ገለታው ዘለቀ
የ ኣቶ መለስን መሄድ ተክትሎ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ባሉ ባለስልጣናት ዘንድ ምን ሊፈጠር ይችል ይሆን? ወታደሩስ ምን ያስብ ይሆን? መቼም ህዝቡ ለውጥ በሃይል ፈልጓልና ከሳቸው መሄድ በሁዋላ ሊነሱ በሚችሉ ትርምሶች ጊዜ ብዙዎች የሚሰጉበት የብሄር ግጭት ይፈጠርስ ይሆን? በሚሉ ሃሳቦች ዙሪያ ጥቂት ግምቶች እንስጥ።ለነዚህ ከባድ ጥያቄዎች መልስ ባይኖረንም እንገምት።
የኣቶ መለስ መሄድ በፓርቲዎቻቸው ውስጥ ምን ኣንድምታ ይኖረው ይሆን?
በእንበል ገበያ ሆነን ኣሁን ኣቶ መለስ ቢሞቱ የሳቸው ሞት በኢህኣዴጎች ዘንድ የኣንድ ሰው ሞት ተደርጎ ሊወሰድ ኣይችልም። ተጽእኖኣቸው እጅግ ጉልህ ነው።ሁሉ በሁሉ የሆኑ ስልጣን ሁሉ ያለ ልክ የተማከለበትን ስርዓት የፈጠሩ ናቸው። ባለፉት ሃያ ኣመታት ከህወሃትና ኢህኣዴግ ትንሽ ሻል ይላሉ ኣገር ይወዳሉ የሚባሉትን በሙሉ ኣጭደው በልተው ጨርሰዋል። ሃይል ቀስ እያለ በጃቸው የገባ ሲሆን ድርጅቶቹ ያለሳቸው ባዶ ናቸው። በመሆኑም ኣቶ መለስ ቢሞቱ ድርጅቶቹ ኣንድ ታጋይ ነው የሞተብን ማለት ኣይችሉም። ኣዋቂ ናቸው እንዲባሉ የተሻለ እውቀት ያላቸውን ኣባረው መተማመን የሌላቸውን በእውቀት የደከሙትን ወደ ላይ ሰብስበው የኖሩ ሰው ናቸው።ብዙዎቹ ባለስልጣናት የሚሰራውን እንኳን የማያውቁ ኣሻንጉሊቶች ናቸው። በሳቸውና በቅርብ ርቀት ባሉ ባለስልጣናት መካከል ሰፊ የስልጣን ልዩነት የነበረ ስለሆነ ይህ ክፍተት ኣቶ መለስ ድንገት ቢያርፉ ተናቦ የሚመጣውን ህዝባዊ ኣመጽ ተቋቁሞ የሚቀጥል መንግስት መመስረት ኣያስችላቸውም።
ኣውሸልሽለው ሊጀምሩት ቢሞክሩም ሩቅ የሚያስኬድ ከባቢ የላቸውም። የኢትዮጵያ ህዝብም ይህን ተንኮል በጅጉ የሚቃወመው የሚያሳምጸው ሲሆን በልመናና በሰባዊ መብት ጥሰት ጆሮውን የያዘው ኣለማቀፍ ማህበረሰብም ቢሆን በዚህ የጉልቻ ልውውጥ የሚረካ ወይም የሚደለል ኣይሆንላቸውም። ኣንዱ ይሄ ነው። ሌላው ደሞ በመካከለኛ ስልጣን ላይ ያሉን የኢህኣዴግ ሰዎች ስናይ ኣሁን ኣቶ መለስ ቢሞቱ ወደ ተለያየ ጥግ የሚበተኑ ይመስላል። ኣንዳንዶቹ የነበራቸውን ሚናና መጋላጥ(exposure) እያዩ የነብር ጅራት ጨብጠናልና ያበጠው ይፈንዳ ኣንዱን ተክተን እንቀጥል ከሚሉት ተስፋ ከቆረጡት የላይኛው ባለስልጣናት ዘንድ ወስዶ የሚጥላቸው ሲሆን ኣንዱ ደሞ ለውጥ ቢመጣ ነጻ ፍርድ ቤት ቢቆም ኣይበላኝም የሚል ኣንጻራዊ የሆነ የተሻለ መተማመን ያላቸው ደሞ ከሚመጣው ለውጥ ጋር ይሰለፋሉ። ኣንዳንዶች ደሞ በግል የሰሩትን እየቆጠሩ ኣገር ጥሎ መጥፋትን ኣማራጭ ያደርጋሉ። ሌሎች ደሞ በመሃል እየሰፈሩ ለውጡን ለመደገፍ ዋስትና የሚሰጣቸውን ፍለጋ ኣይናቸው መንከራተቱ ኣይቀርም።
ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚባሉት ድንገት መሪያቸው ቢሄዱ ያንን በደህና ቀን የሰበሰቡላቸውን ፓርላማ ሰብሰብ ኣርገው ታጋይ ቢሞት ታጋይ ይተካል ብለው ቀለል ኣርገው እንቀጥል የነብር ጅራት ጨብጠናል ሲሉ እስካሁን ሲሞኙ የነበሩ የብኣዴንና ኦህዴድ ሌሎች የዘውግ ፖለቲከኞችም ምናልባት የፍርሃትን ሼል ሰብረው የሚወጡበትን ሁኔታ ሊፈጥርም ይችላል።
ወደታች የኢህኣዴግን መሰረት ስናይ ደሞ ባዶነው። በምርጫ 97 ጊዜ ኢህኣዴግ በኣዲስ ኣበባ ያገኘው ኣጠቃላይ ድምጽ በከተማዋ ውስጥ ካሉ የድርጅቱ ኣባሎቹ ቁጥር በጅጉ ኣንሶ ታይቷል ይህ የሚያሳየው ራሳቸው ኣባላቱ ኣልመረጡትም ነበር ማለት ነው። እነዚህ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኣመራሮች የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው ጊዜ የሚጠብቁ ኣይነት በመሆናቸው ከኣቶ መለስ በሁዋላ ለሚነሱ የህዝብ የለውጥ ጥያቄዎች ተባባሪ እንደሚሆኑ መገመት ይቻላል።
ያም ኣለ ይህ ኢህኣዴግ የተባለው ድርጅት ጥርስ የሌለው ኣንበሳ ኣርገው ስለፈጠሩት ከሳቸው መሄድ በሁዋላ በነበረበት ሊቀጥል ኣመጻዎችን ሊቋቋም ኣይችልም። በመሃከለኛ ና ባንዳንድ ለውጥ ሲፈልጉ ነገር ግን ፈርተው በቆዩ ባለስልጣናት ዘንድ የሚነሱ የ እንለወጥ ጥያቄዎችን ለማስተናገድም ካልሞከሩ ህዝባዊ ማእበል ይጠርጋቸዋል።
ወታደሩ ምን ያስብ ይሆን?
