መካሪዎ ሕሊና አገሬ
ጡር አይሁንብኝና ጠቅላይ አቶ መለስ የታደሉ ነዎት! እውነቴን ነው የለበጣ ወይም የአሽሙር አይደለም። እውነቴን ነው። “ሰው የተወለደበትን እንጂ የሚሞትበትን አያውቅም” ይላሉ እነዚያ ፈረንጅ ጓደኞችዎት። ሰሞኑን በሚናፈሰው ወሬ የሚሞቱበት ቀን ተተንብይዋል አሉ። ምንኛ ታድለው! ለንስሐ ጊዜን ማግኘት የመሰለ ነገር የለም። የት እንደሚሞቱም ሳያውቁየሚቀሩ አይመስለኝም። ስለመታደልዎ ወደኋላ እመለስበታለሁ አሁን ስለ ውስጣዊ ሕመም ላንሳ።
ታመሙ መባልን ስሰማ አባይን ሳይገድቡልን የት ሊሄዱ ብዬ ሰጋሁ። የሕመምዎን ምንነት ስረዳ “ጉድ አልኩኝ!” ጉድ ስል በእንግሊዝኛው ለማፏጨት ብዬ አይደለም በመገረም እንጂ። ሕዝብን ከሕዝብ በማጣላት፤ በሃይማኖት በማጋጨት፤ አንድ የነበረችውን አገር በመበጣጠስ ሥራዎ 21 ዓመታት ቆይተዋል። ይህ የአገርና የሕዝብ ነቀርሳ መሆንዎ የአደባባይ ምስጢር ነው። ነቀርሳ!
ነቀርሳ ምንድነው የሚያደርገው? ውስጥ ያለውን ጤነኛውን አካል ቦጥቡጦ ለሞት ያደርሳል። በኢትዮጵያ ላይ ያደረሱት ግፍ በጤናዎት ላይ እንደደረሰው በሽታ ነው። በኢትዮጵያ ላይ የተከሉት ነቀርሳ በሕዝቧ ትግል ተመንጥቆ ኢትዮጵያ ጥንት እንደነበረች እርስዎ ለድንጋይ ፈለጣ ባስመረቋቸው ሳይሆን በሙያቸው ተሰልፈው በሚገነቧት ልጆቿ የተሻለ ደረጃ ላይ ትደርሳለች። የጊዜ ጉዳይ ነው። እርስዎ ግን ጊዜው አብቅቶልዎታል። አጋዚ ዘብ ቆሞ ሞትን አይከላከልልዎትም። ያ ያሸሹት በቢሊዮን የሚቆጠር የኢትዮጵያ አንጡራ ሃብት መድኃኒት አይፈጥርልዎትም። ከእንግዲህ ፓርላማ ገብተው እንዳይደነፉ የጋዜጠኛ አበበ ገላው ተግሣፅ አደብ አስይዞታል። ከእንግዲህ አይቻልዎትም። ብዙ የማይቻልዎት ነገር አለ። “አልሞትኩም ብለው አይዋሹም”።
ምርጥ የፈጠራ ሥራ ለሠሩት ሽልማት ሊሰጡና ሙገሳና አበራታች ንግግር ሊያደርጉ አልቻሉም። የነፃይቱን ጎረቤት አገር የደቡብ ሱዳንን የነፃነት ቀን ለማክበር አልተቻለዎትም። የአፍሪቃ ኅብረትን ስብሰባ ለመክፈት አልተገኙም። ከእንግዲህ ብዙ ይቀርብዎታል። በጣም ብዙ። ብቸኛ ነዎት!!! አጎብጓቢ እንጂ አጃቢ የለዎትም። የአልጋ ቁራኛ ሆነው የቀረዎት ትዝታ ብቻ ነው። የተቃዋሚዎች ጩኸት! በየሰሌዳው ላይ ከቅንድብዎ በላይ የተሳለው ቀንዳማ ምስልዎት። በሚኩራሩበት አደባባይ ላይ የሽምቅ ተዋጊ ጀግንነትዎ የከሰመበት የዓለም መሪዎች ስብሰባ። ያስራቡትና