Translate

Saturday, July 14, 2012

አንቺም ጨካኝ ነበርሽ ጨካኝ አዘዘብሽ…

ይነጋል በላቸው
አንቺም ጨካኝ ነበርሽ ጨካኝ አዘዘብሽ…
ይነጋል በላቸው
አንቺም ጨካኝ ነበርሽ ጨካኝ አዘዘብሽ፤
እንደገና ዳቦ እሳት ነደደብሽ፡፡
(ለአቶ መለስ ዜናዊ ፣ ከባህላዊ ሥነ ቃሎቻችን)
በመሠረቱ ሞት ለሰው ልጅም ሆነ በአጠቃላይ ሕይወት ላላቸው ፍጡራን የማይቀር የመጨረሻ ዕጣ ፋንታ ነው፡፡ ማንም ከዚህ ተፈጥሯዊ ሂደት አይቀርም፡፡ ነገር ግን አሟሟት ሲያምር
Ethiopian pm Meles Zenawi
Meles Zenawi
ለሟችም ለቋሚ ቤተሰብና ወዳጅም ደስ ይላል ብቻ ሳይሆን ያኮራል – ለዚህ ነው ሀበሻ “አሟሟቴን አሳምረው” ብሎ የሚጸልየው፡፡ ለዚህ ነው አንዳንዶች “ ከሞቴ ይልቅ አሟሟቴን እፈራለሁ” የሚሉት፡፡ አሟሟት ሲባል ደግሞ በአገባብ የተለያዩ አንድምታዎች አሉት፡፡ አሁን አዚህ የምናየው አንዱን ዘርፍ ነው፡፡ በሰው ልጆች ታሪክ እጅግ በርካታ የዓለማችን ዜጎች አጸያፊ ወይም አኩሪ ትውፊት እየተውልን በሞት ተሰናብተውን ሲያበቁ ከህልፈታቸው በኋላ በቀጣይ ትውልዶች ሲወቀሱና ሲረገሙ አሊያም ሲወደሱና ሲመረቁ ይኖራሉ፡፡

ከነዚህ በርካቶች ዜጎች መካከል ማህተመ ጋንዲንና እማሆይ ማርያ ተሬዛን በቅርብ የምናስታውሳቸው ዓለም አቀፍ ሰዎች ናቸው፡፡ በአፀደ ሕይወት ካሉት መካከልም ኔልሰን ማንዴላን መጥቀስ ይቻላል፡፡
መለስ ዜናዊ ይህችን ምድር ሊሰናበት እንደተቃረበ በስፋት እየተወራ ነው፤ የከተማችን ወሬ ከሆነም ሰነበተ፡፡ መለስ ቢሞት እርግጥ ነው አፈር አያሟሽም፡፡ ሞት በርሱ አልተጀመረምና፡፡ የመሞቱ ዜናም እንዲሁ ልዩ ነገር አይደለም፤ ሰው ነው – ሰው ደግሞ ሟች ነው፤ እሱም ይሞታል፤ በጭካው ከእርሱ የማይተናነስ መልአከ ሞት የሚባል ፍጡር አስተካካይ ዳኛ አለ፡፡ ሲሞትና ቢሞትም የምንጠላው ምሥጥ ሆነን አንበላውም – የምንወደውም ፊታችንን ነጭተን ወይ ራሳችንን በርሱ ምትክ ሰውተን አናስቀረውም፡፡ የተፈጥሮ ሕግ በመሆኑ እንደቢጤዎቹ ጨካኝና አረመኔ የዓለም መሪዎች ሁሉ በሚሊዮኖች ዜጎች ዘፈንና እስክስታ ታጅቦ የጀመረውን የሞት ሞት ይወጣዋል፤ አሟሟቱ ግን ያሳዝናል፡፡ ከጥቂቶች በስተቀር እግዜር ይማርህ ሳይባል- አፈሩን ገለባ ያድርግልህ የሚለው አንድ መቶኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይኖር ሞቱ የጭፈራና የደስታ ምክንያት ሲሆን መረገም ከዚህ በላይ እንደሌለ ይገባናል፡፡ ለዚህች አጭር የሥልጣንና የሀብት ዘመን ሲል የሠራውን ግፍና በደል ስናጤን የሰው ልጅ ግብዝነት ምን ያህል እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከል የሚለብስ ይለብሳል፤ የሚደሰትም በደስታ ጮቤ ይረግጣል፡፡ የሚያሳዝነው ግን የአሟሟቱ ሁኔታ ነው፡፡ ሞቱ ተራ ሆኖ አሟሟቱና በቁሙ የሠራው ገድል ግን ከፍተኛ ትርጉም አለው፡፡ ለዚህ ነው የመለስና የአንድ ተራ ዜጋ ሞት አንድ ሊሆኑ የማይችሉት፡፡ ለዚህ ነው ገና ብዙ ማጥፋት እየቻለ ለአቅመ ጥፋት ከመድረሱ ገና በ30ዎቹ ዓመታት ውስጥ በሕዝብ ዕንባና ደም የራሰው የሕይወት መጽሐፉ አጉራ ጠንቶት ገና በ58 ዓመቱ ወጥቶ እስኪገባ ከማያምናት የተንኮልና የጭካኔ ሥራው ሊሰናበት ዳር ዳር ማለቱ፡፡ ለአንድ አምባገነን 58 ዓመት በጣም ትንሽ ዕድሜ ነው፡፡ ካሙዙ ባንዳ እኮ በ94 ዓመቱ አካባቢ ነው የሞተው፤ ሙጋቤ እኮ 88 ዓመቱ ገደማ ነው፤ ኪም ኢል ሱንግስ … ሌሎችስ? እግዜሩ የሚወራውን እውነት ካደረገልን እኮ የኛ እልል በቅምጤ ነው፡፡ እስኪ አስቡት – መለስ በ85 ዓመቱ ሥልጣኑን ለልጁ ለሰምሃል አስረክባለሁ ቢልስ? ገና 27 ዓመት ልንደቆስ ማለት እኮ ነው!
መለስ ምን አደረገ የሚለው ጥያቄ ማንንም አያነጋግርም፡፡ ባጭሩ አንዲት ሀገርና አንድ ሕዝብ በቁም ገድሏል፤ እንጦርጦስ አውርዷል፡፡ ለዚህ ጥፋቱ እኔና አንተ ሳንወድ በግዳችን ካለ ምንም የጎላ ወንጀል ወይም ኃጢያት በተፈጥሮ ሕግ ብቻ ተገድደን የምንሞተው ሞት በእጅጉ ያንሰዋል፤ ግን ግዴለም ቢያንሰውም መሞቱ ካልቀረ በፈጣሪ ትዕዛዝ ይሙትልን፤ የመለስን ያህል ወንጀልና ጥፋት የተሸከመ ሰው፣ ሰው ሊገድለው ያቅተዋልና ሞቱም በእግኤሩ እጅ መሆኑ መልካም ነው፡፡ በዚያም ላይ መለስን እንደ አምላክ ለሚያዩ ወገኖች፣ መለስን እንደ ጣዖት ለሚመለከቱና የማይሞት ለሚመስላቸው ጅላጅል አማኞቹ ከርሱ በላይ ኃያል አምላክ መኖሩን፣ የግፈኞችን አንደበትና እጅ እግር የሚለጉም አምላክ መኖሩን እንዲረዱ ያደርጋቸዋል፡፡ በመሠረቱ ሞት ማንም የማይሰጠን ወይ የማይነፍገን የተፈጥሮ ፀጋ ነው፡፡ በየትኛውም የዕድሜ ክልል እንሞታለን፡፡ ስለዚህ ይህ ሰው አሁን ባለው የሃምሳ ምናምን ዓመት ዕድሜ ቢሞት እንደአካሄድ ተፈጥሯዊ ነው ፤ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ የሠራው ሥራ ግን ቀድመን ለማየት እንደሞከርነው ከሞት የፍርድ ብያኔ በላይ ነው፡፡ ከእርሱ ሞት በኋላም ሊከተል የሚችለው የእርሱ ጦስ ጥምቡስ ገና ሊታሰብበት