ለግምታችን መነሻ የኢትዮጵያን ወታደር ተፍጥሮ በሁለት ከፍለን እንየው። ይህ ተቋም ገና ሲመሰረት ቀድሞ የነበረውን ወታደራዊ ተቋም ሙሉ በሙሉ ኣፍርሶ በሲቪል ታጋዮች (guerilla fighters) የተገነባ በመሆኑ ከወታደራዊ ስሜቱ (Military sentiments) ይልቅ የታጋይነት ስሜት የዋጠው ተቋም ነው። ይህ ተቋም ሲቋቋም ከሌሎች ተቋሞች ባልተለየ ሁኔታ ነበር። ሲቪል ታጋይ የኢሃዴግ ሰራዊት ኣሸንፎ ኣዲስ ኣበባ ሲገባ ገሚሶቹ ታጋዮች ኮትና ሱሪ እየለበሱ በየተቋሙ የሃላፊነት ቦታ ሲይዙ ገሚሶቹ ደሞ የወታደር ልብስ ለበሱና የወታደር ማእረግ እየተጫነላቸው ወታደር ተባሉ። ሁለቱም ቡድኖች በልብስና በስያሜ ይለያዩ እንጂ ህወሃት ኢህኣዴግ የተባለው ድርጅት ኣባሎች ኣብረው የተዋጉ የትግል ጓዶች ናቸው። እንዴውም ኣገሪቱን ሲመሩ ኣብረው እየተደባለቁ የሲቪሉንም የወታደሩንም ስራ ይሰሩ ነበር።
ኣንዳንዶቹ ሲቪል ተብለው የተመደቡ ታጋዮች ጠንከር ያለ ጦርነት ሲመጣ ኣዛዥ የሆኑበት ሁኔታም ታይቷል። የመቶ ኣለቃ ግርማ ወልደጌዎርጊስ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ በቃ መቶ ኣለቅነቱን ትቼዋለሁ እንዳሉት ማለት ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ስነ ልቦናው ከዚሁ ከሲቪል ነጻ ኣውጭነቱ ጋር የተደባለቀ ተቋም በመሆኑ ገለልተኛነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንኳን ለማሰብ የማያስችል ተፈጥሮ እንዲኖረው ተደርጓል። ተዋግቶ የመጣለትን ድርጅት የሚጠብቅ የዘብ ስራ ያለበት የሚመስል ኣይነት ተቋም ያስመስለዋል።
ነጻ የሆነ ሃገራዊ ተቋም እንዳይሆን ተፈጥሮው ራሱ ይከለክለዋል ማለት ነው። ውስጣዊ ማንነቱ የህወሃት ክፋይ ኣካል መስሎ ተፍጥሯል። ከሃያ ኣመት በፊት ህወሃት ኢህኣዴግ ይባል የነበረው ሰራዊት ኣሁን የኢትዮጵያ መከላከያ ይባል እንጂ ታእታይ ቅርጹ ያው የድሮው መልኩ ነው። ከተፈጠረም በሗላ የነበሩት የበፊቶቹ ታጋዮች እረፍት ሲሹ ኣዲስ የሚገቡትን ኣመራሮች ባምሳላቸው እየቀረጹ ነው የሄዱት። የግምገማቸው ኣካሄድ፣ ስብእናቸው፣ የኣስተሳሰባቸው ቅኝት ስነ ልቦናቸው ኣጠቃላይ ኣሰራራቸው በዚያው መንፈስ እንዲቀጥል ጥረዋል። ይህ ጉዳይ ሃገራዊ ራእይ ያለው ተቋም እንዳይሆን የኣንድ ቡድን ጠባቂነት ስሜት እንዲያዳብር ሊያደርገው ይችላል።
