እኔም እንደ ኢቲቪ ወሬ በችርቻሮ ጀምሪያለሁ። ትላንትና ልብ ብላችሁ እንደሆነ ኢቲቪ ነብሴ አንድ የአቶ በረከትን መግለጫ ሶስት ይሁን አራት ዜና አውጥቶለት ነበር። ይሔ ዜና በችርቻሮ ይባላል። እኔስ ከየት እማራለሁ ታድያ… ለነገሩ የምር የማይታለፍ ጉዳይ ሆኖብኝ ነው። ስለዚህ በቀጥታ ወደ አቶ በረከት መግለጫ እንሂድ…!
ትላንት አቶ በረከት ስምዖን ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት ካነሱት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የሙስሊም ወንድሞቻችንን ተቃውሞ ነበር።
“የአክራሪ ሙስሊሞች ጥያቄን በተመለከተ መንግስት እስካሁን ድረስ አስተዳደራዊ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቦ በህብረተሰቡ እንዲመከሩ ሰፊ ስራ ሲሰራ ቆይቷል። የአፍሪካ ህብረት ስብሰባን ለማወክ ያደረጉት ጥረትም በመንግስት ብስለት የተሞላበት ጥንቃቄ ከሽፏል” ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ በረከት ይህንን ሲሉ ቴሌቪዥን የሚመለከተው ህብረተሰብ በርካታ ጥያቄዎችን እጠየቃቸው ነበር። ዳሩ የቴሌቪዥን ተናጋሪ አፍ እንጂ ጆሮ የለውምና አልሰሙም። እስቲ እኔ ጥያቄውን ላስተጋባውና ጆሮ ባይኖራቸው ኔትዎርክ እና አይን ይስጣቸው ብለን ፀልየን እንዲያነቡት እናድርግ!
የሙስሊም ወንድሞቻችን ተቃውሞ እየተደረገ ያለው አወሊያ ግፋ ሲል ደግሞ አንዋር መስጊድ ነው። መንግስት “ብስለት የተሞላበት” በሬ፣ ኩኪስ፣ እና የተለያዩ ምግባ ምግቦችን ሰረቃ እና ንጥቂያ ያካሄደው ከአወሊያ እና ከመርካቶው አንዋር መስጊድ ነው። (በነገራችን ላይ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ እንዳኢታወክ በሚል ሌሊቱን የተከናወነው ብስለት የተሞላበት ተግባር ይሄ ነበር። እንዲህ ነው እንጂ ብስለት! ብለው ያድንቁ እና እንቀጥል) የሙስሊም ወንድሞቻችንም ጥሪ እዛው ነበር። የአፍሪካ ህብረት ስብሰባው ደግሞ ሳር ቤት ነው። ታድያ መርካቶ እና አስኮ በሚደረግ ጉባኤ እና ሰደቃ ፕሮግራም የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ እንዴት ነው የሚስተጓጎለው…!? ተስብሳቢዎቹ የመጡት ለሶላት ነበር እንዴ!? ብለን ጥያቄ አንድ አንላለን።
እኔ የምለው ጋሽ በረከት እርስዎ ሙስሊም ወንድሞቻችንን “ለማህበረሰቡ አስመክርን እንጂ ምንም አስተዳደራዊ እርምጃ አልወሰድንባቸውም” ብለው ከመናገርዎ በፊት እኮ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ራሱ ጮክ ብሎ ወደ ሰባ ምናምን የሚሆኑ ሙስሊም ወደጆቻችንን እንደታሰሩ በኩራት ነግሮናል። ከመግለጫዎም በኋላ በነበረው ዜና ተጨማሪ ሙስሊሞች መታሰራቸውን የራስዎ ቲቪ አውርቶልናል። በፌስ ቡክ ላይም በርካቶች የተገረፈ ገላቸውን በፎቶ አሳይተውናል። ምክሩ ይሄ ነው ማለት ነው…? ማሰር እና መግረፍስ ምክር ከሆነ አስተዳደራዊ እርምጃ ሲወሰድ ምን ይሆን የሚደረገው…!? ጥያቄ ሁለት ይበሉልኝ!
በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “ጥቂት አሸባሪዎች” እየተባለ ዜና ሲሰራ ተመልክተናል። በአንፃሩ ደግሞ በየ አርቡ እያየን ያለነው ትዕይንት ሰዎቹ ጥቂቶች አለመሆናቸውን በብዛታቸው፤ አሸባሪም እንደማይመስሉም፤ በሰላማዊ እና ማራኪ ተቃውሞቸው እየታዘብን ነው። ጥአቄው ይብቃኝ ይልቅስ…
እመክራለሁ
“ጥቂቶች…” እየተባለ በኢቲቪ ደጋግሞ ስለተነገረ ብዙሃኑን ጥቂት ማድረግ አይቻልም። ሰዎች ለምን? ብለው በጠየቁ ቁጥር “አሸባሪ” ማለትም አያዋጣም። እውነት እውነት እላችኋለሁ ዱላ በበዛ ቁጥር ደንዳና ያደርጋል። እና ተዉ!
ለማንኛውም ዛሬም የሙስሊም ወንድሞቻችን ተቃውሞ ቀጥሎ ውሏል። ተቃውሞው በፍፁም ፀጥታ እጅ ለእጅ በመያያዝ የተደረገ ሲሆን ሃምሳ ሺህ የሚሆኑ ሙስሊም ወንድሞቻችን ተካፋይ እንደነበሩ ሰምቻለሁ!
በመጨረሻም
ፍትህ ጋዜጣ ታግታ ዋለች
ተወዳጇ ፍትህ ጋዜጣ በዛሬው እለት ታትማ መውታት ሲገባት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት “እንዳናትም ታዘናል” በሚል ሳይትሙ ማደራቸውን በኋላም በዛሬው እለት አዘጋጆቹ ሄደው በርካታ ሙግት ከተሟገቱ በኋላ ዛሬ መታተም መጀመሯን እና ነገ ለገበያ እንደምትውል ተመስገን ደሳለኝ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ለጥፎልናል።
by Abe tokchaw
No comments:
Post a Comment