Translate

Thursday, July 19, 2012

አቦይ ስብሐት፤ መለስ ሆስፒታል መሆናቸውን፣ ቢሞቱም ችግር እንደሌለው ተናገሩ!

አቦይ ስብሐት ትላንት ከአሜሪካ ድምፅ ራዲዬ ጋር የአቶ መለስን ጤንነት አስመልክቶ ቃለ ምልልስ አድርገው ነበር። “መለስ አውሮፓ የሆነው ሀገር በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ተኝተዋል የት ሀገር የት ሆስፒታል እንደሆነ ግን ለግዜው አይታወቅም” አሉን። ው….ይ እኛ ደግሞ ድነው ወይም ተስፋ ቆርጠው የተመለሱ መስሎን እንጂ አውሮፓ እንደሄዱማ እናውቃለን። አቦይ ካልሰሙ እንንገርዎ ቤልጄም ናቸው! ምስኪን መለስ ወዳጆችዎ እንኳ የት እንዳሉ አያውቁም…! ምን ቢበድሏቸው ነው!!!? ብለን ቃል አጋኖን አብዝተን እናዝናለን።

አቶ ስብሐት ነጋ በቀጣይም ሲጠየቁ “ህመማቸው ለምን ይፋ አልተደረገም? በመንግስት ብዙሃን መገናኛ እንዴት አልተነገረም? ህዝቡ ይህንን የማወቅ መብት የለውም ወይ?” ተብለው ነበር። አቦይስ ምን አሉ…? “እኔ እንደሚመስለኝ ቶሎ ድኜ እመለሳለሁ ብሎ ነው እንጂ ህዝቡ የማወቅ መብት አለው!” ብለዋል። ጎሽ አቦይ እንዲህ ነው እንጂ ይህንን ንግግር መንፈስ ቅዱስ እንዳናገርዎት እቆጥረዋለሁ። እኔ የምልዎ… እርሱማ ህመምተኛ ሁሌም ጉጉ ነው! ነገ ድናለሁ ብሎ ተስፋ ማድረጉ አይቀርም። የገረመኝ ግን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ይሄንን ዜና ለማውጣት አሁንም አቶ መለስ ናቸው የሚያዙት። በአልጋ ላይ ሆነው የዜና ተቋማቱን ሳይቀር የሚያዙ ከሆነ ነገ ህይወታቸው ሲያልፍ ደግሞ ይሄንን ነገር የእርሳቸው መንፈስ ስላልፈቀደ አልተደረገም እንባል ይሆን…!?
አቶ ስብሐት “መለስ ኖረም አልኖረም ኢህአዴግ ኢህአዴግ ነው ይኖራል ምንም የስራ ክፍተት አይፈጠርም” ሲሉ ተናግረዋል።
ለነገሩ ይሄ ንግግራቸው አቶ መለስ ቢሞቱም ይሙቱ የራሳቸው ጉዳይ… የማለት ያኽል መሆን አለበት እንጂ ከላይ እንዳየነው የመለስ መታመም ዜና እንኳን ያልተሰራበት ምክንያት መለስ በቅርቡ እድናለሁ ብሎ ስላሰበ ነው ብለውናል። በዚህም እነ ኢቲቪንም ሆነ እነ አዲስ ዘመንን አሁን እንኳ በአልጋ ላይ ሆነው መለስ እያዘዙ እንደሆነ ያለ እርሳቸው መልካም ፈቃድ ዜና እንኳ የማይሰራ መሆኑን መረዳት ችለናል። (እንደውም ይሄኛው መረዳት የግንዛቤ ሳይሆን የመርዶው ነው…! በእውነት ኢዜአ እና ዋልታ እንኳ ሳኢቀሩ መለስ ይሁን ካላሉ ዜና የማይሰሩ ከሆነ በእውነት መርዶ ነው!)
በነገራችን ላይ አቦይ ስብሐት መለስን መተንኮስ ከጀመሩ ቆይተዋል። አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ከወ/ሮ አዜብ ጋር ያላቸውን ቅያሜ ብዙ ጊዜ የሚወጡት የመለስን ንግግር እና ድርጊት በማጣጣል እየሆነ መጥቷል።
የማስታውሳቸውን አንድ ሁለቱን እንኳ ብንጠቅሳቸው ከዚህ በፊት መለስ ደጋግመው የሚነግሩንን የአውራ ፓርቲ አስፈላጊነት እና የኢህአዴግን አውራነት በሰንደቅ ጋዜጣ ላይ አቦይ አጣጥለዋል። “እኛ የታገልነው ለዲሞክራሲ እና ለመድብለ ፓርቲ ነው። አውራ ፓርቲ የሚባለውን ነገር እኔ አላውቅም!” ብለው ተናግረው ነበር። እኛም እሰይ የኔ አንበሳ ብለን አድንቀናቸዋል።