ሌላው ሁለተኛው የዚህ ተቋም ተፈጥሮ ዘውጌነት ከሌሎቹ ሃገራዊ ተቋማት ሁሉ ጎልቶ የሚታይበት መሆኑ ነው። በተለይ በመካከለኛና በላይኛው ርከን ያሉ ባለስልጣናት በከፍተኛ ሁኔታ የኣንድ ባህላዊ ቡድን ሰዎች በመሆናቸው ተቋሙን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ኣስይዞታል። ይህ ተፈጥሮው በብሄር ላይ ለተቃኘው ፖለቲካ በጣም ስስ ስሜት እንዲኖረውና ገርጋራ እንዲሆን ያደርገዋል።
ከዚህ ተፈጥሮው የተነሳ ለውጥ ሲመጣ የስርወ ኣገዛዝ (statues quo) ጠባቂነት ስሜት እንዲያይልባቸው ያደርጋል።
ታዲያ ይህ ተቋም ዘውጌነት ይታይበት እንጂ በኣቶ መለስ በጥንቃቄ ሲታይና ሲመታ የነበረ ተቋም ም ነው። ኣቶ መለስ ስጋታቸውን ለመቀነስ ጥበቃቸውን ለማጠናከር ሲሉ ኣንዳንድ ደፋርና ተቋሙን ወደ ንጹህ ወታደራዊ ተቋምነት የመቀየር ኣገራዊ ራእይ ያላቸውን በየጊዜው መተው ጨርሰዋል። ኣሁን ያለው በሳቸው ጭንቅላት የሚንቀሳቀስ ነው። ይህም በመሆኑ እሳቸው ድንገት ቢለዩ ባዶነት የሚሰማው ከባድ ክፍተትም የሚፈጥር ነው።
ታዲያ ጦሩ በመዋቅር ደረጃ እንዲህ ኣይነት ተፍጥሮ ቢኖረውም ወደታች በሄድን ቁጥር በተለይ በዝቅተኛና ተራው ወታደር ኣካባቢ ጊዜ ጠብቆ ሊፈነዳ የሚችል እምቅ ብሶት እንዳለ ይሸታል። ይህ እምቅ ብሶት በህቡእ መናበብ ቆይቶ ምናልባትም ህዝባዊ ኣመጽ ሲነሳ ተቃውሞው ሊፈነዳም ይችላል። እንደ ሲሪያ ያለ ተከታታይነት ያለው ህዝባዊ ኣመጽ ቢነሳ እንደ ሲሪያ ወታደር የማይሆንባቸው ጉዳዮች ኣሉ። ታጋዮች ይህን የዘውግ ነገር ወደሰራዊቱ ሲዘረጉ መገንዘብ የነበረባቸው ነገር እነሱ የሚቆረቁራቸው የዘውግ ጉዳይ ተራውን ወታደርም እንደሚቆረቁረው ቀስ ብሎም የከፋ ሁኔታ ሊያመጣ እንደሚችል ማየት ነበር ።
የግብጹን ወታደር ስናይ በሃብት የበለጸገ ባንጻራዊ መልኩም ነጻ የነበረ ተቋም በመሆኑ ለውጡን ለመቆጣጠር ኣስችሎታል። የኢትዮጵያ ወታደር ድንበር ዘለል ለሆኑ ውጊያዎች ጠንካራ መሆኑ ሃቅ ነው። ይህ ጀግንነት በደሙም ስላለ ነው። በሃገር ውስጥ ለሚነሱ ብጥብጦች ግን ምን ሚና እንደሚኖረው በሚገባ በተግባር ኣልተፈተሸም። በ1997 ጊዜ የነበረው ኣጠቃላይ ነገር ያፈዘዘው ቢመስልም ካሁን በሁዋላ ለሚነሱ ህዝባዊ ኣመጻዎች ዝም ብሎ የሚያይ ይሆናል ማለት ያስቸግራል። ራሱ መንግስት የጫረው የዘር እሳት እዚያም ሊቀጣጠል ይችላል።
በኣጠቃላይ ጦሩ እንደ ተቋም ሲታይ በጥብቅ የተያዘ ቢመስልም የታችኛውን የበሸቀውን ክፍል መናበብ ያጠፋዋል ማለት ዘበት ነው። ልዩ ጦር በማዘጋጀት ህዝባዊ ኣመጾችን ለመቋቋም የሚፈልጉ ቡድኖች ቢነሱ ዋናው ጦር ዝም ብሎ የሚያይበት ሁኔታ መንምኗል።
ህወሃት የዘራው የዘር ፖለቲካ በህዝቡ ውስጥ ምን ያህል ሰርጾ ይሆን?
