ገላነው ክራር
Gelanew-kirar@hotmail.com
Gelanew-kirar@hotmail.com
“… ወርቅ ቢያነጥፉለትም (የኢትዮጵያ ህዝብ) ፋንዲያ ነው የሚል ነው”
ኮሎኔል መንግስቱ ሃ/ማርያም
በካምፕ ዴቪዱ ስብሰባ ጋዜጠኛ አበበ ገላው እንዲያ “መለስ ዜናዊ ኢዝ ኤ ዲክቴተር…” እያለ ሲጮህ … የጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊን ድንጋጤ እና መሸማቀቅ ያየ አንድ ነገር ይገነዘብይመስለኛል። (ሰውየው መለስ ዜናዊ ስለማንነታቸው የተነገራቸው እና የተነገረባቸው ሰምተው በማያውቁት ጊዜ እና ቦታ (መቼት) ላይ ነው። አጠገባቸው ያለ አብዛኛው ሰው የሚነግራቸው ስለደግነታቸው እና ስለ መልካም አስተዳደር ችሎታቸው፣ ስለ በሳል አመራራቸው ነው። እንዲያውም እርስዎ ከለቀቁ ኢትዮጵያ ትበታተናለች እያሉ በሚነግሯቸው ሰዎች ነው የተከበቡት። (በያ ሰሞን ደግሞ “ …ከአባይ ግድብ የተጠለፈ ውሃ በየቤታችን ሆነን ሳንጠጣ ስልጣን መልቀቅ የለብዎትም..” አይነት መፈክር በከተማችን በሚታዩ ተሽከርካሪዎች ላይ መለጠፍ መጀመሩን ሰምቻለሁ” (እድሜ ለኢሳት)። እንዲህ እንደ አበበ ተዘጋጅቶ በመግባት እና ተደራጅቶ በመግባትም ባይሆን፣ ይህን አይነት ትችት መለስ ሰምተው ያውቃሉ፣ በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ “አሁንስ መንግስቱ ሃ/ማርያምን መሰልከኝ” ተብለውም ያውቃሉ። (መለስ ይህን የሰሙት፣ የገዛ ደህንነት ሰዎቻቸው ባሉበት፣ ራሳቸው ስብሰባ በጠሩበት፣ የፈለጉትን ፖሊስ አዝዘው የፈለጉትን ማድረግ በሚችሉበት አገር ኢትዮጵያ አዲስ አበባ፣ ቤተመንግስታቸው ውስጥ ነው። ስለ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ውብ ሰብእና እና ሞራሊቲ [ተስፋዬ ገ/አብ “የዋሁ አዛውንት” በሚል እንቶ ፈንቶ ጽሁፉ እና በሌሎችም ጽሁፎቹ እንደተቻቸው ሳይሆን] በሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበታለሁ):: ሌሎችም በተለያየ አጋጣሚ፣ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ሆነው፣ አጠገባቸው ሆነው ተቃውሟቸውን በግልጽ የነገሯቸው በስውር የተቃወሟቸው ሰዎች ነበሩ። መለስ የሚገድሉትን አስገድለዋል፣ አሳስረዋል፣ ከሃገር እንዲወጡ አድርገዋል። በመሆኑም እንደ መለስ ዜናዊ ያሉ አምባገነኖች በቀጥታ የገደሉት እና ያስገደሉትን፣ ያሰሩት እና ያሳሰሩትን ህዝብ፣ በጠቅላላ የሰሩትን ወንጀል እና ጥፋት ሁሉ እስከመርሳት ይደርሳሉ። ዙርያቸውን የተከበቡት ባብዛኛው በንደዚህ ያሉ ሰዎች ነውና። አምባገነኖች “እድሜ ላንተ፣ ኢትዮጵያ ያላንተ ተስፋ የላትም የሚላቸው እና ክፉ ስራቸውን ሁሉ እስከ መርሳት እንዲደርሱ የሚተባበራቸው ሰው ባይሆን ኖሮ፣ በገዛ ክፋት ስራቸው፣ አብደው ጨርቃቸውን የጣሉ እብዶች ይሆኑ ነበር። ምክንያቱም በሌላው ሰው፣ ቡድን፣ ህዝብ እና ሃገር ላይ ክፉ ስራ እንደመስራት ያለ ራስን ለጭንቀትና ለበሽታ የሚዳርግ ነገር ያለ አይመስለኝም።
የዚህ ጽሁፍ አላማ አቶ አበበን እና ዶ/ር ነጋሶን ለማወዳደር አይደለም። አቶ አበበ ወትሮም ኢትዮጵያ ውስጥ እያለ በጋዜጠኝነቱም ብቻ ሳይሆን፣ በአአዩ ተማሪ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ የመለስን አገዛዝ እንደታገለ እናውቃለን። ከእውቅና አንጻር ሁለቱ ያላቸው ልዩነት ግን የትየሌለ ነው። አበበ እጅግ በጣም የታወቀው አሁን ከካምፕ ዴቪዱ ስብሰባ በሗላ ነው። ነጋሶ ደግሞ ያገር ፕሬዜዳንት የነበሩ ናቸው (በሃገር ጉዳይ የነበራቸው የመወሰን እና የውሳኔ አስፈጻሚነት