በርሃብ የቆሉት የትግራይ ሕዝብ። በትግራይ ሕዝብ የሰለጠኑበትን ግድያና ውሸት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያለመታከት ማከሄድዎ። የትግል ጓደኞችዎን አንድ ባንድ ማግለልዎ። ሌላም ሌላም … ቅዠት በቅዠት እንደሚያደርግዎት አልጠራጠርም። ቢሆንም እድለኛ ነዎት! የመሞቻ ቀንዎትን አውቀውታል። ግፍ አይሁንብኝና እኔም አውቄ እየተጠባበቅሁ ነኝ። እድለኛ ነዎት።
እድለኛ እንደሆኑ ደጋግሜ ተናግሬአለሁ። ለምን እንደሆነ ግን አልነገርኩዎትም። አጠቃለው ከመሄድዎት በፊት ልንገርዎት ክቡር ጠቅላይ መለስ። ሞትን ከማንም በላይ ያውቁታል። በየንጹሃኑ ቤት፤ በየአደባባዩ፣ በየእስርቤቱ ሲልኩት ይላክልዎት ነበር። ለካ ሞት ከሃዲ ነው ልበል ጌታውን አይምርም? ጊዜውን ጠብቆ እሱንም አይለቅም። ግን እድለኛ ነዎት እውነቴን ነው! “እኔን ያየህ ተቀጣ… ሥጋ ፈራሽ ነው… ለዚህ አጭር እድሜ ብላችሁ ክፉ አትሁኑ” ብለው ለመምከር እድሉ አለዎት። ያቺ የሚዋዷትን ”ይቅርታ” የሚሏትን ቃል ተጠቅመው የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ይጠይቁ! የሜዳ ጓዶችዎትንም ስለካድኳችሁ ጥፋተኛ ነኝ ብለው ምህረትን ይለምኑ። የኔ መንገድ የሰይጣን መንገድ ነው ብለው በጎሣ የበላይነት ወርቅ ነህ ብለው ያሞካሹትን የትግራይን ሕዝብ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ሁሉ አንድ ነው ማንም ከማንም አይበልጥም ብለው ጥፋተኝነትዎን ይግለፁ። (የትግራይ ሕዝብ ይህንን ያውቃል ግን ሊያሳስቱት የሞከሩት መሆንዎን ብቻ እንዲያረጋግጡ ነው እንጂ) በእግዚአብሔር ባያምኑም እንኳን ከተኙበት እየተኛ፣ መርፌ ሲወጉ አልሞት እያለ፣ ማደንዘዣ ቢደረግልዎት እስኪነቁ የሚጠብቅዎት ሞት ሁሉን እንደሚያደላድል እየታዘቡት ስለሆነ ከእግዲህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ፍቅር ይተዉለት። መከፋፈልን ያውግዙ። እኔ ያመጣሁትና የፈጠርኩት ነውና ከእኔው ጋር ይዤው እሄዳለሁ ብለው እነኚያ ያደናበሯቸውን ከብቶች አገር የጋራ ነው ብለው ይምከሩ። ይህ መቼም አይጠፋዎትም። አገር የጋራ ስለነበር ነው እርስዎ መሃል አገር ያደጉት። ኦሮሞው ወይም አማራው ትግሬ ነዎት ብሎ አላባረርዎትም። የእናት ጡት ነካሽ ሆኑ እንጂ!