የሚገባው ነው፡፡ ብዙ የቤት ሥራ አለብን፡፡ መለስ በ17 + 21 = 38 ዓመታት ውስጥ ተክሎብን የሚያልፈው ደንቃራና መተት በቀላሉ የሚነቀል እንዳልሆነ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ቀርቶ የኢትዮጵያን ሬዲዮና ቴሌቪዥን ከውሸትና ከፈጠራ ወሬ ነጻ ለማውጣት በሕዝብም ዘንድ ተዓማኒ ለማድረግ ብዙ ዓመታትን የሚፈጅ ትግል የሚጠይቀን ይመስለኛል፡፡
መለስ ዜናዊ ራሱ አብዶ ሌሎች አጫፋሪዎቹንና ጋሻ ጃግሬዎቹንም አሽክርና ደንገጡሮቹንም ሁሉ አሳብዶ ሞት አፋፍ ላይ የደረሰ ደመ ሞቃት ግለሰብ ነበር፡፡ የተላከው ከየትም ይሁን ከየት ተልእኮውን ግን በሚገባ የተወጣ የዘመናችን ከሃዲ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በጥፋት ተልእኮው እንደሱ የተሳካለት ዜጋ ማግኘት ይከብዳል፡፡ ምናልባት የቅርብ ዘመዱና ኮትኩቶ አሳድጎ ያሰማራው ሰውዬ ይስተካከለው ይሆናል፡፡
በቁሙ የበሰበሰ ዘረኛ ሥርዓት ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ሲመራ ቆይቶ አሁን በእግዜር እጅ ቢያዝም ለሀገር ጥፋት አሰልጥኖ ያሰማራቸው ሎሌዎቹ አሁንም ከዕብደታቸው ሊመለሱ ቀርቶ እንዲያውም እንደዕብድ ውሻ ህመማቸው እየባሰባቸው ናቸው፡፡
በዛሬው ውሎ ከወጡ የድረ ገፅ ዘገባዎች አንዳንዶቹን ስንመለከት የወያኔው ሥርዓት በለየለት የዕብድ ሥራ መወጠሩን የምንታዘብባቸው በርካታ ተግባራቱን ማጤን እንችላለን፡፡ ከነዚህም አንዱ ከበላዮቹ በስልክ በሚነገረው ትዕዛዝ ዜጎችን ለመቅጣት የተሰየመው የውሸቱ የወያኔ ፍርድ ቤት በኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞችና የተቀናቃኝ ፓርቲ አባላት ላይ ያሳለፈው ህገ ወጥ ፍርድ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ከአንደበቱ ካለ እንታረቅና እንስማማ በስተቀር አንድም ኃይለ ቃል የማይወጣው ኦባንግ ኦ. ሜቶ ሳይቀር የ18 ዓመት እስራት ተፈርዶበታል፡፡ ይህ ዕብደት ካልሆነ ምን ሊሆን እንደሚችል አላውቅም፡፡ በፍርድ ላይ ፍርድ ፣ በበደል ላይ በደል፣ በግፍ ላይ ግፍ መጨመር ዋና ሥራው የሆነው ወያኔ አሁን አሁን የሚሠራውን አጥቷል ማለት ይቻላል፡፡ የሞት ፍርድ በፈረደባቸው ላይ ተጨማሪ የዕድሜ ልክ እሥራት የሚፈርድ ይሠራውን ያጣና የሕይወት ድርና ማግ ውላቸው የጠፉበት ተቋም ቢኖር የወያኔው መንግሥት ብቻ ነው፡፡ ተቋማዊ ዕብደት እንበለው ይሆን?