የእውነትኛ ሃገር ወዳድ የቅን ኢትዮጵያዊያን ስጋት ይሄ ነው። ኣሁን ይሄ መንግስት ድንገት ድርምስ ቢል ተከፋፍለን እንጫረስ ይሆን? የሚል ስጋት ኣለ። ይህን ሃሳብ ለመመለስ ሰፊ ጥናት ያስፈልጋል።የሆነ ሆኖ ዝም ብለን ኣንዳንድ ሃቆችን እያነሳን ብንጥል ምንም ኣይደል። በ ሁለት ምክንያቶች የዚህ የዘር ፖለቲካ ጉዳይ በህዝቡ ዘንድ የሚፈራውን ያህል ሰርጾ የግባ ኣይመስልም።
1) ህዝቡ በሃይል የዘር ፖለቲካውን ጠልቱዋል
መቼም እንደዚህ መንግስት በኣብዛኛው ህዝብ የተጠላ ያለ ኣይመስልም። ለዚህ ጥላቻ ትልቁ መሰረት የኢኮኖሚ እድገት ያለመኖሩ ድህነቱ ወዘተ. ኣይደሉም። ዋናው ከህዝቡ መንፈስ ጋር የተጋጨው የዚህ የዘር ፖለቲካ ጉዳይ ነው። ይህ ተቃውሞ እየከረረ ቀጥሎ መታየቱ ኢትዮጵያ የሆነ የፖለቲካ መተረማመስ ቢገጥማት ህዝቡ በዘር ልዩነት ተንስቶ የሚጨፋጨፍ ኣይሆንም ብሎ ለመናገር ዋቢ ይሆናል።
2) ከፍተኛ የኣንድነት ስሜት በትውልዶች ውስጥ ዘልቆ ገብቱዋል
ኣሁን በህይወት ያለውን ኢትዮጵያዊ እስቲ በ ሶስት ከፍለን እንይ። ኣንደኛው በተለምዶ ያ ትውልድ እያልን የምንጠራው ሲሆን ምናልባትም እድሜው ካምሳዎቹ ጀምሮ ወደ ላይ ያለውን ማለት ነው። ይህ ትውልድ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሳይንሳዊ ለማድረግ የጣረ ግን ደሞ ብዙ መሰናክሎች የገጠሙት ትውልድ ነው። ያ ትውልድ ሲፈጠር ከጎኑ ኣብሮ ያደገ በጥባጭ ቢኖርበትም በ ዴሞክራሲና በ እኩልነት በኣንድነት ስሜት የተቃጠለ ነው። ይዞት ያደገው የኣንድነት ስሜቱ ለፍትህ ያለው ጥማት ለሃገሪቱ የዴሞክራሲ ትግል የመንፈስ ልዕልና ሰጥቶታል። ይሁን እንጂ በስትራተጂ ጉድለትና በሚገባ ካለመደራጀቱ የተነሳ እስካሁን የልቡን ኣላገኘም። ያ ትውልድ ከሱ ዝቅ ባሉት ከሃያ ኣምስት ኣመት ኣካባቢ በላይ ከ ሃምሳ በታች ባሉት ዘንድ እስካሁን የፖለቲካውን የዴሞክራሲውን ትግል በሚመለከት ተሰሚነት ያለውና ተጽእኖ ያለው ትውልድ ነው።
የዴሞክራሲ ትግሉንም በዋናነት በዚሁ ትውልድ መንፈስ የተቃኘ ይመስላል። ታዲያ ያ ትውልድ ኣጥብቆ የያዘውን የኣገር ኣንድነት ጥያቄ በህይወት እያለ የሚይስክደው ኣይኖርም። ከጎኑ ብቅ ያሉት የዘር ፖለቲካ ኣቀንቃኞችን በ እልህና በቁጣ እያየ የኣንድነት ስሜቱን ሲስብክ ይታያል። ያ ትውልድ በቀጣዩ ትውልድ ዘንድ የዚህችን ምድር የፖለቲካ ሩጫውን ይፈጽም ዘንድ በ ኣክብሮት የሚታይና ራእዩን ይፈጽም ዘንድ የተለቀቀ ይመስላል።
ዋናው ነገር ጠንካራ የሆነው የኣንድነት መንፈሱ ወደቀጣዩ ትውልድ በመተላለፉ በህይወት እያለ የዘር ፖለቲካ የሚፈለገውን ያህል እንዲሰርጽ (internalize) ኣላስቻለውም። ከመካከለኛው ትውልድ ዝቅ ያለው ለጋው ትልድም ያባቶቹንና የታላላቅ ወንድሞቹን ምክርና ፈለግ ስለሚከተል የህወሃት የዘር ፖለቲከ ባለፉት ሃያ ኣመታት የተደከመለትን ያህል የህዝቡን የኣንድነት መንፈስ የሰበረ ኣይመስልም።
