ABE TOKCHAW
ይቺ ጨዋታ አሁን በቅርቡ “ቅምሻ” ብለን የተቃመስናት አንድ ጨዋታ ናት። የዛኔ ለእርስዎ ካቃመስኩዎ በኋላ ጨዋታዋ ስትጠናቀቅ ለተወዳጇ ፍትህ ጋዜጣ ልኬያት ነበር። መንግስቴ “ፍትህ የለም” ብሎ ከልክሎ ሳትታም ቀረች።
እንጀምር፤
ባለፈው ሳምንት ፍትህ ጋዜጣችን በፍትህ ሚኒስቴር ታግዳ ነበር። ምነው? ሲባል “ለሀገር ደህንነት ስጋት የሚሆን ወሬ ይዛለች” ተብሏል። እኔ በበኩሌ ያ የሀገር ደህንነት ስጋት የሆነ የፍትህ ወሬ ምን እንደሆነ ለማየት ቸኩያለሁ። ለማንኛውም በዚህኛው ሳምንት የማርያም መንገድ ከተሰጣት ብዬ ይቺን ሰድጃለሁ። ይቺ ፅሁፍ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አብዝታ የምትጨነቅ ናትና ቢያንስ ለዚች ፅሁፍ ሲባል ፍትህ ከእገዳ ነፃ ትሆን ይሆናል የሚል እምነትም አለኝ…!
የዛሬ አስራ አምስት ቀን “ጠቅላይ ሚኒስትሬ ሆይ ከወዴት አሉ” ብዬ አብዝቼ መጮኼን እርስዎ ወዳጄም እኔም እግዜሩም እናስታውሳለን። ከዛ ጊዜ ጀምሮም በየቀኑ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሬ ዝም አላልኩም። በዛ ሰሞን የኮሚኒኬሽን ሚኒስትራችን እጅግ የተከበሩ ደራሲ እና ባለስልጣን አቶ በረከት ስምዖን በስንት ጊዜያቸው በቴሌቪዥን መስኮት ያለሁበት ሀገር ድረስ መጥተው “አታስብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደህና ናቸው፤ ብቻ ሀኪም እረፍት ስለሰጣቸው ለጊዜው ስራ ላይ አይኖሩም” ሲሉ በማባበል እና የሰዉን ወሬ በማስተባበል ነገሩኝ።
ከእርሳቸው በፊት አቦይ ስብሐት፣ ከአቦይም በፊት የጠቅላዬ ምክትል አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስለ ህመማቸው ትንሽ ትንሽ ነግረውኛል። ከሁሉም በፊት ግን በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ መክፈቻ ላይ የሴኔጋሉ ፕሬዘዳንት ናቸው ስለ ሀገሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ህመም በይፋ የተናገሩት። በእውነቱ ይሄ በጣም ሆድ የሚያስብስ ነው። ለመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማናቸው? የእኔ አይደሉምን!? ከእኔና ከሴኔጋሉ ፕሬዘዳንትስ ስለ እርሳቸው የሚጨነቅ የሚቀርባቸውስ ማነው? በእውኑ እኔ በቅጡ ሳልሰማ የውጪ ሰው “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታመዋል እግዜር ቀላሉን ያድርግላቸው” ብለው ሲናገሩ በሰማሁ ግዜ ባይተዋርነት ተሰምቶኝ ያነባሁትን እንባ ሞታቸውን ስሰማ እንኳ አላነባውም።
አንድ ወቅት ክብር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በፓርላማው ጠቅላይ ሚኒስትሩን የጠየቋቸው ጥያቄ ትዝ አለኝ። “እርስዎ የእኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ኖት ለውጪ ሀገር ጋዜጠኞች እና ባለስልጣናት ስልጣንዎን የሚለቁበትን ጊዜ ተናገሩ ሲባል ከውጪ እንሰማለን… ለመሆኑ ለእኛስ ለምን አይነግሩንም? እርስዎ የእኛ ጠቅላይ ሚኒስትር አይደሉም እንዴ?” ብለዋቸው ነበር። አቤት ያኔ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያሳዩት ፈገግታ! በነገራችን ላይ ፈገግታቸው ራሱ እኮ ከቆሎ ተማሪ ቅኔ የበለጠ ብዙ ፍቺ አለው። ብቻ በዛች ፈገግታቸው አቶ ቡልቻን ብዙ ነገር አሏቸው። ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሬ በፈገግታቸው ሲቀኙ አናያቸውም። ምክንያቱም እረፍት ላይ ናቸውና! በርግጥ ህመማቸውም፣ እረፍታቸውም ቅኔ ሆኖብናል። እሰይ የኛ ባለ ቅኔ… እንበላቸው ይሆን!?
