ኢህአዴግ የውጭ ምንዛሪ አሰሳ ሊያካሂድ ነው
ዶላር አምራቾቹና ሰብሳቢዎቹ እነማን ናቸው?
ኢህአዴግ የተጭበረበረ የውጪ ምንዛሪ በማተምና በማሰራጨት ስራ የተሰማሩ እንዳሉ ከበቂ በላይ መረጃ ቢኖረውም ርምጃ እንደማይወስድ መደመጥ ከጀመረ ቆይቷል። በስራ ሽፋን የተጭበረበረ ዶላር የሚያትሙ የውጪ አገር ሰዎችን አስገብተው የሚሰሩት ለራሱ ለህወሃት የቀረቡ ሰዎች ዝርፊያ ስለማካሄዳቸው ፖሊስ ተደጋጋሚ መረጃ ቢደርሰውም ርምጃ ሲወስድ አይታይም በሚል የሚወቅሱት ጥቂት አይደሉም።
ቀደም ሲል የተጭበረበረ ዶላር የሚያስገቡ እንደነበሩ የሚገልጹት የጎልጉል የፖሊስ ምንጮች እነዚሁ ክፍሎች አቅማቸውን በማሳደግ የሐሰት (ፎርጂድ) ዶላር አገር ውስጥ ማተም ከጀመሩ ቆይተዋል። ከሩቅ ምስራቅና “ከትንሿ ታላቅ አገር” ህገወጥ ብር አታሚዎችን ከማሽን ጋር በማስገባት የአዲስ አበባን ሃብታሞች ሙጥጥ አድርገው ዘርፈው አድራሻ የቀየሩ አሉ። በዚህ ስራ ውስጥ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል የህትመት ሰዎችም እንደሚገኙበት ጥቆማ አለ።
የለፉበትንና በብድር ያገኙትን ገንዘብ በሚያምኗቸው ትልልቅ ሰዎች ደላላነት በተጭበረበረ ዶላር ቀይረው የከሰሩ ጉዳዩን ወደ ክስ እንዳይወስዱ ራሳቸው የህገወጥ ስራ ተባባሪ መሆናቸው ያግዳቸዋል። ህግ ፊት እንዳይሄዱ ህገወጥ መሆናቸው የያዛቸው እነዚህ ስግብግቦች ባዶ እጃቸውን አጨብጭበው ለመቀመጥ ተገደዋል። ኃይል ለመጠቀም እንዳይሞክሩ ደላላ ሆነው የሚቀርቡት “ትልቅ” የሚባሉት የዘመኑ ሰዎችና ባለጊዜዎች መከታና ደጀን ስላላቸው ቀላል አይሆንም።
አይ.ኤም.ኤፍ. በሚባል ምህጻረ ቃል የሚታወቁት የኤ.ዲ.ኤች. ዋናሥራአስኪያጅና ባለአክሲዮን አቶ አየለ ደበላ፣ የአያት የመኖሪያ ቤት ድርጅት ሊቀመንበርና ዋና ባለአክሲዮን አቶ አያሌው ተሰማ፣ ጃማይካና ሌሎች አራጣ አበዳሪዎቸ “አራጣ በማበደር በባንክ ስራ ገብታችኋል” ተብለው በቁጥጥር ስር ሲውሉ፣ በተመሳሳይ መንግስት የተጭበረበረ ዶላር በማምረት ዝርፊያ ላይ የተሰማሩትና በየስርቻው እየገቡ ዶላር የሚያስለቅሙት እነማን እንደሆኑ መረጃው እንደነበረው ባልደረባችን ከአዲስ አበባ ያሰባሰበው መረጃ ያመለክታል።
በዶላር ህገወጥ ንግድ ውስጥ በግንባር ቀደም ተዋናይ ከሆኑት መካከል “የክልል አስራ አምስት አባላት” የሚባሉት ቻይናዎች ይገኙበታል። ካልሲና የውስጥ ሱሪ ሳይቀር በየስርቻው ውስጥ በማምረት ቦምብ ተራን የተቆጣጠሩት የቻይና ዜጎች፣ በከፍተኛ ደረጃ በዶላር የጨለማ ገበያ ውስጥ ተሳታፊ ናቸው። ከተማዋ ውስጥ ያለውን ዶላር በመሰብሰብ ወደ አገራቸው በቀጥታ በኤምባሲያቸው አማካይነት በመላክ ዶላሩ አገራቸው ሲደርስ በራሳቸው ገንዘብ ተመንዝሮ ለፈለጉት አገልግሎት እንደሚውልላቸው በቴሌ ከሚሰሩ የቻይና ዜጎች ያገኙትን መረጃ ጠቅሰው ለጎልጉል ይገልጻሉ።
የቻይና ዜጎች የሚሰበስቡትን ብር ወደ ዶላር በመቀየር ወደ አገራቸው መላክ የመሃላ ያህል ተግተው የሚሰሩት ስራ እንደሆነ የሚገልጹት የቴሌ ምንጫችን፣ ዶላር በማቅረብ አብረዋቸው የሚሰሩት ራሳቸው የመንግስት ሰዎች መሆናቸው ያደባባይ ምስጢር እንደሆነ ይናገራሉ።