ድርሻ አጠያያቂ የነበረ ቢሆንም። ለነገሩ ግን የመለስ አገዛዝን ማንነት እያደር በመገንዘባቸው እና በራሳቸው መንገድ ለመታገልም ይመስለኛል ስልጣናቸውን በራሳቸው ጊዜ የለቀቁት። ከዚህ አይነት የሃላፊነት ስልጣን በራሱ ጊዜ ሲለቅ በኢትዮጵያ ታሪክ ዶ/ር ነጋሶ የመጀመሪያው ይመስሉኛል። ከኢህአዴግ ጋር በመስራታቸው በአደባባይ ህዝብን ይቅርታ የጠየቁ የተጸጸቱ የመጀምሪያው ሰው ሳይሆኑ ይቀራሉ? በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የነበረው አቋም የተሳሳተ እንደነበር ባደባባይ የተናገረ እና ህዝብን ይቅርታ የጠየቀ የመጀመሪያው በሃላፊነት ላይ የነበረ ሰው ሳይሆኑ ይቀራሉ?)። ስለዚህ በሁለቱ መካከል የነበረው የሴሌብሪቲ (ታዋቂነት) ልዩነትም ድርሻ አለው ለማለት ነው።
ኮሎኔል መንግስቱ ሃ/ማርያም በ1982 መጨረሻ ግድም ሸሽተው ከመሄዳቸው ጥቂት ሳምንታት አስቀድሞ፣ በኢቲቪ “… ወርቅ ቢያነጥፉለትም (የኢትዮጵያ ህዝብ) ፋንዲያ ነው የሚል ነው” ብለው መናገራቸውን አስታውሳለሁ። አምባገነኖች ሁልጊዜም ከነሱ የተሻለ ለሃገርና ህዝብ የሚያስብ ያለ አይመስላቸውም። አገሪቱ በመንግስቱ ሃ/ማርያም አመራር ስር እያለች በቀይ ሽብር ያለቀው ወጣት፣ ከመንግስት ጋር በነበረው የአመለካከት ልዩነት ምክንያት ወይም የመንግስትን ስልጣን ለመቀማት የታገለ ነው ብለን እናስብ። እንዳሉትም አብዮቱን ይዘውለት ሲመጡ (ወርቅ ሲያነጥፉለት) ጸረ አብዮተኛ ሆኖ (የመንግስቱን አብዮት አጣጥሎ፣ ወይም ፋንዲያ ነው ብሎ) እንደተዋጋቸው እናስብ። በሱማሌ ጦርነት ወቅት (1969-70 አመተምህረት ድረስ እና በኤርትራ እና ትግራይ በረሃዎች ለሃገር አንድነት እና ለአብዮቱ ብለው ከቤት ንብረታቸው እና ቤተሰባቸው ተነጥለው የቀሩት በየበረሃው ወድቀው የቀሩት፤ የቆሰሉት እና አካለጎደሎ ሆነው የቀሩትም ሁሉ ወርቅ ሲነጠፍላቸው ፋንዲያ ነው ያሉ ናቸው? መንግስቱ ካለሳቸው ላገር የሚያስብ ያለ የማይመስላቸው ለመሆኑ እንዲህ እና ሌላም ብዙ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል። በካምፕ ዴቪዱ ስብሰባ መለስም ያሳዩት ይህንኑ ነው። “አባይን የደፈርኩ ጀግና ይህ ይገባኛል እንዴ..?” አይነት። ምእራባዊያኑ አብዛኛዎቹ የመለስን አምባገነንነት እያወቁ፣ ጥቂቶቹ ደግሞ መለስ እውነትም ዲሞክራት እየመሰላቸው፣ አጠገቡ ያሉት ያገሪቱ ባለስልጣናት ደግሞ፣ አብዛኛዎቹ በጥቅም፣ ጥቂቶቹ ደግሞ በፍርሃት ወዘተ… መለስን በራሱ ትንሽ አለም ውስጥ እንዲኖር አድርገውታል። ሙሃመር ጋዳፊ፣ በሽሽታቸው መጨረሻ ሰዓት ላይ፡ አንዱ የተቃዋሚ ጎረምሳ በጥፊ ሲመታቸው፡ “ለመሆኑ ትክክል እና ስህተት ስራን ለይተህ ታውቃለህ? (Do you know what is right and wrong?) ብለው መናገራቸውን አስታውሳለሁ። ጋዳፊ በ40 አመታት አገዛዝ ጊዜያቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሊቢያውያንን የገደሉት እና ያስገደሉት ለሃገራቸው እና ለህዝባቸው ሲሉ የሰሩት “ትክክለኛ ስራ” ነው።
ርቱዕ አንደበቱ፣ ውስጣዊ ውብ ሰብዕናውን የሚመሰክርለት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ስለ አምባገነኖች አስተሳሰብ (mentality) ከስነ ልቦና አስተማሪ ጓደኛው ጋር ያደረገውን ጭውውት አስመልክቶ በኢሳት ቃለመጠይቅ ያቀረበው ትንተና፣ የመለስን ማንነት እና በመለስ አገዛዝ ምክንያት የደረስንበትን የማህበረሰብ ስነልቦና ቀውስ (social psychology crisis) ይናገራል።
ኢትዮጵያዊያን የተሻሉ መሪዎች ይገቡናል።
No comments:
Post a Comment