የሆነ ሆኖ ግን ከድሮም የጠቅላይ ሚኒስትራችን ነገር ለውጪ ሰዎች እንጂ ለእኛ ሽፍንፍን መሆኑ ይደንቃል። አንዳንድ አበወራዎች አሉ፤ እነዚህ አባወራዎች ለቤተሰባቸው ግልፅ ካለመሆናቸውም በተጨማሪ ንፉግ እና ተቆጪም ናቸው። ለውጪ ሰው ግን “ልነጠፍልህ ልዘርጋልህ?” በማለት ትህትናቸው መከራ ነው። ማህበረሰባችን ታድያ ለእንዲህ አይነት አባወራዎች አንድ ስም አውጥቶላቸዋል። “የውስጥ ቀጋ የውጭ አልጋ” የሚል።
እናልዎ ወዳጄ የጠቅላይ ሚኒስትሬን በጠና መታመም ከሀገር ውስጥ “ባሉካዎቻችን” ሳይሆን ከውጪ ሃይሎች ቅድሚያ መስማቴ በጣም ነበር የተሰማኝ።
እርግጥ ነው ኢሳት ቴሌቪዥን ከሁሉም ቀድሞ ታማኝ ምንጮቹን በመጥቀስ የጠቅላይ ሚኒስትሩን በጠና መያዝ ወሬ አድርሶን ነበር። ይህንንም በየፌስ ቡኩ በርካቶች ተቀባብለውታል።
በነገራችን ላይ ባለፈው ጊዜ የኢቲቪው የህትመት ዳሰሳ ፕሮግራም ላይ ከኛም በላይ ትጉህ እና ልማታዊ የሆኑት ጋዜጠኞቻችን “አዲስ አድማስ” የተባለውን ጋዜጣን ጠቅሰው “ፌስ ቡክን የመሰሉ ማህበራዊ ድረ ገፆች ላይ የሚወጣ መረጃ የማይጨበጥ እና የማይታመን ነው።” ብለው የማጣጣል ስራ ሲሰሩ ተመልክቻለሁ። ልክ ይህንን ሳይ “ይሉሽን ባልሰማሽ ፌስ ቡክን ባላማሽ” ስል ለቴሌቪዥኔ ተረትኩላት። የምር ግን አሁን ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የፌስ ቡክን መረጃ ሲያንቋሽሽ ሰዉስ ለምዶታል፤ እግዜሩ ራሱ ቢሰማ ተገርሞ ያባራል…? ለማንኛውም የፌስ ቡክ መረጃዎች ከየትም የሚመጡ አይደሉም። ራሱ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሚጠቅሳቸው እነ ቢቢሲ እነ ሮይተርስ አንዳዴም እነ ዋልታ ሳይቀሩ እንደ ምንጭ ይጠቀሳሉ። ታድያ የሮይተርስን እና የዋልታን ዜና ኢቲቪ እኔ ራሴ ካልነገርኳችሁ የማይጨበጥ ምንጭ ነው ብሎ ማለቱ በእውነት ይሉኝታ ማጣት አይደለም? (አረ “ሼ…!” አሉ የኛ ሰፈር ልጆች)
ከሁሉ የገረመኝ የጠቅላይ ሚኒስትራችንን በጠና መያዝ መንግስታችን ያንን ያህል ጊዜ ያቆየው ለምንድነው? የሚለውን ኢቲቪ ደራሲ በረከት ስሞንን ጠቅሶ ሲመልስ “የኢህአዴግ የጫካ ባህሪ ነው” ብሎ ሲናገር ሰምቼው ይሔ ቴሌቪዥኔ ተበላሽቶ መሆን አለበት እንጂ መንግስትን ያህል ነገር “እስከ አሁንም በጫካ ስርዓት ነው የሚተዳደረው፣ በጫካው ልምድ ነው ያለነው” ብሎ መናገር ትልቅ ሽሙጥ ነው። ብዬ ተበሳጭቻለሁ።
ለማንኛውም አሁንም የአቶ መለስን መያዝ አስመልክቶ በርካታ ጭምጭምታዎች እየተሰሙ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ህመም የተነሳ ቤተመንግስት አካበቢ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒሰትር ማን ይሁን? በሚል ጭንቀት የባለስልጣኖች ግርግር እንደተጧጧፈ ነው። ኧረ እንደውም እንደሰማሁት ከሆነማ… ላለፉት በርካታ ወራት ምንም ያልተባሉ ሰላማዊ የመጅልሱ ተቃዋሚዎች ላይ እርምጃ እና እርግጫ ጠየተወሰደው የቤተ መንግስቱን ግርግር ሰዉ ልብ እንዳይለው እና ትኩረት እንዳይሰጠው ተብሎ ነው እየተባለ ነው።