በበቀደሙ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና አምቦ ዩኒቨርስቲ የምረቃ በዓል ላይ ከተከሰቱ እጅግ በጣም አሳፋሪ ወያኔያዊ ተግባራት አንድ ሁለቱን ልናገርና አንድ ሥርዓት ሲያረጅ ምን እንደሚመስል አመልክቼ ልሰናበት፡፡
እስከሚገባኝ ድረስ የሚጃጅ፣ ሰው ወይም እንስሳ ብቻ ይመስለኝ ነበር፡፡ ለካንስ ሥርዓትም ይጃጃል፡፡ ሰው ሲጃጅ እንደሕጻን ያደርገዋል ይባላል፤ አንደበቱን መቆጣጠር ያቅተዋል፤ ተግባሩም ያው እንደሕጻናት ነው፡፡ ያ ግን በዕድሜ መግፋት ሰለሆነ ቤተሰብ ገመናን በመክተት ይተባበራል ተመልካችም በነግ በኔ ከግፍ ንግግር ተቆጥቦ ‹እንዲህ ሳልሆን በጊዜ ሰብስበኝ› እያለ ወዳምላኩ ይጸልያል እንጂ ብዙም ችግር የለውም፡፡ የወያኔው መጃጀት ግን ድንበሩን ጥሷል፡፡ ሊያውም ገና በ21 ዓመት ውስጥ…
እንዲህ ሆነላችሁ፡፡ አምቦ ዩኒቨርስቲ ሰሞኑን ሲያስመርቅ ከመንግሥት የተላከው የክብር እንግዳ “ በአሁኑ ሰዓት ሥራ የማግኘት ችግር የለም፡፡ ሌላ ቢጠፋ በማኅበር ተደራጅታችሁ የኮብል ስቶን ሥራ መሥራት ትችላላችሁ፡፡ ይህ ገና ያልተበላ የኮብል ስቶን ሥራ…” እያለ በአለቆቹ የተሞላውን ፕሮፓጋንዳ እንደጣቃ ሲቀረደድ ተመራቂው በሞላ ይጮህበትና ያቋርጠዋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ከዕለቱ ተመራቂዎች አንዷ ጨርቋን ቀዳዳ ወዲያውኑ አበደች፡፡ እስካሁን ይሻላት አይሻላት ያወቅሁት ነገር የለም፡፡ ፈጣሪ ይድረስላት፡፡ እግዚአብሔር ከዚህ አብዶ ከሚያሳብድ መንግሥት በአፋጣኝ ይታደገን፡፡
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና እሁድ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ምሁራንን አስመርቋል – በተለያዩ የትምህርትና ሥልጠና ደረጃዎች፤ በዲፕሎማና እስከዶክትሬት ዲግሪዎች፡፡ የቅዳሜ ከሰዓት ምድብተኛው የወያኔ መራቂ ካድሬ ጁነዲን ሳዶ የሚባለው መናጆ ነበር አሉ፡፡
ይህ ሰው እንዲናገር የተሞላውን (በወያኔ ሥርዓት ያልተሞላ ሰው እንዲናገር አይፈቀድለትም፤ ነገር ሊያበላሽ ስለሚችል) ቱሪናፋ በተሰጠው የጊዜ ፕሮግራም መሠረት እንደ አምቦው የወያኔ ካድሬ እንደጣቃ መቀደድ ሲጀምር እንዲህ ይላል፤ ፤ “ በመመረቃችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡ … ሀገራችን ውስጥ ሥራ ሞልቷል፡፡ የምትፈልጉትን ሥራ አሁን ላታገኙ ትችላላችሁ‹፡፡ ነገር ግን በማኅበር እየተደራጃችሁ የኮብል ስቶን ሥራ ብትሠሩ በተመረቃችሁበት ሙያ ልታገኙ ከምትችሉት በላይ ገቢ ታገኛላችሁ፡፡…”እንዲህ ሲል ተመራቂው በአንድነት ይጮኸበትና ንግግሩን እንዲያቋርጥ ያደርገዋል፡፡ አልቀጠለምም፡፡ ወያኔዎች እንዲህም ሆነዋል፡፡
