ብሥራት ደረሰ
አለ ነገር፤ አለ ነገር፤
ቁልቁለቱን ወርደን ወንዙን ስንሻገር፡፡
የሚባለው ፉከራ ይሁን ቀረርቶ አሁን እዚህ ላይ ቢታወስ ይገባዋል፡፡ ሌላም አለ፡- ‹ጠርጥር ገንፎም አለው ስንጥር› የምንለው፡፡ ወያኔዎች ካለወትሮኣቸው እጅግ የተጨነቁ ይመስላሉ፡፡ ምን አገኛቸው ይሆን? እኔን!
ላለፉት 21 ዓመታት ምድረ ኢትዮጵያን እንዳላስጨነቁ ዛሬና አሁን በአንድ ሰው መታመም ወይም ከዚህ ዓለም ወደማይቀረው ወደዚያኛው ዓለም ማለፍ ምክንያት እንዲህ ገና ከአሁኑ ይይዙትንና ይለቁትን ይጡ? አይ የክፉ መጨረሻ! ለማንኛውም አጭሪቱን ‹መጣጥፌን› እነሆኝ!
ከመራጩ ሕዝብ የ99.666 ድምጽ አግኝቶ ከሦስት ተከታታይ ዙሮች ለሚበልጥ ዘመን ሥልጣንን ከሕዝብ በውዴታና በፍቅር የተረከበ የሀገር መሪ፣ ሕዝቡን በርካሽ ኑሮ እያምነሸነሸ ችግርንና ርሀብን ከሀገር በማጥፋት በታሪክ መዝገብ ብቻ እንዲታወሱ ያደረገ ፍቁር ወውዱድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲታመም ወይ በጣር ላይ ሲሆን ለሚወዳቸውና ለሚወዱት የገዛ ሕዝቡ እንዴት አይነገርም? ይህም ይቅር፡፡ ከ85 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ በፍቅር እየወደቀ እየተነሳለት ጠላት ያለው ይመስል ተኝቶ የሚታከምበትን ወይም ለዕረፍት የሄደበትን ሀገር መደበቅና በሕዝብ ሚዲያና እነፎርቹንን፣ አዲስ አድማስንና ሪፖርተርን በመሳሰሉ አድርባይ የወያኔ ዕንባ አባሾች አማካይነት የተሳሳተ መረጃ እየለቀቁ ሕዝብን ማወናበድ ምን ይባላል? ኧረ አቅል ጀባ!
ደግሞስ የኢትዮጵያ ሕዝብ የነበረችውን ብቸኛ መተንፈሻና አንጻራዊ እውነትን ማወቂያ ጋዜጣ ፍትህን እንዳትታተም መዝጋት ከምን ሥጋት የተፈጠረ ድንጋጤና ፍርሀት ነው? ይህችን ሚጢጢዬ የሕዝብ እስትንፋስ ዛሬ የዘጉ አዲሶቹ ጋላቢዎች ነገ ምን ያሳዩን ይሆን? በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሳድረኝም እንደሚባለው ሊሆን ይሆን እንዴ? እንዴ፣ ምን ዓይነት ነገር ነው ምዕመናን? ወዴትስ እያመራን ነው? መርከቢቱ ወዴት እየነጎደች ነው? የምን ዝም ዝም ነው? አንጯጯህም እንዴ?
በውነቱ መጠርጠር ደግ ነው፡፡ ግዴላችሁም እነዚህ ሰዎች የሆነ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ይሄኔ ነው አጣብቂኙን ይበልጥ ማጥበቅ፡፡ ለዚህ ደግሞ የቃዋሚው ጎራ ልዩነቶቹን አቻችሎ በፍጥነት በመቀራረብ ምስማር ማዋጣትና የወያኔን የሬሣ ሣጥን በትኩሱ ማጠባበቅ የሚገባ አሁን ነው ሰዓቱ፡፡ እነዚህ ሰዎች በዝግ ችሎት ሌላ የመከራ ዘመን እያሰናዱልን ነው፤ ሌላና እንዲያውም በእጅጉ የባሰ አሮንቃ ውስጥ ሊዶሉን እየተመሳጠሩብን ነው – አጋነንክ አትበሉኝና እንደ አካሄዳቸው መለስንና መንግሥቱን የሚያስናፍቅ ታላቅ ሤራ እየዶለቱብን ናቸው፡፡ ዛሬ አንዲቷንና ብቸኛዋን የሕዝብ ጋዜጣ እንዳትታተም ያደረጉ ሰሞኑን በቲሪሪም ቲሪሪም ዐዋጃቸው መለስን በሐጎስ የተኩ እንደሆነ ጉዳችን መፍላቱ ነው፡፡ ሌላ ሐጎስ የምንጫንበት ትከሻ እንደሆነ በጭራሻ የለንም፡፡ ሐጎስ ያልኩት በቅኔ ሕወሓት ለማለት ፈልጌ እንጂ አዲሱ የሕዝብ ሰው ፍትዊ ወይም ስንሻው ወይም ገመቹ አሊያም ሌላ እነዚህን መሰል ኢትዮጵያውያን የሕዝብ ወገኖች ሊሆኑ መቻላቸውን አጥቼው እንዳይመስላችሁ፡፡ በነመለስና በማፊያ ሥርዓቱ ምክንያት ጤናማ የትግራይና የኤርትራ ወንድምና እህቶቻችን በአዲሱ ኢትዮጵያዊ እግዜር-ሰጥ ወርቃማ መንግሥት ውስጥ ሥፍራ የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው፡፡ ከአንድ ማሕፀን የወጡ ልጆች መካከል እንኳን አንዱ ሞሽላቃ ሌባ ሌላው ለቃሉና ለእምነቱ ያደረ ግሩም ዜጋ ይሆናሉ፤ አንዱ በዶክትሬት