እንግዲህ በጫካው ደንብና ህግ መመራት ችግሩ ይሄ ነው። ነገሮችን በግልፅነት የሚነገርበት ሁኔታ ከሌለ የህብረተሰቡ የመገመት መብት ሊከበርለት ይገባል እያሉም በርካቶች እያወጉ ነው።
የሆነ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ምን ውስጥ እንደገቡ እስከ አሁንም የጠራ ወሬ አልሰማንም። በምትኩ የተምታታ ዜና እያዳመጥን ነው። ቅዳሜ እለት ለህትመት የበቃው እንግሊዘኛው “ፎርቹን” ጋዜጣ መለስ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን አስመልክቶ ፊት ለፊት ገፁ ላይ አስነብበቦን ነበር። በስንተኛው ቀን ደግሞ ሪፖርተር ጋዜጣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጪ ሃገር በእረፍት ላይ ናቸው ብሎ ዘግቦልናል። (በቅንፍም ሪፖርተር ውጪ ሀገር… ብሎ ሲል፤ መንግስተ ሰማያትን ይሆን ወይስ ገሀነመ እሳትን ይሆንን? ሲሉ ግምታቸውን ተናግረዋል። እኔም እና ጠቅላይ ሚኒስትሬ ከገነት ውጪ የት ሊሆኑ ፈለጋችሁ!? ስል ተቆርቋሪነቴን አሳይቻለሁ።) የፎርቹንን እና የሪፖርተር ጋዜጣን ነገር ልብ ብለን ስናየው ግን ዘጋቢዎቻችን እየዘገቡልን ሳይሆን እያወዛገቡን ነው የሚመስለው።
የመንግስት ሰዎችም ሀቁ ይሄ ነው ብለው ሊነግሩን አልተቻላቸውም። እዝች ጋ ይሔኔ እርሳቸው ቢሆኑ ኖሮ… ብለን አጥብቀን እንቆጫለን! “አጎደሉን እኮ አጎደሉን እኮ…” ብለንም በሀዘን ዜማ እናንጎራጉርላቸዋለን።
አሁን በቅርቡ በዲሞክራትነታቸው የሚታወቁት የጋናው ፕሬዘዳንት “ሚልስ” በድንገተኛ ህመመም መሞታቸው ሲሰማ አንዳንዶች ኧረ ይሄ ነገር የታይፕ ግድፈት ሊሆን ይችላል ብለው ተከራክረው ነበር። የምርም ግን እንደሚወራው ጠቅላይ ሚኒስትራችን እስከ አሁን ድረስ በህይወት ካሉ “እግረ ቀጭን እያለ እግረ ደንዳና ይሞታል” የሚለው የሀገራችን አባባል ሰራ ማለት ነው።
በነገራችን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለመጨረሻ ጊዜ በሙሉ ግርማ ሞገሳቸው የታዩት አሁን ድንገት ከሞቱት የጋናው ፕሬዘዳንት ጋር ነበር። በአሜሪካው ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ጋባዥነት በ ግሩፕ ስምንት ሀገሮች ስብሰባ ላይ ጎን ለጎን ተቀምጠው ተቀምጠው ታይተዋል። ምነው እንኳ የዛኔ አይደል እንዴ… ያ አበበ ገላው የተባለ ጋዜጠኛ ጠቅላይ ሚኒስትራችንን “አንተ” ብሎ ጠርቶ ያንን ሁሉ ነገር የተናገራቸው። ይኸው ከዛ ጊዜ በኋላ “መድፍ ተደግፈው መፅሀፍ ሲያነቡ የነበሩ” ጠቅላይ ሚኒስትራችን በጋዜጠኛው የቃላት መድፍ ጉዳት ደረሰባቸው” እያለ ሀገሬው ሲቧልት መቼም የሰው አፍ ክፉ ነው ይኸው ተይዘው የት እንዳሉ እንኳ በቅጡ አይታወቅም። ከርሳቸውም አልፎ ተርፎ አጠገባቸው ተቀምጠው የነበሩት ምስኪን ፕሬዘዳንት ለሞት በቁ። “ለሀጢያን የመጣ ለፃድቃን ይተርፋል” ሲሉ የተረቱም አሉ።