እውነትን ለመናገር የወያኔዎች ቀመራዊ ቅኝትና አለቦታው መናገራቸው ገረመኝ እንጂ የሥራ ፈጣሪነትን ብልሃት መጠቆማቸው በራሱ ጥፋት አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ምን፣ መቼና ለማን መናገር እንደሚገባቸው ያወቁ አልመሰለኝም፡፡ በሠርግ ዕለት ስለፍቺ ማውራት ተገቢ አይደለም፤ በደስታ ዕለት ስለልቅሶ ማውራትም ተገቢ አይደለም፡፡ ሰውን እያስታረቅን ስለጠብ ማራገብ አግባብ አይደለም፡፡ እጫጩት ፊት ፈንግል አይወራም እንደምንለው ማለት ነው፡፡ ንግግርን ማሳመር የሚጥመው በቦታውና በሰዓቱ ሲሆን ነው፡፡ አለበለዚያ ሴት አማቱ ‹ንግግርህ ከእንትንም እንትን ነው› እንዳሉለት ቂላቂል አማች መሆን ነው፡፡
ከ15 እስከ 20 ዓመት በትምህርትና ሥልጠና ላይ ያሳለፈ ሰው ሲመረቅ ሌላ መልካም ነገር መናገር ባይቻል ስሜቱን የሚጎዳና ከለፋበት ሙያ ወይም ሥልጠና ጋር ፍጹም ተያያዥነት የሌለው የኮብል ስቶን ሥራ ሠርተህ ኑር ማለት ከጤናማ ሰው አይጠበቅም፡፡ ሥራ ስጡኝ ብሎ የሙጥኝ ያላለን ዜጋ በሙሽርነት የምረቃ ጊዜው ድንጋይ ጋር ታገል ብሎ መስበክ በጭራሽ ጤናማነትን አያሳይም፡፡ ለዚያ ለዚያማ ያን ያህል ዓመት ምን አስለፋው? በመሠረቱ ድንጋይ መጥረብም ሆነ ቤት መጥረግ ሥራዎች ናቸው፡፡ ሥራ ደግሞ በምንም መንገድ አይናቅም፡፡ ነገር ግን መቀላቀል የሌለብንን ነገር መቀላቀል አይገባም፡፡ ኩታ በየፈርጁ ይለበሳል ነው ነገሩ፡፡ የእግዜርን ለእግዜር የቄሣርን ለቄሣር ነው ጉዳዩ፡፡ ኮብል ስቶን ሌላ – በዲግሪ መመረቅ ሌላ፤ ኢንጂኔሩንም፣ ሜዲካል ዶክተሩንም፣ የሥነ ልሣን ሊቁንም፣ አካውናንታንቱንም፣ ኢኮኖሚስቱንም፣ ጂኦሎጂስቱንም፣ ማትማቲሺያኑንም፣ ሎዌየሩንም፣ ማኔጀሩንም … ሁሉንም በአንድ ቅርጫት አጭቆ ኮብል ስቶን ሥራ ማለት ዕብደት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፤ እርግጥ ነው ወያኔዎች ዱሮውንም ቢሆን ለትምህርት ያላቸው ግምትና ግንዛቤ እጅግ የወረደ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ቢሆንም እየተሻላቸው ሊሄድ ሲገባ እንዲህ እየዘቀጡ ከመጡ ከማዘን ውጪ ልንረዳቸው በምንችልበት አቅም ላይ ስለማንገኝ ምንም ማድረግ አይቻለንም፡፡ ይህንን ዕብደት ደግሞ በሞልፋጣ የውሸት ማሰራጫ ቲቪና ሬዲዮ እጅ እጅ እስኪል ድረስ ማራገብ በህዝብ ሀብት ማላገጥና በገንዘብ መጫወት ነው፡፡ ቢበዛ በሦስት