በየእሥር ቤቶች (በታወቁና ባልታወቁ) በመማቀቅ ላይ የሚገኙት እነ እስክንድር ነጋ፡አንዱአለም አራጌ ርዕዮት አለሙ ኦልባና ሌልሳ በቀለ ገርባና ሌሎች ብዙ ስማቸው ያልተጠቀሰ የህሊና እስረኞች፡በየመስጂዱ ጩሃታቸውን በማሰማት ላይ ያሉ፡ሙስሊሞች ጋዳማትን አናስደፍርም በማለት በየእሥርቤት በመንገላታት ላይ ያሉ መነኮሳት ለዘመናት ከኖሩበት ቄዬያቸው ተፈናቅለው በህገራቸው ውስጥ ስደተኞች የሆኑት ምን ይሉናል?።
የህዝብ ፍርሃት ዘላለማዊ አይደለም በቃኝ ያለ ዕለት ማንም አይመልሰውም።ያንን በቱኒዚያ፤በግብጽ፤ በሊቢያ፤በይመን ህዝቦች አይተናል በሲሪያም እያየን ነው በሱዳንም ማየት ጀምረናልና።
ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ሉዐላዊነትና በህዝቦቿ ተከባብሮ አብሮ የመኖር አንድነት የሚያምኑ አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅቶች በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ቢኖሩም በአቅም ግንባታ ረገድ በተለይም ሃገር ውስጥ ያሉት ድርጅቶች ህወሃት በሸረበው ተንኩል ትርፋማ ያልሆኑ ድርጅቶችን(NGO) በተመለከተ በወጣው አዋጅ ተዳክመዋል።በአንጻሩ ግን ህወሃት/እህአዴግ ግን ከእፎርት (Endowment Fund For Rehabilitation of Tigray)፡ከህዝቡ በሚሰበስበው ታክስ፡ከሃያላን መንግስታት በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ከሚለመነው እርዳታና እኔና እናንተ ለቤተዘመድ ከምንለከው፡ከአባይ ቦንድ ወዘተ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በመሰብሰብ ለጊዜውም ቢሆን በገንዘብ ጭምር ጡንቻውን አዳብሮ እየገዛ ነው።እኛስ አማራጩ ያለን የፖለቲካ ድርጅቶችን፡የሲቪል ማህበራትን ፡አማራጭ የሚዲያ አውታሮችን በሞራልና በማተሪያል እየረዳን ነውን?
ከነባሮቸ የፖለቲካ ድርጅቶች ሌላ አዳዲሶችም በመፈጠር ላይ ቢሆኑም መሪዎቻቸው የረዥም ጊዜ ልምድ ያካበቱ ስለሆኑ ድርጅቶቻቸውን በመምራት ምን ማድርግ እንደሚገባቸው ጠንቅቀው ያውቃሉ ብዬ አምናለሁ።ችግራቸው ያቅም ማነስ ነው። ትብብር ይጎድላቸዋል። ትብብር ግለሰባዊና በየድርጅቶች መካከል ያለውን ያጠቃልላል።ድረጅቶች መሰረታዊ ባልሆኑ ልዩነቶች ላይ ላለመስማማት ተስማምተው የትግሉን አቅጣጫ ወደ ጎን ከማድረግ ይልቅ ወደፊት አድርገው በዋንኛው ዒላማ (target) ህወሃት/ኢህአዴግን በማስወገዱ ላይ ማነጣጠር ይኖርባቸዋል።ሊያግባቡአቸው የማይችሉ መሰረታዊ ልዩነቶች እንኳን ቢኖሩ በየ ግላቸው ስትራቴጂና ታክቲክ መሰረት ህብረተሰቡን አሳምነው ከጎናቸው በማሰለፍ ትግሉን መቀጠል እንጂ ትግሉ መሰረታዊውን ዒላማ (target) በፍጹም መሳት የለበትም።
አንድ የስፖርት ቡድን ተጫያቾችን ሲያዘጋጅ የጫወታውን ሜዳ አብሮ ማዘጋጀት ይኖርበታል ያለተጫዋች ሜዳ ያለሜዳ ተጫዋች ውጤት አይኖረውም ትርጉምም የለውም።እንድሁም አንድ የፖለቲካም ሆነ የሲቪክ ድርጅት ለትግሉ ስኬታማነትና ለተፈለገው ድል ለመብቃት ምቹ የትግል መድረክ ማዘጋጀት አስፈላጊ ነው።
እርግጥ ለተፈለገው ውጤት ለመብቃት በጋራ ለመስራት የሚቻለው መተማመን ሲኖር ብቻ ነው፡፡ጥርጣሬ ከበዛ ወደ ጥላቻ ስለሚለወጥ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።ጥላቻ ካለ ደግሞ እንኳንስ ለጋራ ዓላማ አብሮ መስራት ቀርቶ ለጉርብትናም ያስቸግራል።ልቅ የሆነ መተማመንም ለስርአተ-አልበኝነት የሚያጋልጥ ከመሆኑም ሌላ አንድነታችንን እንደጦር ለሚፈራው የህዋሃት/ኢህአዴግ ቀዳዳ መክፈት ስለሚሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል።ያልጠረጠረ ተመነጠረ የሚለው አባባል የሚሠራው እዚህ ላይ ነው።
የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት የግድ 90 ሚሊዮን ህዝብ በግንባር መስለፍ አይኖርበትም የተወሰኑ ቆራጥና በዓላማቸው ፅኑ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በቂ ናቸው።እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች፡ ፖለቲከኞች፤ጋዜተኞች፡የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች፡የኪነ-ጥበብ ሰዎች፤ምሁራን…ታሪክ የጣለባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ የኛን የተራ ዜጎቸን የሞራልና የቁሳቁሰ እገዛ ይፈልጋሉ።
በጦርነት ወቅት ሁሉም ወታደር ቢሆንም የግድ ሁሉም በጦርሜዳ ይውላል ማለት አይደለም።ከፈንጂ መርማሪ እስከ እስከስንቅ አቀባይ፤ከቁስለኛ አካሚ እስከ ወሬ ነጋሪ፤ከፕላን አውጪ እስከ በየእምነቱ ጸሎት አድራጊ ሁሉም የጦርነቱ ወይም የትግሉ ተካፋይ ጀግኖች ናቸው።እኛም ከነዝህ ባንዱ እንኳን በመሳተፍ ፍርሃታችንን በመስበር ከአያት ቅድመ አያት የወረስነውን ጀግንነታችንን ማደስ አለብን።ሁሉንም በፖለቲካ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው ላይ ከተውን ትግሉ ረዥም ይሆናል።ሁላችንም የድርሻቸንን ከተወጣን ግን ድርጅቶችና መሪዎቻቸው ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ ለመውቀስ ያመቸናል የአንባገነኖች ዕድሜም ያጥራል።
የትግሉ አንቀሳቃሾቸና ባለቤቶች ሃገር ውስጥ ያሉ ቢሆኑም ዳያስፖራ ኩሚኒቲ ለትግሉ አጋርነት ከፍታኛ አስተዋጽኦ ለማድረግ ብዙ አማርጮች ስላሉ ይህንን አማርጭ በመጥቀም ከህሊናና ከታሪክ ወቀሳ መዳን ይኖርበታል።ዛሬ የወቅቱ የህብረተሰቡ መሠረታዊ ጥያቄ የነፃነት ጥያቄና ሃገር የማዳን ጥያቄ ነው።ይህን ባንድ ጀምበር ጥልቀት መቀዳጀት የማንችልና ትዕግስታችንን የሚፈታተን ቢሆንም ለተፋጠነ ድል ትግሉ የሁላችንም እገዛ ይሻል።ዛሬ ሥረዓቱ ሎሌዎቹ/ሆዳሞች መልሰው ራሱን የሚፈታተኑበት አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ወቅት በፍርሃትና በዝምታ ተውጠን ከሌሎች ውጤት መጠበቅ አግባብ አላመህኑን መረዳት ይኖርብናል።
የፖሊቲካ ድርጅቶችና ሲቪክ ማህበራት መሪዎችና አባላት ከኛ የሚለዩት በትምህርና በተፈጥሮ ባገኙት ዕውቀትና ባካበቱት ልምድ እንጂ የሃገርና የህዝብን ጉዳይ በተመልከተ ከኛ ልዩ የሚያደርጋቸው ነገር የለም።ሀገርንና ህዝብን በተመለከተ ሁላችንም በታሪክ ፊት እኩል ተጠያቂዎች ነን።ስለዚህ ወደ ድርጅቶችና መሪዎቻቸው ጣት ከመቀሰራችን በፊት እኛስ የድርሻቸንን ተወጥተናል ወይ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልጋል።
የህግ የበላይነት የተረጋገጠባቸውና በዲሞክራሲያዊ መርህ በሚመሩ ሃገራት ግልጽነትና ተጠያቂነት ጉልህ ስፍራ ስላላቸው ዜጎች ለሚጠይቁት አገልግሎትም ሆነ ጥያቄ ምላሽ ማህኘት ይኖርባቸዋል።የነዝህ ሃገራት መንግስታት ግልጽና ሚዛናዊ በሆነው ውድድር ተመርጠው ስልጣን ስለሚይዙ ተግባራቸው ህዝብን ማገልገል ነው።ህዝቡ/ታክስ ከፋይ እንደ አንድ ኩባንያ ነው መንግስት የኩባንያው ተቀጣሪ ሥራተኛ ነው።ደሞዝ ከፋዮ ህዝቡ/ታክስ ከፋዮ ስለሆነ መንግስት የተጣለበትን ሃላፊነት ካልተወጣ ከስራ ይባረራል/በምርጫ ይቀየራል።ለዚህም ነው በነዚህ ሃጋሮች መንግስት የህዝብ ተቀጣሪ ስለሆነ ህዝቡን/ቀጣሪውን የሚፈራው።በተቃራኒው የህግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት ሃገር በተለይም በአምባገነኖች በሚመሩ ሃጋራት ህዝብ/ታክስ ከፋዮ መንግስትን ይፈራል።ቀጣሪው ተቀጣርን እንደመፍራት ማለት ነው።ይህ ነው እንግድህ በአሁኑ ጊዜ በሃገራችን እየተገበረ ያለው።ለወደፊቱ እንደዝህ ዓይነቱ እንዳይፈጠር አማራጭ የፖለቲካ ድርጂቶቻችንና መሪዎቻቸው ወደዚያ እንዳያመሩ ካሁኑ መገሰጥ ያለብን።ታዲያ እኛም የምፈለግብን ታክስ እየከፍልን/እየረዳን እንጂ መተቸት ብቻ በቂ አይደልም።ለዝህም ከወዲሁ መዘጋጀት ይኖርብናል።መጥፎም ሆነ ጥሩ ታሪክን በታሪክነቱ መዝግበን ለትውልድ ማስተለልፍ እንጂ በመጥፎ መልኩ ራሱን እንዲደግም መፍቀድ የለብንም።
አላህ ኢትዮጵያን ከነ ህዝቦቿ የጠብቃት።አሚን።
ባህር ከማል
bahirk@hotmail.com
No comments:
Post a Comment