የተመረቀ ምሁር ሌላው ኮብል ስቶን አንጣፊ ያልተማረ ይሆናሉ – የዛሬውን የወያኔን ‹ምሁራን› የኮብል ስቶን ድንጋይ ፈላጮችን ሳናስብ፡፡ የቀን ጉዳይ ነው ዘመዶቼ፡፡ ቀን ሁሉን ያስተካክላል፡፡ አሁን ቢጨልም መንጋቱና እውነት ቦታዋን መያዟ አይቀርም፡፡ በጥንቱ አማርኛ – ይህ ሁሉ ቁሣካላዊ እውነታ ነው እንደ አካሄድ – ወደድንም ጠላንም በውስጡ ማለፍ ያለብን፡፡ አንድ ክስተት ስለጠላነው አይቀርም – ስለወደድነውም አይመጣም፤ ጠቢቡ ሶሎሞን ‹ቦ ጊዜ ለኩሉ›(ለሁሉም ጊዜ አለው) ያለውም ለዚህ ነው፡፡
ለማንኛውም ጠርጥር ገንፎም አለው ስንጥር፡፡ የነጻነትን ዘመን በተዓምር ከተዓምረኞች ከመጠበቅ ይልቅ የኛም አስተዋፅዖ ይታከልበት፡፡ ‹አንተው እንዳመጣህ አንተው መልሰው› ማለቱ በራሱ መጥፎ አይደለም፡፡ ግን እኛም ኃላፊነት አለብን፡፡ በዱላ መቀጥቀጥ ምርጫችን ከሆነ ፈጣሪም ያን አያሳጣንም፡፡ ምርጫችን ነጻነት ከሆነ ደግሞ የድርሻችንን እንወጣና እርሱ ይታከልበታል፡፡ ቃሉም ‹እሹ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል› እንጂ ደንዝዛችሁ እኔን ብቻ ጠብቁ አላለም፡፡ አሁን እንደሚስተዋለው ከሆነ ሁላችን ደንዝዘናል፤ የነካንን እንጃ፡፡ ባለቤት ካልጮኸ ደግሞ ጎረቤት ሊረዳ አይችልም – ፀጥታችን ያስፈራል – ወያኔ የተስማማንም ይመስላል ለየዋህ ወይም ለብልጥ ተመልካች፡፡ ስለሆነም በድብቅ እየተሰለቀ፣ እየተቦካና እየተጋገረልን ያለውን በርበሬና ሚጥሚጣ እንረዳ፡፡ ይህን አስነጣሽና አቃጣይ ድግስ በቶሎ ማክሸፍ ከእያንዳንዱ ሀቀኛ የሕዝብ ወገን ይጠበቃል፡፡ ይህ ዕድል ካመለጠን በርግጥም የመቶ ዓመቱ የቤት ሥራ በተገቢው መንገድ እየተጓዘ ነው ማለት ነውና ከጥቂት ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያዊ የሚባል ሰው ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የምንላት ሀገር ራሷ ስሟም ይጠፋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሰዎቹ ክፉኛ ተጨንቀዋልና ባላሰቡትና ባልጠበቁት መንገድ እንድረስላቸው፡፡ ለፍልስፍናና ለዲስኩር እስካሁን ያሳለፍነው ጊዜ ከበቂ በላይ ነው፡፡ ሃያ አንድ ዓመት ተናግሮና አስፈራርቶ ለአንድ ሳምንት ወደ ተግባር ሊገባ የማይችል የፖለቲካ ስብዕና ከነአካቴው ባይፈጠር ይሻለዋልና ንድፈ ሃሳባዊ ዝግጅቶቻችንን ሁሉ ወደተግባር የምንለውጥበት ጊዜ ላይ መድረሳችንን ማወቅ አለብን፡፡ ዕውቀት ያለው በዕውቀቱ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ – ‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ› ብለን ሆ ብለን ባንድነት እንነሳ፡፡ ስንነሳም የዘርና የጎሣ፣ የሃይማኖትና የሀብት፤ የትምህርትና የሌላም ልዩነቶቻችንን ወደጎን በመተው በአንድ የኢትዮጵያዊነት ትንሣኤ የጋራ መንፈስ ሥር ሆነን ሊሆን ይገባል፡፡ ቅድሚያውን ለሀገር ትድግና እንስጥ፡፡ የበሰበሰውን የዛሩን መንግሥት ግንብ እነሌኒን ናቸው በድንገት ፍርስርሱን ያወጡት፡፡ የወያኔ ግንብ ከመበስበስ አልፎ በራሱ ጊዜ እየተናደ ነው፡፡ ነገር ግን እንደጥንቱ ጠንካራ እየመሰለን እንፈራዋለን፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ሥልታዊ አቀራረብ እንጂ ይሄ ከሕዝብ የተነጠለ፣ ከራስጌው እስከ ግርጌው በሙስናና በወንጀል የተግማማ የነጨቡዴ ሥርዓት በቀላሉ እንደሚንኮታኮት መገመት አይከብድም፡፡ እንሞክር፤ ስንሞክር እናየዋለን፡፡ የነጻነቱን ትግል መጀመር የሚጠብቁ ሚሊዮኖች አሉ፤ በቁጭትና በእልህ እየተምቦገቦጉ ያሉ፡፡ ግን ማንና የት ይጀምር? የሚሌኒየሙ ትልቅ ጥያቄ!
No comments:
Post a Comment