ወር ሙያዊ ሥልጠና ልንሠራው የሚቻለንን የኮብል ስቶን ሥራ ከሃያ ዓመት በላይ የዕድሜውን ክሬም አካል ያጠፋበትን ዜጋ ድንጋይ ፍለጥ ብሎ ያውም ዘመድ አዝማዱ በተሰበሰቡበትና አበባው ወደፍሬ የሚለወጥበት ቅጽበት በሚታወጅበት ሰዓት እንደመርዶ ነጋሪ በአደባባይ ማርዳት የበሽታ እንጂ የጤንነት ምልክት አይደለም፡፡ ለድርጊታቸው ቀርቶ ለንግግራቸው ደንታቢሶቹ ወያኔዎች ወጣቱን እያስኮረፉት ያሉት እንግዲህ በዚህ መልክ ነው፡፡ ቂልነት አይሉት ማይምነት ነገሩ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ በሌላ በኩል የነሱን ልጆች ሁኔታ ስናይ የተለዬ ምስል እናስተውላለን፡፡ በሀገር ውስጥ ያሉት በዓመት በጣም ብዙ ሺ ብርና ዶላር በሚከፈልባቸው ሳንድፎርድንና አይ ሲ ኤስን በመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች በውድ ክፍያ ያስተምራሉ፤ ሴንት ጆሴፍና ናዝሬት የሚባሉት ትምህርት ቤቶችማ የነሱ ብቻ ናቸው፤ ሌላ እንዳይማርባቸው ማዕቀብ የተጣለ ነው እሚመስል፡፡ በውጪ ደግሞ በቻይና ሥዩም መሥፍናቸውን በአምባሳደርነት ሹመው በዚያችው ሀገር እያስተማሩ ነው – እንዲተኳቸው፡፡ የሚማሩትም የነማን ልጆች እንደሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ የሚነግዱት እነሱ፣ የሚያስነግዱት እነሱ፣ የግዙፍ ሕንጻዎች ባለቤቶች እነሱ፣ የገንዘብ ዝውውሩን የተቆጣጠሩት እነሱ፣ እስትፋሳችንን ሳይቀር የተቆጣጠሩት እነሱ፣ በስለላ መረባቸው እግር ከወርች ያሠሩን እነሱ፣ ሁሉንም ነገር በግል የተቆጣጠሩት እነሱ፣ ግብር የማይከፍሉ እነሱ፣ ቦታ እየወሰዱ እሚሸጡና እሚከብሩ እነሱ፣ ሕግ የማይገዛቸው እነሱ፣ ነጋዴን የሚነቅሉ እነሱ፣ ቫት የማይከፍሉ እነሱ፣ ቫት የተከሉ እነሱ፣ ቀረጥ የማይከፍሉ እነሱ፣ ንጉሠ ነገሥታት እነሱ፣ የማይምነትና የሆዳምነት መባቀያ እነሱ፣ ሥጋችንን ስለተቆጣጠሩ ብቻ መንፈሳችንንና ነፍሳችንን የገዙ የመሰላቸው ሞኞች እነሱ፣ እነሱ ጋር በአካል ስላለን ብቻ አብረናቸው ያለን የሚመስላቸው ቂሎች እነሱ፣ አሁን በዘረፋ ስለጠገቡ ዝንተዓለሙን እንደጠገቡ የሚኖሩና የማይራቡ የሚመስላቸው ነፈዞች እነሱ፣ መኪናውን ቤቱን ሆቴሉን ሱቁን ጋራጁን ትምህርት ቤቱን ክሊኒኩን ሆስፒታሉን … የተቆጣጠሩ እነሱ፣ ሀገሪቱን ለብቻ ይዘው ያሻቸውን እያደረጉ ያሉ እነሱ፣ ይህ የክፋት ሌሊት የማይነጋ የመሰላቸው እነሱ፣ በትንሽ ኪራይ የመንግሥትን ቤት የሚይዙ እነሱ፣ ያለመያዣ በቀጭን የበላይ ትዕዛዝ ከባንክ ገንዘብ የሚበደሩ እነሱ፣ ብድሩን የማይመልሱ እነሱ፣ ከየት መጡ ሳይባል