ሌላው ቀርቶ በዚህ በዘር ፖለቲካ በቀላሉ እንይዘዋለን የተባለው ያልተማረው ገበሬ እንኳን የተማረ ይግደለኝ እያለ ልጆቹን የሚሰማ ሆኖ ተግኝትዋል። እነዚህ እንደ ኣረም ከዚያ ትውልድ ጋር የበቀሉትን ቡድኖች የሚቀበል ሳይሆን ያኔ የተነሳውን የመሬት ላራሹን ጥያቄ ያነሳውን ልጁን ዛሬም መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል ብሎ ይጠብቃል። በዚህ መሰረት በሃገራችን የሆነ ፖለቲካዊ ትርምስ ቢፈጠር በዘር ተለያይቶ የሚነሳ ችግር ዝቅተኛ ሊሆን እንደሚችል ልንገምት ያስችለናል።ይህ ማለት ግን ላለፉት ሃያ ኣመታት የተዘራው ዘር ምንም ተጽእኖ የለውም ለማለት ኣይደለም። በደንብ ኣለው። ይሁን እንጂ የሆነ ክፍተት ቢፈጠር የሚፈራውን ያህል ችግር እንዳይፈጠር የሚያስችል ዋስትና ኣለን ለማለት እንጂ። ላልታቀደ ህዝባዊ ኣመጽ መነሳት ይህ የዘር ፖለቲካ መሰናክል ቢመስልም ሃገሪቱ ያልሆነ የፖለቲካ ትርምስ ውስጥ ብትገባ ከባድ የዘር መተላለቅ እንዳይከሰት የሚያደርጉ መሰረቶች ኣሉ ለማለት ነው።
በለውጥ ጊዜ ሊከሰቱ የምችሉትን ችግሮች ለመቀነስ የኢትዮጵያ የዴሞካሲ ሃይሎች ምን ያድርጉ?
ኢትዮጵያ የለውጥ ባቡር መንዳት ከጀመረች ውላ ኣድራለች። በርግጥ ባቡሩን የሚያሰጉ ችግሮች ኣሉ። እነዚህን ችግሮች ለመቀነስ የሃላፊነት ስሜት ካላቸው ሃይሎች የሚጠበቅ ዋና ነገር ኣለ ይሄውም ዋስትና ነው። በዘውግ ፖለቲካ በታመሰ ስርዓት ውስጥ የታቀፉ ሰራተኞች ወይም የተነካኩ ሃይሎች የሚመጣው ለውጥ በስነ ልቦና ወይም በኣካል የሚቀጣን ይሆናል ብለው የሚሰጉ ኣሉ። እነዚህ ሃይሎች ኣያሌ ሊሆኑ ይችላሉ። ታዲያ ከተቃዋሚው ጎራ ቆይ ግዴለም ዴሞክራሲ ይምጣ ፍርድ ቤት ይቁም ዋጋህን ታገኛለህ በማለት ማስበርገጉ ላሃገሪቱ የመጀመሪያ የዴሞካሲ ስርዓት ለማቆም ጠቃሚ ኣይመስልም። ይልቁን ኣዲስ የሚመጣው ለውጥ ምህረትን ይቅርታን መሰረት ኣድርጎ የሚቆም መሆኑን መስበክ ይሻላል። ርግጥ ነው ይቅርታና ምህረት ዋጋ ያስከፍላል ይሁን እንጂ የመጀመሪያውን መሰርት ስንጥል በዚህ ላይ ካልተመሰረተ ኣስቸጋሪ ይሆናል። ይህ ዋስትና የማሳየቱ ጉዳይ የሰጋውን ኣካል ስነ ልቦና ወደ ኣንድ ጥግ ሊሰበስበው ይችላል። ከሁሉም በላይ ደሞ የሚመጣውን ለውጥ የሚደግፉ ሰራዊቶች ይሆናሉ።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ
ቸር ያሰማን
ገለታው ዘለቀ
geletawzeleke@gmail.comhttp://www.ecadforum.com/Amharic/archives/3527
No comments:
Post a Comment