እውነት ግን ጠቅላይ ሚኒስትራችን የሆነ ነገር ውስጥ ተደብቀው እየሰሙን ይሆን!? ወይስ በሰማይ ከአባታቸው ዘንድ ቁጭ ብለው እየፀለዩልን ይሆን!? የምር እኮ ግራ የሚያጋባ ነው። የጋናው ፕረዘዳንት ሞትም ሆነ ህመም እንዲሁም ተተኪያቸው ወዲያውኑ ነበር ለሀገሬው ህዝብ የተገፀው የእኛ ግን…
በኢትዮጵያ ታሪክ ከዚህ በፊትም ምኒሊክ የሞቱ ጊዜ ለሶስት አመታት ሞታቸው ተደብቆ “አሉ እረፍት ላይ ናቸው” እየተባለ ህዝቡ “ንጉስ ሆይ ሺህ አመት ይንገሱ” እያለ ቀጥ ለጥ ብሎ ተገዝቶላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከአይናችን ከተሰወሩ ሁለት ወር ሊጠጋን ነው። ታድያ አሁን ማን እየመራን ነው? በእውኑ መልካሙ እረኛችን እርሳቸው አልነበሩምን!? ከእንግዲህስ ማን ይሆን በእርሳቸው እግር የሚተካው ወይስ እውነትም “ከሽርሽሩ” መልስ ይመጡና እንደቀድሞው “አንቀጥቅጠው” (አንቀባረው ማለቴ ነው!) ይመሩን ይሆን። ለማንኛውም ስለ ጠቅላይ ሚኒሰትራችን ቁርጥ ያለውን የሚነግረን እስክናገኝ ድረስ ግራ መጋባታችን ቀጥሏል። እናም ሁላችንም በየጓዳው እያንጎራጎርን እንገኛለን።
ሞተዋል እንዳልል ቀብርዎን አላየው፤
አሉም እንዳልልዎ ድምፅዎን አልሰማው
ምን ብዬ ልናገር ለጠየቀኝ ሰው…?
እኔ በበኩሌ ዛሬም በጠቅላይ ሚኒስትሬ ጉዳይ እየተጨነቅሁ መሆኑን የእርሳቸውን ነገር ለአፍታም እንኳ ቸል የማልለው ጉዳይ መሆኑን ለማሳወቅ እወዳለሁ። እርሳቸው ለእኛ ጊዜ እንደዚህ አልበሩም። በየሄድንበት፣ በየገባንበት እና በየ ወጣንበት ይከታተሉን ነበር። እርሳቸው እንኳ ባይሳካላቸው ለእያንዳንዳችን የሚከታተለን ሰው መደበውልን ነበር። ታድያ እርሳቸውን የሚከታተል አንድ ሰው እንዴት ይጠፋል? ስላሉበት ሁኔታስ በቅጡ የሚነግረን አንድ እንኳ እንዴት አይገኝም?
በመጨረሻም
ፕሬዘዳንታችን
የኦሎምፒክ ቡድናችን ወደ ለንደን መጓዙን ሰምተናል። የዘንድሮ ኦሎምፒክ ቡድናችን በጣም ተስፋ የተጣለበት እንደሆነም ተነግሮለታል። በርካታ ወጣት አትሌቶችን ማካተቱ እና እስከዛሬ ተሳትፈንበት የማናውቀው ውሃ ዋና ላይ መሳተፋችን ውጤቱን የምንጓጓለት እንዲሆን አድርጎታል። በዚሁ አንቀፅ ለቡድናችን መልካም ውጤት እመኛለሁ።
የኦሎምፒክ ቡድናችን ሽኝት በብሔራዊ ቤተ መንግስት የተደረገ ጊዜ በዛን ሰሞን ብዙ ሲወራባቸው የነበሩት ክቡር ፕረዘዳንታችንን ተመለከተናቸው ነበር። ታድያ አንድ ወዳጄ ክቡርነታቸውን ሲመለከት “እንዴ…!” ሲል ከጣራ በላይ ጮክ ብሎ ደነገጠ። ምነው? አለነው ማ….? እኛ! እርሱም ሲቀጥል፤ “እኔ የምለው ክቡርነታቸው ዳይቨርት አደረጉት ማለት ነው!?” አለን። ምኑን…? ስንለው ምንም ሳይመልስልን። “ምስኪን ጠቅላይ ሚኒስትሬ!” ሲል ተቆጨ። የሰዉ ሰምና ወርቅ መከራ ነው።
ወዳጄ ይበሉ እስቲ ለማንኛውም ቸር እንዲገጥመን አጥብቀው ይፀልዩ!
እኔ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሬ ዝም አልልም። እርስዎም ቢያንስ በፀሎትዎ አይርሷቸው። “መንግሰተ ሰማያትን ያውርስልን!” ይበሏቸው።
አማን ያሰንብተን!
http://www.abetokichaw.com/2012/07/29
No comments:
Post a Comment