ይህ ሁሉ ጉድ ህጋዊ ሆኖ በሚከናወንበት ባሁኑ ወቅት፣ ራዲዮ ፋና ታህሳስ 25 ቀን 2005 ዓ ም ህግን በማንተራስ ባሰራጨው አስተያየት መሰል ዜና “የውጭ ገንዘቦችን ለመዘርዘር ፈቃድ የተሰጣቸው ባንኮች ብቻ ሲሆኑ ፥ ከዚህ ውጭ ማንኛውም የውጭ ሀገር ገንዘብ ፈቃድ ሳይኖረው የገዛ፣ ከውጭ ሀገር ያስመጣ፣ ወደ ውጭ ሀገር የላከ ያስቀመጠ፣ የመነዘረ፣ የሸጠ ወይም ለሽያጭ ያቀረበ ገንዘቡ ሙሉ በሙሉ እንደሚወረስ ፥ እንዲሁም ከ10 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከ50 ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ በሀገሪቱ የወንጀል ህግ አንቀጽ 346 ተደንግጓል” በማለት ዋናዎቹን የውጪ ምንዛሪ ቀበኞች ወደ ጎን በመተው ልጥፍ ሱቆች ላይ ያነጣጠረ መረጃ አስተላልፏል።
በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ድርጊቱ ተስፋፍቶ እንደቀጠለ ፥ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሆቴል በስተጀርባ ፣ በጋንዲ ሆስፒታልና አካባቢው ፣ በአሜሪካን ግቢ፣ ቦሌ ሩዋንዳና በሌሎችም አካባቢዎች በመዘዋወር ይህንኑ ህገወጥ ዶላር ገበያ የተመለከተው የፋና ዘጋቢ የመንግስት ቤቶች፣ የኢትዮጵያ ሆቴል ሱቆች የሆኑና ለጫማ እና ለተዘጋጁ ልብሶች መሸጫ፣ የጽሁፍ አገልግሎት ለመስጠት የተከፈቱና በዚያው አካባቢ የሚገኙ የግለሰብ ሱቆች፣ ለአነስተኛና ጥቃቅን ተብለው የተገነቡ በጋንዲ ሆስፒታል ፊት ለፊትና አጠገብ የሚገኙ ሱቆች በዚህ ህገ ወጥ ተግባር እየተሳተፉ መሆናቸውን መታዘቡን ይገልጻል።
አንዳንዶቹ ሱቆች የታሸገ ውሃ፣ ሶፍት፣ ጥቂት የተዘጋጁ ልብሶችን ለሽፋን ያህል ደርድረው ቢታዩም ዋና ተግባራቸው ህገወጥ የውጭ ምንዛሪ ግብይት መፈፀም ነው ። ከዚህም ባለፈም በርካታ ገንዘቦችን ወደ እነዚህ ስፍራዎች ይዘው የሚሄዱ ግለሰቦችን ፥ በዋጋ ሽያጭ ድርድሩ እንዳልተግባቡ በማስመሰል በሀሰተኛ የውጭ ገንዘቦች የሚቀይሩ እንዳሉና፣ ይህም አልፎ አልፎ እንደሚከሰት የድርጊቱ ሰለባ የሆኑ ተጠቃሚዎች መናገራቸውን ያመለከተው ዘጋቢ የተጭበረበሩ የውጪ ምንዛሪዎች /ፎርጂድ ገንዘቦች/ ምንጫቸው ከየት እንደሆነ በሪፖርቱ አልገለጸም።
ዘጋቢው ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ብሩክ ዓለሙ፥ የውጭ ገንዘቦችን ስልጣን ከተሰጠው አካል ውጪ መዘርዘርና መለወጥ ሀገርና ህዝብን ለጉዳት እንደሚዳርግና የንግድ ስርዓቱን በማዛባት የዋጋ ግሽበትን እንደሚያባብስ ሲገልጹ፣ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር አሳይ አምባዬ ችግሩን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የተደረገው ጥረት ዝቅተኛ የሚባል እንደሆነ ነው የተናገሩት።
በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ልዩ ወንጀል ምርመራ ዲቪዚዮን ሃላፊ ኢንስፔክተር አበራ፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ችግሩን ለመከላከል እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ችግሩን ለመቅረፍ ጋንዲ ሆስፒታል አጠገብ የውጭ ምንዛሪ መስጫ ቢሮ ቢከፍትም፥ ህገ ወጥ ድርጊቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመስፋፋት እንዳላገደው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ ጸጋዬ ደስታን የገለጸው ፋና ዘገባ ያስረዳል። ጋዜጠኛው በመጨረሻ “ህገ ወጥ ተግባሩን ለመከላከል ፖሊስ ያደረገው ጥረት ዝቅተኛ መሆኑንና በቀጣይም ለድርጊቱ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ብሏል።
በዘገባው ደቃቃዎቹ የዶላር ማዘዋወሪያ ኪዎስኮች እንጂ በትላልቅ ሆቴል የሚካሄደውን ዝርፊያና ወንጀል አልነካውም። ዱባይና ናይሮቢ እየሄዱ የሚዳሩት “ደላላ ባለሀብቶች” በከፍተኛ የምንዛሪ አደን ላይ ሃይል በቅጥር አሰማርተው እንደሚሰሩ ፖሊስም፣ መንግስትም፣ አብሮ አረቄ የሚጋተው ደህንነቱም እንደሚያውቅ የጎልጉል ምንጮች ያብራራሉ።
ህገወጥ ተግባርን ተከታትሎ እልባት መስጠት አግባብ እንደሆነ የሚጠቁሙት ክፍሎች “መንግስት የችግሩን ዋና መነሻና አስኳል ስፍራ የትና እነማን ጋር እንደሆነ ያውቃል፣ ነገሩን ከቆሰቆሰው “እጄን በእጄ” ስለሚሆንበት ህዝብን እያስለቀሰ ይኖራል። ይህ አካሄድ ራሱን ይደፋዋል” ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
በድንገት አሰሳ የማድረግ እቅድ የያዘው ኢህአዴግ ስለያዘው ኦፕሬሽን ዝርዝር መረጃ ባይሆንም “ቀደም ሲል በድንገት በተደረገ ወረራ ለከፍተኛ ኪሳራ የተዳረጉ የምንዛሪ ሰራተኞች እንደቀድሞው በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ቢሯቸው ያስቀምጣሉ ተብሎ አይገመትም” የሚል የፖሊስ ትንተና መኖሩ ተሰምቷል። ይሁን እንጂ የተወሰኑ ሰዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የመጠቀም አዝማሚያ አለ።
በውጪ ምንዛሬ እጥረት ዙሪያ ሙስና መኖሩ፣ አንድ ዶላር ለመውሰድ አንድ ብር ከሃያ ሳንቲም ጉቦ እንደሚሰጥ በመግለጽ ሪፖርተር ዜና ማውጣቱን ተከትሎ ብሄራዊ ባንክ በመላው የአገሪቱ ባንኮች ላይ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል። አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት መንግስት ከየስርቻው የሚለቅመው የውጪ ምንዛሪ አሁን ተፈጠረ ለሚባለው የምንዛሪ እጥረት መፍትሄ አይሆንም።
በከፍተኛ ደረጃ ገንዘብ በማጋዝ ላይ በተሰማሩ “ወኪል ባለሃብት አሽከሮቻቸው” ላይ ትኩረት ማድረግ፣ አቶ መለስ እንዳሉት “የመንግስት ሌቦች” ላይ ጨክኖ ርምጃ መውሰድ ዋና መፍትሄ እንደሆነ የሚጠቁሙት አስተያየት ሰጪዎች፣ መንግስት በራሱ ላይ ርምጃ ሲወስድ ታይቶም ተሰምቶም ስለማይታወቅ ችግሩ እንዳለ እንደሚቀጥልና ቀን ጠብቆ ግን መልሶ ኢህአዴግን ለህልውናው በሚያሰጋ ከፍተኛ አደጋ ላይ እንደሚጥለው አስታውቀዋል።
No comments:
Post a Comment