በቅርቡ ደግሞ በየ ጎዳናው እና በየ መስሪያ ቤቱ በትልልቅ ወጪ የሚሰራ (እና አንዳዴም የሚሰረቅ ብዬ ልጨምር እንዴ? መቼ እለት ነው… አዋሬ አካባቢ በ35 ሺህ ብር የተሰራ መለስ አባይን ሲደፍሩ የሚያሳይ ቢል ቦርድ ተሰርቆ የለ…? ) እና “መለስ ዜናዊ አባይን የደፈረ መሪ” የሚል ቢል ቦርድ እነ ፖስተር ስራ አስመልክቶ ሲጠየቁ “እንደኔ እምነት አባይን እንኳን መለስ ዜናዊ እና ኢህአዴግም ደፍሮታል ብዬ አላስብም! እንዲህ አይነት የግለሰብ ገፅታ ግንባታ ከድርጅታችን አካሄድ ውጪ ነው” ብለው ተናግረው ነበር። ይሄንን እንኳ ሲናገሩ መለስ በእግዜር እጅ ተይዘው ነበር። ነገር ግን ከዚህ በፊት የተናገሩትን ስናስታውስ እውነትም ተንታኞቻችን እንደሚሉት አቦይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ እንዲህ የሚጨክኑባቸው ከእርሳቸው ጋር እንኳ ፀብ ባይኖራቸው ከወይዘሮ አዜብ ጋር በላው ቁርሾ የተነሳ ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው።
ይኸው አሁን እንኳ መላው የኢህአዴግ አባላት በሆዳቸው ይዘው አንዴ “ድነው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ”… ሌላ ጊዜ ደግሞ “ከነጭርሹ አልታመሙም” እያሉ በሚናገሩበት ጊዜ አቦይ “አዎ መለስ ታሟል ቢሞትም ችግር የለም!” አባባላቸው የፀብ እንጂ የወዳጅነት አይመስልም።
በሀገራችን ባሀል መሰረት አንድ ሰው የማይተርፍ መሆኑ ሲረጋገጥ “ለማንኛውም ቤቱን አፀዳዱ የሚሆነው አይታወቅም” የሚባል ንግግር አለ።
እንደኔ ግምት ከሆነ የአቶ መለስ መሞት ብዙ ነገር ነው። አቦይ እንዳሉት “መለስ ቢሞትም ችግር የለም” ለማለት የሚያስችል ቁርሾ የለኝም። መለስ ቢሞቱ ችግር አለው። ክፍተት ይፈጠራል። ኢህአዴግ ያለ እርሳቸው የሸዋ ዳቦ ነው። (በነገራችን ላይ ሸዋ ዳቦ አንዷ ብር ከአርባ መግባቷን ነገሬዎታለሁ አይደል። ታድያ ያ ሁሉ ዋጋ የወጣባት ዳቦ እርሾ ንፍት አድርጓት እንጂ ሲነኳት ፍርክስክስ ነው የምትለው… “አንድ ለከንፈር አንድ ላፈር” ሲሏትም ሰምቻለሁ። ፍርክስክስ ማለቷን ያዩ የተናገሩት ነው።
ለነገሩ ብዙዎች ይሄንን ድሮም እናውቀዋለን። እኔ በበኩሌ ገና እምዬ ኢህአዴግ ሲባል ከ አርማው ቀድሞ በአዕምሮዬ የሚመጣው የአቶ መለስ ስዕል ነው። ስለዚህ አቶ መለስ ብሎላቸው ከሞቱ ኢህአዴግ ሲባል በአዕምሮዬ የሚመጣው ባዶ ቤት ይሆናል ማለት ነው…!!! ውይ አረ አያድርገው ሌላው ቢቀር ለእኒያ ወ/ሮ ሲባል ትንሽ ይቆዩላቸው…! እንኳንስ ጥለዋቸው ሞተው ይቅርና እንዲሁም…
እኔ የምለው የአቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት በቁጥጥር ስር ዋሉ የተባለውን ዜና እንዴት አዩት? ወዳጃችን አርአያ በፌስ ቡክ የሰጠው አስተያየት በጣም አዝናንታኛለች “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ እንዲሉ አበው አሁንም ባለቤቱን ካልናቁ ሚስቱን አይነቀንቁ!” ነው ነገሩ ብሏል።
እና ታድያ ወ/ሮ አዜብም ባለቤታቸው አንድ ነገር ከሆኑ የሚፈጠረባቸው ነገር ቀላል አይደለም። ለርሳቸው ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የአቶ መለስ ፍፃሜ የሆነ ነገር ይዞ የሚመጣ ይመስላል።
እናም ለማንኛውም የሚሆነው አይታወቅምና ቤቱን አፀዳዱ! ይሄ መልዕክት የአቶ መለስ ነገር ለሚያሳስበው ሁሉ ነው። እደግመዋለሁ፤ የሚሆነው አይታወቅምና ቤቱን አፀዳዱ!
abe tokchaw

No comments:

Post a Comment