የአዲስ አበባን የንግድና የኢኮኖሚ ተቋማት የሞሉ እነሱ፣ የአዲስ አበባን ንግድ ቤቶች ከየጎሣው ቀምተው የተቆጣጠሩ እነሱ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ተቆጣጥረው የሚገኙ እነሱ፣ ስለሀገር የሚቆረቆርን ዜጋ እየተበቀሉ ከሥራም ከንግድም ከመኖሪያም የሚያፈናቅሉ እነሱ፣ የሚያስሩና የሚያሰቃዩ እነሱ፣ የሚያደኸዩን እነሱ፣ ኑሮውን የሚያስወድዱ እነሱ፣ የተማረውን እያፈናቀሉ በደደብ ማይማን የሀገሪቱን የሥልጣን ቦታዎች የሞሉ እነሱ፣ ፍርድ የሚያዛቡ እነሱ፣ ሕግን የሚረጋግጡ እነሱ፣ የፍትህን ዐይን የሚደነቁሉ እነሱ፣ በዘረኝነት ፈውስ የለሽ ደዌ ተለክፈው ከነሱ ውጪ ሰው ሰው የማይመስላቸው ደናቁርት እነሱ as adding an insult to injury የሚያደርጉትን እያደረጉ ‹አህዮች› ብለው የሚሰድቡን እነሱ፣ አርቀው እንደቀበሩን እሚያወሩና እሚያስወሩ እነሱ፣ በገንዘብና በሥልጣን ስካር ኅሊናቸውን የሳቱ በዚያም ምክንያት የሚናገሩትንም የማያውቁ እነሱ … እንዴት ያለ ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው እባካችሁን… ኤዲያ … ተናግሮ አናጋሪ ጅል ዘመን… ለማንኛውም የነሱ ልጆች ኮብል ስቶን ስለሚባለው ነገር ስሙንም ስለማወቃቸው አላውቅም፡፡ ይህ የሚመር እውነት የማይዋጥላችሁ አላችሁ፡፡ አዝናለሁ፡፡ እውነቱ ግን በጥቁር ቀለም ተጽፎ በኢትዮጵያ ታሪክ ይቀመጣል፡፡ ይህን ጽሑፍ የማታስተናግዱ ድረ ገፆች ቢያንስ ራሳችሁ አንብቡት፤ ሰው በሰው ላይ ሲጨክን ሰውነቱን እስከመርሳት እንደሚደርስ ትረዱበታላችሁ፡፡ የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም፡፡ በወያኔያዊ የመከራ ዝናብ የበሰበስን እኛ ብሶታችንን ከመናገር ወደ ኋላ አንልም፤ ቢያንስ መናገሩ አይቀርብንም፡፡ ሌላው ለሚመለከተው ይሁን፡፡
በዚሁ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የተከሰተና በተባራሪ የሰማሁትን ሌላ ምሥጢር ደግሞ ላካፍላችሁ፡፡
ጋዜጠኞች በትምህርቱ ብልጫ ያገኘን ተመራቂ እያሳደዱ ቃለ መጠይቅ እናድርግህ/ሽ ይላሉ፡፡ የሚገርመው ግን በሀገራችን የጋዜጠኝነት ሙያ ሞቶ መቀበሩን የምንረዳበት ጉዳይ እዚህ አካባቢ መታዘባችን ነው፡፡ አንዱ ጋዜጠኛ ከነካሜራማኑ ወደ አንዱ ሰቅሎ የተመረቀ ወጣት ይቀርብና “ይህችን ወረቀት ተቀበለኝ” ይለዋል፡፡ የሚሰጠው ወረቀት ለሚጠይቀው ጥያቄ አስቀድሞ መልስ የተጻፈበት ወረቀት መሆኑ ነው፡፡ “እንዴ – ምን ማለትህ ነው፤ ከጠየቅኸኝ ዝም ብለህ ጠይቀኝና የምችለውን መልስ ልስጥህ፡፡ ለምትጠይቀኝ ጥያቄ አንተው ከመለስክልኝ ምኑን ቃለ መጠይቅ ሆነ” ይለውና በሰው ፊት ያዋርደዋል -(ለነገሩ ወያኔዎች ውርደትና ቅሌት ሲያልፉ አይነኳቸውም፤ አይተዋወቁምም)፡፡ ቢያግባባውም አልሆነለትም፡፡ ትንሽ ቆይቶ በሌላ የፎቶ መነሻ ሥፍራ ተመሳሳይ ጥያቄውን ያቀርብለትና ካሜራውን ይደቅንበታል፡፡ ይህ ወጣት ከጥያቄው መንፈስ በመረዳት ያቺው የፈረደባትና የወያኔው ልክፍት የሆነችው የኮብል ስቶን ጣጣ እንዲናገር በተሰጠው የመልስ ወረቀት ውስጥ ተሰንቅራ ሲመለከት “ ወንድሜ እንዲህ ያለ ጋዜጠኝነት አይቼ አላውቅም፤ አትልፋ፡፡ እኔ ደግሞ ዱሮውን በጥሩ ደመወዝ ተቀጥሬ እየሠራሁ የምገኝ እንጂ ሥራ ፍለጋ ላይ ታች የምንከራተት እንዳልመስልህ፡፡ …” ሲለው ካሜራማኑ በንዴት ቀበል አድርጎ “ ምን ታካብዳለህ!” ይለዋል፡፡ ልጁ ተናደደና ጥሏቸው ዘወር አለ፡፡ የ‹ጋዜጠኞቹ› ሥራ ግን በርግጥም በጣም ያናድዳል፡፡ ወያኔና ኢትዮጵያ እንግዲህ እንዲህ ባለ አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ናቸው፡፡ ነገሩ ብዙ ነው፡፡ ቢያወሩት አያልቅም፡፡ ጉድ ሆነናል ጎበዝ!
ለማንኛውም የታመመውን መሪያችንን ይማርልን፡፡ ኢትዮጵያ ያለ መለስ ብትንትኗ ስለሚወጣ የመለስን ዕድሜ ቢያንስ እንደማቱሳላ 960 ዓመት ያድርግልን – ከተቻለም ከናካቴው ይርሳው፡፡ ከአሰቃቂው ብሔራዊ ሀዘን ይሠውረን ወንድሞቼ እንዲሁም እህቶቼ፡፡ ደግሞም የትኛውን ባንዲራ ዝቅ አድርገን ማውለብለብ እንዳለብን በአዋጅ ስላልተገለጸልን ይቸግረናልና መለስ ከሚሞት እንደኤርየል ሻሮል ኮማ ወስጥ ገብቶም ቢሆን እስከወዲያኛው ይኑርልን፡፡ የአባይ ውሃ በየቤታችን በቧንቧ ገብቶ ሳንጠጣ ባጭር እንዳይቀርብን አንድዬ አደራውን፡፡ እሱ ቢሞት እኮ ራሱን የሚያጠፋ ሰሜነኛ ሞልቷል፤ እንዴ – ስሙ በክፉ ሲነሳ ስቅስቅ ብለው የሚያለቅሱ አሉ ይባል የለም? ኧረ ለምን ይሙትብን? ለምንስ ጅቦቻችንና ዓሣሞቻችን ሃሳብ ይግባቸው? የሀገራችን ጠላቶችስ ለምን ደስ ይበላቸው? ከዚህ በላይ ብመርቅ የኔንም ዕድሜ እንዲያሳጥረው የሚራገም አይጠፋምና ይቅርብኝ፡፡ ለአልቃሾች መልካም ሀዘን፤ ለልቅሶ ደራሾች መልካም የአስተዛዛኝ ወቅት ይሁንልን፡፡ ሰው ሲሞት የሚደስት አይጠፋምና አደራችሁን ሁሉም ወገን ሀዘኑንና ደስታውን በቅጡ ያድርግ፡፡ ዕንባ ሲበዛ ዐይንን ያጠፋል፤ ሀዘን ሲበዛ ቀሪን ያስከትላል፡፡ ደስታ ሲበዛም ሀዘንን ይጠራል፡፡ እናም ሁሉም በመጠን ይሁን፡፡ ሁሉም ከተባለው አያልፍም፡፡ የተባለውም አይቀርም፡፤ የሚሞት ይሙት – ቀሪን ልብ ይስጠው፡፡ አሜን፡፡

No comments:

Post a Comment