እድለኛ ነዎት በውነት! ለልጆችዎንና ለባለቤትዎ ምክር ሰጥተው ለመሄድ እድሉ አለዎት! ገንዘብ ያለ አገርና ሕዝብ ዋጋ እንደሌለው ይምከሯቸው። በውሃ ፈንታ አፈር የሚያቁር ግድብ፤ ልማትዎ በስኳር ስካር ያበደ ታሪክዎት የእንቧይ ካብ መሆኑን ምግብ በጡጦ ከሚመገቡበት ማረፊያ ተጋድመው እያሰቡ ሲተክዙ የገላመጡት የሚንቅዎት ጊዜ ላይ መውደቅዎ እየተሰማዎትም ስለሆነ ተመክሮዎን እነበረከትን ሕይወት አይበረክትም አያሉ ይምከሯቸው። ጣት እንቆርጣለን የሚለው ምላስዎት መላወስ ሲችል ወያኔዎችን በሰላም “እጅ ስጡ” በሏቸው። እነሱም እኮ ቃሬዛ ላይ አልወደቁም እንጂ በድናቸው ነው እየተደናበረ ያለው። አገር ቆርሶ ድንበር በማሳጣት ቀዳሚና ተወዳዳሪ እንደሌለዎት ሁሉ የሕዝብ ንብረትን በመመለስ መንፈስዎ እረፍት ያግኝ፣ እርስዎም ይረፉ! አዎን ይረፉ!!! ሞትዎን በመመኘት ሳይሆን ከስቃይዎት እንዲገላገሉ በማሰብ ነው።
ስቃይ ስል ትዝ አለኝ። ስለ ስቃይ ትምሕርት ሳያገኙ አይቀርም። አገሪቱ ነርሶች እንጂ ዶክተሮች አያስፈልጋትም ያሉት ትዝ ይልዎታል? እርስዎ በሥልጣንዎና በተዘረፈ ገንዘብ አውሮጳ ድረስ ሄደው በመዳን የሕዝቡን ስቃይ ሊያራዝሙበት እየታከሙ ይገኛሉ። ሕዝቡ በጠኔና በበሽታ ምን ያህል መሰቃየቱን አሁን ተረዱት? ከሆነ ስለ ዶክተሮች አሁን ምን ይላሉ? እርግጥ እኔም ስለ ዶክተሮች እንደርስዎ ችግር አለብኝ። እንደርስዎ (እንደ ፕሮፌሰር አስራት የአዕምሮ ሀኪሞችን) የተማሩትን በመጥላት ሳይሆን የፓለቲካ ሊቅ ነን የሚሉ ሊጦች ያቦኩት ርዕዮተዓለም ተከታዮችን ነው።
መቼም ፓርላማዎት ውስጥ ከ500 በላይ ሊጦች ሲያቦኩ ኖረዋል። ፓርላማዎት ሕግን ማፅደቅ እንጂ እርስዎ በል ካላሉት ሕግን መከተል አይችልም። የፊዚካል ጉዳይ ሆኖብዎት ነው በዘንድሮ የፓርላማው ፊዚካል… ይቅርታ…ፊስካል… (ይቅርታና ፊስካል ኹለቱም የርስዎ ማኅተም ያለባቸው ቃላት ናቸው) የፊዚካል ጉዳይ ሆኖብዎት የፓርላማው ፊስካል አልዘጋም ያለው። ሕጉን ተከትሎ ሰኔ 30 እንኳን ፓርላማው ሥራውን አላቆመም። ሊጦች ያልኩበት ምክንያት ለዚህ ነው።
ወይ የነበርዎት ጡንቻ! ፍርጥሙ ፈረጠ ማለት ነው? መቼም ይኽንን የምልዎት ኹለት ምላስ ስላለዎት አንዱ ሲያገግም ኹለተኛው አልደነፋም አይልምና ነው። ለመሆኑ ዘንድሮ የመቃብር ሥፍራዎት የት ነው የታረሰልዎት? መቼም ለዐረቦች፣ ለሕንዶች፣ ለምኖች እያሉ ሸጠው ጨርሰውታል፤ እስክናስመልሰው ድረስ!
መቼም ምላሶች እንጂ ጆሮ አልሰጥዎት፤ የየመስጊዱ “ኣላህ ወኧኣክበር” ይሰማዎታል? የየገዳማቱን “የሚያደርጉትን አያውቁምና መንገዱን አሣያቸው” የሚለውንስ? ልብ ያድርጉ መንገድዎ ወደሞት እንዲሆን አይደለም፤ ከሞት እንዲድኑ እንጂ! ከታሪክ የሞት ሞት! እድለኛ ነዎት! ውነቴን ነው!
ሙባረክን ያስታውሱታል፣ አይደለም? ለፍርድ በቃሬዛ የቀረበው። እኔ መቼም ጤናውን ይስጥዎት ነው የምለው። ምክንያቱም ጀግኖቹ ከዋሉበት መድረክ አንድ ጊዜ ቀርበው ላይዎት እፈልጋለሁና። የጫካው ጀግንነትዎን ከባልደረቦችዎ ሰምተናል። በዓለም አደባባይ አንገትዎን መስበርዎን ታዝበናል። አዎን ጀግኖቹ እነ አንዷለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ ከቆሙበትና አንገት ካልደፉበት ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቀርበው ላንዴና ለመጨረሻ መንታ ምላስዎት ምን እንደሚል ለመስማት እወዳለሁ።
ሌላ የምሰጥዎት አማራጭ ደግሞ የፖለቲካ እሥረኖቹን ፈትተው ለእስክንድርና ለርዕዮት ቃለመጠይቅ ሲሰጡ ኢቴቪ እንዲያሳየን ነው።
አዎን እድለኛ ነዎት! እርስዎ የተበተቡትን ውል ፈትተው መሥመር ሊያሲዙት ይችላሉ። ለርስዎ በማሰብ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሆነ የክተት ቀኑን ብቻ እየጠበቀ ነው። ከእንግዲህ እርስዎን የሕይወት እስረኛ ያደረገዎትን ሞትን፣ ያልጋ ቁራኛ ያደረገዎትን ሞትን የሚያሞግስ ዘፈን የሚዘፍን ሙሾ አውራጅ ወዳጅዎት እንዳይኖር እሰጋለሁ!
እድለኛ ነዎት! ይቅርታን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠይቁ!!! መንገድዎን ያስተካክሉ! በመጨረሻም እነዚያ በርሃብና በጦርነት ያስጨረሷቸው ሁሉ እንዳያይዎት ሞት ሲወስድዎት ደብቀህ ከምሄድበት አድርሰኛ ይበሉት! ጡር አይሁንብኝና ክቡር ጠቅላይ መለስ መቸም ሞት ተቆራኝተዎታልና! ከእንግዲህ አይለቅዎትምና! መልካሙን አስብልዎታለሁ ጌታው፣ ወርቃማው ገላዎትን ትል አይብላው እላለሁ ሞት ሲወስደው። ወርቅን ትል ከበላው ሥጋ ምን ጉልበት አለው? እንዲያው ደከሙ እንጂ “ወርቅ ነህና ወደ መሬት ትመለሳለህ አይልም መጽሐፉ… አፈር ነህና እንጂ!” እንግዲህ መሬት ሲቀርብዎት ሰማዩ ነው የሚታይዎት፤ ያ ቀስተደመና የሚታይበት። መቼም ጨርቅ ነህ አይሉት አረንጓዴ፣ ብጫ ቀዩን ቀለም ሲያዩት። አይ ሞኝነት! የሞኝም ሞኝ ኖሮ ነው ብልህ ናቸው ያለዎት! የነሱም ባሰ በደደብነት።
ለራሳቸው ሲሉ የሚጨነቅልዎ ከመንደሬ አይጠፉም። ብቻ ይማርህ፣ ይማርዎት የሚል እንዳጡት ሙሾ አውራጅ አያሳጣዎት። መቼም አይሰሙትም አያዩትም እንጂ አባ ጳውሎስ በአስከሬንዎት ዙሪያ ውድ እጣን ተጭሶ ለነፍስዎ ይማፀኑ ይሆናል። ኢትዮጵያን እንደበደሏት ይህች ጊዜ ካመለጠችዎት ለነብስዎት ዋስትና ምንም ነገር አይኖርም። ከአበበ ገላው ድምፅ በላይ የሚያስፈራ ገሳጭ ካለበት ነው የሚሄዱትና ሞት ፋታ ሲሰጥዎት ወዲያውኑ ምክሬን በተግባር ላይ ያውሉ።
መካሪዎ ሕሊና አገሬ
No comments:
Post a Comment